Thu02232012

Go to :English Edition

Back ቢዝነስና ኢኮኖሚ ቢዝነስና ኢኮኖሚ የተሻረው የመንግሥት ዕርምጃና የዋጋ ግሽበት ከዓመት በኋላ

የተሻረው የመንግሥት ዕርምጃና የዋጋ ግሽበት ከዓመት በኋላ

  • PDF

መንግሥት ልክ የዛሬ ዓመት፣ ለገና ዋዜማ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ እንደጀመረ አስታውቆ 18 ያህል ሸቀጦች ላይ የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር በጋዜጣ እያወጣ፣ በሬዲዮና ቴሌቪዥን እያስነገረ ዋጋ አረጋጋለሁ በማለት የወሰደው ዕርምጃ መንፈቅ ሳይሞላው ለማንሳት መገደዱን ሳይወድ ያስታወቀው አምና ነበር፡፡

ንግድ ሚኒስቴር በወቅቱ የዋጋ ቁጥጥር ዕርምጃን ሲወስድ መነሻ ያደረገው በተለይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበትን እያባባሱ ስለነበር ነገሩ መያዣ መጨበጫ ከማጣቱ በፊት መንግሥት ጣልቃ መግባት እንዳለበት አሳስቦ ‹‹በጥናት ላይ የተመሠረተ›› ዕርምጃ እንደነበር መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

በሳሙና፣ በፓስታ፣ በማካሮኒ፣ በስኳር፣ በዘይት፣ በዳቦ፣ በዳቦ ዱቄትና በመሰል ሸቀጣ ሸቀጦችና በዓይነታቸው የውጭ፣ የአገር ውስጥ፣ የታሸገ፣ ብትን፣ በኪሎ፣ በቁጥር እየተባሉ ዋጋ ሲቀመጥላቸው ሕዝቡ እፎይታ የሚያገኝ መስሎት የነበረ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ የማያዋጣ አካሄድ የሆነበት ንግድ ሚኒስቴር ‹‹የተፈለገው ቀርቶ ያልታሰበው ተከስቶ ስለተቸገርን›› ለጊዜው የስኳር፣ የዘይት፣ የዳቦና የዳቦ ዱቄት ዋጋ ሲቀር የሌሎቹን የዋጋ ተመን አንስቻለሁ ብሎ ለማስታወቅ ተገዷል፡፡

ዋጋ ተመኑ ሥራ ላይ ውሎባቸው በነበሩት አምስት ወራት ዋጋ የተተመነላቸው፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ ሥጋ፣ ቢራና ለስላሳ መጠጦች ሳይቀር አቅርቦታቸው እንደ አንታርክቲክ ፀሐይ የተናፈቀበት ጊዜያት ነበሩ፡፡ ከቸርቻሪ ኪዮስክ እስከ አምራች ፋብሪካዎች የከረረ ተቃውሞ ያስተናገደው መንግሥት፣ በምሁራንም ዘንድ የተነቀፈበት፣ የኢኮኖሚ ሳይንስ ሀሁ የቆጠረ እንኳ የማይሳሳተውን ቀሽም ስሌት የሳተበት ዕርምጃ እንደነበር በመግለጽ ተተችቷል፡፡

ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ 584 የአገሪቱን ዋና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነጋዴዎች በጽሕፈት በታቸው ሰብስበው አግባብ ያልሆነ የዋጋ ንረት መፍጠር እንደማይገባቸው አሳስበዋል፡፡ በታህሳስ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. ደግሞ ንግድ ሚኒስቴር 18 ያህል ሸቀጦች ላይ ዋጋ መተመኑን፣ ሻጭና ገዥም በዚሁ መሠረት እንዲገበያዩ ቀጭን ትዕዛዝ አሳልፏል፡፡

ውሎ ሳያድር ግን የተመኑ ጉዳይ አነጋጋሪነቱን ቀጥሎ ሕዝቡም ነጋዴም ማማረር ጀምረዋል፡፡ ሕዝቡ ዋጋው የቀነሰባቸውን ዕቃዎች ከገበያ ሲያጣ ነጋዴም ስለማያዋጣኝ እያለ መሸጥ ሲያቆም፣ ቢቸግረው እኔው ራሴ አስመጣለሁ ብሎ በተለይ ዘይት ላይ ቢገባበትም አቅቶት የተወበት አጋጣሚ የአደባባይ ሚስጥር ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንዳልቻለ የገባው መንግሥት፣ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በታች በነበረበት ወቅት ገበያው ላይ ጣልቃ የገባው ከዚያ በታች ሊያወርደው አስቦ ቢሆንም፣ አቅቶኛል ብሎ የወጣው ግን ግሽበቱ ከ30 በመቶ በላይ አድጐ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የዋጋ ተመኑ ከወጣ ከአምስት ወራት በኋላ ሰብስበው ያነጋገሯቸውን ነጋዴዎች፣ መንግሥት የዋጋ ቁጥጥሩን እንደሚቀጥልበት በገለጹና ባሳሰቡ ማግስት፣ ንግድ ሚኒስቴር ለሰበሰባቸው አስመጪዎችና ሌሎች ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች የዋጋ ተመኑ መነሳቱን ያስታወቁት፣ መነሳቱን ብቻ ሳይሆን የተፈለገው ውጤት (የዋጋ ግሽበትን መቀነስ) ሳይሆን ያልተፈለገ የገበያ ትርምስ መፈጠሩን ጭምር በመግለጽ ነበር፡፡

በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት፣ በታህሳስ ወር 2003 ዓ.ም. ከ20 በመቶ በታች የነበረው የዋጋ ግሽበት ዘንድሮ በህዳር ወር እንኳ 39 ከመቶ በላይ ሆኗል፡፡ የችርቻሮ ዕቃዎች የመሸጫ ዋጋ ጠቋሚም 40 በመቶ ገደማ ላይ ይገኛል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ከዚህ በተጨማሪ የዋጋ ተመን ያወጣበት ወቅት በቱኒዝያ የኑሮ ውድነት ሕዝቡን ያስቆጣበት ሁኔታ በኢትዮጵያ እንዳይፈጠር መፈለጉንም አስታውቆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በህዳር 2003 ዓ.ም. የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ስምንት በመቶ ገደማ፣ የምግብ ዋጋ ግሽበትም ከአንድ በመቶ በታች፣ ምግብ ነክ ያልሆኑት ሸቀጦች ደግሞ 19 በመቶ ገደማ ነበሩ፡፡ በዘንድሮው ህዳር ወር አጠቃላይ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት 39.2 በመቶ ነክቷል፡፡ የምግብ ዋጋ በ36 በመቶ ጦዟል፡፡ ምግብ ነክ ያልሆኑት ደግሞ በ25 በመቶ ዋጋቸው ጨምሯል፡፡

በአንድ ዓመት ልዩነት ምግብ ላይ የታየው ጭማሪ እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ከአንድ በመቶ ወደ 36 በመቶ ጭማሪ ታይቷል፡፡

ከዚህ በላይ ደግሞ በበዓል ወቅት በደህናውም ጊዜ ቢሆን ነጋዴው ለወትሮው ከሚሸጥበት ዋጋ ጨምሮ የሚሸጥ ሲሆን፣ በገና በዓል ይታይ ከነበረው ሁኔታ በተለየ ዘንድሮ የበግ፣ የዶሮና የከብት ዋጋ ንረት ይታያል፡፡

በቄራ ገበያ መካከለኛ የሚባለው በግ ከ1,000 ብር በላይ ይጠራለታል፡፡ ጠቦት በጐች ደግሞ ከ900 ብር ጀምሮ ይሸጣሉ፡፡

በብሥራተ ገብርኤል ገበያም መካከለኛ በግ፣ ዋጋው እስከ 1,200 ብር ይባላል፡፡ ደህናው ግን ከ2,400 ብር ጀምሮ የሚሸጥ እንደሆነ ለማየት ተችሏል፡፡

በመርካቶ መካከለኛው ዶሮ 130 ብር ሲጠራ ደህና ብልት አለው የሚባለው ደግሞ 150 ይባላል፡፡ ሴት ዶሮ ከ110 ብር ጀምሮ ትሸጣለች፡፡ የኤልፎራዋ 75 ብር ናት፡፡ ደህናው የሸኖ ቅቤ በኪሎ 140 ብር ይሸጣል፡፡ መካከለኛ በሳል ቅቤ 120 ብር ሲያወጣ፣ የጐጃም 100 ብር፣  የወላይታ ቅቤ በ85 ብር ይገበያል፡፡

እንቁላል በጉልት ገበያ 2.10 ይሸጣል፡፡ ሱፐር ማርኬቶች 2.90 ብር ድረስ ይሸጣሉ፡፡ አይብ በጣሳ 50 ብር ሲያወጣ በኪሎ 45 ብር ይሸጣል፡፡ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ሰባት ብር እየተሸጠ የቆየበት የሐሙሱ የመርካቶ ገበያ፣ ነጭ ሽንኩርት ከ45 ብር በላይ በኪሎ ተጠይቆበታል፡፡ በርበሬ በፈረሱላ 700 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የዳቦ ዱቄት በኩንታል 1,350 ብር ሲያወጣ፣ በኪሎ 16 ብር ድረስ የሚሸጡ አንዳንድ አምራቾችንም ለመታዘብ ተችሏል፡፡

የፓልም ዘይት በሊትር ከ28 ብር በላይ የሚሸጥ ቢሆንም፣ እንደ ልብ በችርቻሮ መሸጫ ቤቶች አይገኝም፡፡ ሌሎች የዘይት ዓይነቶች የሱፍ ዘይት (ከውጭ የሚመጣው) 60 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ አምና በወጣለት ተመን ይሸጥ የነበረው 16.50 ሲሆን መልሶ 24 ብር እንደገባ የሚታወስ ነው፡፡ ከዋጋ ተመኑ ቀድሞ 36 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ ሥጋ አምና በተመን ይሸጥ በተባለበት ወቅት ዋጋው በኪሎ 52 ብር ተደርጐ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከ70 እስከ 110 ብር በልኳንዳ ቤቶች ይቸበቸባል፡፡ ከጥቂት ምርቶች በስተቀር አብዛኞቹ የዋጋ ተመኑ ከመውጣቱ በፊት ይሸጡ ከነበረበት ዋጋ በላይ ጭማሪ ተደርጐባቸው ለገበያ እየቀረቡ ይታያል፡፡

አንዴ በዋጋ ተመን፣ ሌላ ጊዜ በንግድ አሠራር በምዝገባ አዋጅ ዓመቱን ሙሉ ከነጋዴዎች ጋር ግራ ቀኝ ሲባባል የሰነበተው ንግድ ሚኒስቴር፣ ዘንድሮ ደግሞ በአስገዳጅ ደረጃዎች እንዲሁም በቴክኒክ ደንብ ላይ እንድታውቁልኝ የምፈልጋቸው ጉዳዮኝ እንካችሁ ቢልም ነጋዴዎቹ ግን ከሚናገረው እኩል ያልሆነው አቅሙን በመተቸት፣ ከዚህ ቀደም የወጡትን አዋጆች የማስፈጸም ችግር እንዳለበት፣ የዋጋ ተመን መውጣቱን ተከትሎ ሸማችና ትክክለኛው ነጋዴ የተጐዱበት ሁኔታ በንግዱ ማኅበረሰብ የተነሱ ጥያቄዎችና ትችቶች ነበሩ፡፡ ዘንድሮም እንዳምናው ሲፈለግ እየተነካኩ አልሆን ሲል የሚተው አሠራሮች መደገም እንደሌለባቸውም ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል፡፡        

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የንግድ ሚኒስትሩ አቶ አብዱርሃማን ሼክ መሐመድና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ቱሳ ከኃላፊነታቸው ለመነሳታቸው የዋጋ ተመኑ ውሳኔ አለመተግበር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አሁንም ቢሆን የንግዱ ማኅበረሰብ በሚኒስቴሩ የማስፈጸም አቅም ላይ ስጋት እንዳለው በያዝነው ሳምንት አስታውቋል፡፡