Thu05172012

Go to :English Edition

Back ቢዝነስና ኢኮኖሚ ቢዝነስና ኢኮኖሚ ሕብር ስኳር የቢዝነስ ፕላኑን በመቀየር ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታወቀ

ሕብር ስኳር የቢዝነስ ፕላኑን በመቀየር ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታወቀ

  • PDF

•    የህንድና የብራዚል ኩባንያዎች ፈተና ሆነውበት እንደነበር ገለጸ

በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመሳተፍና በዓመት ከ1.2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር ለማምረት የሚችል ግንባታ ለማካሄድ የአክሲዮን ሽያጭ ሲያካሂድ የቆየው ሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር፣ በማልሚያ ቦታ ዕጦት የተፈጠረበትን ችግር በመፍታት ወደ ሥራ እንደሚገባና ቀድሞ የነበረውን የመመሥረቻ ጽሑፍ ቢዝነስ ፕላን መቀየሩን አስታወቀ፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በተካሔደው የአክሲዮን ማኅበሩ 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው፣ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቅበት ጊዜ የዘገየው በማልሚያ ቦታ ችግር ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ችግር መፍታቱን የሚገልጽ ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔው አቅርቧል፡፡

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ለሥራ እንቅስቃሴው መዘግየት የአገዳ ልማቱና ፋብሪካው ይተከልበታል የተባለው መሬት ላይ ለመጠቀም በወቅቱ የመሬቱ ባለመብት ከነበረውና በአክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ትልቅ አክሲዮን ይኖረዋል ተብሎ ሲጠበቅ ከነበረው ቢዲኤፍሲ ከተባለ ኩባንያ ጋር የተፈጠረ አለመግባባትና በመሬቱ ላይ ያልተጠበቁ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ከቢዲኤፍሲ ጋር በጥምረት ለመሥራት ስምምነት ላይ ከደረሰ በኋላ ቢዲኤፍሲ የልማት ቦታው ሕጋዊ ባለመብት ነኝ በማለቱ የተፈጠረው ችግር ለአክሲዮን ማኅበሩ አብይ ፈተና ሆኗል፡፡ በተለይ ምንጣሮ ሳይቀር ተደርጐበት የነበረውና ቀደም ብሎ በቢዲኤፍሲ የተመዘገበውን ቦታ ከብዙ ድርድር በኋላ ሕብር ስኳር ወደ ራሱ ይዞታ ለማዛወር መሞከሩን ያትታል፡፡ ሌሎችም ጥረቶች መደረጋቸውን የሚገልጸው ሪፖርት፣ መጨረሻ ላይ መሬቱን የክልሉ መንግሥት እስከመረከብ  በመድረሱ ሌሎች አማራጮች እስኪገኙ ድረስ የግንባታው ጊዜ መዘግየቱን አስታውቋል፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላም ግንባታው ይካሄድበታል በተባለው አካባቢ 6,138 ሔክታር መሬት በሕብር ስም በማግኘቱ ይህንኑ የመሬት ባለቤትነት የሚያረጋግጠው ስምምነት ባሳለፍነው የካቲት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ሊፈጸም ችሏል፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ ተደርጐበታል የተባለው መሬት ግን ቀድሞ ሲጠቀምበት ከነበረው በግማሽ ያህል የሚያንስ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ አክሲዮን ማኅበሩ ቀደም ብሎ የነበረውን የመመሥረቻ ጽሑፍና የቢዝነስ ፕላን ቀይሮ በአዲስ ዕቅድ ወደ ሥራ እንዲገባ ያስገደደው መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ቀደም ብሎ በነበረው ዕቅድ 12 ሺሕ 500 ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ፋብሪካ በሁለት ዙር በመትከል፣ ከ11 ሺሕ 500 ሔክታር በላይ የስኳር ልማት ይከናወናል የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡

አሁን ባለው መሬት ስፋት ግን የፋብሪካው የመፍጨት አቅም በጀመርያው ዙር ወደ 4,400 ቶን ቀጥሎ ወደ 6,600 ቶን ለማሳደግ እንደሚቻል ሲታወቅ፣ አዲሱ ዕቅድም ዓመታዊ የስኳር ምርቱ 900 ሺሕ ቶን እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ አባላት ባቀረቡት በዚሁ ሪፖርት፣ በመሬት የመጠቀም መብታቸው በተለያዩ መንገዶች በመስተጓጐሉ፤ ከኩባንያው ጋር ለመሥራትና ብድር ለመስጠት የመግባቢያ ስምምነት ሐሳብ አቅርበው የነበሩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ለመፈራረም እንዳላስቻለው ጭምር ተጠቁሟል፡፡

የአክሲዮን ኩባንያውን አዋጭነት በመረዳት ኢንቨስትመንቱን በጋራ ለማካሄድም ሆነ ብድር ለመስጠት የመግባቢያ ስምምነት ሐሳብ አቅርበው እንደነበር የሚያስታውሰው ይኸው ሪፖርት፣ በፋይናንስ ጭምር ሊያግዙ ነበር ከተባሉት የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ ሽሪ ሬኑካ እና ኤፍሲኤሲፒ የተባሉ ሁለት ኩባንያዎች ተጠቅሰዋል፡፡ የጣሊያኑ ኤርዲኒያ፣ የደቡብ አፍሪካው የጂቢዲ እና አፍሮፔን የተባለው የኬንያ ኩባንያዎች ጋር በመሬት ችግር ሳቢያ ወደ ሥራ መግባት ባለመቻሉ ስምምነት ላይ ለመድረስና ለመፈራረም አለመቻሉን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ከተጠቀሱት ኩባንያዎች ጋር ግንኙነቱን ለመቀጠል ዕቅድ ተይዟል ተብሏል፡፡ በተለይ ከብራዚሉ ኩባንያ ጋር ያለው ግንኙነት ችግር ያለበት መሆኑ በሚታወቅበት ወቅት በአማራጭነት ተይዞ የነበረው የህንዱ ሽሪ ሬኑካ ኩባንያም ያልተጠበቀ ችግር እንደፈጠረ ተገልጿል፡፡ የህንዱ ኩባንያ ከአክሲዮን ማኅበሩ ጋር ልማቱን ለማካሄድ ከፍተኛ ፍላጐት በማሳየቱ ባለፈው ዓመት በተካሄደ ጠቅላላ ጉባዔ የቦርድ ውክልና እንዲኖረው ተፈቅዶለት፣ ወኪሉም በምርጫ እንዲወዳደር ተደርጐ የነበረና ገንዘብ ከመክፈሉ በፊትም የተለያዩ ጥናቶችን እንዲያካሂድ ዕድል የተሰጠው ነበር፡፡ በተለይም ስለሕብር ስኳር በኧርነስት ኤንድ ያንግ ኩባንያ በኩል የጥናት ሪፖርት እንዲቀርብለት አድርጐ በሕብር ስኳር ውስጥ ለመሥራትና የሚፈለገውን ክፍያ ለመክፈል በደብዳቤ ጭምር ካሳወቀ በኋላ ሐሳቡን ሊለውጥ ችሏል፡፡

ኩባንያው ሐሳቡን ለመቀየሩ ዓይነተኛ ምክንያት የተደረገው ያልታሰቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በማቅረቡ ነው ተብሏል፡፡ ኩባንያው አቀረባቸው የተባሉት ምክንያቶች የጣና በለስ የልማት ቦታ 84 ሺሕ ሔክታር መሬት መሆን አለበት፣ ከሕብር የአክሲዮኖች ድርሻ አንጻር የሽሪ ሬኑካ ድርሻ 85 በመቶ የግድ መሆን አለበት፣ መንግሥት ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ባለው መንገድ ላይ ከሚገኙ ፋብሪካዎች አንዱን እንዲሰጠኝ አሳምኑልኝ የሚሉ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ይህ ቅድመ ሁኔታ በሕብር ስኳር በኩል ሊፈጸሙና ለትግበራም የማይመቹ ጥያቄዎች ሆነው በመገኘታቸው አክሲዮን ማኅበሩ ሊቀበላቸው እንዳልቻለ ሲገልጹ፣ ብዙ ርቀት ተጉዘንበት ነበር ያሉት ግንኙነት እንዲቋረጥ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የህንዱ ኩባንያ ከዚህም በላይ ያልተገባ ድርጊት መፈጸሙን የሚያመላክት ሐሳብም የሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር ቦርድ በሪፖርቱ ውስጥ አስፍሯል፡፡ ሽሪ ሬኑካ በመጨረሻው ሰዓት ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ተከትሎ የአገሪቱን የስኳር አዋጭነት መረጃ አሰባስቦ በኋላ የራሱን መሬት ለማግኘት መንቀሳቀሱን ማረጋገጡንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

‹‹ይህ የህንድ ድርጅት ምንም እንኳ ባሰባሰበው መረጃ የራሱ የሆነ ስኳር ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለመክፈት ጠይቆ በደቡብ ክልል የተሰጠው መሬት ለልማቱ አመቺ አይደለም በሚል እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉን ተገንዝበናል፤›› የሚለው ሪፖርት ያለቅድመ ሁኔታና የአገሪቱን ጥቅም ባልተጻረረ መልኩ ከሕብር ስኳር ጋር ለመሥራት ከፈለገ ሊቀበሉት እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

የጠቅላላው ጉባዔ አባላት ግን እንዲህ ካደረገ ድርጅት ጋር ከዚህ በኋላ ሌላ ግንኙነት ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ እንገባለን ያሉት የአክሲዮን ማኅበሩ አመራሮች፤ አክሲዮን ማኅበሩ እስካሁን የሰበሰበው ካፒታል መጠነኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ሁሉ ፈተና ገጥሞት እያለ እንኳ በዘርፉ ከፍተኛ አዋጭነት የተነሳ ከዚህ ደረጃ መድረሱ የሚያበረታታ እንጂ ተስፋ አያስቆረጥም፤›› በማለት ባለድርሻዎችን ያፅናናሉ፡፡ ይህም በመሆኑ በተለይ የመሬት ችግሩ አሁን ስለተፈታ አክሲዮን በደንብ የሚሸጥለት በመሆኑ ይህንኑ ሥራ አጠናክሮ ለመሥራት የሚችልበት ዕቅድ እንዳለው ተነግሯል፡፡ ነባር አባሎችም ከ10 ሺሕ ብር ጀምሮ ተጨማሪ አክሲዮን እንዲገዙ ጥሪ ተላልፏል፡፡ የብድር ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ሥራ ለመግባት ሐሳብ ያለው መሆኑንም ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በግንባታ ጊዜው መዘግየት ምክንያት ቅሬታ ያደረባቸው ባለአክሲዮኖች የቀረበላቸው ሪፖርት ብዥታቸውን እንዳጠፋላቸው በመግለጽ በዕለቱ የሁለተኛ ጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳዎችና የቀረቡትን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርትና የኦዲት ሪፖርት አጽድቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አንድ የቦርድ አባል ስለጐደሉ በምትካቸው ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፣ በሥራው መዘግየት ቅሬታ ገብቶት የነበረው ባለአክሲዮን ከቦርዱ የቀረበለትን ማብራሪያና ሪፖርት በመቀበል ከዚህ በኋላ የሚጠበቅባችሁን ሥሩ ብሎ አሳስቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዕለቱ ይካሄዳል ተብሎ ተይዞ የነበረው 2ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ግን ምዕላተ ጉባዔ ባለማሟላቱ ሳይካሔድ ቀርቷል፡፡ በአክሲዮን ማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ለመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ 25 በመቶ አክሲዮን ያላቸው አባላት መገኘት የሚገባቸው በመሆኑ በዚሁ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው ሊካሄድ ቢችልም፣ ለድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ግን ከ50 በመቶ በላይ ስለሚያስፈልግና በዕለቱ የተገኘው ግን 38 በመቶ አካባቢ በመሆኑ ድንገተኛው ጠቅላላ ጉባዔ አልተካሄደም፡፡

ስለሆነም በሕጉ መሠረት ለድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ድጋሚ እንዲጠራ ተወስኗል፡፡ በዕለቱ ለድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔው ሊቀርብ የነበረው አጀንዳ በማኅበሩ የመመሥረቻና የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች መካከል ለመሻሻል የሚገባቸውን ማሻሻል እንደነበር ታውቋል፡፡     

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ሁለት ግለሰቦች የገዙትን አክሲዮን እንዲመለስላቸው በመጠየቃቸው በመወያያ ለአጀንዳነት እንዲያዝ ያቀረቡት ጥያቄ በጠቅላላ ጉባዔው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ከ5,400 በላይ ባለአክሲዮኖችን ያቀፈ ሲሆን፣ ወደ 90 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውን አክሲዮኖችንም ሸጧል፡፡