ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጣው ቡድን በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በኢሉባቦር ዞን በመቱ ወረዳ በሚገኙ በልዩ ልዩ ቀበሌዎች፣ በቬቲቫር ሳር አማካይነት የተከናወነውን የአፈርና ውኃ ጥበቃና የውኃ አዘል መሬቶችን እንክብካቤ ሥራ አስመልክቶ ግምገማ ባደረገበት ወቅት ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ሥልጠናው ትኩረት ያደረገው ኅብረተሰቡ በልማቱ ሥራ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ለማድረግ ነው፡፡
‹‹የአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ችግር መንስዔው መሬቱ ምርታማነቱን ማጣቱ ነው፤›› ያሉት አቶ ሀብቱ፣ ይህን ዓይነቱ መሬት ወደ ምርታማነት መመለስ እንዳለበትና ለዚህም ስኬታማነት የተፋሰስ ልማት በዋነኝነት አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በተጠቀሱት ንዑስ ተፋሰሶች ውስጥ ከሚከናወኑት በርካታና ልዩ ልዩ የልማት ተግባራት መካከል የአፈርና የውኃ ጥበቃ፣ እርጥበት ወይም ውኃ አዘል መሬቶችን የመጠበቅና የመንከባከብ፣ ደን ተከላ፣ የክትርና እርከን ሥራ፣ ወዘተ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተፋሰስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የምዕራብ ዝዋይ ሐይቅ ተፋሰስ ልማት አስተባባሪ አቶ አስማማው ቁሜ ‹‹በመላ አገሪቱ እስከዛሬ ድረስ የተገነቡትንና ወደፊትም የሚገነቡ የውኃ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ ዕድሜያቸው ወይም የአገልግሎት ዘመናቸውን ለማራዘም የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቦቻቸውንና ኩሬዎችን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ግድቦቹና ኩሬዎቹ ከተሞሉ የሚይዙት የውኃ መጠን አነስተኛ ይሆንና የኤሌክትሪክ ማመንጫዎቹ ተሰነካክለው ይቀራሉ፤›› ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ችግር ለማስወገድ የሚያስችል ዘላቂ የሆነ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ወይም የተፋሰስ ልማት ሥራን፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለማከናወን የሚረዳ ስትራቴጂ በመቀየስ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለስትራቴጂውም መፋጠንና ተግባራዊነት ብሔራዊ የተፋሰስ ልማት ኮሚቴ በማቋቋም ቢጋር በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ተሞክሮ ውጤታማ የሆነውና በጋራ የሚካሄደው ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ የተፈጠሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተከናወነበት ቴክኖሎጂ፣ ለውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትልቅ ግብዓት ሆኖ መገኘቱን ከአስተባባሪው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ተመራማሪዎችን፣ የእርሻ ባለሙያዎችንና ጋዜጠኞችን ያቀፈው ይህው ቡድን ጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ግምገማውን ያካሄደው የሥነ ሕዝብ፣ ጤናና የአካባቢ ጥበቃ ጥምረት አባል የሆነው ኢትዮ ዌት ላንድስ ኤንድ ናቹራል አሶሴሽን ማኅበረሰቡን አሳታፊ በሆነ መንገድና ቬቲቫር ሳርን በመጠቀም ያከናወነውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን በመጐብኘት፣ እንዲሁም በዚሁ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮችን በማነጋገርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት በማካሄድ ነው፡፡
የኢትዮ ዌት ላንድስ ኤንድ ናቹራል አሶሴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አፈወርቅ ኃይሉ፣ ‹‹ውኃ አዘል ወይም እርጥበታማ ቦታዎችን የሚመለከት ፖሊሲ አገሪቱ እንዲኖራት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ተከናውኗል፡፡ በዚህ ዓመት ሕግ ሆኖ ይወጣል የሚል እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡
አሶሴሽኑ በአሁኑ ጊዜ በሦስት ክልሎች ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንና ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው በኦሮሚያ ክልል አራት ወረዳዎች በመካሄድ ላይ ያለው ልማት የቡና አርሶ አደሮችን የሚደግፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በአማራ ክልል ፎገራ ወረዳ ሲሆን፣ በዚህም እርጥበታማ መሬት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ማኔጅመንት የሚል ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሶችና ሕዝቦች ክልል በደንና በጫካ ቡና ላይ ትኩረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን አሶሴሽኑ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኅብረተሰቡን አሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉት እነዚሁ ፕሮጀክቶች የሚንቀሳቀሱት፣ በውጭ አገር ከሚገኙ አንድ ዩኒቨርሲቲና ተቋም ጋር በመተጋገዝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ አፈወርቅ አባባል ከሆነ፣ ቬቲቫር ወይም የሳር እፅዋት ሦስት ዝርያዎች አሉት፡፡ እነርሱም የህንድ፣ የካምቦዲያና የቬትናም ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ ዝርያዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ በመሰራጨት ላይ ያለው ለአካባቢ በጣም ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ የህንድ ዝርያ የሆነውን ቬቲቫር ሳር ነው፡፡ በ70 አገሮችም ተስፋፍቷል፡፡
ቬቲቫር ወይም የእፅዋት ወይም የውኃ ውስጥ ሳር ቋሚ ተክል ሲሆን፣ የተለያየ የአየር ፀባይንና እሳትን መቋቋም እንደሚችል፣ የወራሪነት ባህሪ እንደሌለው፣ ከመሬት በላይ እስከ ሁለት ሜትር እንደሚበቅል፣ ወደታች ደግሞ እስከ አምስት ሜትር እንደሚዘልቅ አስረድተዋል፡፡ ዝናብ ሲዘንብ ውኃ መሬት ውስጥ እንዲቆይ፣ ውኃ አዘል መሬቶች እንዲያገግሙ የማድረግ፣ የመንገድ ዳርቻን ከመናድ የመከላከልና የቆሸሸን ውኃ የማፅዳት ችሎታ እንዳለው ከአቶ አፈወርቅ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህን ዓይነቱ ልማት በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ ውጤታማ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሌላው በተለየ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ሊከሰትበት የሚችልበት አካባቢ ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ያለበትና አፈሩ ደግሞ በቀላሉ ተጠራርጎ ሊወሰድ የሚችል በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ግምት ውስጥ አስገብቶ ችግሩ ከመምጣቱ በፊት በቬቲቫር ሳር መከላከሉ ብልህነት መሆኑን አቶ አፈወርቅ ተናግረዋል፡፡
‹‹የቬቲቫር ሳር ለሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደ ብቸኛ መፍትሔ ወይም እንደ መጨረሻ አማራጭ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን በዚሁ ሳር የተወሰኑ አካባቢዎችን ማዳን የሚቻል መሆኑን በተጨባጭ መናገር ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
በመቱ ወረዳ የቬቲቫር ሳር በመትከል ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል የአዲሌ ቢሴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተገኝ ተወልደ፣ ሰለሞን ሙሉጌታና ደምሴ ዓለሙ ይህንኑ ሳር ለአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ከማዋላቸውም ባሻገር ለቤት ጣርያ ክዳን፣ ለከብት መኖና ለጉዝጓዝ እንደሚገለገሉበት፣ የተወሰነውንም ለሌለው እየሸጡ ተጨማሪ ገቢ እንዳስገኘላቸውና በዚህም የዕለት ችግራቸውን እንደሚወጡበት አስረድተዋል፡፡
ሳሩ ከጎተራ ሥርና አፍ ላይ በመጐዝጐዝ እህል ከነቀዝ እንዲጠበቅና በዝናብ ከመበስበስ እንዲድን አድርጓል፡፡ በእርሻ ማሳቸው ዙርያ ተክለው አፈሩና የተዘራው ሰብል በጎርፍ ኃይል ተሸርሽሮ እንዳይወሰድ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር ተገኝ የቬቲቫር ሳር ከመጠቀማቸው በፊት አፈሩና ሰብሉ በጐርፍ እየተወሰደባቸው ለፍቶ መና ሆነው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ሳሩን መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ግን እስከ አራት ጐተራ (ጐምቢሳ) ምርት አግኝተዋል፡፡ አርሶ አደር ሰለሞንም ከሁለት ሔክታር መሬት ላይ 90 ኩንታል የማምረት አቅም እንደተፈጠረላቸው አስረድተዋል፡፡


