Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

የበዴሳ ጅብ ሰለባው አፍና አፍንጫው ተስተካከለለት

  • PDF

•    በአሜሪካ የሚያሳድገው ቤተሰብ አግኝቷል

ሐቻምና በምሥራቅ ሐረርጌ በዴሳ አካባቢ፤ የላይኛው ከንፈሩን፣ መንጋጋውንና አፍንጫውን በሙሉ በጅብ ተበጭቆ በስቃይ ላይ የነበረው ሕፃን ሲሳይ ሽመልስ፤ በአሜሪካ በተደረገለት ቀዶ ሕክምና ፊቱ ተስተካከለለት፡፡ በአሜሪካ የሚያሳድጉትና የሚያስተምሩት አሜሪካውያን ቤተሰቦችም አግኝቷል፡፡

የኆኅተ ተስፋ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ በሆነችው አርቲስት ቻቺ ታደሰ አነሣሽነት፤ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ከጓደኛቸው ጋር በመሆን ቅዱስ ያሬድ ሆስፒታልን በመክፈትና በመሥራት ላይ በሚገኙት ዶ/ር አከዛ ጠዓመ ተባባሪነት ወደ አሜሪካ ሄዶ የመታከም ዕድል ያገኘው ሕፃን ሲሳይ፤ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝና በአሜሪካም የሚያሳድጉት ቤተሰቦች ማግኘቱን አርቲስት ቻቺ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

“መረዳዳትና ቤተሰባዊ ፍቅር ማለት ይህ ነው፡፡ ችግረኛና የተጐዱ ሕፃናትን መርዳት፣ ማገዝና የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው መተባበር ያስፈልጋል፡፡ ሕፃን ሲሳይ ከችግረኛ ቤተሰብ የወጣ ነው፡፡ በጅብ ሲበላ ቤተሰቦቹ ሊያሳክሙበት የሚያስችል ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡ ሕፃኑ ከደረሰበት ጉዳት አንፃር በኢትዮጵያ ሊታከም የሚችልም አልነበረም፡፡ በአገር ውስጥና በአሜሪካ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም አሜሪካውያን ዶክተሮች በመተባበራቸው ሕፃኑን ለመታደግ ችለናል፡፡ ሊወድቁ ያሉትን ማንሣትና መለወጥ የኛ አቅሙ ያለን ፈንታ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ሰብዓዊነት ያስደስተኛል፤” ስትል አርቲስት ቻቺ ተናግራለች፡፡

ሕፃን ሲሳይ ተጫዋች፣ ደፋርና ከሁሉ የሚግባባ ልጅ ነው፤ ዕድለኛም ነው፡፡ በአሜሪካ ተምሮ ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ ተስፋ አለኝ የምትለው አርቲስት ቻቺ፤ የሕፃን ሲሳይን ጉዳት ለማከም ብሎም የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው ለማስቻል በአሜሪካ በነበረው ቆይታ በተለይ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆነው ዶ/ር አዳም ዋቅሶር ትልቁን መስዋዕትነት መክፈሉን ተናግራለች፡፡

ዶ/ር አከዛም የሕፃን ሲሳይን፣ የአባቱን የአቶ ሽመልስና የቻቺን ሙሉ የአሜሪካ ጉዞ ወጪ ሸፍነዋል፡፡ አሜሪካ እስከሚሄድ ድረስ በሆስፒታላቸው በኋላም ከቻቺ ጋር በመሆን አዲስ አበባ ውስጥ ቤት በመከራየት እርዳታ ሲያደርጉለትም ቆይተዋል፡፡

አርቲስት ቻቺ እንደምትለው፤ የሕፃን ሲሳይ ቤተሰቦች የሚያሳድጓቸው አምስት ልጆች አሏቸው፡፡ ችግረኛና አቶ ሽመልስ ሠርተው በሚያመጡት ብቻም የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ የነሱ ሕይወት ባልተስተካከለበት ደግሞ አሜሪካ ለሕክምና የሄደውን ሕፃን ሲሳይ መልሶ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ሕይወቱን አይለውጠውም፡፡ ይልቁንም በአሜሪካ ቢማር ለአገሩም፣ ለወገኑም የሚጠቅም ዜጋ ማድረግ ይቻላል፡፡ በመሆኑም በአሜሪካ የሚያሳድጉት ወላጆች ለመፈለግ በድረ ገጽ ታሪኩ ተለቀቀ፡፡ “በጅብ የተበላውን የፈቱን ገጽታ ቀየርን እንጂ ሕይወቱን አልቀየርንም፡፡ በመሆኑም እዛው የሚኖርበትንና የሚማርበትን መንገድ እንዲያመቻቹለት ለዶ/ር አዳም ነገርኩት፡፡”

የሕፃን ሲሳይ ታሪክ ሲሰማ፤ ሊያኖሩት የሚፈልጉ አሜሪካውያን ብቅ አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችም ገንዘብ ለገሱ፡፡ ሕፃን ሲሳይ ለሚያሳድጉት አሜሪካውያን ቤተሰብ እንዲሰጥ፤ አብረውት የተጓዙት አባቱ አቶ ሽመልስ በሕጋዊ መንገድ መፍቀዳቸውንና እሳቸውም ከዘጠኝ ወራት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በሰላም ወደቀያቸው መመለሳቸውን አርቲስት ቻቺ ተናግራለች፡፡

በሌላ በኩል፤ የሕፃን ሲሳይ ቤተሰቦች ችግረኛ በመሆናቸው፤ ሕፃን ሲሳይን አስመልክቶ በድረ ገጽ ከተደረገ ገቢ ማሰባሰቢያ በተገኘ ገንዘብ፤ ለእናቱ ሱቅ፣ ለአባቱ ደግሞ ከጓደኛቸው ጋር በጋራ የሚሠሩት የከብት መኖ ማቀናበሪያ እንደተከፈተላቸውና መኖርያ ቤታቸውም ተስተካክሎ እንደተሠራላቸውም ገልጻለች፡፡

በአሜሪካ ፔንሴልቪንያና ኒውዮርክ ሕክምና የተደረገለት ሕፃን ሲሳይ፤ የሕክምና ወጪው እስከ መቶ ሺሕ ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ዶ/ር አከዛ ተናግረው ነበር፡፡ ሕፃን ሲሳይ የካቲት 24 ቀን 2002 ዓ.ም. በጅብ ጉዳት እንደደረሰበት፣ በአገር ውስጥ ሕክምና ሊድን እንደማይችል፤ ውጭ መሄድ እንዳለበትና ለዚህም አቅሙ ያላቸው እንዲረዱት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የአሜሪካ ዜጐች የሕጻኑን ሕይወት ለመታደግ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናዋን ያቀረበችው አርቲስት ቻቺ በቀጣይም ለተጐዱና ረጂ ለሌላቸው ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸው አገሬው ተባብሮ ሰብአዊ እርዳታውን እንዲለግስ ጥሪ አቅርባለች፡፡