“ጉልበት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ለኢትዮጵያ ትልቁ ሀብቷም የጉልበት ዋጋ ነው፡፡ በመሆኑም ዓረቦች ለሥራ በሚሄዱ ሴቶች ላይ ሊፈነጩ አይገባም፡፡
ለዓረቦች ሀብታቸው ጋዝ ነው፡፡ ለኛ ደግሞ ጉልበት፡፡ ጉልበት ሥርዓቱን ጠብቆ ጥቅም ላይ ከዋለ ዋጋው ከነዳጅ አይተናነስም፡፡ ቀጥሬ እስካሠራሁ ድረስ ትረገጣለች የሚለውን አልስማማበትም፡፡ ክፍያው፣ ጉልበቱና የሰብዓዊ መብት አያያዙ እስከተመጣጠነ ብቻ ነው ሴቶቻችን ከአገር ወጥተው መሥራት ያለባቸው፡፡”
ይህን ያሉት ወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ሕዝቅኤል ዋና መሥርያ ቤቱን በሲያትል ያደረገው ዮናይትድ ሆፕ ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ከአሜሪካ በመምጣት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመታደግ በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍተው መሥራት ከጀመሩ ጊዜ አንሥቶ ለመገንዘብ የቻሉት፣ ዓረብ አገር የሚሄዱ ሴቶች የሚደርስባቸውን እንግልትና ስቃይ ለመቀነስ፤ ብሎም ከአገር ወጥተው የሚሠሩበት ቦታ እስኪደርሱ ያለውን አካሄድ ሕጋዊ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ ይህንንም ያህል ለውጥ አለማምጣቱን ነው፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በኤጀንሲዎች፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ የሺመቤት፤ ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንፃር ችግሩን መታደግ አልተቻለም፣ አሁንም በዓረብ አገሮች የሚሠሩ ሴቶች መብታቸው ተረግጦ በስቃይና በሰቆቃ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ሕገወጥ የሰው ዝውውርን ለመቀነስ ዲያስፖራው ተሳታፊ እንዲሆን በመንግሥት በኩል ፍላጐት አለ፡፡ ዲያስፖራውም አብሮ ሊሠራ ይችላል፡፡ ሆኖም የሚቋቋሙ ድርጅቶች አገራዊ ሆነው ከተመዘገቡ መንግሥት ባስቀመጠው መመርያ መሠረት ገቢያቸው አሥር በመቶ ከውጭ፤ 90 በመቶ ከአገር ውስጥ የሚለው መከለስ ካልቻለ፤ ዘርፉ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ገንዘብ አንፃር ችግሩን ለመቅረፍ ያዳግታልም ብለዋል፡፡
ሴቷ በምትሠራበት መካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ስትጐዳ ወደ አገሯ ለመመለስ ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ደግሞ ከአገር ውስጥ በሚሰባሰብ ገንዘብ መወጣት ይቻላል ብዬ አላስብም የሚሉት ወ/ሮ የሺመቤት፣ ኅብረተሰቡ በድርጅት ደረጃ የመርዳት ባህሉ ባልዳበረበት፤ በመንግሥት በኩልም የገንዘብ ዕርዳታ ለሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የታክስ ማበረታቻ በሌለበት ማኅበራዊ ችግሮችን መታደግ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በኤጀንሲዎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን ዓረብ አገር የሚሄዱ ሴቶችን በተመለከተ አገሮች የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ኢትዮጵያ ሸክም የሆነ ችግር ይገጥማታል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል አንዳንድ ዓረብ አገሮች ከ25 ዓመት በላይ ያልሆነች ሴት ለሥራ የማይቀበሉ ቢሆንም፣ ዕድሜያቸው 20 ያልሞሉት ሁሉ የውሸት ዕድሜ እየሞሉ እንደሚሄዱ የሚገልጹት ወ/ሮ የሺመቤት፣ በኢትዮጵያ በኩል የመንግሥት ጣልቃገብነት ኖሮ ከአገር ቤት ጀምሮ የሚሠሩ ስህተቶችን ማረም ይገባልም ብለዋል፡፡
በድርጅታቸው በኩል ባደረጉት ጥናትና በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመሥርተው በሠሩት ዶክመንተሪ ፊልም፤ ሴቷ ከአገሯ በሕጋዊ የሂደት መረብ ብትነሣም ከአገሯ ስትወጣ ወዲያውኑ ሕገወጥ የአሠራር መረብ ውስጥ እንደምትወድቅ፣ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ጭምር ሕገወጥ አሠራር ውስጥ ተሳታፊ እንደሆኑም ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
“እውቀቱና አቅሙ ያለው ዲያስፖራ በየአገሩ ለሥራም ሆነ ለኑሮ ሲዘዋወር የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እየተጐዱ እንደሆነ ያያል፡፡ አኗኗሩንም ያውቀዋል፡፡ እኔም የሰማሁትን ሳይሆን ያየሁትን እየተናገርኩ ነው፡፡ እህቶቻችን ከጥቂቶቹ በስተቀር በሰቆቃ ውስጥ ናቸው፡፡ መንግሥት ከዲያስፖራው ጋር ለመሥራት ሁኔታዎችን አመቻችቶ ችግሩን በጊዜው መቅረፍ ያስፈልጋል፤” ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
መንግሥት ማለት ሕዝብ፣ ሕዝብ ማለት መንግሥት እስከሆነ ድረስ ሕገወጥ የሰው ዝውውርን ለመቀነስ ከፍተኛ የመንግሥት ጣልቃገብነት እንደሚያስፈልግ ያሰምሩበታል፡፡ ፊሊፒንስም ፊሊፒናውያን ለመታደግ የቻለችው መንግሥት ባደረገው ጣልቃ ገብነት ነው፡፡
“ሴቷ በኤጀንሲዎች በኩል ሄዳ መብቷ ይጠበቃል ወይም በነፃ ትሄዳለች ማለት ወሬ ነው፡፡ ሠራተኛ የሚፈልጉ አገሮች በመንግሥት ደረጃ እንዲጠይቁ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም እንደ መንግሥት እንዲልክ አቅጣጫ መቀየስ ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩ የሰው ጉልበትና ሕይወት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ለግል ኤጀንሲዎች ዕድል ተሰጥቷል፡፡ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር እንዲሠሩም እየተደረገ ነው፡፡ ሴቶቹ ከአገር ሲወጡ ያለው ታሪክ ግን ሌላ ነው፡፡ አሠራሩ ተሳክቷል ብዬ አልልም፤” የሚል አመለካከትም አላቸው፡፡
መንግሥት ብቻውን መወጣት ይችላል? ስንል ጥያቄ አንሥተን ነበር፡፡ መንግሥት በራሱም ባይሠራው ከሌሎች መንግሥታት ለሚቀርብለት የጉልበት ጥያቄ ኃላፊነቱን ወስዶ ጨረታ ማውጣት ይችላል፡፡ ለዚህ የራሱ ሚኒስቴርና መዋቅር ያስፈልገዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ትልቅ የገቢ ምንጭ የሆነውን የጉልበት ዋጋ መጠቀም የሚቻለውም ይህ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
“በዓረብ አገሮች ብዙ ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡ ሥራ ከጀመርኩ ስድሰት ዓመት ሆኖኛል፡፡ ባብዛኛው የማየው መስዋዕትነትን እንጂ ውጤትን አይደለም፡፡ በተደጋጋሚም ተናግሬያለሁ፡፡ የመጣ ለውጥ የለም” የሚሉት ወ/ሮ የሺመቤት፣ ሕገወጥ የሰው ዝውውርን ከታች ጀምሮ ለመከላከል፤ ሴቶቹ ዓረብ አገር ሲጐዱ ለመታደግ ድርጅታቸው የሚሠራ ቢሆንም ከመንግሥት ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ከሌለ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡
የሴቶችን አቅም ለመገንባት የሚያስችል የሥልጠና ማዕከል ለማቋቋም እየሞከሩ ሲሆን፣ ማዕከሉን ለመገንባት ገንዘብ ለመስጠት ቃል የገቡላቸው ቢኖሩም፤ በድርጅቱ ብቻ እንዲሠራና እንዲተዳደር አልፈለጉም፡፡ ከመንግሥት ጋር አብረው መሥራት፤ ሥራው ቀጣይ እንዲሆን ያስችላል፤ ቋሚም ያደርገዋል ብለው ስላመኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ ነው፡፡
ወደ ዓረብ አገሮች የምትሄድ ሴት ቢያንስ አምስተኛ ክፍል የደረሰች፣ መሠረታዊ የሆኑ ሥራዎችንና የዕቃ አጠቃቀሞችን የምታውቅ ብትሆን ይመረጣል የሚሉት ወ/ሮ የሺመቤት፣ “ኢትዮጵያዊቷ በዱባይ የዓረብ ሴቶች ከላይ የሚለብሱትን ልብስ ስትተኩስ አቃጠለችው፡፡ ይህ የሆነው ካውያው ላይ ያለውን ማመጣጠኛ ማንበብ ባለመቻሏ ነበር፡፡ ልብሱ ሲቃጠል ያየችው አሠሪዋ የተቃጠለውን ጨርቅ አንሥታ ፊቷ ላይ መታቻት፡፡ በኋላ ስትጠየቅ 7 ሺሕ ድራሀም አውጥቼበታለሁ ነበር ያለችው፤›› ብለው የገጠማቸውን በማስታወስ በአሠሪዎች የማይፈረድበት አጋጣሚም እንዳለም ይናገራሉ፡፡


