Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

ኢትዮጵያ 35 ሺሕ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞችን ተቀበለች

  • PDF

በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ 35 ሺሕ ያህል ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኗን ኢትዮጵያ ማስታወቋን ኢዜአ ዘገበ፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ስደተኞች ችግራቸው እስኪቃለል ተቀብላ የምታስተናግድ መሆኗን፣ በስደተኞች ላይ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከለጋሾች ጋር በትብብር በመሥራት ዘላቂ መፍትሔና ድጋፍ እየሰጠች መሆኑንም ዘገባው ያስረዳል፡፡

አገሪቱ ከአገራቸው ተፈናቅለው የሚሰደዱ ወገኖችን ተቀብሎ የማስተናገድ ባህል እንዳላት፣ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ አሁንም ድረስ የዘለቀ ባህል እንደሆነ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ከትናንት በስቲያ በ2011 ሪፖርት አዲስ አበባ ውስጥ ይፋ ሲደረግ መግለጻቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚገቡ ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል ፖሊሲ መቅረፁንና በዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡ ድርጅቱ በዓለም አቀፍ፣ በአህጉራዊና በአገር ደረጃ ተፈናቃይ ወገኖችና ስደተኛ ዜጎችን ወደ ትውልድና መኖሪያ አካባቢያቸው ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ሚኒስትሩ ማድነቃቸውን ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡

በተለይ በቅርቡ በየመንና በሊቢያ በተቀሰቀሱት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለጥቃት የተጋለጡ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው በመመለስ ረገድ ድርጅቱ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም አስረድተዋል፡፡ በድርጅቱ ሪፖርት መሠረት በመላው ዓለም በአሁኑ ወቅት 214 ሚሊዮን ስደተኞች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡