Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

ለዋጋ ንረቱ የብሔራዊ ባንክ ሚና ምን መሆን አለበት?

  • PDF

በአብዱልአዚዝ በህሩ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት በብዙ ረገድ አወንታዊ እመርታዎችን አሳይቷል። በዕድገቱ ትክክለኛ አኅዝ ላይ ውዝግብ ቢኖርም፣ ኢኮኖሚው ዕድገት ማስመዝገቡን ግን ብዙ ወገኖች ይስማማሉ። በመሠረተ ልማት መስፋፋት በኩልም አበረታች የሚባል እመርታ ታይቷል። እንደ ጤናና ትምህርት ባሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋትም ላይ እንዲሁ አመርቂ ውጤቶች ተመዝገበዋል።

የኢንዱስትሪው መስክም በተለይ በቆዳና በጨርቃጨርቅ መስኮች አበረታች የሆኑ ማቆጥቆጦች ታይተዋል። በማዕድኑ፣ በግብርናውና በውጭ ንግዱም እንዲሁ። በአንፃሩ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ አለመረጋጋትና ንረት በኢኮኖሚው ላይ ጥላውን አጥልቶ ቆይቷል። የዋጋ ንረቱ ከፍተኛነት ኢትዮጵያን ቅጥ ባጣ የዋጋ ንረት ሳቢያ የራሷን ገንዘብ መጠቀም ሙሉ ለሙሉ ከተወችው ዚምባብዌ ቀጥሎ በሁለተኛነት አሰልፏታል። የዋጋው ንረት በብዙው ሰው ኑሮ ላይና በአጠቃላይም በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት የሚያደርስ ክስተት ነው።

ንረቱ ብዙውን ጊዜ በትሩን ያሳረፈው ደግሞ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰቡ አካላት ላይ ነው። በዚህ ዓመት በነበረው ወደ 40 በመቶ የዋጋ ንረት ብቻ በቋሚ ደመወዝ በሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በዓመት ውስጥ የሦስት ወራት ደመወዝ እንደማጣት ነው። ንረቱ ኢኮኖሚው እያደገም ብዙ ሰዎች እንዲደኸዩ ምክንያት ሆኗል። ንረቱ በኢኮኖሚ ዕድገቱም ላይ በሁለት ዋንኛ ምክንያቶች ሳቢያ ጫና ይፈጥራል። አንደኛ ሰዎች በዋጋዎች ላይ እምነት ስለማይኖራቸው የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለማውጣትና የረጅም ጊዜ የግብይት ውሎች ውስጥ ለመግባት ይቸገራሉ (በዋጋ መዋዠቅ ምክንያት እንዳይከስሩ ስለሚሰጉ)። ይህ ደግሞ ለዕድገት መሠረት የሆኑትን የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንቶችን አዳጋች ያደርጋቸዋል። የዋጋ ንረት በዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የኤክስፖርት ሴክተሩን ስለሚጎዳ ነው። የዋጋ ንረት ሲኖር ኤክስፖርተሮች ወደ ውጭ የሚልኩዋቸው ዕቃዎች አገር ውስጥ ይወደድባቸዋል (አሁን ባለው የብሔራዊ ባንክ አሠራር መሠረት ምንዛሪው በዋጋ ንረቱ ልክ ስለማይቀየር)። የ40 በመቶ የዋጋ ንረት አለ ማለት የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ዘርፍ ከሌሎች አገሮች አንፃር በአማካይ የ40 በመቶ ተጨማሪ ወጪ ይጠብቀዋል ማለት ነው። ይህም ለዕድገት ወሳኝ የሆነውን ዘርፍ በተወዳዳሪነት አቅሙ ላይ ምን ያህል ጫና እንደሚፈጥር መገመት አያዳግትም።

ስለዋጋ ንረቱ መነሻና መፍትሔ በርካታ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል። በዚህ ጽሑፌም የዋጋ ንረትን በተመለከተ በሚደረጉ ውይይቶች ውስጥ የተስተዋለ የሚመስለኝንና መሠረታዊና ወደተሳሳተ ፖሊሲ ሊመራ የሚችልን የግንዛቤ ክፍተት ለማሳየት እሞክራለሁ። የግንዛቤው ክፍተት የሚመነጨውም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ንረቱን ያስከተሉትን ክስተቶች ማወቅ አለብን ከሚለው የተሳሳተ ታሳቢ ነው። ቀጥሎ እንደማሳየው የዋጋ ንረትን ለመግታት ንረቱን ያስከተሉትን ክስተቶች ማወቅ አይጠበቅብንም። ይህ ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙት ግራ አጋቢ ቢመስልም እንዴት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ብዙም አዳጋች አይደለም። በአሁኑ ጊዜም በዋጋ ንረት ላይ የሚሠሩ የመስኩ ምሁራን (Monetary Economists) በአብዛኛው የሚቀበሉት አስተሳሰብ ነው። በዓለማችን የሚገኙ ብዙ ማዕከላዊ/ብሔራዊ ባንኮችም በዚህ አስተሳሰብ ነው የሚመሩት። ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት በተጨባጭ የታዩ ልምዶችን ያጠኑ ኢኮኖሚስቶችም፣ የዋጋ መረጋጋትን ከማስፈን አንፃር ይህ አስተሳሰብ ውጤታማ እንደሆነም አረጋግጠዋል። አስተሳሰቡ የሚያተኩረውም በብሔራዊ ባንኩ ሚና ላይ ነው። እንደሚታወቀው የብሔራዊ ባንክ ዋና ኃላፊነት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ነው።

የዋጋ ንረት ምንነትንና መሠረታዊ መንስዔዎቹን ባጭሩ እዳስሳለሁ። ቀጥሎም የዋጋ ንረቱ መንስዔ ምንም ይሁን ምን ማዕከላዊ ባንኩ ያለው ብቸኛ አማራጭ የገንዘብ ዝውውርን መቆጣጠር እንደሆነና ይህንንም ማድረግ እንዳለበት አብራራለሁ። ብዙ ጊዜ ብሔራዊ ባንኩ የገንዘብ መጠንን በመቀነስ የዋጋ ንረት መቆጣጠሩን የሚቃወሙ ወገኖች የሚያነሱት መከራረከሪያ፣ ‹‹የዋጋ ንረቱ የተከሰተው በገንዘብ መብዛት አይደለም›› የሚል ነው። በአንፃሩ፤ ባንኩ የገንዘብ መጠንን መቀነስ አለበት የሚሉ ወገኖች ደግሞ እንደመከራከሪያ የሚያነሱት፣ ‹‹ለዋጋ ንረቱ ዋንኛው ምክንያት የገንዘብ መብዛት ነው›› የሚል ነው። ወደኋላ እንደማሳየው ሁለቱም ወገኖች የሚሳሳቱት፣ ‹‹የዋጋ ንረትን የገንዘብ መጠንን በመቀነስ መቆጣጠር ያለብን የዋጋ ንረቱ በገንዘብ መብዛት የተከሰተ ከሆነ ነው›› ከሚለው ታሳቢያቸው (Assumption) ነው። ትክክለኛው አካሄድ ግን የዋጋ ንረቱ የተከሰተው በአንድም ይሁን በሌላ ክስተት (ለምሳሌ የነዳጅ መወደድ፣ የሕዝብ ቁጥር መብዛት፣ የምርት መቀነስ፣ የዓለም አቀፍ ዋጋዎች ለውጥ፣ ወዘተ)፣ የብሔራዊ ባንኩ ምላሽ መሆን ያለበት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን መቀነስ ብቻ ነው። ስለዚህ የዋጋ ንረት ሲከሰት ንረቱ የተከሰተበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ባንኩ ንረቱን ለመግታት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን መቀነስ አለበት። በሌላ አባባል፤ የዋጋ ንረት ሲከሰት ‹‹ንረቱን ያመጣው የገንዘብ መብዛት አይደለምና የገንዘብ ብዛትን መቀነስ የለብንም›› የሚለው መከራከሪያ ስህተት ነው። ንረቱ የተከሰተው በገንዘብ መብዛት ባይሆንም እንኳን፣ የገንዘብ መጠንን በመቀነስ ንረትን መቆጣጠር ያስፈልጋል። ትክክለኛ ፖሊሲም ነው። የጽሑፌም ዋንኛ ዓላማም ይህን ማስገንዘብ ነው።

1. የዋጋ ንረት ምንነትና መንስዔዎቹ
የዋጋ ንረት ምንድነው? ይህ ጥያቄ በአንድ በኩል በጣም ቀላል ነው፤ ሁላችንም የዋጋ ንረት ምንነትን በኑሮዋችን ውስጥ በሚፈጥረው መመሳቀል የምናቀው ስለሆነ። በሌላ በኩል ደግሞ ስለዋጋ ንረት የተሳሳተ ግንዛቤ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ለዚህ ጥያቄ ከምንሰጠው መልስ ነው። የዋጋ ንረት ስንል የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ማለታችን ነው። የጥቂት ዕቃዎች ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረት አይባልም። ለምሳሌ ጤፍ በጣም ተወዶ ስንዴና በቆሎ ቢረክሱ የዋጋ ንረት የለም ልንል እንችላለን። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ገንዘብ ጤፍ የመግዛት አቅሙ ቢዳከምም፣ ስንዴና በቆሎ የመግዛት አቅሙ ግን ተጠናክርዋል። ስለዚህ በአማካይ ስናስበው የገንዘብ ዋጋ ላይዳከም ይችላል። በአንፃሩ የጤፉም፣ የስንዴም፣ የበቆሎውም፣ ወዘተ ዋጋዎች በሙሉ ቢንሩ የዋጋ ንረት አለ ማለት እንችላለን። ምክንያቱም ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከብዙ ዕቃዎች አንፃር ስለተዳከመ። ስለዚህ የዋጋ ንረት መሠረታዊ ትርጉም የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ነው።

የዋጋ ንረት ስንል የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ነው ካልን፣ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው፣ ‹‹የገንዘብ የመግዛት አቅም የሚዳከምበት ምክንያት ምንድነው?›› የሚል ነው። የገንዘብ የመግዛት አቅምን የሚያዳክሙ አራት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን መብዛት ነው። ሁለተኛው ምክንያት ኢኮኖሚው ውስጥ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ፍጥነት ሲጨምር ነው። ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ በአገር ውስጥ የሚመረተው የምርት መጠን መቀነስ ነው። አራተኛው ምክንያት ዓለም አቀፍ የዋጋ ለውጦች ናቸው። አራቱንም ምክንያቶች ቀጥሎ ለማየት ሞክራለሁ።

1.1 የገንዘብ መጠን
ይህ ብዙው ሰው በቀላሉ የሚገነዘበው ነው። ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የገንዘብ መጠን ሲበዛ ገንዘቡ ዋጋ ያጣል። ስለዚህ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን መቆጣጠር ያስፈልጋል። አሁን ባለው የገንዘብ ሥርዓትም መንግሥት የፈለገውን ያህል ገንዘብ አትሞ ኢኮኖሚው ውስጥ ማሰራጨት ይችላል። ወርቅም ሆነ ሌላ ነገር ማስያዝ አያስፈልገውም። ብር ማተም ፓስፖርት እንደማተም ነው። የኢትዮጵያን ፓስፖርት የማሳተም ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ነው (ባለው ሕግና ደንብ መሠረት)። ልክ እንደ ፓስፖርት ሁሉ የአገሩን ገንዘብ የማሳተም ሙሉ ሥልጣን ያለውም መንግሥት ነው። ስለዚህ መንግሥት በሚያትመው የገንዘብ መጠን ላይ በራሱ ገደብ ካላደረገ፣ ኢኮኖሚው ውስጥ ብዙ ገንዘብ ይሰራጭና ገንዘቡ ዋጋ ያጣል። መንግሥት ደግሞ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚሰራጨውን የገንዘብ መጠን ከሞላ ጎደል የሚያውቅበትና የሚቆጣጠርበት አቅም አለው። የብሔራዊ ባንኩም ግንባር ቀደም ሥራ የሚሰራጨውን የገንዘብ ብዛት መከታተልና መመጠን ነው።

1.2 ገንዘብ የሚዘዋወርበት ፍጥነት
ገንዘብ የሚዘዋወርበት ፍጥነት ስንል ገንዘብ ከአንዱ ገበያተኛ እጅ ወደ ሌላኛው እጅ የሚያደርገውን የቅብብሎሽ ብዛት ማለታችን ነው። ለምሳሌ ያህል ‹‹በአማካይ አንድ ብር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በስንት ገበያተኞች እጅ ውስጥ ያልፋል?›› ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ገንዘብ የሚዘዋወርበትን ፍጥነት ያሳየናል። የቅብብሎሹ ቁጥር ሲጨምር ገንዘብ የሚዘዋወርበት ፍጥነት ጨምሯል እንላለን። ገንዘብ የሚዘዋወርበት ፍጥነት ከጨመረ የዋጋ ንረትን ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውን ቤታቸው ውስጥ በሳጥን ቆልፈው የሚያስቀምጡ ከሆነ ገንዘብ ብዙ አይዘዋወርም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ኢኮኖሚው ውስጥ ብዙ ገንዘብ ቢኖርም የኑሮ ውድነትን ላያስከትል ይችላል። በአንፃሩ ሰዎች ያገኙትን ገንዘብ ቶሎ ለግዢ የሚጠቀሙበት ከሆነ የገንዘብ ዝውውር ፍጥነት ይጨምራል። የዝውውሩ መጨመር ደግሞ የዋጋ ንረትን ሊያስከትል ይችላል (በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ ብዛት ባይጨምርም)።

የማዕከላዊው/ብሔራዊው ባንኩ የገንዘብ ብዛትን መቆጣጠር የሚችልበት መረጃና አቅም ቢኖረውም፣ የገንዘብ የዝውውር ፍጥነትን ግን በአብዛኛው መቆጣጠር አይችልም። ይህም የሚሆንበት ምክንያት በአንድ በኩል የገንዘብ ዝውውር እጅግ ተለዋዋጭ የሆነ ክስተት ስለሆነና በምን ምክንያት እንኳን እንደተቀየረ ማወቅ አዳጋች ስለሆነ ነው። በተጨማሪም፣ የገንዘብ ዝውውሩን የቀየሩትን ምክንያቶች እንኳን ብናውቅ፣ ምክንያቶቹ ብዙ ጊዜ ከብሔራዊ ባንኩ ቁጥጥር ውጭ ናቸው። የዝውውር ፍጥነቱን ያስከተሉትን ምክንያቶች መቆጣጠርም ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝንም ይችላል። ይህን በምሳሌ ለማየት፣ የገንዘብ ዝውውርን ሊቀይሩ ከሚችሉ ምክንያቶች አንዱ የሆነውን የመገናኛ ቴክኖሎጂን እንውሰድ። የመገናኛ ቴክኖሎጂ መስፋፋት የዝውውር ፍጥነቱን ሊጨምረው ይችላል። የመገናኛ ቴክኖሎጂ ደካማ በሆነበት ጊዜ ገንዘብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ አዳጋች ነው።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ንግድ የሚያካሂዱ ኩባንያዎችም ፈጣን የመገናኛ ቴክኖሎጂ ከሌለ በየቅርንጫፍ ቢሮአቸው በርከት ያለ ገንዘብ በመጠባበቂያነት ማስቀመጥ ሊኖርባቸው ይችላል (ክፍያ ሲያስፈልግ ለመፈጸም)። የመገናኛ ቴክኖሎጂ ሲሻሻል ግን ገንዘብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወርን በደቂቃዎች ውስጥ መፈጸም ስለሚቻል፣ ኩባንያዎቹ ለእያንዳንዱ ቅርንጫፍ በርከት ያለ ገንዘብ መያዝ አያስፈልጋቸውም። አንዱ ቅርንጫፍ ገንዘብ ሲያጥረው ከሌላኛው ቅርንጫፍ በቀላሉ ማዛወር ይችላልና። እናም ኩባንያው አነስ ያለ ገንዘብ ይዞ እሱኑ በፍጥነት በማገላበጥ ግብይቱን መፈጸም ይችላል። ብሔራዊ ባንኩም እንግዲህ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች የሚያመጡትን እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ መቆጣጠር አይችልም። መቃወሙም ሆነ ለመቆጣጠር መሞከሩም ውጤታማነትም ሆነ ጠቀሜታ የለውም። የገንዘብ ዝውውር ፍጥነት የሚቀየርባቸው ምክንያቶችን ዘርዝሮ መጨረስ እንኳን ከባድ ነው። በጣም ብዙ ናቸው። በአጠቃላይ ስናየው ግን የዝውውር ፍጥነቱን የሚጨምረው ዋናው ምክንያንት ሰዎች/ድርጅቶች በእጃቸው ላይ እንዲቆይ የሚፈልጉትን የገንዘብ መጠን ሲቀንሱ ነው። ለምሳሌ ያህል ሰዎች ሀብታቸውን የሚያስቀምጡበት አማራጭ ሲያገኙ በእጃቸው መያዝ የሚፈልጉትን የገንዘብ መጠን ይቀንሳሉ።

አንዱ አማራጭ ለምሳሌ ያህል አክሲዮን መግዛት ሊሆን ይችላል። ሀብትን በገንዘብ መልክ ከመያዝ አክሲዮን መግዛት ከተሻለ ሰዎች መያዝ የሚፈልጉትን የገንዘብ መጠን ይቀንሳሉ። ይህም የገንዘብ ዝውውር እንዲጨምር ያደርጋል። የመሠረተ ልማቶች መስፋፋት ገበሬዎች ሀብታቸውን በገንዘብ መልክ ሳጥናቸው ውስጥ ከማስቀመጥ ይልቅ ሌላ አማራጭ የሚከፍትላቸው ከሆነም፣ ገበሬዎቹ መያዝ የሚፈልጉት የገንዘብ መጠን ይቀንሳል። ሌሎች ብዙ ምክንያቶችንም መዘርዘር ይቻላል። እነኚህ ሁሉ እንግዲህ የገንዘብ ዝውውርን ይጨምራሉ ማለት ነው።

1.3 የምርት አቅም
በኢኮኖሚው ውስጥ የሚመረተው የጠቅላላ ምርት ብዛት ሲጨምር የዋጋ ንረት ይቀንሳል። የገንዘቡ ብዛትና ዝውውር ሳይጨምር ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ምርት ከጨመረ፣ ዕቃ በዝቶ ገንዘብ ያንሳል። ይህም የገንዘብ ዋጋ እንዲጨምርና የዕቃ ዋጋ እንዲቀንስ ያደርጋል። የምርት መጠን መጨመርና የገንዘብ ብዛት መቀነስ በዋጋ ንረት ላይ ተመሳሳይ ውጤት ነው ያላቸው። ሁለቱም የዋጋ ንረትን ይቀንሳሉ። በአንፃሩ፤ የምርት መጠን መቀነስና የገንዘብ ብዛት መጨመር የዋጋ ንረትን ይጨምራሉ። ምርት በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀንስ ይችላል። ዝናብ ቢያንስና ድርቅ ቢከሰት የምርት መቀነስ ሊከሰት ይችላል። የንግድ ኅብረተሰቡ መደናገጥም እንዲሁ ምርትን ሊቀንስ ይችላል (እንቅስቃሴያቸውን ስለሚገድበው)። የአገር ሰላም መረበሽ፣ የመሠረተ ልማቶች መጎዳት፣ የተሳሳቱ የቁጥጥርና የታክስ ፖሊሲዎች፣ ወዘተ ምርትን ይቀንሳሉ።

1.4 የዓለም አቀፍ ዋጋዎች ተፅዕኖ
አራተኛው ምክንያት የዓለም አቀፍ ዋጋዎች ተፅዕኖ ነው። የዓለም አቀፍ ዋጋዎች በአገር ውስጥ የዋጋ ንረት ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ወሰብሰብ ያለ ነው። እኔም ይህን በተመለከተ ዝርዝር ውስጥ አልገባም። ይሁንና የዓለም አቀፍ ዋጋዎች ተፅዕኖ የጽሑፌን ዋና መደምደሚያ የሚቀይር አይደለም። በዚህ ጽሑፌ አንድ ነጥብ ግን ታሳቢ አደርጋለሁ። ይኸውም ታሳቢዬ ብሔራዊ ባንኩ የአገር ውስጥ ላኪዎች ከሌላ ተወዳዳሪዎቻቸው አንፃር እንዳይጎዱ የሚያስችላቸውን የምንዛሪ ፖሊሲ ይከተላል የሚል ነው። ማለትም ባንኩ የሚያወጣው የብር ምንዛሬ በአገር ውስጥ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ያካካሰ ይሆናል (Stable Real Exchange Rate)። የዋጋ ንረትን አካክሶ የተረጋጋ ምንዛሪም ከብሔራዊ ባንኩ የምንዛሪ ፖሊሲ ግቦች ውስጥ አንዱ በመሆኑ ይህ ታሳቢዬ የተቃርኖ ምንጭ ሊሆን አይችልም።

2. የዋጋ ንረትን መቆጣጠር
ከላይ እንዳስቀመጥኩት የዋጋ ንረት አራት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉት። ይሁንና ንረቱ የተከሰተው በየትኛውም ምክንያት ይሁን የገንዘብ መጠኑን መቀነስ የዋጋ ንረትን ይቀንሳል። ሌሎች የዓለማችን ማዕከላዊ ባንኮችም የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ሁሉም የዓለማችን ብሔራዊ ባንኮች የሚጋፈጡት እውነታ ነው። የኢትዮጵያን ዋጋ ንረት ያስከተሉት ክስተቶች ምን እንደሆኑና የእያንዳንዱ ክስተት አስተዋፅኦ ምን ያህል እንደሆን ማወቅ ቀላል አይደለም። ብዙ ጥናት ይጠይቃል። ከብዙ ጥናት በኋላም አስተማማኝ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻል ይሆናል። በአንፃሩ ንረቱን ያስከተሉትን ክስተቶች ማወቅ በራሱ ጠቃሚ ቢሆንም ንረቱን ለመከላከል ግን የግድ አይደለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረት በተከሰተ ቁጥር የገንዘብ መጠን እንደሚቀንስ የሚያረጋግጥ ግልጽ ፖሊሲ መከተል አለበት። ይህንንም ፖሊሲውን የባንኩ ባለሥልጣናት በግልጽ ለሕዝብ ማሳወቅ አለባቸው።

የዋጋ ንረት ግባቸው ስንት ፐርሰንት ነው? ሦስት በመቶ፣ አምስት በመቶ ወይስ አሥር በመቶ? ይህን ግባቸውን ለመምታት የሚከተሉት የገንዘብ ፖሊሲ ምንድነው? ፖሊሲው ግቡን የሚመታበት ምክንያት ምንድነው? የገንዘብ መጠኑ በስንት ፐርሰንት ነው እንዲያድግ የሚፈቅዱት? 10 በመቶ፣ 15 በመቶ ወይስ 20 በመቶ? ይህን ሲያደርጉ ጥናት ላይ ተንተርሶ መሆንም አለበት። ሕዝብም በገንዘቡ ላይ ይበልጥ እምነት እንዲኖረው ያስችለዋልና። ካልሆነ ግን ኢኮኖሚው ውስጥ ገበያው ያለው ሚና እየጨመረ ሲመጣ የዋጋ ትርምሱን መቆጣጠር በዚያው ልክ እየከበደ ይመጣል። የግሉ ዘርፍ ተፅዕኖ እየጨመረ ነውና የባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ ግልጽነትም መጨመር አለበት። አለበለዚያ ዋጋ ተማኙ የግል ዘርፍ ስለባንኩ ፖሊሲ ያለው እርግጠኛነት ደካማ ይሆናል። ይህም የዋጋ መዋዠቅ እንዲበዛ ያደርጋል። የብሔራዊ ባንኩ ባለሥልጣናት ሌሎች በዓለማችን ያሉ ጠንካራ ማዕከላዊ ባንኮች እንደሚያደርጉት ሁሉ ለጋዜጠኞች በየተወሰነ ጊዜ (ከሁለት እስከ አራት ወራት) መግለጫ በመስጠት ፖሊሲዎቻቸውን ግልጽ ማድረግ አለባቸው።

ከአዘጋጁ፡- አብዱልአዚዝ በህሩ በሙያቸው ማክሮ ኢኮኖሚስት ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ነው፡፡
በኢሜይል አድራሻቸው This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it ማግኘት ይቻላል።