ጉዳዩ የገባኝ የሠፈሬ ልጆች እጆቻቸውን ዩኒፎርማቸው ኪስ ውስጥ ከተው ሲሄዱና ሲመጡ ሳይ ነው። ‹‹ብላችሁ ብላችሁ ቦርሳ መያዙንም ተዋችሁት?›› ብላቸው፣ ‹‹አይ ጋሼ አንበርብር ወቅቱ እኮ የፈተና ነው፤›› አሉኝ። ‹‹ተማሪ ደብተሩን በትኖ ከመቼ ወዲህ ፈተና መቀመጥ ጀመረ?›› እያልኩ ለብቻዬ አወራሁ። መቼም የዘንድሮ ተማሪ ቦርሳ አንግቶ ወደ ትምህርት ቤት ቢጓዝም፣ ከበስተጀርባው ያለው ጉድ ብዙ ነው፡፡ ያለ ዕድሜያቸው ብዙ ነገር እያወቁ ያሳቅቃሉ፡፡
የሠፈሬ ተማሪዎች ብዛታቸው ለጉድ ነው። ግን ምን ያህሉ ተማሪ ይሁኑ ወይም አይሁኑ ጠይቄም አጣርቼም አላውቅም። ይኼን በተመለከተ ማንጠግቦሽን መጠየቅ ነው። ታዲያ ፈተና ላይ መሆናቸውን ሲነግሩኝ በዋዛ ልተዋቸው ስላልፈለግኩ የፈተናውን ድባብ ብሎም ጥሩ ውጤት ያመጡ እንደሆነ ጠየቅኳቸው። አንገታቸውን ዘንበል አድርገው ፀጉራቸውን እየጠቀለሉ፣ ‹‹ምን እባክህ ውጤትም እንደ ኑሮው ተወዷል፤›› አሉኝ፡፡ ‹‹በምን ምክንያት?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹አስኮራጅ የሚባለው አባቱ ከታመመ ቆየ፤›› ሲሉኝ መሃል አናቴ እንደተተረከከ ክው አልኩ። ‹‹እንዴት ዓይን ያወጣ ትውልድ ነው እባካችሁ? ለምን አጥንታችሁ ሞዴል ተማሪ አትባሉም?›› ብላቸው፣ ‹‹ማጥናት የፋራ ነው የተማረ የት ደረሰ?›› አይሉኝ መሰላችሁ? ‹‹የጉድ ቀን ቶሎ አይመሽ›› አለ የአገሬ ሰው። ትንሽ ከቆየሁ ‹‹አራድነት›› የሚባለው ‹‹ፍልስፍናቸው›› ናላዬን ያዞረዋል ብዬ ስላሰብኩ መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ ላጥ አልኩ። ድህነት ላይ ስንፎክር ስንፍና ተባዝቶ እንዳይመጣብን ሰጋሁ፡፡ በደላላ ዕውቀቴ ሳስበው ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› መሰለኝ፡፡
በአግራሞት ተጠምጄ ዙሪያ ገባውን፣ ሻጭና ሸማቹን፣ የሰውን ትርምስ እያስተዋልኩ መንገዴን ተያያዝኩት። የሠፈሬ ተማሪዎች ያነሱዋት ‹‹ኩረጃ›› የምትባለውን ነገር ሳስብ በእኛ በትልልቆቹም ዘንድ ዘልቆ እንደጋባ አላጣሁትም። በአብዛኛው የከተማችን ጎዳናና ሕንፃ ውስጥ የሚከፈቱት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተመሳሳይነታቸው ለጉድ ነው። አንዷ የጀበና ቡና ስትጀምር ሌላውም አጠገቧ ሄዳ ትጥድላታለች። አንዱ ፒዛ ቤት ሲከፍት ጎረቤቱ ያለው የስቴሽነሪ ንግዱን ቀይሮ ‹‹ምርጥ ፒዛ›› ብሎ ይከተላል። ለዚያ ሳይሆን አይቀርም ሬስቶራንትና ካፌው በሰው ቁጥር ያህል የተከፈተ የሚመስለው። አዲስ ነገርና ፈጠራ በእጅጉ ርቆን ስንቀዳዳ መኖር ሥራችን ሆነ። ለአፍታ ያህል ዓይናችንን ጨፍነን ብናስብ እኮ ስንትና ስንት የብልፅግና መስክ አለ? ስንዴ ሲታደል ሁሉም ንፍሮ ከሚያደርገው ቂጣ፣ ቆሎ፣ ጨጨብሳ ወይም ሌላ ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡
አሁንም እያሰብኩ ስጓዝ ሳለሁ አንድ ሥራ የሚያገናኘን ወዳጄ መንገድ ላይ አገኘኝ። ለአገር ምድሩ የሚታወቅበት መለያ ፈገግታው ጠፍቶ አቀርቅሮ ይጓዛል። ‹‹ምን ሆንክ?›› አልኩት። ‹‹እረፈው የሊዝ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ መፅደቁ ነው፤›› አለኝ። ከመልሱ እንግዳ ነገር ባጣበት፣ ‹‹ታዲያ ምን ይጠበስ?›› አልኩት። ‹‹እንዴት እንዲህ ትላለህ አንበርብር? ሥራችን እኮ ከበፊቱ የበለጠ መቀዝቀዙ እኮ ነው፡፡ ካሁን በኋላ ግን ሥራ መቀየር ነው የሚሻለው፤›› ብሎ በጥርጣሬ ተመለከተኝ። ሆሆ ደግሞ ምን መስዬ ታየሁት ይሆን? እናንተዬ ዘንድሮ እኮ ማንነታችሁን እንደ ቦሎ ግንባር ላይ መለጠፍ ብትችሉ እንኳን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ጠርጣሪና መርማሪ መሆን የማያሰኘው የለም። ሲበዛ ደግሞ ያንገፈግፋል። ኧረ ሲበዛ ማርም ይመራል።
‹‹አይዞህ እሱ የከፈተውን ጉሮሮ እሱ መሙላቱ አይቀርም። እስካሁንስ እኛ እንዳሰብነው መቼ ኖርንና? ደግሞ ምን ይጠበስ ማለቴ መንግሥት አንዴ ከተናገረ ቃሉን እንደ እግዜር ቃል እንደማይሽረው ስላየን ነው፤›› ስለው ተረጋጋ። ውጥረት ያረበበትን ኅብረተሰብ በእዝነ ህሊናዬ አየሁት። መቼም የማይለመድ የለም ስንቱን እንግዳ መሳይ ነገር ስንሆንና ስንመስል ኖረናል። እንግዲህ ይህም ከእነሱ ጋር ተደማሪ መሆኑ ነው። ግን አንዳንዱ አካሄድ በእጅጉ የሚያስተዛዝብ ነው። ባንኮቻችን፣ ‹‹ብድር እናመቻቻለን ብቻ የሚሠራ ሰው ይገኝ፤›› ሲሉ እንዳልነበሩ አሁንማ የፊት በራቸውን ዘግተው በኋላ በር መውጣት ጀምረዋል አሉ። ዝም ብዬ ይህን ሳሰላስል የማንጠግቦሽ ነገር ይመጣብኛል። የማትፈልገው ወይም ያልቀጠረችው ሰው ቤት ድንገት ከመጣ ‹‹የለችም በል›› ብላኝ በጓሮ በር ወጥታ እልም ትላለች። አንዳንድ ሹሞችም ለሚቀርብላቸው አቤቱታ ወይም ጥያቄ መልስ ሲያጡ ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው፤ አገር ውስጥ የሉም፤ ወዘተ . . . ›› እያሉ የሚጠፉት ለዚህ ይሆን?
ወዳጄን ተሰነባብቼ መንገዴን እንደቀጠልኩ በበርካታ መኪኖች ጥሩንባ የታጀበ የሠርግ ዕድምተኛ በአጠገቤ ሲያልፍ አየሁ። ሲያልፍ ሳይሆን እንደ ጅረት ሲፈስ ማለት ይቀላል፡፡ ኃይለኛ ትዝታ እየተቀሰቀሰብኝ ሙሽሮቹን ከመላው መንገደኛ ጋር ቆሜ በአድናቆት ተመለከትኩ። በሐመር ሊሞዚን መስኮት ሙሽሪትና ሙሽራው ወጥተው እጃቸውን እያውለበለቡ ሰላምታ ለሕዝቡ ይሰጣሉ። አጠገቤ እንደኔው ቆሞ ትዕይንቱን የሚታዘብ መንገደኛ፣ ‹‹እየተሳደቡ ነው ወይስ ሰላምታ እየሰጡን?›› ሲል ሰማሁት። መቼም አንዳንድ አቃቂር አውጭ ሰው አይጠፋም እያልኩ ሰምቼ እንዳልሰማሁ ላልፈው ብሞክርም አባባሉ እያቃጨለ አባነነኝ። የሐመር ሊሞዚን ለዚህ ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ ያልገባቸው ሙሽሮቹ ሰላምታቸውን ቀጥለው ገፉበት። ሠርግ የቃል ኪዳን ማሰሪያነቱንና ባህላዊ ወጉን ተላልፎ የንዋይ ጥንካሬን ማሳያና የማንነት ማስመስከሪያ የሚሉት ‹‹ፖለቲካ›› ውስጥ ከገባ እንደቆየ አስታወስኩ። ድንቄም ፖለቲካ እቴ! በድሃ አገርና በድሃ ሕዝብ ላይ ይኼ ሁሉ ቀረርቶ ሲበዛ የጤና አልመስልህ ይለኛል፡፡ ጎበዝ ቅናት ይሆን እንዲህ የሚያንጨረጭረኝ? እንጃ!
መቼም ጨዋታን ጨዋታ ካነሳው ላይቀር ትንሽ ስለኢራንና ተቃዋሚዎቿ የሰሞኑን ሁኔታ ማንሳት ተገቢ ነው። እህሳ? ቅምጥሏ አሜሪካ የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር እንደ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ አላየውም ብላ፣ ማዕቀቧን በኢኮኖሚዋ ልክ እየሰፋች ማልበሷን ቀጥላለች። ኢራንም አፀፋዊ ምላሼ ይከፋል ማለቷን ባሻዬ አጫውተውኛል። ‹‹ሲከር ይበጠሳል›› ይባል የለ? እናንተዬ ለውድቀትና ለጥፋት እንዲህ መባዘንን ምን ትሉታላችሁ? ‹‹ከማታሸንፈው ሰው ጋር አትግጠም›› ይሉ ነበር አበው። የኋላ ኋላ ተጎጂው ማን ይሆንና? ያው ሕዝብ ነው። በማናቸውም ሁኔታ ጦርነት ኪሳራው እንጂ ትርፉ ታይቶ አያውቅም። እንዲህ ያለው ነገር ሲሰማ ብቻ ዝም ብሎ ልቦና ይስጥ ማለት ይሻላል። አዎ ልቦና ይስጠን!
በነገራችን ላይ ባሻዬ ሰሞኑን ከቴሌቪዥኑ ላይ አልነቀል ብለው አስቸግረው ነው የከረሙት። ለያዥ ለገናዥ እንቢ ብለው ከከፈልኩበት ላይቀር ተጎልቶ ምን ይሠራል እያሉ ቴሌቪዥናቸውን ሲያስለፈልፉት መዋል ጀምረውላችኋል። እኔም ልጃቸውም ብንመክራቸው አሻፈረኝ ብለው ከጎረምሳውና ከወጣቱ በላይ የሰሞኑን የአፍሪካ ዋንጫ ከማጣሪያው ጀምረውታል። ‹‹የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ እንዴት አገኙት?›› ስላቸው፣ ‹‹አዬ ዘንድሮ አመዱ ቡን ብሎ ብሶበታል። ቆይ አፍሪካ ለአመፅ፣ ለግርግርና ለጠብ እንጂ ይኼን መልካም ነገር ለመከወን አያምርባትም ልበል?›› አሉኝ። ያዩትን አይተው እንዲያ እንዳሉኝ ቢገባኝም፣ ‹‹ታገሱ ማጣሪያ እኮ እንዲህ ነው›› ብዬ ነገራቸውን አለዘብኩት። ‹‹የአፍሪካ መሪዎች ሊሰበሰቡ ነው አሉ፡፡ ምን ዋጋ አለው? እነሱ ሥልጣናቸውን ማደላደል እንጂ ለሕዝቡ ኑሮ፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት ደንታ የላቸው፤›› ብለው አቀረቀሩ፡፡ ባሻዬ ወትሮም ቢሆን የአፍሪካ መሪዎች አይጥሟቸውም፡፡ ‹‹ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ብለው የቅንጦት ኑሮ ይውደዱ እንጂ ምን ይፈይዳሉ?›› ማለት ይወዳሉ፡፡
ምሽት ላይ ሥራዬን ሠራርቼ የማገናኘውን አገናኝቼ የባሻዬን ልጅ የቀጠርኩበት ግሮሰሪያችን ሄድኩ። ምን አግኝቶ እንደሆነ አላውቅለትም ካልጋበዝኩህ ብሎ ሊገለኝ ነው። ብርጭቆዎቻችንን እያጋባን እየተጨዋወትን ሳለ ስለሠፈሬ ተማሪዎች አንስቼ ያሉኝን ብነግረው፣ ‹‹አይ አንበርብር ምናልባት ልማታዊ አርሶ አደር፣ ልማታዊ ባለሀብት፣ ልማታዊ ጋዜጠኛ፣ ወዘተ ይኖር ይሆን እንጂ ልማታዊ ተማሪ ከጠፋ ቆይቷል። ይኼ በካሮት ዓይኑን እያጠራ የሚመጣ ‹‹ጥገኛ ተማሪ›› መባል አለበት፤›› ሲለኝ፣ ጥገኝነት የሚለው አገላለጽ ከበደኝ፡፡ ለነገሩ ስንቱ የማንም ጥገኛ እየሆነ አይደል? ‹‹ጥገኝነትና ዝቅጠት›› ሲባል ይገርመኛል፡፡
‹‹ኧረ ዓይንስ አለልህ የቻይና›› አልኩት ርዕሱን ለመለወጥ ብዬ። ምን ዓይናቸው ቢያናንስም ድንቅ የሥነ ሕንፃ ጠበብት እንደሆኑ አስመስክረዋል። ‹‹ለመሆኑ አዲሱን የአፍሪካ ሕብረት ሕንፃ አየኸው?›› ሲለኝ፣ ‹‹ባልገባም ከደጅ እንደ ማንኛውም ሰው አይቼዋለሁ፤›› አልኩት የሕንፃውን ውበት ለማሰብ እየሞከርኩ። ከት ብሎ ስቆብኝ ሲያበቃ፣ ‹‹የሚገቡት ምንም ረብ ያለው ነገር እንደማይፈይዱበት እየታወቀ አንተ ጭራሽ ውስጡ ለመግባት አሰብክ? ለአፍሪካ አፍሪካውያን መድረስ እንደሚያቅተን ያስመሰከረ ኅብረት ነው ባይ ነኝ። ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ ሲባል አልሰማህም? እንቶ ፈንቶ ወሬ ተጎልቶ ለማውራትማ ድድ ማስጫዎች አሉ አይደል? ብቻ ተወው ለማንኛውም ግን ሕንፃው በጣም ያምራል፤›› አለኝ ለዘብ ብሎ። የአፍሪካችን ነገር ሆዱን የማይቆርጠው ማን አለ? እንዲያው ነገሩ ሁሉ ውሉን አጣ እንጂ! መልክ ብቻ! ‹‹መሪዎቹ ይህን የመሰለ ሕንፃ ውስጥ ሲገቡ ስለ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ሰላም ቢወያዩና ቁርጠኛ አቋም ቢይዙ ኖሮ አፍሪካም ሆነች አገሮቹ መዘባበቻ አይሆኑም ነበር፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል እኛን የሚጠሙን እነዚህ እሴቶች፣ እነሱን የተጠናወታቸው አምባገነንነት . . . ›› እያለ ሲመረር መሸብን፡፡ ዲሞክራሲ ወይስ አምባገነንነት? ያሉት ምርጫዎች እነዚህ ብቻ ናቸው፡፡ መልካም ሰንበት!


