Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

የእናቶች እፎይታ

  • PDF

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የሕፃናት ማቆያና ማዋያ ቦታዎች እየተለመዱ ከመምጣታቸው ባሻገር ለበርካታ እናቶች እፎይታንና ግልግልን እያጎናጸፉ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳን ‹‹እናትነትን›› በሌላ ግለሰብ መተካት ባይቻልም፤ በሥራና በትምህርት የተጠመዱ እናቶች ልጆቻቸውን ወደ ሕፃናት ማቆያና ማዋያ ማዕከላት በመላካቸው፣ ልጆቻቸው ንጽሕናው በተጠበቀ መልኩና ‹‹ሥራዬ›› ብለው በዘርፉ በተሰማሩ ባለሙያዎች እጅ ሥር በመዋላቸው ከእናትነት መጠን ያለፈ ጭንቀት እንደሚገላገሉም ይናገራሉ፡፡

‹‹ያገኘነው እፎይታን ብቻ አይደለም›› የሚሉት እነኚህ እናቶች፤ ‹‹ልጄን ለሠራተኛ ሰጥቼ በሥጋት እየዋልኩ ካሁን ካሁን ልጄ ላይ አንድ ጉዳት ይደርስ ይሆን (በጥንቃቄ ካለመያዝ የተነሣ)፣ በቆሸሸ ጡጦ መልሰው ያጠቡት ይሆን? ሠራተኞቹ ባላቸው የተለያየ ባሕርያት ተጽዕኖ ልጄ አጉል ባሕርይ ይዞ ያድግ ይሆን?›› ከሚሉ ሥጋቶች ጭምር ተገላግለናል ባይ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሥጋቶች በተጨማሪ ደግሞ የበርካታ ሴቶች ራስ ምታት የሚሆነው የቤት ሠራተኛ ለማግኘት መክበዱ ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹ሥራዬንም ሆነ ትምህርቴን ትቼ ቢያንስ ለሦስትና አራት ዓመታት ልጄን ቁጭ ብዬ ላሳድግ›› ከሚል ጭንቀት አዘል ከባድ ውሳኔ እነዚህ የሕፃናት ማዋያና ማቆያ ማዕከላት እንደመፍትሔነት ሴቶችን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ልጅን ወልዶ በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ፣ ታዳጊው ወደፊት ለሚሸከማቸው በርካታ ኃላፊነቶች የእድገቱ መልካም መሆን ጥሩ መሠረት እንደሆነ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ይህ ሲሆን ግን ኃላፊነቱ የወላጅ ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መልኩ የማኅበረሰቡም ጭምር መሆኑ ይታመናል፡፡

በመሆኑም ሥጋት በሌለበት፣ ለልጆች ምቹ በሆነ ቦታና ባሕሪ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች የተሻለ ጤናማነትንና የተሻለ ማንነትን አዳብረው እንደሚያድጉ ግልጽ ነው፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያትና የአኗኗር ዘዬ መሠረት ልጆችን ለማሳደግ ቤትን የመሰለ ነገር አልነበረም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሙሉ በሙሉ ተማምኖ ሕፃናትን እቤት ውስጥ በሞግዚት እንዲያድጉ የማድረጉ ነገር ከገንዘብ ባሻገርም አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ ይህ ሲባል ግን በአሁኑ ወቅት የሚታመኑ ሞግዚቶች የሉም አያስብልም፡፡ ከሞላ ጎደል አቅም ያላቸው እናቶች ልጆቻቸውን ተማምነው ለሞግዚቶቻቸው ትተው ያለመሄድና ልጆቹም ከሌሎች ልጆች ጋር እየተጫወቱ እንዲያድጉ፣ ምግባቸው በትክክለኛው ሰዓት ንጽሕናው በተጠበቀ መልኩ እንዲሰጣቸው፣ በባሕርያቸውም ሆነ በሥነ ምግባራቸው የታነጹ እንዲሆኑ በሚል ሕፃናት ልጆቻቸውን ወደ ማቆያና ማዋያ ቦታዎች መላክን ምርጫ ሲያደርጉ ይታያል፡፡

ከዚህ በተጨማሪና በዋናናነት ግን ‹‹ምን ያህል ሴቶች በመውለዳቸው ምክንያት ሥራ አቁመዋል? ምን ያህል ሴቶች ልጅ በመውለዳቸው ምክንያት ትምህርቶቻቸውን አቋርጠዋል? ምን ያህል ሴቶች እቤት ውስጥ ልጆችን በማሳደግ ብቻ ጊዜአቸውን በማሳለፋቸው የማኅበራዊ ሕይወታቸው ላልቷል? እንዲሁም ምን ያህል ሴቶች ልጆች ከወለዱ በኋላ ዘና ያለ የትዳር ሕይወትን ያሳልፋሉ? የሚሉት ጥያቄዎች በየሰው አእምሮ የሚመላለስ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉት የሕፃናት ማዋያና ማቆያ ማዕከላት መካከል በአንዱ ተጠቃሚ ከሆኑት ሴቶች መካከል የሦስት ልጆች እናት የሆነችውና የ35 ዓመቷ መሳይት (ስሟ ተቀይሯል) አንዷ ነች፡፡ ይህች እናት ተቀጥራ የምትሠራበት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ካለባት ጫናና የሥራ ኃላፊነት በተጨማሪ፣ የማስተርስ ዲግሪዋን ውጭ አገር ባለ አንድ ዩኒቨርሲቲ በርቀት የምትከታተል በመሆኑ፣ ልጆቿን ለማሳደግ የሚቀጠሩ ሞግዚቶች ትተዋት በሄዱ ቁጥር በጣም ትቸገር እንደነበርና ጊዜዋም እጅግ ይጨናነቅ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

‹‹የመጀመርያ ልጄ በሦስት ዓመቷ መዋለ ሕፃናት እስክትገባ ድረስ በተለያዩ ሠራተኞች እቤት ውስጥ ነበር ያደገችው፡፡ ከባድ የነበረው ሁኔታ ግን ሠራተኞቹ በሄዱ ቁጥር ከሥራ እየቀረሁ ልጄን መጠበቅ ነበር፤›› ስትል ሁኔታውን አስታውሳለች፡፡

ይህች እናት ሁለተኛ ልጇን ከሦስት ዓመታት በኋላ ስትወልድ ግን ሁለት የቤት ሠራተኞች (አንድ ሞግዚትና አንድ የቤቱን ሥራ የምትሠራ ሠራተኛ) ነበሯት፡፡ ይሁንና ሁለቱ ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ይጣሉ ስለነበር ለሕፃኑ ተገቢውን እንክብካቤ ይሰጡ እንዳልነበር ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ሠራተኞቹ ባለመስማማታቸው ምክንያት የነበረው ችግር የልጄ ተገቢው እንክብካቤ ማግኘት፣ በሚገባ እስከአለመመገብ የከፋ ነበር፡፡ ልጄ መራመድ በሚገባው ወቅት አልተራመደም፣ ምክንያቱም ሠራተኞቹ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም ሕፃኑ እንዲራመድ አያለማምዱትም ነበር፡፡ ከምንም በላይ አስደንጋጭ የነበረው ክሥተት ግን ልጁ ገና የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሕፃን በነበረበት ወቅት፣ በምግብ ብክለት በከፍተኛ ሁኔታ መታመም ነው፤›› ብላለች፡፡

አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ የልጇ ሁኔታ እየተወሳሰበ ሄደ፡፡ በአጋጣሚ ግን ‹‹ጥሩ›› ስለተባለ አንድ የሕፃናት ማቆያና ማዋያ ሰማች፡፡ ቢሆንም ግን የማቆያው ነገር እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ፣ መሳይት ወስና ልጇን ወደ ማቆያው ለመውሰድ  አልደፈረችም ነበር፡፡ ግን ልጇን በተመለከተ ቤት ውስጥ የነበረው ሁኔታ ጥሩ አለመሆን ልጇን ወደማቆያው ለመውሰድ ድፍረት ሆናት፡፡ ይኼኔ ነበር ቤት ውስጥ በሠራተኞች አማካይነት በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት፣ መሳይት ከሥራዋ መቅረትም ሆነ ትምህርቷን ለመከታተል እንቅፋት ለሚሆኑባት ጉዳዮች እልባት ማግኘት የጀመረችው፡፡ ይህ ችግር የመሳይት ብቻ ሳይሆን እናቶች በተመሳሳይ መልኩ በሥራና በትምህርት የተጠመዱ የእሷን መሰል ሴቶችም ጉዳይ ጭምር ነው፡፡

የሕጻናት ማቆያ ማእከላቱ በመኖራቸው ሦስተኛ ልጇን እንደወለደችና እሷንም በስድስት ወሯ ወደ መረጠችው ማቆያ እንዳስገባቻት መሳይት ትናግራለች፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበረው ሁኔታ ሴት ትምህርቷንና ሥራዋን አቋርጣ ልጅ ብታሳድግ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና አይፈጠርም የሚል እምነት የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ባለው የኑሮ ውድነት ይህ ሐሳብ የማያስኬድ በመሆኑ የእናቶች መሥራትና መማር ምርጫ የሌለው ውሳኔ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡

ይህንን ሐሳብ ‹‹የብርሃን ሕፃናት ማዋያ፣ መንከባከቢያና ማቆያ›› መሥራች ከሆኑት ስድስት ግለሰቦች ውስጥ አንዷ የሆኑት ሲስተር ያለምወርቅ ሐረጉ ይጋሩታል፡፡ የሕፃናት ማቆያው ከተቋቋመ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ማቆያው ዕድሜያቸው ከሦስት ወር ጀምሮ የሆኑ ሕፃናቶችን ይቀበላል፡፡

በዚህ በነርስና በአዋላጅነት ሙያ ተሰማርተው በነበሩና በሕክምናው ዘርፍ ውስጥ ድርሻ ባላቸው ሴቶች አማካይነት የተቋቋመው የሕጻናት ማቆያ ውስጥ ለሚፈጠር ማንኛውም አደጋ የመጀመርያ ደረጃ ዕርዳታ እንደሚያደርጉና በቀጣይም ሕጻናቱ ተገቢውንና አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ ወደ ሕክምና ቦታ ሕጻናቱ የሚወስዱበት ሥርዓት መኖሩን ሲስተር ያለምወርቅ ተናግረዋል፡፡

ባለሙያዋ እንዳሉትም፣ ‹‹አንዲት እናት ተማሪ፣ ነጋዴ፣ የቢሮ ሠራተኛ ወይም ደግሞ በሆነ ዘርፍ ኤክስፐርት ልትሆን ትችላለች፡፡ በመሆኑም ሴቶቹ ልጆቻቸውን በእርግጠኝነት ወደ ሕፃናት ማቆያ በላኩ ቁጥር፣ ልጆቻቸው ላይ በእንክብካቤ ጉድለት ችግር ይፈጠርባቸዋል ከሚችል ሥጋት ውጪ ሆነው ሲንቀሳቀሱ በሥራቸውም ሆነ በትምህርታቸው ውጤታማ መሆን ይችላሉ፡፡››

ይህ የሕፃናት ማቆያ ሕፃናትን ከሦስት ወር ዕድሜያቸው ጀምሮ የሚቀበል ሲሆን፣  ልጆች በማቆያው የቀን ውሎአቸውን እንዲያሳልፉ ለማድረግ በየሦስት ወሩ የሚፈጸመው ትልቁ ክፍያ 3620 ብር እንደሆነ ሲስተር ያለምወርቅ ገልጸዋል፡፡ ማቆያው በአሁኑ ሰአት 28 ልጆችን የሚንከባከብ ሲሆን፣ ከተጀመረ ጀምሮ ግን ቢያንስ 400 ልጆችን እንዳሳደገ አመልክተዋል፡፡

ይሁንና ሁሉም እናት ልጆቻቸውን ወደ ሕፃናት ማቆያ ማዕከላት የመላክ አቅም እንደሌላቸው ቢታወቅም፣ ልጅን ለማሳደግ ሴቶች ላይ የሚወድቀውን ጫና እነዚህ ከጊዜ በኋላ ተቀባይነትን እያገኙና እምነት እየተጣለባቸው የመጡት የሕፃናት ማቆያዎች፣ የሴቶችን ልጅ የማሳደግ ጫናን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ቀለል እንዳደረገው ሴቶቹ ይገልጻሉ፡፡