Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

ረቂቅ የሊዝ ሞዴል ደንቡ የባንኮችን ስጋት ያስወግድ ይሆን?

  • PDF

የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም. ከወጣ ጀምሮ አከራካሪነቱ እስካሁን ያቆመ አይመስልም፡፡ ባንኮችን በተመለከተ ለብድር ዋስትና የተሰጡ መያዣዎች ላይ የሚኖረው አሉታዊ ውጤትም እንዲሁ በየአውዱ ሲገለጽ ነበር፡፡ አዋጁ ባንኮች በተግባር የሚጠቀሙበትን የአካባቢ ዋጋ ግንዛቤ ውስጥ አያስገባም፤ የፎርክሎዠር መብትን ይጋፋል፤ እስካሁን የተሰጡ ብድሮችን ለማስመለስ ያስቸግራል  ወዘተ. ከሚቀርቡት ትችቶች የተወሰኑት ናቸው፡፡ እነዚህ የባንኮች ስጋት (Concerns) መፍትሔ የሚያገኙት አዋጁን በማሻሻል እንደሆነ የሚገልጹ የሕግ ባለሙያዎች በርካታ ቢሆኑም፣ አዋጁን ያረቀቁትና በጉዳዩ ላይ በየመድረኩ አስተያየት የሚሰጡት የመንግሥት ተወካዮች ግን አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጣው ደንብና መመርያዎች ስጋቱ እንደሚወገድ ገልጸዋል፡፡

አሁን በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተዘጋጀው ሞዴል ደንብ አዋጁን ለማስፈጸም እንዲረዳ ታስቦ የወጣ በመሆኑ፣ የባንኮችን ስጋት ሊቀርፍ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ለመሆኑ ረቂቅ የሊዝ ደንቡ በአዋጁ ከባንኮች ዋስትና ጋር በተያያዘ የታዩትን ክፍቶች ሸፍኖ ይሆን? የሚለውን ነጥብ በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ በዚሁ መሠረት የረቂቅ የሊዝ ደንቡን ይዘት በመዳሰስ፣ የደንቡ ወሰን (Scope) በአዋጁ ከተደነገጉት ሐሳቦች ጋር ያለውን ግንኙነት በማየት፣ ለደንቡ መዳበር የተወሰኑ ግብዓቶች ለመስጠት ሙከራ ያደርጋል፡፡

የሞዴል ደንቡ ይዘት
ሚኒስቴሩ በአዋጁ አንቀጽ 32(5) አዋጁን ማስፈጸሚያ ሞዴል ደንብ የማዘጋጀት ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ በዚሁ መሠረት ሞዴል ደንቡን አጋጅቷል፡፡ ዋናውን ደንብ የሚያወጡት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ቢሆኑም፣ የወጣው ሞዴል ደንብ ሰፋ ያለ ተፅዕኖ ስለሚኖረው የአዋጁን ብሔራዊ አፈጻጸም ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ ሞዴል ደንቡ 42 አንቀጽ ያሉት ሲሆን፣ የተወሰኑት ድንጋጌዎች በአዋጁ በተቀመጠው መልኩ በጠቅላላ አነጋገር የተቀረጹና አዲስ ሐሳብ ያልያዙ፣ የተወሰኑት በአዋጁ ፈጽሞ ያልተዳሰሱ አዲስ ጉዳዮች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በአዋጁ በአጠቃላይ አነጋገር የተገለጹ ሐሳቦችን በዝርዝር የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡ የትርጓሜው ክፍል፣ የግንባታ ማጠናቀቂያና የቅጣት አወሳሰን፣ የሊዝ ውል ስለማቋረጥና ካሳ አከፋፈል እንደ አዋጁ በጠቅላላ አነጋገር ተደንግገዋል፡፡ ወደሊዝ ስሪት ስለማይገቡ ቦታዎች የሚደነግገው የሞዴል ደንቡ አንቀጽ 7 በአዋጁ ያልተገለጹ ነጥቦችን አካትቷል፡፡ በፍቺ ውሳኔ ክፍፍል የተገኘ ንብረት፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከነባር ይዞታቸው ተነሽ የሆኑ ባለመብቶች በምትክነት በሚያገኙት ቦታ፣ ሰነድ አልባ ይዞታዎች ክልሉ ወይም የከተማው አስተዳደር በሚያወጣው መመርያ መሠረት ሰነድ እንዲያገኙ ሲደረግና በፍርድ አፈጻጸም ወይም በባንክ ብድር ዕዳ ተይዘው በሐራጅ የተላለፉና በስም ዝውውር ሒደት የንብረት ሽያጭ (የካፒታል ጌይን) ታክስ የሚከፈልባቸው ነባር ይዞታዎች ወደሊዝ ስሪት እንደማይገቡ በደንቡ መገለጹ በአዋጁ ያልተካተተ አዲስ ሐሳብ ነው፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 6(3) ‹‹በነባር ይዞታ ላይ የሰፈረ ንብረት የተላለፈለት ሰው የቦታው ባለይዞታ ሊሆን የሚችለው በሊዝ ስሪት መሠረት ይሆናል፤›› በሚል ስለሚደነግግ በደንቡ ለተጨመሩት ልዩ ሁኔታዎች ቦታ የለውም፡፡ በዚህ ረገድ ሞዴል ደንቡ በአዋጁ ያልተገለጹ ድንጋጌዎችን መጨመሩ አዋጁን የማሻሻል ውጤት እንዳይኖረው ስጋት አለ፡፡ የሞዴል ደንቡ ሌሎች ድንጋጌዎች በአዋጁ በጠቅላላው የተገለጹ ሥርዓቶችን በዝርዝር በመግለጽ፣ የጊዜ ገደብና የአሠራር ደንቦቹን በማስቀመጡ ጠቃሚነቱ ሰፊ ነው፡፡ በሊዝ ጨረታ ስለሚሰጥ መሬት ከአቀራረቡ ጀምሮ በዝርዝር ሒደቱን የሚያሳየው ክፍል፣ የሊዝ ምደባ መሬት የሚሰጥበትን አግባብና የከተማ መሬት የሊዝ ዋጋን የሚደነግገው (የችሮታ ጊዜን ጨምሮ) ያሉት ክፍሎች ዝርዝር ድንጋጌዎችን ማስቀመጣቸው የደንቡ አዎንታዊ ጎን ነው፡፡

በሞዴል ደንቡ የተጨመሩት አዲስ ሐሳቦች አግባብነት
የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ደንብ የሚያወጡበት አግባብ በሕግ ሙያ አስተምህሮ በውክልና (Delegation) በተሰጠ ሥልጣን ነው፡፡ አስፈጻሚው አካል ካለው ሙያዊ ብቃት (Expertise)፣ ሕጉን በማስፈጸም ለሕዝቡ ካለው ቅርበትና ሕግ አውጪው ሁሉንም ሕጎች ለማውጣት ጊዜም ስለማይኖረው አስፈጻሚው በሕግ አውጪው በሚሰጠው ፈቃድ ደንቦችን ያዘጋጃል፤ ያወጣል፡፡ ይህ በአገራችንም በሌሎችም አገሮችም የሚሠራበት ነው፡፡ ሆኖም አስፈጻሚው የሚያወጣቸው ደንቦች በሕግ አውጪው ከተሰጠው ፈቃድ እንዳይወጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሕግ አስፈጻሚው ሕግ አውጪው ያወጣውን ሕግ ይዘት በመቃኘት፣ ሪፖርት በመስማት፣ ጠርቶ በመጠየቅ ወዘተ. በውክልና የተሰጠው የሕግ ማውጣት ሥልጣን በአግባቡ ስለመፈጸሙ ሊያረጋግጥ እንደሚገባ የሕግ ሳይንሱ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ረገድ ሞዴል ደንቡ የያዛቸው አንዳንድ አዲስ ሐሳቦች በሊዝ አዋጁ ያልተካተቱ ወይም በግልጽ በአስፈጻሚው እንዲካተቱ ያልተፈቀዱ በመሆናቸው አዋጁን የማሻሻል ውጤት እንዳይኖራቸው ስጋት አለ፡፡ አዋጁን ደግሞ ራሱን በማሻሻል ካልሆነ በቀር በደንብ እንዲሻሻል ማድረግ የሕግ ሙያውን አስተምህሮ የሚጥስና አርአያ የማይደረግ ልምድ (Wrong precedent) ይሆናል፡፡ የሊዝ አዋጁ በነባር ይዞታ ላይ የሰፈረ ንብረት ባለቤትነት ከውርስ በስተቀር በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ከተላለፈ በሊዝ ስሪት መሠረት እንደሚፈጸም ግልጽ አድርጓል፡፡ አዋጁ ከውርስ ሌላ ምክንያቶችን በልዩ ሁኔታነት (Exception) የማይዘረዝር ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ በሞዴል ደንብ ወይም የክልልና የከተማ አስተዳደሮች በሚያወጡት ደንብ እንደሚዘረዘሩ አይገልጽም፡፡ ከዚህ አንጻር በሞዴል ደንቡ የተዘረዘሩት ተጨማሪ ወደሊዝ ስሪት የማይገቡ ቦታዎች በሕዝቡ የቀረቡ ጠቃሚ አስተያየቶችን ያካተቱ ቢሆንም፣ አዋጁን በማሻሻል ካልሆነ በደንቡ ሊሸፈኑበት የሚችልበት የሕግ ሙያ አስተምህሮ የለም፡፡ አዋጅን በደንብ ማሻሻል ከሕግ የተዋረድ ደረጃ (Hierarchy of laws) ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ሕግ አስፈጻሚው አካልም የደንቡን ይዘት ሊያርም የሚችልበት አጋጣሚ ካለ በሞዴል ደንቡ የተካተቱት ጠቃሚ የሕዝብ አስተያየቶች የሕግ ውጤት ላይሰጣቸው ይችላል፡፡

በሞዴል ደንቡ ስለባንክ ዋስትና የተቀመጡት ድንጋጌዎች
የባንኮችን ስጋት ከሚያስወግዱ ድንጋጌዎች አንዱ በደንቡ አንቀጽ 7(6) የተቀመጠው ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት በፍርድ አፈጻጸም ወይም በባንክ ብድር ዕዳ ተይዘው በሐራጅ የተላለፉና በስም ዝውውር ሒደት የካፒታል ጌይን ታክስ የሚከፈልባቸው ነባር ይዞታዎች ወደሊዝ ስሪት አይገቡም፡፡ የዚህ ድንጋጌ ዋና ዓላማ ባንኮች ወይም የፍርድ ባለመብቶች በነባር ይዞታ ላይ ያላቸውን መብት በቀደመው ሥርዓት መሠረት (ከሊዝ ውጭ) ለማስተዳደር ነው፡፡ ድንጋጌው ስለባንክ ብድር ዕዳ አንድም ቃል ካላሰፈረው አዋጅ የተሻለ ጥቅም ለባንኮች ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ ሆኖም የድንጋጌው የተፈጻሚነት ወሰን ባንኮችን የመጥቀሙን ነገር ዋጋ የሚያሳጣ ይመስላል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሁሉም በባንክ ብድር ዕዳ ተይዘው በሐራጅ የተላለፉ ንብረቶች ከሊዝ ሥሪት ውጭ አይሆኑም፡፡ ከሊዝ ስሪት ውጭ የሚሆኑት መያዣዎቹ ሲተላለፉ የካፒታል ጌይን ታክስ የሚከፈልባቸው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በገቢ ግብር አዋጁ አንቀጽ 7 መሠረት ደግሞ የካፒታል ጌይን ታክስ የሚከፈለው ንብረቶቹ ሲተላለፉ ጥቅም ከተገኘ ሲሆን፣ ይሄውም በግል መኖሪያነት የተያዘ ቤት ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ከዚህ አንጻር ባንኮች የመያዣ ንብረት በጨረታ ሲያስተላልፉ ጥቅም ካላገኙና መኖሪያ ቤት በሆነ ጊዜ በደንቡ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ በባንኮች በአብዛኛው በመያዣነት የሚሰጡ የግል መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው ሲታሰብ ባንኮች ንብረት ሲያስተላልፉ ካፒታል ጌይን ታክስ ስለማይከፍሉ የነባር ይዞታው አሻሻጥ በአዲሱ ሊዝ አዋጅ ሥርዓት የሚወድቅ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሞዴል ደንቡ አቀራረጽ ባንኮችን የሚጠቅም ቢመስልም፣ ጥቅሙ ሰፊና መሠረታዊ ስለማይሆን ድንጋጌው ከካፒታል ጌይን ታክስ ጋር መያያዙ ካልቀረ የባንኮች ስጋት ሊወገድ አይችልም፡፡

የባንኮች ሌላው ስጋት የሚመነጨው ከሊዝ መብት መያዣ ጋር በተያያዘ ያለው የተጣበበ መብት ነው፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 24 በግልጽ እንደሚያመለክተው፣ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የሊዝ መብት በዋስትና ሲሰጥ ባንኮች በአዋጁ አንቀጽ 22 መሠረት ተቀናሽ ከሚደረጉ ክፍያዎች ውጭ ባለው በተከፈለ ቅድሚያ የሊዝ ክፍያ መጠን ነው፡፡ የባንክ ዕዳ ሳይከፈል ዋስትናው ላይ ሲፈጸም አግባብ ያለው አካል እነዚህን ክፍያዎች ተቀናሽ በማድረግ ቀሪውን ለአበዳሪው ይሰጣል፡፡ ደንቡ ከአዋጁ ጋር ተመሳሳይ ድንጋጌ በአንቀጽ 31(6) ላይ ያስቀመጠ ቢሆንም፣ የሊዝ ቅድሚያ መብትን በስፋት በመደንገግ የባንኮችን የመያዣ ቅድሚያ መብት ሸርሽሮታል፡፡ የሊዝ ዕዳ ያልተጠናቀቀበትን ወይም የቅድሚያ ክፍያ ብቻ የተፈጸመበትን ግንባታ ያልተገነባበት መሬት የዕዳ ቅድሚያ መብት የሊዝ ውል ሰጪው አካል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሊዝ ክፍያው ሙሉ በሙሉ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ባንኮች በመያዣው ላይ ምንም የቅድሚያ መብት አይኖራቸውም፡፡ በአዋጁ ከውዝፍ ዕዳና ሰባት በመቶ የአጠቃላይ የሊዝ ክፍያ ተቀናሽ በተጨማሪ የሊዝ ዕዳው ሙሉ በሙሉ ካልተጠናቀቀ ባንኮች መብት እንደማይኖራቸው የደንቡ ገጸ ንባብ ስለማያስረዳ፣ በአዋጁ መሠረት ባንኮች በሊዝ መሬት ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ጠባብ የመያዣ መብት የበለጠ አጣብቦታል፡፡ በተጨማሪም ባንኮች በመያዣ የያዙትን የሊዝ መብት በፎርክሎዠር የመሸጥ መብታቸውም በአዋጁ በተቀመጠው መልኩ ተነፍጓል፡፡ አዋጁ ባልተሻሻለበት መንገድ ይህን መብት ደንብ የሚሰጣቸው ባይሆንም ባንኮች ከሊዝ ሥርዓት ውጭ ደንቡ ባደረጋቸው መንፈስ አልተቃኘም፡፡ በሌላ በኩል አዋጁ በአንቀጽ 24(5) ላይ ‹‹የፍርድ አፈጻጸም ትዕዛዝ የተላለፈበት የዕዳ ጥያቄ›› የሚለውን የባንኮችን የፎርክሎዠር መብት ስለመሸፈኑ አሻሚ መሆኑን ለማስቀረት ይመስላል በደንቡ አንቀጽ 31(6) (ሠ) ‹‹በዋስትና መያዣው ላይ የፍርድ አፈጻጸም ትዕዛዝ የተላለፈለት ወይም ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው የዕዳ ጥያቄ ከቀረበ፤›› በሚል የተወሰነ ለማብራራት የተሞከረው፡፡ ‹‹ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው›› የሚለው ኃይለ ቃል ባንኮች ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ በፎርክሎዠር አዋጅ ባገኙት ሥልጣን የሚያስፈጽሙትን የመያዣ መብት ስለሚያካትት ስጋቱ ይወገዳል፡፡

ከግማሽ በታች ግንባታ የተፈጸመበት የሊዝ መያዣን በተመለከተም ደንቡ የሚለው ነገር አለ፡፡ ሲጀምር መያዣው ለባንክ ብድር ሲያዝ በአዋጁ አንቀጽ 22(3) መሠረት ተቀናሽ የሚሆኑት ክፍያዎች ቅድሚያ ታሳቢ ተደርገው ስለመሆኑ ደንቡ በግልጽ አመልክቷል፡፡ የደንቡ አንቀጽ 31(7) (ለ) መያዣ ተቀባይ (ባንኮች) የግንባታ ዋጋውን ግምት እንደሚያከናውን፤ መዝጋቢው አካል አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ እንደሚመዘገብ ይገልጻል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መነሻነት ባንኮች ንብረቱን ሲገምቱ የአካባቢውን ዋጋ (Location Value) እንዳይጨምሩ የማይከለከሉ ቢመስልም፣ ‹‹የግንባታ ዋጋ›› የሚለው ኃይለ ቃሉ ክፍተቱን እንዳይዘጋው ስጋት አለ፡፡ ሆኖም የመዝጋቢው አካል ሥልጣን ዕዳና እገዳን ከማጣራት ባለፈ በግምቱ አግባብነት ላይ ሥልጣን ስለማይኖረው የባንኮች የአካባቢ ዋጋን የመጨመር መብት ተነፍጓል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከግማሽ በታች ግንባታ የተፈጸመበትን የሊዝ መሬት መያዣ ማን እንደሚሸጥ የአዋጁ 24 (2) ግልጽ ባያደርግም፣ ደንቡ መንግሥት (አግባብ ያለው አካል) እንደሚፈጽመው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የአዋጁ ዝምታ የባንኮችን የፎርክሎዠር መብት እንደሚጠብቅ ለሚያስብ የሕግ ባለሙያ ደንቡ ከአዋጁ መንፈስ ውጭ መውጣቱን ያምናል፡፡

በሌላ በኩል ደንቡ ከግማሽ በታች ግንባታ በተፈጸመበትም መሬት ላይ ቀሪ የሊዝ ዕዳ ያለበት ዋስትና የሚመዘገበው በሁለተኛ ደረጃ የዕዳ ባለመብትነት በመሆኑ ባንኮች አጠቃላዩ የሊዝ ዕዳ (ውዝፍ ሳይሆን ቀሪ የሊዝ ዕዳ) ባልተከፈለበት ሁኔታ የቀዳሚነት መብታቸውን በደንቡ አጥተዋል፡፡ ከግማሽ በታች ግንባታ ከተፈጸመበት መሬት መያዣ ጋር በተያያዘ ደንቡ ባንኮችን የሚጠቅም ድንጋጌ ያስቀመጠው በደንቡ አንቀጽ 31 (7) (ሸ) ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ‹‹ደንቡ ከመውጣቱ በፊት በዋስትና የተያዙ መብቶች ላይ የዋስትና ግዴታውን ባልፈጸመ አካል ላይ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በቀድሞው አሠራር መሠረት የሚፈጸሙ ይሆናል፤›› ስለሚል ባንኮች በዚህ ረገድ የያዙትን መያዣ በፎርክሎዠር መሸጥ የሚችሉ ሲሆን፣ አሁን ባለው አሠራርም ውዝፍ የሊዝ ዕዳ ካልሆነ በቀር በገበያ ዋጋ ንብረቱን በሽያጭ ሲያስተላልፉ የቀዳሚነት መብት ይኖራቸዋል፡፡

ግንባታው የተከናወነ ወይም የተጠናቀቀ መያዣ በሆነ ጊዜ ግን በማናቸውም ሁኔታ የባንኮች የፎርክሎዠር መብት የተጠበቀ ስለመሆኑ ደንቡ በግልጽ አመልክቷል፡፡ ባንኮች በመያዣ የሰጡትን ንብረት ገምተው በጨረታ በመሸጥ ዕዳቸውን ማስመለስ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በጨረታ የሚተላለፈው መብት የሊዝ ዕዳ ያለበት ሆኖ ሲገኝ ባንኮች ቀሪ የሊዝ ‹‹ዕዳውን ለሚመለከተው አካል የመፈጸም ግዴታ እንዳለባቸውና ገዥው በባንኩ አማካኝነት ካልከፈለም የስም ዝውውር እንደማይፈጽም ይደነግጋል፡፡ ድንጋጌው ውዝፍ የሊዝ ዕዳን ከቀሪ የሊዝ ዕዳ ጋር የሚቀላቅል ከመሆኑ በተጨማሪ በአዋጅ ስለሊዝ መብትና ግዴታ መተላለፍ ከተደነገገው አንቀጽ ጋር ያጣረሳል፡፡ በአንድ በኩል ባንኮች ለሚመለከተው አካል ቀንሰው ቅድሚያ ሊከፍሉት የሚገባው ቀሪ የሊዝ ዕዳ ሳይሆን ውዝፍ የሊዝ ዕዳ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ቀሪ የሊዝ ዕዳው ወደ ገዥው የሚተላለፍ እንጂ በአንድ ጊዜ የሚከፈል ሊሆን አይገባም፤ አይችልም፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 24(8) ‹‹የሊዝ መብት በማናቸውም ሁኔታ ሲታለለፍ በሊዝ ውሉ የተመለከቱት የሊዝ ባለይዞታው ግዴታዎች በሙሉ ያለቅድመ ሁኔታ መብቱ ለተላለፈለት ሦስተኛ ወገን ይተላለፋሉ፤›› ሲል የደነገገ በመሆኑ ደንቡም በተመሳሳይ መልክ ቢቀረጽ የተሻለ ይሆናል፡፡ 

በደንቡ ያልተሸፈኑ ስጋቶች
ደንቡ የባንኮችን ስጋቶች በሙሉ መፍትሔ ሰጥቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በቀድሞው አዋጅ መሠረት በመያዣ የተሰጡ የሊዝ መሬቶች አፈጻጸም በነበረው አሠራር እንደሚሸፈን የአዋጅ አንቀጽ 37(2) የደነገገ ቢሆንም፣ ብድሩን ለማስመለስ የሊዝ መብቱን ሲያስተላልፉ በገበያ ዋጋ ወይስ በአዲሱ የሊዝ ሥርዓት እንደሚያስተላልፉ በግልጽ ስላልተቀመጠ በደንቡ ቢብራራ፡፡ የሊዝ መነሻ ዋጋ መከለስ ባንኮች ብድር ሲሰጡና መያዣውን በጨረታ ሲያስተላልፉ ያለው ልዩነት ሊኖረው የሚችለው ውጤት ከግምት ውስጥ ገብቶ ልዩ ሁኔታዎችን ደንቡ ቢያካትት፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 25 መሠረት የሊዝ ይዞታ ሲቋረጥ በሊዝ መብቱ ላይ ሦስተኛ ወገኖች (ባንኮችን ጨምሮ) በዋስትናው ላይ ያላቸው መብት እጣ ፈንታ በግልጽ ስላልተመለከተ ደንቡ ይህንንም ክፍተት ቢሞላ ምሉእነት ይኖረዋል፡፡ ባንኮች ተጨማሪ ስጋቶች ካሉዋቸው ከሚኒስቴሩ ጋር በሚያደርጉት መደበኛ ውይይት ጥሩ ግብዓት እንደሚሰጡ ይታመናል፡፡

ለማጠቃለል እንሞክር፡፡ ደንቡ ከባንኮች አንጻር የተወሰኑ ድንጋጌዎችን በመያዙ ጠቃሚነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ደንቡ በዝርዝር ያስቀመጣቸው የጊዜ ገደቦች፣ የተዘረጉ ሥርዓቶችና የማስፈጸሚያ ደንቦች በሕዝብ አስተያየት ከዳበሩ አዋጁን ለመረዳት ያስችላሉ፡፡ የሆኖ ሆኖ ሦስት ነጥቦችን ግን ለጥንቃቄ እናስታውስ፡፡ ቀዳሚው የደንቡ ይዘት አዋጅን የማሻሻል ውጤት ስለሚኖረው የሕግ ሙያ በሚጠይቀው መስፈርት በአዋጅ ሊታዩ የሚገቡት በአዋጁ፤ በደንቡ ሊታዩ የሚገቡት ደግሞ በደንቡ ሊካተቱ ይገባል፡፡ ሌላው ለባንኮች ብድር አመላለስ ይረዳሉ ተብለው የተደነገጉት አንቀጽ የተፈጻሚነታቸው ወሰን በእርግጥ የባንኮችን ዓላማ (ኢንቨስትመንትን መርዳት) ስለማስቻሉ ቢፈተሽ፤ በተለይ የባንኮች የፎርክሎዠር ሥልጣንና ከቀሪ የሊዝ ክፍያ ጋር ያለው የቀዳሚነት ደረጃ በጥንቃቄ ቢታይ መልካም ነው፡፡ የመጨረሻው ነጥብ ባንኮች በኢኮኖሚ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ሰፊ በመሆኑ በደንቡ ያልተካተቱ ነጥቦች ካሉ ከባንኮች ጋር በሚደረግ መደበኛ ውይይት እንዲካተቱ ቢደረግ፣ ሞዴል ደንቡ ከባንኮች ጥቅም አንጻር የተሟላ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡