ዋና ኦዲተር መሥርያ ቤት በተለያዩ ጊዜያት ለፓርላማ ከሚያቀርባቸው ሪፖርቶች አንፃር አገሪቱ በፋይናንስ ባለሙያ ክህሎት እጦትም ሆነ ሆን ተብሎ በሚፈጸሙ ስህተቶች የተነሳ የሚታዩት የገንዘብና የንብረት ጥፋቶች ምን ያህል አገሪቷን እንደሚጎዳትና እየጎዳት ያለ መሆኑን መረዳት ቀላል ነው፡፡ ያውም በዋና ኦዲተሩ የሚቀርበው ሪፖርት በናሙናነት በተመረጡ መሥርያ ቤቶች የተገኙ ውጤቶችን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡ ከሚፈጸሙት የሀብት ብክነቶች አንዱ ደግሞ የሙያዊ ክህሎት እጦት ወይም የብቃት ማነስ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ይኸው መሥርያ ቤት ከተሰጠው ሥልጣን አንዱ ለግል ኦዲተሮችና ለሒሳብ ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ መስጠት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በሥራ ላይ የሚገኙ ከ50 የማይበልጡ ኦዲተሮችና ከ300 የማይበልጡ አካውንታንቶች ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከአምስት ዓመታት በፊት በኬንያ ከ3000 በላይ የሆኑ Charterer Certified Accountants በኦዲተርነትና በአማካሪነት አገሪቷን እያገለገሉ እንደሆነ ሲታወቅ፣ በእኛ በኩል ብዙ እንደሚቀረን ያሳያል፡፡
የእኛ ጥያቄ ለአካውንታንት የተቀመጠው መስፈርት ላይ ነው፡፡ በመሥርያ ቤቱ የተቀመጠው መስፈርት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለውና ስምንት ዓመት የሠራ የሚል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከንግድ ሥራ ትምህርት ኮሌጅና ከሌሎችም በዲፕሎማ ተመርቀው በመንግሥት መሥርያ ቤትና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከጁኒየር እስከ ሲኒየር ማኔጀር ደረጃ በአካውንታንትነትም ሆነ በኦዲተርነት ሲያገለግሉ የቆዩ ቦታ የላቸውም፡፡ ወረቀት የሌላቸውና ዛሬ ላይ በጡረታና በተለያዩ ምክንያት ከሥራቸው የተገለሉ አንጋፋ ባለሙያዎች ያውም ከትምህርት ቤት ተመርቀው የሚመጡትን በአለቅነት ሳይሆን ሥራን በተግባር ያስተማሩ፣ በዋናው ኦዲት ቢሮ ብቃት የላችሁም መባሉ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡
በዋናው ኦዲት መሥርያ ቤት ለረጅም ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪ ያገለገሉና ሥራውን በሚገባ የተካኑ ማኔጀሮች እንዳሉ ሁሉ Chartered Certified Accountant ሆነው የበታች ሠራተኞች በሥራቸው እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ የእኛም እምነት ማንኛውም ዜጋ ክህሎቱ ታይቶና ተፈትኖ ተመጣጣኝ እውቅና እንዲሰጠው እንጂ ወረቀቱ ክህሎት እንደማይሆን ሕዝብም መንግሥትም ተረድቶት Certificate of Competence (COC) እንዲጀመር መደረጉ ሚስጥሩ የተለየ ነገር ኖሮት አይደለም፡፡
ዛሬ አገሪቷ ከምታሳየው ፈጣን ዕድገትና ማንኛውም የንግድ ሰው ወደ ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር እንዲገባ ግፊት በሚደረግበት ወቅት ለረጅም ዓመታት ዕድሜያቸውን በሙያው ያሳለፉ ሰዎች፣ ለንግዱ ኅብረተሰብም ሆነ ሙያቸውን ለሚፈልግ ማንኛውም አካል እንዳያካፍሉ መስፈርቱን አታሟሉም ማለቱ አግባብ ሆኖ አላየነውም፡፡
ለምሳሌ ከቴሌና ከተለያዩ መሥርያ ቤቶች በጡረታና በአገልግሎት ካሳ የተሰናበቱ ነገር ግን ከ20 ዓመታት በላይ በሲኒየር አካውንታንትና በኦዲተርነት ያገለገሉ ባለሙያዎች የመንግሥትን እጅ ሳይጠብቁ ሥራ ፈጣሪ (Self-employed) በመሆን ፈቃድ ተሰጥቷቸውና ታክስ በመክፈል ሕጋዊ ሥራ እንዳይሠሩ እንቅፋት መሆኑ አነጋጋሪ ይመስላል፡፡
ስለዚህ መሥርያ ቤቱ የብቃት ማረጋገጫውን ከሙያ ብቃት አንፃር እንጂ የወረቀት ማረጋገጫ ባያደርገው መልካም ነው፡፡ በተጨማሪም የብቃት ማረጋገጫው አሰጣጥ በመሥርያ ቤቱ ውስጥ የትርፍ ሥራ ተደርጎ ስለሚታይ ከክልል የሚመጡ ባለጉዳዮች በቀን ውስጥ ለሚያልቅ ሥራ ለወራቶች እየተመላለስን ስለሆነ፣ ጉዳዩ በሚገባ ተጠንቶና ውክልና በክልል ለሚገኙ መሥርያ ቤቶች ቢሰጥ ጥሩ ነው፡፡ እንዲሁም አሁን አገሪቷ ከምትፈልገው አካሄድ አንፃር የሚቀጥረውን የሚፈልግ ሳይሆን ሥራ ለሚፈጥር ትውልድ ማበረታቻ ከመሆን አንፃር መስፈርታችሁን ብታዩት የተሻለ ነው እንላለን፡፡ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ክትትል እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡
(ጢሞቲዎስና ጓደኞቹ ከዝዋይ)
***************
በሊዝ ወይስ?
በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 9 ውስጥ በ2002 ዓ.ም. የገዛሁት የነባር ይዞታ አለኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የስም ማዛወሪያ የክፍያ ደረሰኝ ተሠርቶልኝ በወቅቱ አጋጥሞኝ በነበረ ችግር ምክንያት ሳልከፍል ቆየሁ፡፡ ዘንድሮ በህዳር ወር ለመክፈል ወደ ክፍለ ከተማው ስሄድ የተሠራው ደረሰኝ ሁለት ዓመት ስላለፈው እንደ አዲስ የመሐንዲስ ተከፍሎ ግምት መውጣት አለበት ተባልኩ፡፡ የመሐንዲስ ከፍዬ መሐንዲሱ ቦታውንና ቤቱን አይቶ መረጃውን አቀረበ፡፡ አዲስ የስም ማዛወሪያ የክፍያ ደረሰኝ ሊሰጠኝ ለጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም. የቀጠሮ ወረቀት ተሰጠኝ፡፡ ጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ወደ ክፍለ ከተማው ስሄድ፣ አዲስ መመርያ እስከሚደርሰን ድረስ የስም ዝውውር ሥራ ላልተወሰነ ጊዜ ቆሟል ተባልኩ፡፡
ህዳር 18 ቀን 2004 ዓ.ም. የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ 721/2004 አንቀጽ 37 ንዑስ አንቀጽ 1፣ “ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቀደም ሲል ቀርበው በእንጥልጥል ላይ ያሉ የከተማ ቦታ ጥያቄዎችን በሚመለከት ይህ አዋጅ ከፀናበት ቀን ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በቀድሞው ሕግ መሠረት ውሳኔ መስጠት አለባቸው፤” ይላል፡፡
ይህ ከላይ የጠቀስኩት የስም ዝውውር ጉዳይ እስከ የካቲት 18 ቀን 2004 ዓ.ም. በእኔ ምክንያት ሳይሆን በክፍለ ከተማው ለማስተናገድ ያለመቻል ወይም ያለመፈለግ ምክንያት ባይጠናቀቅ፣ ሽያጩ ቀድሞ የተፈጸመው ይዞታዬ ወደ ሊዝ ሊዞርብኝ ነው ወይ? ብዬ ብጠይቅ፣ በክፍለ ከተማው ውስጥ መልስ የሚሰጠኝ አጣሁ፡፡ እባካችሁ የት አቤት እንደሚባል ስላልገባኝ የሚመለከተውን ባለሥልጣን መልሱን ቢሰጠኝ መልካም ነው፡፡
(ወ/ሮ ዝናሽ ከበደ፣ ከአዲስ አበባ)


