ገናናው በረሃ
ያ ሁሉ አፍላነት ለዘለዓለም መስሎን
ከጠይም ጉንትቶ ጦፊጦ ጨው ልሰን
ጆርጊስን አራዳ ምን አመጣው ብለን፣
ኤይድስ አልገባ ገና ሃያን አላሟላን
ከማህሌቱ በስተ ምሥራቅ ደፍረን ተሸራሙጠን
እቼቼ ገዳሜ በታንጎ ተለዝቦ
አሰሌነት ከረመጥ ፍም ጎልቶ
ሲረገድ ተመሽቶ ሲረገድ ተነግቶ፣
ልጅነትና አረቄን በቁርባን አጋብተን
እከበሮው እምብርት ጋደም ብለን ቃዥተን
እያላበን ውበቷ ቁልቁል ታይቶን፣
በቀላ ውጋጋን ድንጉጥ አስደንሰን
ለሉሲፈር ጭፍሮች እልቂት አስፈትፍተን
አፍላ ነበርንና ሸርሙጠን ወስውሰን
ሥልጡን ነበርንና ጦቢያት አድባራትን ገፍተን
ከእምሆቴፕ ከሆመር ያማልክት ስም ተውሰን
መልከ መልካም ጠንቋይ ዳፍንት አስገልጠን
ላፍላነት ቅዳሴ ጧፍ ሆነን ቀጠልን፡፡
ከልዝቡ ሸገር ሰማይ ምሕረትን እንደሚሻ
እጣን ጪሶ ሲዝለገለግ እንጦጦ መርገጫ
እንኳን የገጠማት አልታየችኝ እሷ
በንቶን ጭነት ተጎትተን ወርደን
ለምድራ’ለም ተስለን
ዓይናችንን ሳናሽ እነ ፀጉን ቀብረን
ህያው ነበርንና
ዘለዓለማዊ ልዑካን ሆነነ ነግሰን
ያ ሁሉ አልፎ ባእድ መንገድ ቀረን፡፡
- ሰሎሞን ደሬሳ፤ ዘበት እልፊቱ ወለሎታት፣ 1991
************
ሕልም እንደፈቺው ነው
ሰውዬው ሕልም አለምኩ በሎ ከፈቺው ይነግረዋል፡፡ ፈቺውም “ምን አየህ?” ቢለው “ነጭ ሸማ ለብሼ በአልጋ ላይ ተኝቼ አየሁ” አለው፡፡ ፈቺውም ሲተረጉም “ውይ መሞትህ ነው” አለው፡፡ አላሚውም ደንግጦ “ወርጃለሁ እኮ” አለው፡፡ ፈቺውም መልሶ “አርሱም ወደ መቃብር መውረድህ ነው” አለው፡፡ በዚህ ጊዜ አላሚው ተበሳጭቶ “በቃ አላየሁም” አለው፡፡ ለምን? ቢሉት “ፈቺ ቆረጠኝ” አለ ይባላል፡፡
ከሕልም ሕግጋት አንዱ “ሕልም እንደ ፈቺው ነው” የሚለው ትልቁ አንቀጽ ነው፡፡ ራእይ ግን እንደ ንባብና ትርጓሜ እንጂ እንደ ሕልም ፍቺ አይደለም፡፡ ማንም ሰው እንደ ፈለገው የተረጎመልንን ነገር የምናስተናግድበት ሳይሆን እውነተኛ መገለጥ ነው፡፡ ራዕያችንንም በየአስተርጓሚ ቦታ ይዘን ከሄድን ጥንቱንም ራእይ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ባለ ራእይ ሌሎችን ያስከትላል፡፡ ነገር ግን ደጋፊ አይፈልግም፡፡ የሚያጨበጭቡለት ስለሌሉ ሩጫውን አያቆምም፡፡ በሚወረወርበት ትርጉምም አይደናገርም፡፡ የገባውን ለማድረግ ብቻ ይተጋል፡፡
- አሸናፊ መኮንን “ራእይ ያለው ትውልድ” በሚለው መጽሐፍ እንደከተበው (2003)
*****************
ፈረንጅኛና ጥቅሙ
አዲሳባ ባለፉት አሥር ዓመታት መቶ ሺሕ ህፃናትን ወልዳለች፡፡ መቶ ምናምን አዳዲስ ሰፈሮችን ፈጥራለች፡፡ ሺ መኖርያ ቤቶችን ገንብታለች፡፡ ይህንንም ተከትሎ በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ብዙ የግል ትምህርት ቤቶች መሽቶ በነጋ ቁጥር በቅለውባታል፡፡ ሰፋ ያለ ግቢ ያላቸው መኖርያ ቤቶች ድንገት መዋእለ ህፃናት ሆነው ይነጋል፡፡ ትምህርት ቤት መክፈት ኪዮስክ ከመክፈት ዘለግ ያለ መሰናዶ የሚደረግለት አይመስልም፡፡
ወላጆች ለአብራክ ክፋዮቻቸው ትምህርት ቤቱ ሲመርጡ የቅድሚያ መመዘኛቸው ትምህርት ቤቱ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጠው ክብደት ብቻ ነው፡፡ ይህን እውነታ የተገነዘቡ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መላ አፈጣጠራቸውን ፈረንጅኛ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ጥረታቸው የሚጀምረው ደግሞ ለትምህርት ቤት ከሚሰጡት ስያሜ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በህይወት ካሉ ትምህርት ቤቶች ምሳሌ ብጠቅስ ሙግቴን ያጠናክርልኝ ይሆናል፡፡
“ጊብሰን አካዳሚ”፣ “ስኩል ኦፍ አሜሪካ አካዳሚ”፣ “አሜሪካና አካዳሚ”፣ “ካምብሪጅ አካዳሚ”፣ “ኦክስፎርድ አካዳሚ”፣ “ማክሚላን አካዳሚ”፣ “ማጂክ ካርፔት ስኩል”፣. . . . .ወዘተ፡፡
ትምህርት ቤቶቹ ብዙ ተማሪ እንዲመዘገብላቸው በክረምት ወራት በሚያስለፍፏቸው የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ውስጥ አንድ ፈረንጅ እንዲታይ ያደርጋሉ፡፡ “ይህንን አለማድረግ ከፍተኛ ኪሳራን ያስከትላል” ይላል በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች ለዘጠኝ ዓመት በመምህርት የሠራው አቶ ሞገስ፡፡ እርሱ እንደሚለው ምስላቸው በቴሌቪዥን እንዲታይ የሚደረጉት ፈረንጆች አንዳንዴ ለማስታወቂያው ብቻ በኪራይ መልክ የሚመጡበት አጋጣሚ አለ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በሚያመጡበት ሰዓትና ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት በሚወስዱበት ሰዓት እነዚህ ፈረንጆች በር ላይ ሆነው የማስተባበር ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያነጋገረው አንድ መምህር በአንድ ወቅት ባስተማረበት የግል ትምህርት ቤት የነበረ ጃማይካዊ ወላጆች በሚገኙበት ሰዓት ከፈረንጅ መምህራን ኋላ እንዲሆን በትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ስለተነገረው ከፍተኛ ቅሬታ ተፈጥሮበት ትምህርት ቤቱን መልቀቁን ያስታውሳል፡፡
- መሐመድ ሰልማን፤ በፒያሳ ማሕሙድ ጋር ጠብቂኝ ላይ እንደተረከው (2004)
*****************
የጊዜ አጠቃቀም
ገንዘብ ኖሮን ገንዘባችንን ለኢቨስትመንት ብንመድበው ልናተርፍ የምንችለው ገንዘብን ነው፡፡ በጊዜ ላይ ኢንቨስት ብናደርግ ግን የምናገኘው ስኬት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወታችን፣ በአእምሮ ብልጽግናና ሰላም በማግኘት፣ በፋይናንስ ዕድገትና በመሰል ጉዳዮች ተጠቃሚ እንደሆናለን፡፡ ወደምንፈልገው ቦታ ለማድረስ የሚያስችለን ድልድይ ጊዜ ነው፡፡
ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም ግልጽ የሆነ የሕይወት ዓላማና ግብ ሊኖረን ይገባል፡፡ ዓላማና ራዕያችንን ግልጽ አድርገን ከቀረጽን እዚህ ግብ ላይ የምንደርስበት የጊዜ አጠቃቀም በአግባቡ መንደፍ ይኖርብናል፡፡ ስኬት፣ ደስታ፣ አሸናፊነት . . . ከሚገኙባቸው መንገዶች አንዱ ግልጽ የሕይወት ዓላማ ቀርጾ ወደ ግባችን ለመድረስ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡
ጊዜን በአግባቡ ማስተዳደርና ከሰዎች ጋር መልካም ግነኙነት መፍጠር መቻል የመሥራት ብቃትን ለማሳደግና ዓላማን በወቅቱ ከግቡ ለማድረስ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የመሥራት ብቃት የሚገኘው ከዕውቀት ነው፡፡ የአሠሪው፣ የሠራተኛውም፣ የአለቆችም ዕውቀት ባደገ ቁጥር ሥራችን በያዝንለት ዕቅድ መሠረት ይሠራል፡፡
- ከዶ/ር ወሮታው በዛብህ እና ብርሃኑ ሰሙ “የብልጽግና ቁልፍ” የተወሰደ (2004)
*******************
የወቅቱ እንቆቅልሽ
በልዊስ ካሮል “Alice in Wonderland” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ፣ አሊስ ከአንድ ባርኔጣ አምርቶ ከሚሸጥ የተጃጃለ እብድ ጋር ሐሳብ በማንሣት ሲከራከሩ ይታያል፡፡
አሊስ “አንድ ነገር በዚህ መልኩ ማመን አይገባህም በፍጹም የሚቻል ነገር አይደለም” ብላ አስተያየት ስትሰጠው፡፡ ይህ ባርኔጣ አምራች ወፈፌ በኩራትና በመጀነን፤ “ከንቱ የሆንሽ ነገር! እኔ ሁሌም ጧት ጧት ቁርስ ከመብላቴ በፊት ቢያንስ ሁለት የማይቻሉ እምነቶች በማዳበር ለውጤት በማብቃት ልምድ አካብቻለሁ” በማለት መልስ ሰጣት፡፡
አብዛኛው አካባቢያችንና ዓለም በጠቅላላው ማለት ይቻላል የውስጥ ጥቅም ማስጠበቅን፣ ጉጉትንና መሃይምነትን አንድ ላይ ተቆራኝተው በሕዝቡ ላይ በመስፈን የዚህ ዓይነቱን የማይቻል አዋጅ ሲያስነግሩ ይደመጣል፡፡ የማይቻለው ይቻላል የማይሆነው ይሆናል ሲሉም ይታያል፡፡
የሆነ ነገር ስለተናገሩ ብቻ እውነት አይሆንም
የሚንጫጩ ድምፆች ከምክንያታዊነት ሲርቁና ሲነጠሉ ልማዶች ይሆናሉ ታማኝነታቸውንም ያጣሉ “ተዉት እሱ ልማዱ ነው” የሚል ስያሜ ያሰጣሉ ወይም ደረቅ ሙግት ፍሬ አልባ ጩኸት ይሆናሉ፡፡ የሆነ የመናገር ስሜት ካደረባቸው ወይም የማይቻለውን ነገር መጻፍ ካለባቸው በፈለጉት አቅጣጫ ይከትቡታል፣ በቃ በሆነ መልኩ እውነት መምሰል ይጀምራሉ፡፡ ልክ እንደተረት ሰሚ ያገኛሉ፡፡
በናዚ ፕሮፖጋንዳ 1930ዎቹ “ግዙፍ ውሸት” ዳብሮ የጀርመን ሕዝብን በማደናገር ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ የዚህ ንድፈ ሐሳብ ወገብህን አስረህ በቂ የሆነ ውሸት በስፋት ካናፈስክ ቀስ በቀስ ሰዎችን ማመን ይጀምራሉ፤ ምንም እንኳን በውስጡ ቅንጣት ታህል እውነት ባይዝም ያምኑሃል ይላል፡፡
አንዴ አንድ ሰው የሆነ ነገር ማመን ከጀመረ፣ ሆን ብሎ እየመረጠና እየለየ፣ ያንን እምነቱን የሚፃረረውን ችላ በማለት አዲሱን መረጃ ብቻ ያጠናክራል ውሸትን እያመነ ይሄዳል፡፡ በተቻለው መጠን በይበልጥ ያንን እምነቱን የሚያጠናክርለትና ወደ ትክክለኛነት የሚያመጣ መረጃ ያሰባስባል፡፡ የዚህ እምነቱ አፍራሽ የሆነ ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለም፡፡ እንደውም ውሸት ነው ያለውን አካል ከማጥቃት አይመለስም፡፡ ከቻለም አምበርክኮ የእምነቱን ተሸካሚ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡
- ከአካሉ ቢረዳ “ያለልፋት መቋመጥ ሐብት” መጽሐፍ የተወሰደ (2003)
***************
ገራገር
የ4 ዓመቱ ሕፃን ማሪዋና ይዞ ተገኘ
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ኮኔክቲከት የመልመጃ ክፍል ተማሪ የሆነ የአራት ዓመት ሕፃን በሻይ እረፍት ሰዓት ላይ ዘጠኝ የማሪዋና እሽጎችን ከጃኬቱ ውስጥ በማውጣት በቦታው የነበሩትን ማስደንገጡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሕፃኑ በሚማርበት ሀኖቨር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ይዞ የተገኘው ዘጠኝ እሽግ ማሪዋና ለሽያጭ ታስቦ ለየብቻ ለየብቻ የታሸገ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ኃላፊ የሆኑት ሚጉኤል ካርዶና እንደዚህ ዓይነቱ ነገር አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመው በትላልቆች ላይ መሆኑን በመጥቀስ ሁኔታው አሳዛኝና አስደንጋጭ መሆኑን ለሮይተርስ ገልጸዋል፡፡ “ይህ ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት ይዞ ስለመጣው ነገር የሚያውቀው አንዳችም ነገር የለም” ብለዋል፡፡
ፖሊስ የጉዳዩን መገናኛ ብዙኀን ላይ መቅረብ ተከትሎ ማሪዋናውን ይዞ የተገኘውን ሕፃንም ሆነ ወላጆቹን ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል፡፡ ጉዳዩ ይመለከተኛል ያለው የሕፃናትና የወላጆች ጉዳይ ተቋምም ሁኔታውን እየተከታተለው ነው፡፡
አሰናጅ፣ ምሕረት አስቻለው


