ከዳማው አስፋው
በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አማካይነት ተዘጋጅቶ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው ቁጥር 721/2004 የሊዝ አዋጅ ከታወጀበት ከመስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ የመነጋገርያ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሕዝባችን ለመሬት ከሚሰጠው ዋጋ አንፃር አዋጁ መነጋገርያ ርዕስ ሆኖ መክረሙ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ ፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ በአዋጁና ሪፖርተር ጋዜጣ ህዳር 13 ቀን 2004 ዓ.ም እትሙ የሊዝ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ እየተዘጋጀ ነው በሚል ባቀረበው ጽሑፍ መሠረት የደንቡ ዝግጅት ሊይዛቸው ይገባል ባልኳቸው ሐሳቦች ዙርያ የበኩሌን ለማለት ወደድኩ፡፡በአገራችን የመጀመርያው የሊዝ አዋጅ በ1986 ዓ.ም ወጥቶ በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ አዋጁ በ1994 ዓ.ም በድጋሚ ተሸሽሏል፡፡ የአሁኑ የሊዝ አዋጅ ለሦስተኛ ጊዜ ተሸሽሎ ነው የፀደቀው፡፡ አገራችን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃና በኅብረተሰቡ ካለው ከፍተኛ የሆነ የከተማ መሬት ፍላጎት አንፃር አዋጁ በድጋሚ እንዲሻሸል መደረጉ ተገቢም ትክክልም ነው፡፡
በዚህ ረገድ የሚነሳ ነገር ቢኖር የሚወጡ ሕጎች ያለፈውን ገምግመውና አሁን ያለውን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ከተው፣ የወደፊቱን በጥናት ላይ በመመሥረት ገምተው ዘላቂነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ቢያደርጉ በሚወጡ ሕጎች ላይ መተማመን ያጠናክራል፡፡ ሕጎቹ በየጊዜው የሚለዋወጡ ከሆነ የተዓማኒነት ደረጃቸው ይቀንሳል ሕዝቡም ነገ ይሻሻላል የሚል ጥርጣሬ ስለሚኖረው በአፈጻጸም ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡
አዲሱ አዋጅ የራሱ የሆነ ጥንካሬን እንደያዘ ሁሉ ማስተካከያ ሊደረግባቸው የሚገቡ አንቀጾችንም ይዟል፡፡ ጥንካሬውን ከማስተዋወቅ አንፃር ብዙ ተሠርቷል ለማለት አልደፍርም፡፡ በተለይም በሚኒስቴሩ ውስጥ የመጀመርያውን ሊዝ አዋጅ ከማዘጋጀት ጀምሮ በሊዝ ላይ በአገር ውስጥም በውጪም ከፍተኛ እውቀት ያካበቱ፣ ስማቸው ሳይቀር “እገሌ ሊዙ” በመባል የሚጠሩ ታዋቂ ባለሙያዎች ያሉት ተቋም፣ አዋጁን ከማስተዋወቅ አንፃር ብዙ ርቀት አለመሄዱ ኅብረተሰቡ በአዋጁ ላይ ለሚያነሳቸው ጥቄዎች መበራከት በር ከፍቷል፡፡ ስለሆነም ሚኒስቴሩ በውስጡ ያሉትን የአሠራር ችግሮች ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው አልፎ አልፎ “ባለሙያ” በሚባሉ ሰዎች የሚሰጡ አስተያየቶች ባለሙያ ከሚባሉ ሰዎች ሊቀርቡ የሚገባቸው አይደሉም፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይ የበሰሉ ናቸው ለማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ ያለው ክፍተት እየተሞላ ያለው በክቡር ሚኒስትሩ [አቶ መኩርያ ኃይሌ] የግል ጥረት ይመስለኛል፡፡ ይህን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ አዋጁ ቀደም ሲል ከወጡት ሕጎች አንፃር ሲታይ ዘርዘር ያለ ለግልጽና በፍትሐዊ የመሬት አቅርቦት ትኩረት በመስጠት ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በአብዛኛው ለመድፈን የሞከረ በመሆኑ፣ በመሬት ላይ ያለውን ያልተገባ አሠራር ለመከላከል በተወሰነ ሁኔታ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በአዋጁ ላይ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በተመለከተ
አዋጅ ቁጥር 721/2004 ቀደም ሲል ከወጡት ሕጎች አንፃር ነባር ይዞታን (የምሪት ይዞታን) ወደሊዝ ከማሸጋገር አኳያ በመርህ ደረጃ ልዩነት የለውም፡፡ የምሪት ይዞታ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ወደሊዝ ሥሪት ይገባል የሚለው የአዲሱ አዋጅ አንቀጽ፣ ቀደም ሲል በነበሩትም ሕጎች ላይ በተለይም በ1986 ዓ.ም. በወጣው የሊዝ አዋጅ በግልጽ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን፣ በአዋጅ ቁጥር 272/94 በተፈጻሚነት ወሰኑ ላይ የሊዝ አዋጁ በሊዝ/በምሪት ወይም በሌላ ሁኔታ በተያዙም ሆነ ከዚህ በኋላ በሚፈቀዱ የከተማ ቦታዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፣ ይልና እንዴት እንደሚፈጸም ዝርዝሩ በክልሎች የሚወሰን ይሆናል ይላል፡፡
ይህ የሚያሳየው ነባር ይዞታ በሊዝ ሥርዓት መተዳደር እንዳለበት የቀድሞዎቹም ሕጎች ያስቀመጡት በመሆኑ፣ አዲሱ አዋጅ በዚህ ዙርያ የተለየ ያመጣው ነገር እንዳለ ሊታሰብ አይገባም፡፡ ቀደም ሲል የነበሩትም ሕጎች ቢሆኑ በዚህ ዙርያ የነበራቸው አቋም ትክክል አይደለም የሚባል ከሆነ፣ በሚነሱ ጥያቄዎች የከተማ መሬትን ወጥ በሆነ ሁኔታ በሊዝ ሥሪት ብቻ ማስተዳደር ተገቢ አይደለም፤ ሁለቱም ሥሪቶች ሊቀጥሉ ይገባል የሚል ነው መሆን ያለበት፡፡
ሁለቱንም ሥሪት ማራመድ አይቻልም የሚል አመለካከት ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህንኑ ተግባራዊ የሚያደርጉ ሌሎች አገሮች እንዳሉ የሚታወቅ በመሆኑ፣ ከእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታና ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች አንፃር የትኛው ነው ለአገራችን የሚስማማው የሚለውን በተመለከተ፣ አገሪቱን የሚያስተዳድረው ገዥ ፓርቲ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 87/5 የተደነገገውን ለማስፈጸም እንዲረዳው፣ የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ፖሊሲውን ሲያፀድቅ ወጥ በሆነ ሁኔታ በከተሞች የሊዝ ሥሪት እንዲተገበር ማድረግ፣ ለአገራችን ዕድገት ተመራጭ ነው በሚል በፖሊሲ ሰነዱ ውስጥ ይኼው ሥሪት ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል፡፡ ይህን ተከትሎ የወጣው የሊዝ አዋጅም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተጠንቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚፀድቅ ነባር ይዞታዎችን እንዴት ወደሊዝ ሥሪት ይቀየሩ የሚል ጥናት እንደሚያቀርብ ተደንግጓል፡፡ መቼና እንዴት የሚለው ወደፊት በጥናት የሚመለስ መሆኑን አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ከዚህ አንፃር አሁን ባለው ሁኔታ ጥናቱ እስኪቀርብ ነባር ይዞታ ለሦስተኛ ወገን እስካልተላለፈ ድረስ በነበረበት የሚቀጥል በመሆኑ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚነሱት ጥያቄዎች አዋጁን ካለመረዳት ስለሚመጡ፣ በቀጣይ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አዋጁን በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ነባር ይዞታ ከውርስ በስተቀር ባለቤትነቱ ሲተላለፍ ወደ ሊዝ ሥሪት መግባቱን በተመለከተ
ቀደም ሲል በ1986 ዓ.ም በወጣው አዋጅ ላይ ነባር ይዞታ ከውርስ በስተቀር ባለቤትነቱ ሲተላለፍ ወደ ሊዝ ሥሪት እንደሚቀየር ተደንግጎ የነበረ ሲሆን፣ በ1994 ዓ.ም በወጣው የሊዝ አዋጅ ላይ ይህ አንቀጽ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ አሁን በድጋሚ የአዋጁ አካል የሆነበት ምክንያት ምንድነው ብለን ብንጠይቅ ብዙ ምላሾች የሚሰጡ ቢሆንም፣ ዋናው ግን የምሪት ይዞታዎች በሽያጭ ወቅት ገበያውን ማዛባታቸው (Market Distortion) መፍጠራቸው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህን ሒደት በሌላ ሁኔታ ለምሳሌም መንግሥት የንብረት ሽያጭ ታክስ (Capital gain Tax) በመጣል የዋጋውን ልዩነት ማስተካከል ማቀራረብ ይችላል፡፡ አዋጅ ቁጥር 272/94 ታሳቢ ያደርግ የነበረው ይህንኑ በመሆኑ በሚል የሚጠይቁ ሰዎች አሉ፡፡ በእርግጥ በገበያ ውስጥ ያለውን ልዩነት ለማጥበብ በነባር ያዞታ ላይ የንብረት ሽያጭ ታክስ በመጣል፣ በነባር የይዞታ ሥሪት በተያዙ ይዞታዎችና በሊዝ ሥሪት በተያዙ ይዞታዎች መካከል በገበያው ላይ የሚፈጠረውን መዛባት በማስተካከል፣ መንግሥት ለአካባቢ መሠረተ ልማት ዝርጋታና ለአካባቢ መለወጥ ያወጣውን ወጪ በተዘዋዋሪ ማግኝት የሚችልበትን አሠራር መዘርጋት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ሁኔታ የነባር ባለይዞታውን መብት የበለጠ የሚያጠበው በተደጋጋሚም በየልውውጡ ለክፍያ የሚዳርገው ሲሆን፣ ወጥ ሥሪት ልተግብር ብሎ ለተነሳው መንግሥት ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ይሆንበታል፡፡
ከዚሁ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ግን የነባር ይዞታዎች ከውርስ በስተቀር በማንኛውም ሁኔታ ወደ ሦስተኛ ወገን ሲተላለፉ ቀድመው ወደ ሊዝ ሥሪት እንዲገቡ ለምን አስፈለገ የሚለው ነው፡፡ በአገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ነባር ይዞታዎች ላይ ሊዝ ተግባራዊ ሲደረግ አብሮ እንዲፈጸም ከማድረግ ይልቅ፣ አሁን በሽያጭ ወቅት ማንኛውም ነባር ይዞታ በመነሻ ዋጋ ወደሊዝ ይግባ መባሉ፡-
1. አሁን ያለውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ይገታል፤
2. አሁን ነባር ይዞታዎች በመነሻ ዋጋ የሚገቡ ከሆነ ወደፊት ይቀርባል ከሚባለው ጥናት ኅብረተሰቡ የተለየ ነገር ለመጠበቅ ይቸገራል፡፡ የተለየ ሁኔታ ይኖራል ብሎ ከገመተም በተለይም ከመነሻ ዋጋ ያንሳል የሚል ግምት ከተፈጠረ፣ ለተወሰኑ ጊዜያት በከተሞች የሚካሄድ የመኖርያ ቤት ሽያጭ አይኖርም፤
3. በፌደራል ደረጃ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ይዞታዎች በመነሻ ዋጋ ወደ ሊዝ ሥሪት ይግቡ ብሎ መወሰኑ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄን የሚያስነሳ ይሆናል፤
4. የመነሻ ዋጋ በራሱ በትክክለኛው ሁኔታ ቢሰላ ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም በላይ ስለሆነ፣ ውሳኔው የሕዝቡን የመክፈል አቅም ግንዛቤ ውስጥ ያልከተተ ይሆናል፤
ነባር ይዞታ በሽያጭ ወቅት በመነሻ ዋጋ ወደ ሊዝ ሥሪት ይገባል መባሉ ከላይ እንደተገለጸው የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ይጎዳል፡፡ ይህ አንቀጽ የግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይጎዳባቸው ሲሉ ከተሞች አዋጁ ማሻሻያ እንዲደረግበት ድምፃቸውን ማሰማት አለባቸው፡፡ የንብረት ገበያው ያለበት ደረጃ በዚህ በአንድና ሁለት ወር ውስጥ እንኳ ምን እንደሚመስል በመታየት ላይ ያለ እውነታ ነው፡፡
ሌላው በመነሻ ዋጋ መባሉ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 97/2 ላይ ክልሎች የመሬት መጠቀሚያ ክፍያ ይወስናሉ፣ ይሰበስባሉ በሚል ሥልጣን የተሰጣቸው በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥት የነባር ይዞታ ባለቤትነት ከውርስ በስተቀር በማንኛውም ሁኔታ ሲተላለፍ በመነሻ ዋጋ ይሆናል በሚል፣ በአዋጁ የመሬት መጠቀሚያ ዋጋን መወሰኑ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡
ይህን አንቀጽ እንዳለ እንውሰደው ብንል እንኳ የመነሻ ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው በአዲስ አበባ ነው፡፡ ጸሐፊው ባለው መረጃ መሠረት አዲስ አበባ ላይ የሊዝ መነሻ ዋጋው ዝቅተኛው 200 ብር ከፍተኛው ደግሞ 400 ብር አካባቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትክክል የመነሻ ዋጋን አያሳይም፡፡ ለዚህም ነው አዋጁ የሊዝ መነሻ ዋጋን ቢያንስ በየሁለት ዓመቱ መስተካከል እንዳለበት ያስቀመጠው፡፡ የመነሻ ዋጋ ማለት በአዋጁ እንደተሰጠው ትርጓሜ ዋና ዋና የመሠረተ ልማት አውታሮች የመዘርጊያ ወጪን፣ ነባር ግንባታዎች ባሉበት አካባቢ የሚነሱ ግንባታዎችና ንብረቶችን ለማንሳት የሚያስፈልገውን ወጪ፣ ለተነሺዎች የሚከፈል ካሣንና ሌሎች አግባብ ያላቸው መስፈርቶችን ታሳቢ ያደረገ የመሬት የሊዝ ዋጋ ነው፡፡ ይህን ስናይ በአዲስ አበባ ያለው የሊዝ መነሻ ዋጋ ትክክለኛ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ በትክክል ይሰላ ከተባለ አዲስ አበባ ውስጥ ከቦታ ቦታ መለያየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአማካይ የመነሻ ዋጋው ከአንድ ሺሕ ብር የሚያንስ አይሆንም፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ እንኳ በመቀሌ ከተማ የሊዝ መነሻ ዋጋ አሁንም ከቦታ ቦታ መለያየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ እስከ 700 ብር ደርሷል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት የመነሻ ዋጋ በየሁለት ዓመቱ መሻሻል እንዳለበት በአዋጁ ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ሁኔታ የመነሻ ዋጋ እየተስተካከለ ሲሄድ በሁለትና በሦስት ዓመት ውስጥ አሁን ካለበት ሁለትና ሦስት ጊዜ እጥፍ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም የመሠረተ ልማት ወጪዎች የቱን ያህል ዋጋቸው እየጨመረ እንደመጣ የሚታይ ነው፡፡
የዋጋዎች መጨመር በመነሻ ዋጋ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ስላለው፣ ነባር ሥሪትን ወደሊዝ ሥሪት በመነሻ ዋጋ የመቀየሩን ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ያደርገዋል፡፡ በውጤቱም የከተሞች ገቢ ክፉኛ እንደሚቀዛቀዝ መገመት አያዳግትም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ሕጋዊ ያልሆኑ ሽያጮች እንዲበራከቱ በማድረግ በሒደት ተጠቃሚ እንዳይኖር ያደርጋሉ፡፡
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉት የኮንዶሚንየም ቤቶች ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ባለው ሁኔታ የኮንዶሚኒየም መኖርያ ቤቶች ለአምስት ዓመታት መሸጥ መለወጥ የተከለከለ ነው፡፡ ይህ የተደረገበት የራሱ የሆነ ዓላማ ያለው ቢሆንም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ውስጥ ለውስጥ ይሸጣሉ፤ ይህን ሁሉም ሰው ምናልባትም መንግሥትም ጭምር የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት ተጠቃሚው ማነው ብለን ብንጠይቅ መልስ አናገኝም፡፡ ምክንያቱም ሻጭ ቤቴ ነው ብሎ በሚገባ ተደራድሮ ለመሸጥ አይችልም፡፡ በሕግ የተከለከለ በመሆኑ ገዥ እምነት አሳድሮ ንብረቱን ለመግዛት አይደፍርም፡፡ ስለሆነም ኃላፊነቱን በመውሰድ ለንብረቱ ትክክለኛውን ዋጋ ሳይሆን ባወጣ ያውጣው የሚል ዋጋ ሰጥቶ ይገዛል፡፡ በእነዚህ ሒደቶች መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ታክስ አያገኝም፡፡ ሽያጩ ሕጋዊ ዕውቅና የሌለው በመሆኑ ከዚህ የምንረዳው ሻጭም፣ ገዥም፣ መንግሥትም ተጎጂ እየሆኑ ያሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው፡፡
በነባር ያዞታዎችም ላይ ይህ ሥጋት መከሰቱ አይቀርም፡፡ ነባር ባለይዞታው የተሻለ ክፍያ ለማግኝት ሕጋዊ ሽያጭ ለመፈጸም አይደፍርም፡፡ ምክንያቱም ገዥ ለንብረቱ ዋጋ የሚሰጠው የሊዝ ክፍያውን ጭምር አስቦ ስለሚሆን፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ንብረቱን ቢሸጥ ያገኝ ከነበረው ገንዘብ በታች ስለሚያደርግበት፣ ወይ ንብረቱን አይሸጥም ከሸጠም ልክ እንደ ኮንዶሚኒየም ቤት ሻጭ ለምዝገባ ወደ መንግሥት ተቋም አይሄድም፡፡ ገዥም ወደ ሊዝ ሥሪት ይዞታው እንዳይገባ በመፈለጉ የተነሳ የነባር ይዞታዎች ልውውጥ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በሒደቱም መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ታክስ ያጣል፡፡
በዚህ ሒደት የአዋጁ ዓላማ የሆነው የተሳለጠ፣ ውጤታማ፣ ፍትሐዊና ጤናማ የመሬትና መሬት ነክ ንብረት ገበያ ልማት እንዲኖር ማድረግና ቀጣይነት የተላበሰ የነፃ ገበያ ሥርዓት ማስፋፋት፣ ተቃራኒ ውጤት ሊገጥመው እንዳይችል በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ካልተቻለም አሁን በየከተሞቹ ያለው የመነሻ ዋጋ ብቻ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ ደንቡ ሲዘጋጅ ታስቦበት እንዲካተት ማድረግ የተጀመረውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተወሰነ ሁኔታ ለመደገፍ የተወሰነ አቅም ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገርግን በአዋጁ እንደተቀመጠው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሊዝ መነሻ ዋጋን ባስተካከሉ ቁጥር ነባር ይዞታም ይህንኑ ክፍያ እየከፈለ ነው ወደ ሊዝ ሥሪት የሚቀይረው የሚባል ከሆነ፣ መንግሥት ወጥ ሥሪት የሚባለውን ሁኔታ የፈለገው ከነባር ባለይዞታዎች ላይ ገንዘብና ገንዘብ ብቻ ለመሰብሰብ አስቦ ያደረገው ያስመስልበታል፡፡
ይህ አካሄድ ደግሞ ነባር ባለይዞታዎች ለቦታው የሊዝ ዋጋ መሻሻል ምንም አስተዋጽኦ እንደሌላቸው የሚቆጥርና ልማት የሚመጣው በመንግሥትና በመንግሥት ብቻ ነው ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ለአካባቢው መለወጥ ያደረገውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ የሚከት ካለመሆኑም በላይ፣ ንብረቱን ለመሸጥ የሚነሳ ማንም ሰው አካባቢው ከፈጠረለት ዋጋ ምንም ድርሻ እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው፡፡
ባንኮችን በተመለከተ በተለይም አሁን በመያዣነት በያዟቸው ንብረቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ቀደም ሲል ሲሰጡ በነበሩ የብድር አሰጣጥ ሒደቶች ወቅት መሬቱ ዋጋ ስለሚሰጠው የሚፈቀደው ብድርም መሬቱን ታሳቢ በማድረግ መጠኑ ከፍ ወይም ዝቅ ይል የነበረ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን መሬቱ ወደ ሊዝ ሥሪት ስለሚገባ ቀደም ሲል በተያዙት ንብረቶች ላይ ባንኮች ለኪሳራ የሚዳረጉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ምክንያቱም የፎርክሎዠር አዋጁ በግልጽ የተሻረ ስለሆነ ባንኮች በዚህ ጉዳይ የበኩላቸውን ማለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ደንቡ ቢያንስ ቢያንስ ለአፈጻጸም ምቹ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር፡፡
በቤት ሽያጭም ሆነ በባንክ መያዣ የሚያዙ ቤቶች የተሻለ ሽያጭ ወይም ብድር ሊያመጡ የሚችሉት በተሻለ የመኖርያ አካባቢ ላይ ቤቶች በመገንባታቸውና ባለመገንባታቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በባንክም ያለው የብድር አሰጣጥ ሒደት ከዚሁ የተለየ ባለመሆኑ አዲሱን የሊዝ አዋጅ ለማስፈጸም የሚወጣው ደንብ በማያሻማ ሁኔታ ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን የነባር ሥሪት ባለይዞታዎች ለባንክ ብድር ማስያዣነት ንብረታቸውን ቢያቀርቡ ተገቢውን የገንዘብ መጠን በብድር መልክ ለማግኝት እንቅፋት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ባንክም በሊዝ ላልተያዙ ይዞታዎች ብድር መስጠት አንድ ውሳኔ አስካልተወሰነ ድረስ አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በሒደቱም ባለይዞታዎች ተጎጂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም ቢያንስ ቢያንስ የጥናቱ ውጤት አጠቃላይ መፍትሔ እስኪሰጥ ድረስ እየተዘጋጀ ነው ወይም ረቂቅ ሆኖ ወጥቷል የሚባለው ደንብ እነዚህን ሁኔታዎች ሊያስታርቅ የሚችል ሆኖ መቀረጽ ይኖርበታል፡፡ ወይም ቀደም ሲል ለስም ዝውውር በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወጥቶ እንደነበረው መመርያ ሁሉ፣ በሽያጭ ወቅት ባንኮች ትርፍ እስካላገኙ ድረስ ከባንክ ላይ ንብረት (አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ለተያዙ ንብረቶች) የሚገዛው ሰው የሊዝ ክፍያ አይጠየቅም የሚል አቅጣጫ መቀመጥ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it ማግኘት ይቻላል፡፡


