Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

ቡልቶን ተስፋ ያደረጉ

  • PDF

ከአዲስ አበባ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው መቂ ዱግዳ ወረዳ ውስጥ ካሉት ቀበሌዎች አንዱ ሹሚ ገሞ ነው፡፡

ሰንቦ ስስት በሚል ልዩ ስሙም ይታወቃል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱት አሸዋን ከወንዝ ውስጥ እያወጡ በመሸጥ ነው፡፡

የአሸዋን ሥራ የሚሠሩት ‹‹ቢቂልቱ ጉዲና›› የሚል መጠሪያ ባለው ማኅበር ስር የተደራጁት ወጣቶች 86 ናቸው፡፡ እነዚህ በማኅበሩ ውስጥ የታቀፉት ወጣቶች በስምንት በስምንት ተቧድነው ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ 

አሸዋውን የሚያወጡት በአካባቢው ከሚገኝና ቡልቶ የሚል መጠሪያ ካለው ወንዝ ውስጥ ነው፡፡ አሸዋውን ሲያወጡ ማን ከየትኛው ቦታ ላይ ማውጣት እንደሚችል ለመለየት፣ ለእያንዳንዳቸው ሦስት እርምጃ ያህል ተለክቶ ይሰጣቸዋል፡፡

ከዚያም በስምንት የተቧደኑት እነዚህ ወጣቶች ይከፋፈሉና የተወሰኑት ከወንዙ ውስጥ አሸዋውን ወደ ወንዙ ዳርቻ ሲያወጡ የተቀሩት ደግሞ ከወንዙ ዳርቻ በማንሣት የአሸዋ መኪና ወደሚገኝበት አውራ ጎዳና በአህያ አማካይነት በጉርድ ጀሪካኖች ያመላልሳሉ፡፡

በወጣቶቹ ዘንድ በብዛት የተለመደው በአንድ አህያ ላይ አራት ጀሪካኖችን በአሸዋ ሞልቶ በመጫን 50 ጊዜ ማመላለስ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ተመላልሶ የተከማቸው የአሸዋ መጠን አንድ የአሸዋ ገልባጭ መኪናን መሙላት ከቻለ 700 ብር ይሸጣል፡፡ እነርሱ የሚሉት ብዙውን ጊዜ የሚሆነው ግን የሚያከማቹት አሸዋ ግማሽ መኪና ብቻ ስለሚሆን አሸዋውን በ350 ብር ይሸጣሉ፡፡

ወጣቶቹ በማኅበር ተደራጅተው መሥራታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡

ትምህርታቸውን አቋርጠው፣ ኑሯቸውን ለመደጎም በአሸዋ ሥራ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አንዱ የ20 ዓመቱ ፈይሳ በዳሶ ነው፡፡ ወደ አሸዋ ሥራ የገባው  ትምህርቱን ከአምስተኛ ክፍል አቋርጦ ነው፡፡ ፈይሳ በአሸዋ ሥራው በቀን 50 ብር ቢያገኝም አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ትንሽ እንደሆነ ይናገራል፡፡

እጅን አጣጥፎ ሥራ አጥ ሆኖ የቤተሰብ ተጧሪ ከመሆን ይልቅ፣ ያገኘውን ሠርቶ ራሱን መደገፍና በተቻለው አቅምም ገንዘቡን አጠራቅሞ ትምህርቱን መቀጠልም ይፈልጋል፡፡ ወጣቱ አሁን በሚሰራው ስራ ተጠናክሮ የተሻለ ገቢን የሚያስገኝለት ዘርፍ ውስጥም በቀጣይነት መሰማራትም እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

ፊታላ ቶፋ የ21 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ፊታላ ትምህርቱን ከሰባተኛ ክፍል ያቋረጠ ሲሆን፣ ሁኔታዎችን አመቻችቶ የተሻለ መኖር ሲጀምር በትምህርቱ ገፍቶ ወደፊት ዶክተር መሆንን ይሻል፡፡

ወጣቱም እንደ ፈይሳ በቀን የ50 ብር ገቢ ያለው ሲሆን፣ የአሸዋውን ሥራ ባይጀምረው ኖሮ ግን ቤተሰቦቹን በእርሻው ዘርፍ ያግዛቸው እንደነበር ገልጿዋል፡፡

ፊታላ ከቤተሰቦቹ በውርስ በሚያገኘው አንድ ሔክታር መሬት ላይ ለማረስ ግን የግድ በሬ ያስፈልገዋል፡፡ “አሁን የማገኘውን ገንዘብ እንደምንም አጠራቅሜ አንድ በሬ መግዛት አለብኝ፤” ብሏል፡፡ አንድ በሬ ቢያንስ አራት ሺሕ ብር ያወጣል፡፡ በአሸዋ ሥራ የተሰማሩት እነዚህ ወጣቶች በውስጣቸው የተሻለን ነገን እንደሚያዩ እርግጠኞች እንደሆኑ ስሜታቸውም ሆነ ወኔያቸው ይገልጻል፡፡

ወጣቶቹ ሥራቸውን ሲሰሩ ሰብሰብ ብለው በቡድን እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ስራቸውን የሚያከናውኑት በጨዋታና በቀልድ በታጀበ ስሜት በመሆኑ ስራቸውን ካለመሰልቸት ከጧቱ ሁለት ሰዓት ጀምረው እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ያጠናቅቃሉ፡፡

የእነዚህ ወጣቶች ስብስብ ዕድሜ ከ23 የማይበልጥ ሲሆን፣ ሁሉም በተለያየ አጋጣሚ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ ይሁንና ራሳቸውን የማስተዳደር ከፍተኛ ጉጉት ያደረባቸው እነዚህ ወጣቶች ምንም ቢሆን ምን ከመሥራት ወደኋላ እንደማይሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ የተስፈኛነት ስሜት ብዙ ጉልበት የሚፈጀውን የአሸዋን ሥራ በመልካም ፈቃደኝነታቸው እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፡፡