ከመድን ሽፋን አሰጣጡ ጋር ተያይዞ ነገ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ክፍተቶች ይታያሉ በሚል በአንዳንድ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ትችት እየቀረበበት ያለው አንዱ ጉዳይ የተሽከርካሪዎችን የተሳፋሪ ልክ የሚመለከት ይሆናል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የመድን ሽፋኑን የሚሰጡት የተሽከርካሪውን ሊብሬ አይተው ነው፡፡ በሊብሬው መሠረት አንድ ሚኒባስ መያዝ የሚችለው 12 ሰዎች ነው፡፡ በሦስተኛ ወገን የዓረቦን ግዥ የሚካሄደው ደግሞ በየአንዱ ሰው ተሰልቶ ስለሆነ የዚህ በተሽከርካሪው ውስጥ መኖር የሚገባው ሰው ቁጥር ወሳኝ ነው፡፡
በሦስተኛ ወገን አስገዳጅ የኢንሹራንስ ሽፋን አዋጅ መገንዘብ እንደሚቻለው ደግሞ በተሽከርካሪ ውስጥ ያለም ሆነ ከተሽከርካሪው ውጭ መኪናው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ በሚፈጠር አደጋ ለሚጎዳ ሰው ካሳ ክፍያ እንዲያገኝ የሚያደርገው በተናጠል ለእያንዳንዱ ሰው የጉዳቱ ልክ ታይቶ ነው፡፡
እያንዳንዱ ተሽከርካሪ አስገዳጁን የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ይግዛ ሲባል አዋጁ እያንዳንዱ ተሳፋሪም ሆነ እግረኛ የመድን ሽፋን እንዲኖረው ያደርጋል የሚል እምነትን ያሳድራል፡፡
የዚህ የመድን ሽፋን አሰጣጥ ግን በተሽከርካሪው ይይዛል ተብሎ በሚታሰበው የሰው መጠንና ሽፋን እንዲሰጥበት ዓረቦን በሚገዛበት ሰው ብዛት መካከል ልዩነት መኖሩ ግን አፈጻጸም ላይ ክፍተት እንዲኖር የሚያደርግ ይመስላል፡፡
አሁን በከተማችንም ሆነ ከከተማ ውጭ የሚሠሩ ሚኒባሶች እንዲጭኑ የሚፈቀድላቸው ሾፌሩን ጨምሮ 13 ሰዎችን ነው፡፡ የኋላ መቀመጫ ወንበር ሦስት ሰው የሚይዝ ቢሆንም መንግሥት አራት እንዲሆን ፈቅዷል፡፡ ሆኖም የአንድ ሚኒባስ የመጫን ትክክለኛ አቅም ሾፌሩን ጨምሮ 12 ሰው ነው፡፡ መኪናው ወደአገር ሲገባም አብሮት የሚቀርበው ሊብሬም የሚያመለክተው 12 ሰው መጫን ይችላል የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሚኒባሶች ለአስገዳጅ ሕጉ ዓረቦን የሚገቡት ደግሞ በ12 ሰው ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ተጨማሪ አንድ ሰው ጨምረው 13 ሰዎችን መያዝ ቢችሉም፣ ሊብሬው 12 ሰው ስለሚል ኢንሹራንስ ኩባንያው በዚሁ ሊብሬ መሠረት ያስተናግዳቸዋል፡፡
በሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን በ12 ሰው ሽፋን የተሰጠው ተሽከርካሪ አያድርስና በሁሉም ላይ አደጋ ቢደርስ ደግሞ ኢንሹራንስ ኩባንያው ሊከፍል የሚገደደው ለ12ቱ ብቻ ነው፡፡ አሁን ሕጉ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ቢፈጠር እንዴት ሊስተናገድ ይችላል የሚለው ጉዳይ ገና ከወዲሁ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሌላው መታሰብ ያለበት ጉዳይ ደግሞ ከ12ቱ ተሳፋሪዎች ሌላ ሾፌሩና ረዳቱ ሲጨመሩ 14 ይደርሳሉ፡፡ ስለዚህ የሁለት ሰዎች ዋስትና በእንጥልጥል ላይ እንደሆነ የሚያመላክት በመሆኑ የሦስተኛ ወገን የኢንሹራንስ ሽፋን አሰጣጥ ጋር ተይይዞ ይህ ክፍተት የታየ አይመስልም፡፡ ይህ እንግዲህ ታክሲዎቹ መንግሥት በፈቀደላቸው የተሳፋሪ መጠን ሲሰላ የምናገኘው ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን እጅግ አሳሳቢ የሚሆነው የከተማ ታክሲዎችም ሆኑ የከተማ ውጭ የሚሠሩ ሚኒባሶች በአብዛኛው ከ12 ወይም ከ14 በላይ ተሳፋሪዎችን የሚጭኑ በመሆናቸው፣ አሁንም አደጋ ቢከሰትና ተሳፋሪው ላይ ጉዳት ቢደርስ ኢንሹራንስ ኩባንያው እኔ የማውቀው 12 ተሳፋሪዎችን ብቻ ነው በሚለው አቋሙ ከፀና፣ ሌላው ተጎጂ እንዴት ሊደገፍ ነው; የሚለው ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከትራንስፖርት እጥረት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የተገልጋይ ፍሰት ባለበት ሰዓት አንድ ሚኒባስ ታክሲ እስከ 20 ተሳፋሪዎችን እንደሚጭን ስናስብ ደግሞ የጉዳዩን አሳሳቢነትን በግልጽ የሚያሳይ ይመስላል፡፡
የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ደግሞ የእኛ ግዴታ በሊብሬው ላይ የተጠቀሰው የ12 ሰው ዋስትና ብቻ ነው ቢሉ፣ ቀሪውን የማስተናገድ ግዴታ የማን ነው የሚሆነው; ዓረቦኑን ሲሰበስቡ ለ12 ሰዎች ብቻ በመሆኑ እነሱን አስገድዶ ለተጨማሪዎቹ ተጎጂዎች የጉዳት ካሳ ሊከፍሉ አለመቻላቸው በራሱ ነገሩ በድጋሜ መታየት ይኖርበታል ወደሚለው ሐሳብ ያስኬዳል፡፡ ከሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ጋር የሚታዩትን እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች በመንቀስ የሚስተካከሉበትን መንገድ ማመቻቸት ደግሞ አስገዳጁን ሕግ ለማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው መንግሥታዊ ተቋም ቢሆንም፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ባለሙያዎች ክፍተቶችን በማየት የመፍትሔ ሐሳብ የማቅረብ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡
የዚህ ሕግ መውጣት በዋናነት ተጎጂዎችን መደገፍን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ ወደ ትግበራ ሲገባ ክፍተቶቹን እየተከታተሉና እያሻሻሉ መሄድ የሚፈለገውን ግብ በማሳካቱ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡


