Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

ሞገደኛው የቴዲ አፍሮ አድናቂ - በኃይሌ ሩትስ ኮንሰርት

  • PDF

ዲቪ ሎተሪ

ምን ዓይነት ዘመን ነው የጉድ የፈንጣጣ
አንዱም ልውጣ ይላል አንደኛው ሲመጣ
ያኛው መረረኝ ሲል ካገሩ የወጣ

ይኸም መረረኝ ሲል ካገሩ ሊወጣ
እኔስ የፈራሁት ያ ሲከንፍ ይህ ሲከንፍ
ሰዎች በጉዞ ላይ እንዳንተላለፍ
እኔስ የፈራሁት አለ አንድ ነገር
ሁሉም ሂዶ ሂዶ ብቻዬን እንዳልቀር
ካልያም የሔደው ሁሉም ተመልሶ
አውሮፓ ኒዮርክ ቤሩት ቢሆን ፈልሶ
ሰፋፊው ጐዳና የሚጠርገው ሲያጣ
ስደተኛው ሁሉ ሀገሩ ሲመጣ፡፡

የዲቪ ሎተሪ በብዛት መጣልን
ይኸው ሠልፍ ይዘናል በየፖስታ ቤት
ሴቶችና ወንዶች ወጣት አዛውንት
አግብተን የፈታን አምና እንደሄዱት
ዲቪዋን ቢደርሰን እንደታደሉት
በጠዋት ተስለናል ለሚሰማን ጌታ
በሩቅ ለሚታየን ባሕር ማዶ ፌሽታ፡፡
- አሥራት እንለይ፣ ‹‹የመጀመሪያዪት›› (2000)

*    *   *   *   *   *   *   *   *   *   *  *  *  *  * 
ብሔር - ተኮር ማዘር ቤቶች
አንዳንድ ማዘር ቤቶች በአካባቢያቸው ያሉ ነዋሪዎችን፣ ወንዛዊነት ተመርኩዘው የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ለዚህ እንደ አብነት ከሚጠቀሱት መካከል የትግራይ ተወላጆች በሚበዙበት ተክለ ሃይማኖት አካባቢ የሚገኘው ‹‹ዐደይ ቤት›› ነው፡፡ በትግራዊ ሹሩባ አሠራር ተውበው ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ ተፍ ተፍ የሚሉትና በዕድሜ ጠና ያሉት የቤቱ እማወራ (ዐደይ) ላለፉት ዐሥር ዓመታት ደንበኞቻቸውን መግበዋል፡፡

ዐደይ በእነዚህ ዓመታት ኹሉ አንድም ቀን የፍስክ ምግቦችን አላቀረቡም፡፡ ሽሮ፣ ክክ፣ ምስር፣ ተልባ በእንጀራ፣ ጎመን እና ሕልበት ምግቦችን እንደ ልብ ለደንበኞቻቸው አቅርበዋል፡፡ ዐደይ ቤት የኹሉም ዐይነት ምግቦች ዋጋ ሰባት ብር ነው፡፡

የወላይታና የዶርዜ ብሔረሰቦች በሚበዙባቸው ሽሮ ሜዳና አዲሱ ሚካኤል ጀርባ ባሉ ሠፈሮች ብሔር ተኮር ማዘር ቤቶች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ደንበኞቻቸው ‹‹አዬ›› ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ በዶርዝኛ ‹‹እናት›› እንደማለት ነው፡፡ በእነዚህ ማዘር ቤቶች ለብሔረሰቡ ቅርብ የኾኑ እንደ ‹‹በሶ››፣ ‹‹ቦርዴ›› እና ‹‹ፈቴላ›› የመሳሰሉት ምግቦችና መጠጦች ይዘወተራሉ፡፡ ዋጋቸውም ሁለት ብር ከ50 ሳንቲም ነው፡፡ ፈቴላ የሚባለው ጎመን፣ በቆሎና ድንች ተቀላቅለው በጆግ የሚቀርብ ጣፋጭ ምግብ ሲኾን ተመጋቢው ዘይት ከራሱ በትንሹ ብልቃጥ ይዞ መምጣት ይኖርበታል፡፡
-    መሐመድ ሰልማን፣ ፒያሳ ማሕሙድ ጋ ጠብቂኝ ላይ እንደተረከው (2004)


*    *   *   *   *   *   *   *   *   *   *  *  *  *  *
እንዲህ ተብሏል
* ሥልጣኔ እንቅስቃሴ እንጂ ቅድመ ሁኔታ አይደለም፤ የመርከብ ጉዞ እንጂ የመርከብ ማረፊያ ወደብ አይደለም፡፡
(ኦርኖሲድ ቶይንቢ)
* ‹‹መቅኒ ካለኝ ከሥጋው ምን አለኝ››
* በፍቅር የተያዘና ያላገባ ሰው ጎደሎ ነው ካገባ በኋላ ደግሞ አለቀለት፡፡
(ዚዘ ጋየሮ)
* ዝነኛው ፍቅር ሆይ አንዳንዴ አውሬን ሰው ታደርገዋለህ፣ አንዳንዴ ደግሞ ሰውን ወደ አውሬነት ትለውጠዋለህ፡፡
(ዊሊያም ኤክሰር)
* ሀፍረት ማለት ሴት ልጅ አንተን ልክ እንዳሰበችው እንዳገኘችህ ስትነግርህ የሚሰማህ ስሜት ነው፡፡
(ካርል ሳንደበርግ)
* የነፃነት ጠላቶች ሙግት አይገጥሙም፣ ይጮሃሉ ይተኩሳሉ ይገድላሉ፡፡
(ዲንዌሊያም)
* እንዲቀናብኝ እፈልጋለሁ፣ ስለሆነም እኔ ብቻ የማፈቅራትን ሴት ለማግባት አልሻም፡፡
* ለብቻ ማፍቀር ለብቻ እንደመብላት ይቆጠራል፡፡
(ዊሊያም ዋይቸር ሌይ)
*ሀሳባቸውን የማይለውጡ ወይ ጅሎች ወይ ሙታን ናቸው፡፡
(ጀምስ ሪስል ሎወል)
* በምንሳሳም ጊዜ አንድ ከንፈሬን ብቻ ነው የምሰጥሽ ምክንያቱም ሁለቱንም ከሰጠሁሽ ልትቋቋሚው አትችይም፡፡
(ውድ አለን)
-    ምርጥነህ ታምራት፤ በ‹‹ጣዝማ›› ድርሳኑ እንደጻፈው፣ (2000)


*    *   *   *   *   *   *   *   *   *   *  *  *  *  * 
አንድ ዚቀኛ
ዚቀኛ የሆነ አንድ ሰው ሐሩን አራሽድ ከሚባለው ከባግዳድ ንጉሥ ዘንድ አቅርቡኝ ብሎ ስለ ለመነ ተፈቀደለትና ከንጉሡ ዘንድ ገብቶ ንጉሥ ሆይ ከእኔ በቀር ሌላ ማንም ሰው ሊሠራው የማይችለው ትንግርት የሆነ ነገር አሳይዎታለሁና ይፍቀዱልኝ ብሎ ተናገረ፡፡ ንጉሡም አሳየኝ ብሎ ፈቀደለት፡፡ ሰውዬው ከኪሱ ውጅሞ መሳይ ጎትቶ አውጥቶ በውስጡ ብዙ መርፌ በጫፍዋ መሬት ላይ ተክሎ አቆማት፡፡ ከዚህ በኋላ ራቅ ብሎ ቆመና ከውጅሞው ውስጥ ያሉትን መርፌዎች አንድ ባንድ አውጥቶ እየወረወረ መሬት ላይ በተከላት መርፌ ቀዳዳ ውስጥ እያሳለፈ ሁሉንም ጨረሳቸው፡፡ ይህንንም ሲያደርግ አንድ ጊዜ እንኳ አልተሳሳተም፡፡

ሐሩን አራሽድ ለዚህ ሰው መቶ ወርቅ ሰጥተውት መቶ ጅራፍ እንዲገርፉት አዘዘ፡፡ እዚያ የነበሩ መኳንንትና ባለሟሎቹ ቅጣትና ሽልማት ማዘዝህ በምን ምክንያት ነው ብለው ጠየቁት፡፡ ይህን ያህል የሠለጠነ እጅ እያለው ቁም ነገር ያለው ሞያ እንዳይማርበት ድካሙና ጊዜውን በማይረባና ለአገር በማይጠቅም ጨዋታ ላይ በማዋሉ ተናድዶ እንዲቀጣ አዘዝሁ፡፡ የሸለምሁበትም ምክንያት ይሁን እንጂ ይህ የሠራው ሥራ የሚያስደንቅ መሆኑ የማይካድ ስለሆነ ዋጋውን እንዳልነሳው ብዬ ነው ሲል ሐሩን አራሽድ መለሰላቸው፡፡
- ከከበደ ሚካኤል፣ የዕውቀት ብልጭታ (1999) የተወሰደ


*    *   *   *   *   *   *   *   *   *   *  *  *  *  * 
የዓለማችን እጅግ አስደናቂ ፍጥረታትና እውነታዎች
* አቦ ሸማኔ በመሬት ላይ ከሚገኙ ረዋጭ እንስሳት ሁሉ በፍጥነት ቀዳሚውን ሥፍራ የጨበጠ ሲሆን በሰዓት 110 ኪ.ሜ ያህል ይሮጣል፡፡፡ ከዚህም የተነሳ አንዳንድ እንስሳትን የሚያሰለጥኑ አገሮች ለድኩላና ለአጋዘን አደን ይጠቀሙበታል፡፡

* በቲቤት ምድር የሚገኘውና ‹‹ያክ›› በሚባል ስም የሚታወቀው ጎሽ መሰል እንስሳ የሚኖረው ከባህር ወለል 6ሺሕ 100 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፡፡ ይህ እንስሳ ከትላልቅ ጡት አጥቢ እንስሳት መካከል እጅግ ቀዝቃዛ በሆነ ስፍራ በመኖር ቀዳሚውን ቦታ ይዟል፡፡

* ፍልፈል ማየት የማይችሉ ዓይኖች ቢኖሩትም በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ እስከ 23 ሜትር ርዝመት የሚደርስ የውስጥ ለውስጥ ጉድጓድ መቆፈር ይችላል፤ ይህ እንስሳ የእድሜው አብዛኛ ጊዜ መሬት ውስጥ በማሳለፍ ከጡት አጥቢዎች መካከል የመጀመሪያው ስፍራ ይዟል፡፡

* ‹‹አላስካን ሙዝ›› በመባል የሚጠሩ የዩናይትድ ስቴትስ አጋዘኖች ቁመት ከ2 ሜትር የሚበልጥ ሲሆን፣ ክብደታቸው ከ810 ኪሎ ግራም ይበልጣል፤ የእነዚህ ቀንዶች ክብደት ከ38 ኪ.ግ. የሚበልጥ ሲሆን፣ በቀንድ ታሪክ ከፍተኛውን ክብደት የያዙ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

* ‹‹የባህር ተኩላ›› በመባል የሚታወቀው ዓሳ-ነባሪ በባህር ውስጥ ከሚገኙ እንስሳት ሁሉ እጅግ አደገኛው ሲሆን፣ ቁመቱ 10 ሜትር ያህል ይደርሳል፤ የዚህ እንስሳ ሆድ ርዝመት ብቻ እስከ 7 ሜትር ያህል የሚደርስ ሲሆን፣ በሆዱ ውስጥ እስከ 50 የሚደርሱ የተለያዩ ግዳዮችን አግበስብሶ መያዝ ይችላል፡፡
- ፈቃዱ ሺፈታ ከሐዋሳ ‹‹ምጥን›› ብሎ ካሳተመው የተወሰደ (2003)


*    *   *   *   *   *   *   *   *   *   *  *  *  *  *
ውስጣዊ ማንነት
ራስን መሆን ሁሌም ማራኪ ግብ ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሌላ ሰው መሆንን ወይም ሌላ ቦታ መገኘትን እንመኛለን፡፡ ‹‹ይኼን ሥፍራ ብለቅ ኖሮ…››፤ ‹‹ሌላ ሥራ ቢኖረኝ ኖሮ…››፣ ‹‹አዲስ አፍቃሪ ባገኝ ኖሮ…››፣ ‹‹በርከት ያለ ገንዘብ ቢኖረኝ ኖሮ…››፣ ‹‹እገሊትን ብሆን ኖሮ…›› ወዘተ፡፡ ሳሩ በሌላኛው ጎን ሲታይ አረንጓዴ ቢመስልም ቀርባችሁ ስታዩት የተለየና አስገራሚ እውነትን ታገኛላችሁ፤ ውስጣዊ ማንነታችሁን ከእናንተ ጋር ወስዳችኋል፤ ከረሳችሁ ልታመልጡ አትችሉም፡፡ የደረሰባችሁን ሁኔታዎችና ክስተቶች መለወጥ ደስተኛ አያደርጋችሁም፡፡ በራስ መብቃቃት የሚጀምረው ራስን በማወቅና ራስን በመቀበል ነው፡፡ ይህ ክሕሎት አሁን ባለ ነገር ላይ ያተኩራል፡፡ ነገሮች እንዲለወጡ ስትመኙ ሁልጊዜም ባገኛችሁት ነገርና አሁን ባለ ማንነታችሁ አትረኩም፡፡ ለዚህ ብዥታ ዘላቂው መፍትሔ ሙሉ ማንነታችሁን/ ከማትወዱዋቸው ሰብዕናዎቻችሁና ጠባዮቻችሁ ጭምር/ መቀበል ነው፡፡ ከራሳችሁ ጋር ሳትስማሙ ውስጣዊ ሰላም በማግኘት ይህን ማንነታችሁን በየሄዳችሁበት ትወስዱታላችሁ፡፡

ስኬት በበርካታ መንገዶች ቢለካም በውጫዊ መመዘኛዎች ልንገልጸው አንችልም፡፡ በሌላ አባባል ዝናና ሀብት ብቻቸውን ትክክለኛ የስኬት መመዘኛ የማይሆኑበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ድብቅና የድህነት ሕይወትም ስኬታማ ያስብለናል እያልኩም አይደለም፡፡ እውነተኛ ስኬት ውስጣዊ ነው፡፡ አንድ ሥራ በድንቅ ብቃት ሲሠራ ከላቀ ውጤት ላይ ሲደርስ የተገኘ አጋጣሚን ባግባቡ ሲጠቀሙ እንዲሁም ለብርቱ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሔ ሲያበጁ የሚሰማ ውስጣዊ እርካታ ደስታ ነው፡፡ ይህ ለቀጣይ ስኬት የመነቃቃትን ስሜት ይፈጥራል፡፡
- ከበረከት ብርሃኑ፣ ‹‹ራስን መሆን›› የተወሰደ (2001)


*    *   *   *   *   *   *   *   *   *   *  *  *  *  * 
ቤተሰብ
ወደዚህ ምድር በአጋጣሚ አልመጣህም፡፡ በመጀመሪያ ግዴታህን የመውጣት ጉዞ የሚጀምረው አንተን የፈጠሩህን ወላጆች ከመታዘዝ ነው፡፡ ምክንያቱም የነሱም በዚህ ቦታ መገኘት በምክንያት የተደገፈ ነገር ነውና፡፡

 

ስለዚህ ከሁሉም ነገር በፊት መጀመሪያ ጥሩ ባል፣ ጥሩ ሚስት፣ ጥሩ ወንድ ልጅ፣ ጥሩ ሴት ልጅ መሆን ካንተ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ሁለተኛው ልትወጣ የሚገባህ የግዴታ ማዕቀፍ ደግሞ በሕይወት ጉዞህ የምታውቃቸውን ሰዎች ያጠቃልላል፡፡ ጓደኞችህ የሥራ ባልደረቦችህና ለሰው ዘር በጠቅላላ ያለህ ቀረቤታ ጥሩነት የሞላበት ሊሆን ይገባል፡፡

ቤተሰቦችህ መሆን ያለባቸው ግን የግድ በአንድ ጣሪያ ስር የተወለዱትን ብቻ የያዘ መሆን የለባቸውም፡፡
ቤተሰብ አንተ የምትፈጥረው ነገር ነው፡፡ በኑረትህ ውስጥ ከሁለቱም ስብስብ የተጠራቀሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ጥሩ ባህሪ ምርጥ የሆነ መታወሻ ሀውልት ነው፡፡ በሚወዱህና በሚያስታውሱህ ዘንድ ‹‹እንዳትረሱኝ›› የሚል ማሳሰቢያ መንገር ሳያስፈልግህ ሁሌም በህያውነት ውስጣቸው እንድትኖር ያደርግሃል፡፡ ስምህን እብነ በረድ ላይ ሳይሆን ሰዎች ልብ ውስጥ ቅረፅ፡፡
- ከዳንኤል ጥሩነህ፣ ጽሞና (2002) መጽሐፍ የተወሰደ

አሰናጅ - ሔኖክ ያሬድ