ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የግብፅ አቻውን በደርሶ መልስ 6ለ4 አሸንፎ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ትኩረት እንዲያገኝ ተጠየቀ፡፡ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ የሴቶች ሊግ በሌለበት ይህን ያህል መንቀሳቀስ ቢቻል ኖሮ በመድረኩ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ቀላል ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሴቶች የተጀመረው የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጠናከረ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት የሚናገሩ የእግር ኳስ ቤተሰቦች በበኩላቸው፣ ‹‹የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዓላማና ግብ ትርጉም ላለው የእግር ኳስ ዕድገት ከሆነ አሁን በአገሪቱ በሚታየውና በተበታተነ አኳኋን እዚህ ደረጃ የደረሰውን የሴቶች እግር ኳስ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፤›› ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፎ ከማጣርያው ውጭ የሆነው የግብፅ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ስብስብ መነሻው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው ዓይነት ተጫዋቾቹ በፍላጐታቸው ተነሳስተው ሳይሆን፣ መደበኛ ዓመታዊ የውድድር መርሐ ግብር ተይዞላቸው ከሚከናወን የሴቶች ሊግ የተመረጡ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አቶ አብርሃም ተክለሃይማኖት በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ የወንዶቹን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ አሁንም በ2004 ዓ.ም. በመደበኛነት በአገሪቱ ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቀው የሴቶች የሊግ ውድድር እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፌዴሬሽን ምንጮች በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ አሁን ባለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወቅታዊ ሁኔታ ተቋሙ ከፍተኛ በሆነ የፋይንስ ችግር ውስጥ ነው፡፡ ከእሑድ ዕለቱ ጨዋታ በፊት ቡድኑ ወደ ግብፅ ተጉዞ የመጀመርያውን ጨዋታ ሲያደርግ ፌዴሬሽኑ አንድ ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ እንደጠየቀው ነው የሚያስረዱት፡፡
ይህ ሁኔታ ባለበትና ቡድኑ በቀጣይ ለሚያደርጋቸው ዝግጅቶች ፌዴሬሽኑን የሚረዳው አካል ካላገኘ በስተቀር የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ህልውና አደጋ ላይ ስለመሆኑ እነዚሁ ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ይሁንና በፕሪምየር ሊጉ እየተሳተፈ የሚገኘውና በዚህ የውድድር ዓመት በሴቶች እግር ኳስ እየተካፈለ ያለው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን አባላት 36 ሺሕ ብር ሰጥቷል፡፡ የደደቢትን አርዓያነት በመከተል ሌሎችም ክለቦችና ግለሰቦች ለቡድኑ እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም የሚናገሩ አሉ፡፡
ባለፈው እሑድ በአዲስ አበባ ስታዲዮም ከኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ያደረገው የግብፅ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከጨዋታው በፊት ባረፈበት ቸርችል ሆቴል የአየሩ ሁኔታ አስቸግሯዋቸው ከካዲስኮ ሆስፒታል ኦክስጅን በማስመጣት ከተጠቀሙ በኋላ መረጋጋት እንደቻሉ የሆቴሉ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የግብፅ ብሔራዊ የሴቶች ቡድን አሠልጣኝ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጣዊ መግለጫ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቢቆዩም፣ ነገር ግን ከቆይታ በኋላ የኢትዮጵያን የሴቶች ቡድን አስመልክቶ እንዲነግሩን ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ቡድናችሁ ያለመዋሸት ጠንካራና ተጫዋቾቹም ኳስን በአግባቡ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ የአየሩን ሁኔታ ከተጫዋቾቻችን አቅም በላይ ቢሆንም የተሸነፍነው ግን ተበልጠን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአፍሪካ ዋንጫ በጠንካራነቱ የሚጠቀሰው የግብፅ ቡድን ነበር፡፡ ነገር ግን እየተከናወነ ካለው የ2012 የአፍሪካ ዋንጫ ውጭ ሆኗል፡፡ የወንዶቹን ቁጭት በሴቶቻችን እናካክሳለን የሚል ተስፋ ቢኖረንም አልተሳካም፡፡ ሆኖ ግን ጥሩ ቡድንና ደስ የሚል ደጋፊ አላችሁ፤›› በማለት የኢትዮጵያን ብሔራዊ የሴቶች ቡድን አድንቀዋል፡፡
8ኛውን የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ የምታዘጋጀው 28ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከጋቦን ጋር በጋራ እያስተናገደች ያለችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ስለመሆኑዋ ቀደም ብሎ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡
ይሁንና ይህንኑ አስመልክቶ በአንዳንድ ድረ ገጾች የተለቀቀው መረጃ ደግሞ 8ኛው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ዚምባቡዌ መሆኑዋን ያስረዳሉ፡፡


