Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

እኛና ቻይና

  • PDF

ዛሬ ጉዞው ከሜክሲኮ ቦሌ ነው። ታክሲ ማግኘት የናፈቀው ሕዝብ ተሰብስቦ በፀሐይ ሲጠበስ ማየት ሰሞኑን የተለመደ ትዕይንት ሆኗል። ትዕግስታችንና እንግዳ ተቀባይነታችን በብዙ የተፈተነበት እንዳሁኑ ያለ ጊዜ አላየሁም። ፀሐይዋ ከእነዘመድ አዝማዶቿ የወጣች እስኪመስል ድረስ አናትን የሚበሳው ጨረሯ የሚታወቀው እንዲህ በታክሲ እጦት ሲጉላሉ ነው። ከአሁን አሁን ይመጣል ለምንለው ታክሲ ለግፊያና ለሽኩቻ እየተዘጋጀን ዓይናችንን እናቅበዘብዛለን። ለነገሩ ታክሲ በማጣት ተገትሮ ከቀጠሮ፣ ከስብሰባ፣ ከቢሮና ከትምህርት ቤት ማርፈድ ሰሞኑን መሪዎቻችን ሲሰበሰቡ፣ ቢብስበትም የተለመደው ተግባራችንና ችግራችን ነው። ችግሮቻችንን መፍታት ሳይሆን ማባባስ የያዙ የሚመስሉ መፍትሔ እናመጣለን የሚሉ ስብሰባዎች ተበራክተዋል ያሰኛል፡፡ እንዲህ እንደ እኔ የተቃጠለ ደግሞ መጥኔ ቢል ይበዛበታል?

ድንገት ከቆምንበት በማዶ አቅጣጫ አንድ ታክሲ ሲዞር ስናይ ሁሉም እርስ በርሱ እየተያየ ለጉሽሚያና ግብግብ ተዘጋጀ። አንዲት አዛውንት እናት ጮክ ብለው፣ “ዋ ዛሬ ዋ ብያለሁ አልሳፈርና አሳይሃለሁ አንተ ውሪ ሁላ” ሲሉ ፈገግ እያልን ቅድሚያ ሰጠናቸው። መቼም የአሁኑን ትውልድ እንጃ እንጂ ታላላቅን ማክበር ለቀደሙት በትህትና የሚተላለፍ ሰናይ ምግባር ነበር። አዛውንቷ ምርቃታቸውን አዥጎድጉደው ሳይጨርሱና እኛም ሳንሰማቸው በሽኩቻው መሀል ባዶ ኪሳችን ጨምድደን ይዘን ገባን።
‘የሌለው ያው የሌለው ይወሰድበታል’ የሚለውን ምሳሌ በልቦናችን እያሰላሰልን። የገባው ገብቶ የተረፈው እዚያው ፀሐይ ላይ ሲቀር ያየን ተሳፈሪዎች ከንፈራችንን መጠጥን። “. . . እያዘንኩኝ በዓይኔ አይቼ ምን ላድርግ አዘንኳቸው ትቼ” የሚለው ዘፈን ትዝ አለኝ። አዝኖ ከመተው ያላለፈ ነገር ማድረግ የምንጀምረው መቼ ይሆን? ማለቂያ የሌላቸው መቼዎችስ የሚቆሙት መቼ ይሆን?

“መሪዎቻችን ሲሰበሰቡ እኛ እንደ ቻይና ዕቃ ረክሰን የምንታይበት ብሂል ነው አልገባ ያለን፤” ሲል አንድ ተማራሪ ተሳፋሪ በምሬት ተነፈሰ። ፀሐይ ያጋለው ግንባሩ ላብ እንደ ምንጭ ይፈልቅበታል፡፡ ወያላው በንቃት ተሳፋሪዎቹን የማስተናገዱን ሥራ እየሠራ ሐሳቡን ከመሰንዘር አልተቆጠበም። “ሰማህ ፍሬንድ የቻይና ዕቃ ርካሽ ነው የሚባለው ለጊዜው ነው፡፡ አላየህም እንዴ የሠሩትን ሕንፃ? መንገድ ሥራ ላይም ብትመጣ እንዲሁ ጠቅልለው ይዘውታል። እንዲያውም በቅርቡ ከአውሮፓ የሚበልጥ መንገድ ሠርተው ያስደምሙሃል። ሰው ሥራው ካስከበረው እንግዲህ ቻይናን ሥራዋ ሊያስከብራት ይገባል፤” ሲለን ተገርመን የተጫማው የቻይና ጫማ ላይ ተተክለን ቀረን። አቃጥሎት አሥሬ እየተንቆራጠጠ ስለቻይና ታታሪነት የሚሰብከን ያለምንም ጥቅማ ጥቅም ሳይሆን አይቀርም ብለን ጠረጠርን። ይኼኔ ከኋላ የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ “እኔ የምፈራው ቻይና በሚቀጥለው ምርጫችሁ ልወዳደር ብላ እንዳታርፈው ነው፤” ሲለን በምፀት ፈገግታ እርስ በርስ ተያየን። “የባሰ አታምጣ” የሚባለው ይኼኔ ነው።

በአስቀያሚ የማስታወቂያ ፖስተሮች ቅጥ ማጣት፣ በሽርሽር አዘውታሪያን፣ እዚህ ሐገር ሊነዱ ተገቢነታቸው በሚያጠራጥሩ መኪኖች መጨናነቅ የሚታወቀው የቦሌ መንገድ ቀልቡ ግፍፍ ብሎ ግርማውን አጥቷል። እንደለመደበት ሽርጉድ የሚሉበትን ደንበኞቹን በቅርቡ ሊያጣቸው የደረሰ ይመስላል። ደህና ሁን ብለውት ፊታቸውን ወደጊዜው ተወዳጅ ቦሌ መድኃኔአለም አካባቢ ያዞሩበትን ወዳጆቹን ማኩረፉ ያስታውቅበታል። “አቤት ወረት ስንቱን አለያየው?” አለ ሾፌራችን በድንገት ጮክ ብሎ። “ለወረት ለወረትማ እነኦባማ ሳይቀሩ ምርጫ ሲደርስ የሕዝብ ጫማ ሊልሱ ምንም አይቀራቸውም እኮ፤” አለው ወያላው። “አንተስ ብትሆን የአሁኗን ከመጥበስህ በፊት ለዚያችኛዋ በረኪና አልገዛህም?” ሲለው ሾፌሩ፣ ወያላው እንደማፈር አለ። ሰው ነገር እንዴት ለምዷል እባካችሁ? የሥራ ፈጠራ በሚጠየቅበት ዘመን ነገር መዘምዘም ምን ይባላል?

ከፊቴ የተቀመጡት ተሳፋሪዎች ግን የሌሎቻችን ነገር ከቁብ ሳይቆጥሩ ስለኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ይጨዋወታሉ። “ይገርምሃል ለማንም ያልደረሰውን ለእሱ ደርሶት አሁንማ ደረቱን ነፍቶ ይንጠባረራል፤” ይለዋል አንደኛው። ሌላኛው ደግሞ፣ “ኧረ ዝም በለው ስንቱ በትስስር ቁልፍ ሲረከብ እሱን እግዚአብሔር ዘመድ ስለሆነው ሊኮራ ይገባው ነበር?” እያለ ይነጫነጫል፡፡ “በቃ እኮ አሁን መንግሥት ዕጣ ወጥቶላቸው ሳይገቡ ወይ ሳይረከቡ የቀሩትን ሰርዞ ድጋሚ ዕጣ ሊያወጣ ነው፤” እያለ በእሰይ ቅላፄ ሌላኛው ወዳጁ ላይ ያሾፋል። “አፍ ሲያርፍ ወዳጁን ያማል” እውነት ሆኖ ሲታይ አጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ፣ “እስኪ አሁን ለእነሱ ባይደርሳቸው ደርሰው በሰው ሕይወት ገብተው ሰው እስኪታዘባቸው የሚያሙት ለምን ይሆን?” ብሎኝ በግርምት ራሱን ነቀነቀ። በማያገባህ አትግባ በቤት ጉዳይ እንዴት ዝም ይባላል ልለው ፈልጌ እኔ ራሴ በማያገባኝ መግባት ሲሆንብኝ ተውኩታ! “በማያገባቸው የሚገቡ ወደ ቃሊቲ ይላካሉ” የሚለውን የታክሲ ውስጥ ጥቅስ ያላየ ጉድ አይሆንም ብላችሁ ነው?

ወያላው ምን እንዳሰብኩ ያወቀ ይመስል ጠጋ አለኝና፣ “አንድ ጨዋታ ላጫውትህማ” አለኝ። እኔም መቼም የወያላ ዓይን አያርፍም አንዷን ቆንጆ አይቶ ተለከፍኩ ሊለኝ ይሆናል ብዬ “ምን ነበር?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት። “አንድ የሞራል ሰው አንድ ሲጋራ የሚያጨስን ሰው አግኝቶ እንዲህ አለው፤” አለኝ። “እንዴት?” አልኩት ጥርጣሬዬን ውኃ ሲበላው እያየሁ። “የሞራል ሰው ነኝ የሚለው ስማ አምስት በመቶው የአገራችን ሕዝብ የሚሞተው በምን እንደሆነ ታውቃለህ? በትንባሆ ነው ይለዋል። በተራው ሲጋራ የሚያጨሰው ሰው ዘጠና አምስት በመቶው ደግሞ በምን እንደሚያልቅ ታውቃለህ? በማያገባው እየገባ ብሎት አንዴ አቀመሰውና . . . ” አለኝና እሱም ወደ ሥራው ዞረ። ብቻዬን መሳቅ አልሆንልኝ ብሎ አጠገቤ ላሉት በሙሉ ብነግራቸው ታክሲዋ በሳቅ ፈረሰች። ታዲያ ተካፍለን መብላት ቢያቅተን ተካፍለን መሳቅ እናቁም እንዴ? ክንዳችንን ሳንንተራስማ ፍቅራችን አይሞትም። “ሐበሻ ኖሮት አይነፍግም” አለ አዝማሪው! ዲያስፖራው ደግሞ ይኼን ሰምቶ፣ “እንካ በዶላር፣ እንካ በዩሮ” እያለ ግሽበት በግሽበት አደረገን ተብሎ ሲወራ ድንጋጤዬ ዋሽንግተን ድረስ ተሰማ፡፡ ከቻይና ጋር እፍ ያለ ፍቅር ውስጥ ስንወድቅ ሳቃችን ቤጂንግ ድረስ ይሰማልን ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል?

ጉዟችን ቀጥሏል። በቀኝና በግራ የአስፓልቱ መንገድ ላይ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በየሜትር ርቀት ቆመው እያንዳንዱን ዕርምጃ በንቃት ይከታተላሉ። ይህን ስንታዘብ ድንገት ወራጅ ተባለና ታክሲያችን ቆመ። ወራጆች ሲወርዱ ወያላው ሌላ ተሳፈሪዎች አግኝቶ እነሱን ሲያስገባ ትዕግስታቸው ያለቀ ፖሊሶች መጡና ማን ቁም አለህ እያሉ ያርበደብዱት ጀመር። የገቡት ተሳፋሪዎች ቦታቸውን ሳይዙ ሾፌሩ ታክሲውን እግሬ አውጪኝ አስባለው። ይህን ስትታዘብ የቆየች አዲስ ተሳፋሪ ታዳጊ አባቷን፣ “አባዬ ፖሊሱ ለምንድነው የሚያሸብረው?” ብላ ጠየቀችው። ታክሲዋ ፀጥ አለች። ሁላችንም ዓይን ዓይኗን እያየን የወላጆቿን መልስ ለመስማት ከእሷ እኩል አሰፈሰፍን። “ተረቱ ሳትወልድ ብላ ሳይሆን ሳትወልድ አስብ” ሊሆን እንደሚገባ በየልባችን ያሰብን መሰለኝ። መሰለኝ ነው ያልኩት፡፡ ያውም በቻይንኛ፡፡

“ፖሊሱ አሸባሪ ሳይሆን ሥርዓት የሚያስከብር ነው” አላት አባቷ። “ታዲያ ለምን ታክሲ የምንይዝበት ቦታ ላይ መጥቶ ተቆጣ?” አለችው። ስለ አገር ደኅንነት ለማስረዳት ቢሞክር የማይጨርሰው መጽሐፍ ሊጽፍባት እንደሚችል አሰበ መሰል ተወው። “እ አባዬ ንገረኛ?” ብላ ሙጭጭ አለች። “አይ ሚጥዬ ራሱን ፖሊሱን መጠየቅ ነዋ፤” ብሏት እርፍ። ይኼኔ ሁላችንንም የሚያስደነግጥ መልስ መለሰች። “ቢያስረኝስ?” ሁላችንም ተያየን። “በሕፃናት አዕምሮ እንኳ ምን እደተቀረፀ እንዲህ ላስተዋለ፣ ትውልዱ ምን እየሆነ እንደሚሄድ እርግጠኛ ሆኖ መናገሩን እንጃ፤” አለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ። “እውነቱን ተናግረሽ ቢያስርሽ ምንም ማለት አይደለም፡፡ መታሰር እኮ መሞት አይደለም፤” ብሎ አባት የሞት ሞቱን ለእውነት መቆም እንዳለባት መከራትና ታዳጊዋ ጥያቄዋን ስትገታ እፎይ አልን። “ዲሞክራሲ ሆይ የሚሉሽን በሰማሽ አገሬ ባልመጣሽ” የሚል ጥቅስ ተለጥፏል። ሌላ ጥቅስ ፍለጋ ወደ አንድ አቅጣጫ ሳንጋጥጥ፣ “አፍሪካ ሆይ በወጣቶችሽ ዕውቀት ካልተመካሽ፣ በቻይና ዳረጎት የትም አትደርሺም” የሚለውን አይቼ ከልቤ ሳቅኩ፡፡ አሳሳቄ ቻይንኛ መሰለኝ፡፡

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ስንመጣ በድንገት ወደቀኝ ታጥፈን አንድ ስርቻ ውስጥ ገብተን እንድንቆም ታዘዝን። “መንገዱ መዘጋቱ ነው” አለ ወያለው ወደ እኛ ዞሮ ችግሩን እያሳወቀን። ስለ ግልጽነትና ተጠያቂነት ከሚያወሩት ይልቅ እዚህ ወያላ ዘንድ የሠራ ይመስላል። ትንሽ እንደቆየን የገባንበትን አካባቢ ትዕይንት ማስተዋል ጀመርን። ከአሥራ አምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲጋራ ያጨሳሉ፤ መጠጥ ይጠጣሉ። አካባቢውን የሞላው ወጣት በሙሉ በሱስ ራሱን ስቷል። የአካባቢው ነዋሪዎች ውኃ ጠፍቶባቸው ላይ ታች ይንቆራጠጣሉ። ጠና ጠና ያሉት ደግሞ ሰብሰብ ብለው በብብታቸው ሥር የመሬት ካርታቸውን ይዘው ይጨቃጨቃሉ። ታክሲ አጥቶ በእግር የሚሄደው ሕዝብ እንዲቆም ታዞ የማያውቀው አካባቢ ገብቶ የሰው ሠፈር ያዳምቃል። “አየህ ሕይወታችንን?” አለ ሾፌሩ ለወያላው፡፡ “ያውም ተኑሮ ነዋ” አለው ወያላው። “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ሲሉ እኛ እናት ሳቃችንን መቆጣጠር አቃተን። ወዲያው ወያላው፣ “ትንሽ ስለቀራችሁ በእግራችሁ ብትሄዱ ይሻላል፤” ብሎ መጨረሻችንን ሲያውጅልን እኛም ያን አስፈሪ ትዕይንት ተቀላቀልን። ጠባቡ መንገድ በሰው ተጨናንቆ እኛም እንደ ቻይና የበዛን መስለናል፡፡ አዎ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኛና ቻይና እኩል እየተጋፋን ኢትዮጵያ ውስጥ ግሎባላይዜሽንን እናደምቀዋለን፡፡ መልካም ጉዞ!