Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

ኮስታ ኮንኮርዲያ - የታይታኒክን ታሪክ ለመድገም የተቃረበችው መርከብ

  • PDF

ባለፈው ዓርብ ሌሊት ድንገት ሳይታሰብ በጣሊያን ምዕራባዊ የባህር ዳርቻ ላይ ከአለት ጋር ተጋጭታ የተፈነገለችው ኮስታ ኮንኮርዲያ የተባለችው የሕዝብ መጓጓዣ መርከብ፣ የዛሬ 100 ዓመት ገደማ ከእንግሊዝ ወደ ኒውዮርክ ስታመራ በደረሰባት አደጋ 1,517 መንገደኞቿ ያለቁባትን ታይታኒክ መርከብ ታሪክ ከመጋራት ለጥቂት ተርፋለች፡፡ በአሁኑ አደጋ ሰባት መንገደኞች መሞታቸው ሲረጋገጥ 29 የሚሆኑት የደረሱበት አልታወቀም፡፡

እ.ኤ.አ. በ2006 አገልግሎት መስጠት የጀመረችው ኮስታ ኮንኮርዲያ ጣሊያን ውስጥ ከተሠሩት የሕዝብ መጓጓዣ መርከቦች ትልቋ ናት፡፡ ርዝመቷ 290.20 ሜትር ሲሆን፣ ወርዷ ደግሞ 35.50 ሜትር ነው፡፡ ከታይታኒክ መርከብ በ21 ሜትር ትረዝማለች፡፡ 1,500 ክፍሎች ያሏት ይህች እጅግ በጣም ዘመናዊ የሆነች መርከብ አደጋው በደረሰባት ወቅት 4,229 መንገደኞችን አሳፍራ ነበር፡፡

የመርከቧ መንገደኞች በአምስቱ ሬስቶራንቶቿ፣ ኮንኮርዲያና ሳማርያ በተሰኙ ክለቦቿ፣ በ13 ባሮቿ፣ በሲጋራ ማጨሻ ላውንጇ፣ በቡናና በኮኛክ መጠጫ ክፍሎቿ ውስጥ እንዳሉ ድንገት ከፍተኛ ድምፅ ይሰማል፡፡ መርከቧ ከአደጋው በፊት የባህር ዳርቻ በጣም ተጠግታ እንደነበርና ያ የተፈጠረው ከፍተኛ ድምፅ ከአለት ጋር መጋጨቷን አመላካች ነበር፡፡ ድምፁ ያስደነገጣቸው መንገደኞች ወዲያውኑ መርከቧ ወደ አንድ ጎኗ ማዘንበል መጀመሯን ተረዱ፡፡ የፈሩት አልቀረም ቀስ በቀስ በጎኗ ወደቀች፡፡ ከዚያ በኋላ የታይታኒክን ታሪክ እያስታወሱ መተራመስ ጀመሩ፡፡

ከመርከቧ በሕይወት አድን ጀልባዎች አማካይነት ወደ ባህር ዳርቻ የደረሱ አንድ ግለሰብ መርከቧ በጎኗ ከወደቀች በኋላ የተፈጸመውን ድርጊት አሳፋሪ ብለውታል፡፡ ‹‹እኔና ባለቤቴ ጥግ ላይ ተቃቅፈን ተቀምጠናል፡፡ ጉልበት ያላቸውና ጠንካራ የሚባሉ ሰዎች ሕፃናትን፣ አረጋውያንና ሴቶችን ባለ በሌለ ኃይላቸው እየገፈታተሩ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ሲሯሯጡ ሳይ በሰው ልጅ ድርጊት አፈርኩ፤ አደጋውም የታይታኒክን ዓይነት ይመስል ነበረ፤›› ብለዋል፡፡

የመርከቧ ካፒቴን ፍራንቼስኮ ሼቲኖ ኮስታ ኮንኮርዲያ ከተፈቀደላት የጉዞ መስመር ውጪ በማስወጣት ፈጠረው ለተባለው አደጋ፣ አደጋው ከተፈጠረ በኋላም መንገደኞች ከመርከቧ ደኅንነታቸው ተጠብቆ ሳይወጡ ከማንም በፊት ቀድሞ ወጥቶ በታክሲ ሸሽቷል በመባል በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ የጣሊያን ዓቃቤ ሕግ ፍራንቼስኮ ቬሩሲዮ ለሲኤንኤን እንደነገሩት፣ የመርከቧ ካፒቴን በፈጸመው ድርጊት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 15 ዓመት እስራት ይጠብቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በካፒቴኑ ላይ የጀመረው ምርመራ ሲጠናቀቅ ክስ ይመሠርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለኮስታ ኮንኮርዲያ መርከብ አደጋ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ የቀረበው የባህር ዳርቻውን በጣም መጠጋቷ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የካፒቴኑ ስህተት ጎልቶ እየተነገረ ነው፡፡ የመርከቧ ኩባንያ ኮስታ ክሩዝ ባወጣው መግለጫ፣ የካፒቴኑ ድንገተኛ አጋጣሚዎችን የማገናዘብ ብቃት የኩባንያውን ደረጃ የጠበቀ አይደለም ብሏል፡፡ የጣሊያን ጠረፍ ጥበቃ ተቋምም ካፒቴኑ ለምን የጂግሊዮን ደሴት ባህር ዳርቻ መጠጋት እንደፈለገ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ካፒቴን ሼቲኖ ግን የቀረበበትን ውንጀላ አስተባብሏል፡፡ መርከቧን ወደ መሬት አስጠግቷል የሚባለውን ሲያስተባብል፣ ‹‹በወቅቱ ከባህር ዳርቻው 300 ሜትር ያህል ርቀት ነበረን፡፡ በመርከቧ ካርታ ላይም አለት እንዳለ ምልክት አልተደረገም፤›› ሲልም ራሱን ተከላክሏል፡፡ ‹‹በጉዞ መስመሩ ቻርት ላይም አለቱ ውኃ እንደሆነ ነው ምልክት የተደረገው ሲል፤›› በጣሊያን ቴሌቪዥን አስረድቷል፡፡

የጣሊያን ጠረፍ ጥበቃ የካፒቴኑን አስተያየት በማጣጣል መርከቧ የተፈነገለችበት ቦታ በሚገባ ካርታ ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ አለታማ መሆኑ ይታወቃል ብሏል፡፡ አንድ አሳ አጥማጅ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው የጂግሊዮ የባህር ዳርቻ የሚታወቀው በአለታማ ንጣፉ ነው፡፡ የጠረፍ ጥበቃ ተቋሙ ይህንን ቦታ በርካታ ሰዎች ለመዋኘትና በጀልባ ለመንሸራሸር እንደሚመጡበት አስታውቆ፣ ከአለቱ ጋር በተገናኘም አደጋውም የዚያኑ ያህል ይታወቃል በማለት አስረድቷል፡፡ የአካባቢው ባለሥልጣናትና ነዋሪዎች መርከቧ ከአለት ጋር ከተጋጨች በኋላ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ከግማሽ ኪሎ ሜትር በላይ መጓዟን፣ ነገር ግን ካፒቴኑ ወደ ባህር ዳርቻው ሲወስዳት በጎኗ መውደቋን ተናግረዋል፡፡

በኮስታ ኮንኮርዲያ ላይ በደረሰው አደጋ በርካቶች በካፒቴኑ ላይ ቁጣቸው ተቀስቅሷል፡፡ በፌስቡክ ከጥቂት አዛኞች በስተቀር እጅግ በጣም ብዙዎቹ ካፒቴኑን አውግዘዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2002 ጀምሮ የኩባንያው ተቀጣሪ የሆነው ካፒቴን ሼቲኖ በተደጋጋሚ ሥልጠና የወሰደና ሁሉንም ፈተናዎች በማለፍ የሚታወቅ ነው ተብሎ በኩባንያው ተመስክሮለታል፡፡ ከዚህ ቀደምም አደጋ እንዳላጋጠመው ተነግሮለታል፡፡

መርከቧ ያጋጠማት አደጋ በኩባንያው ላይ የ95 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚያስከትል ተተንብይዋል፡፡ እስከሚቀጥለው ህዳር 2012 መጨረሻ ድረስም አገልግሎት እንደማትጀምር ታውቋል፡፡ 450 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላት መርከብ የደረሰባት አደጋ ለባህር ዘርፍ የኢንሹራንስ ዘርፍ ታላቅ ኪሳራ ተብላለች፡፡ ኪሳራዋ ወደ 750 ሚሊዮን ዶላር ሊያሻቅብ ይችላል ተብሎም ተሰግቷል፡፡ ከመርከቧ ወደ ባህር ይፈሳል በመባል የተፈራው ነዳጅ ደግሞ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል ተብሎ ነው፡፡ በውኃ አካሉ ላይ ነዳጅ ከፈሰሰ ለበርካታ የውኃ ውስጥ ፍጡራን አደጋ ነው ተብሏል፡፡ ከመርከቧ ሊፈስ ይችላል የተባለው ነዳጅ መጠን 2,300 ሜትሪክ ቶን ነው መባሉ የጣሊያን መንግሥትን ጭንቀት ውስጥ ከቶታል፡፡

እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 15 ቀን በ1912 ከበረዶ ግግር ጋር ተላትማ አስከፊ አደጋ የደረሰባት ታይታኒክ 100ኛ ዓመቷ ሊዘከር የአራት ወራት ዕድሜ ሲቀረው፣ በ1,517 መንገደኞች ላይ በደረሰው የሰላም የባህር ላይ አደጋ በአጠቃላይ 2,223 መንገደኞች ተጭነው ነበር፡፡ የኮስታ ኮንኮርዲያ አደጋ ባህር ዳርቻ ላይ በማጋጠሙ እንጂ ታይታኒክ እንደሰመጠችበት ጥልቅ ባህር ላይ ቢሆን ኖሮ አደጋው የከፋ ይሆን ነበር፡፡ በዚህኛው አደጋ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ቢረጋገጥም፣ 29 ሰዎች ባለመገኘታቸው ፍለጋው ቀጥሏል፡፡ በቀደም በድንገት ያጋጠመው አደጋ ግን የባህር ላይ ተጓዦችንና የመርከብ ኢንዱትሪውን አስደንግጧል፡፡