በኢራን የአገሪቱን ጦር እንደ ግል ዘበኛው አድርጎ ሊጠቀም የሚችል ግለሰብም ሆነ ቡድን የለም ይባላል፡፡ የኢራንን ሀብት እንዳሻው በማናለብኝነት እየዛቀ ወደ ኪሱ የሚያስገባ ቡድንም ሆነ ግለሰብ እንደሌለ ይነገራል፡፡ በኢራን ሀብት ላይ ያሻውን ሊፈጽም የሚችል የውጭ ኃይል የለም፡፡ በኢራን በዘርና በጎሳ ከፍና ዝቅ መደረግ የለም፡፡ በኢራን ትምህርት ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ኢራን የራሷ የሆኑ ተሽከርካሪዎችንና መለስተኛ አውሮፕላኖችን የምታመርት አገር ናት፡፡ ኢራን በሕክምና ነክ ምርምር ብዙ የገፋችና ዓለም ዓቀፍ ሽልማት ያገኙ ተመራማሪዎችን ያፈራች ምድር ናት፡፡ ኢራን በሕዋ ቴክኖሎጂ በመጠኑ ተራምዳለች፡፡ የራሷን ሳተላይት ሠርታ አምጥቃለች፡፡ ወደ ሕዋ ህያው ፍጡር ለመላክ በቅርቡ ሙከራ ማድረጓን የዘገበው የአሜሪካው ሲኤንኤን ጦጣ የያዘው ጉዞ መክሸፉን የሚገልጽ የለበጣ ዜና በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎም ኢራን በሕዋ ውስጥ ያለ ሳተላይትን ለመምታት የሚችል ሚሳይል ሠርታ ሙከራ አካሂዳለች፡፡ ኢራን የተሳካ ሙከራ ነበር ስትል፣ የአሜሪካ ሚዲያዎች ግን ከሽፏል ብለዋል፡፡ ሩሲያና አሜሪካ የፀረ ሳተላይት ሚሳይል ባለቤት ሆነው ለረዥም ዓመታት ከዘለቁ በኋላ ከጥቂት ዓመታት በፊት ቻይና የዚህ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሆናለች፡፡
በፋርስ ቋንቋ ፀረ ኢራን የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ሥርጭት ያልከፈተ ትልቅ የሚዲያ ካምፓኒ የለም፡፡ ቪኦኤ ፋርስ፣ ቢቢሲ ፋርስ፣ ዩሮ ኒውስ ፋርስ በሳተላይትና በአንቴና በሚለቀቅ ሞገድ ኢራንን ያብጠለጥላሉ፡፡ በተጋነኑና ፈጠራ ባየለባቸው ዜናዎች ኢራንን የጥንቱ የሄኖም የድኝ እሳት ሸለቆ ሲያስመስሏት ውለው ያድራሉ፡፡ ማንም ሊሟገትበት የማይችለው የኢራን ነዳጅ እንደገና ለምዕራባውያኑ ካምፓኒዎች ጀባ ቢባል፣ እነዚህ ሚዲያዎች የኢራን አያቶላዎችን ቀን ከሌት በማሞጋገሱ ሥራ የሚጠመዱ መሆኑን ነው፡፡
አሁን እንደ ጥፋት መሣርያ ተደርጎ ብዙ የሚወራለትን የኑክሌር ቴክኖሎጂ ግንባታ ኢራንን አደገኛ አገር አድርጎ ለማቅረብ እንደ ዋና አጀንዳ ይወሰድ እንጂ፣ ይህ የኑክሌር ግንባታ ሥራ የተጀመረው በራሳቸው በምዕራባውያኑ ነው፡፡ ለሻሑ ወዳጆች በነበሩበት ጊዜ፡፡ ምዕራባውያ አሁን ለኢራን ጠላት የሆኑት ለሻሑ የነበራቸው ፍቅር ግድ ብሏቸው አይደለም፡፡ የእነሱን ትኩሳት ጣራ ያደረሰው እንዳሻቸው ሲቀዱት የነበረው የነዳጅ ዘይት ሀብት ከእጃችው ወጥቶ ብሔራዊ ሀብት መደረጉ ነው፡፡
በቅርቡ ለአሥር ቀናት የተካሄደው የኢራን የጦር ልምምድ ብዙ አነጋግሯል፡፡ ይህ የጦር ልምምድ የጦር መሣርያዎች መሞከሪያነቱ ያመዘነበት ነው፡፡ ትልቅ ስጋት የፈጠረውም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ በማዕቀብ ላይ ማዕቀብ እየተነባበረባት ከ30 ዓመታት በላይ የቆጠረችው ኢራን፣ ልክ በኢራቅ ላይ ሲሆን እንደታየው እጇ ታስሮ ወራሪዎች ጓዳና ጎድጓዳዋ ውስጥ እንዲገቡ ብሎም እያተረማመሱ እንዲዘርፉ ላለመፍቀድ እየተውተረተረች ነው፡፡ ከባዱ ማዕቀብ ገና ሲጀማምር አገሪቱ የማጥቂያም ሆነ የመከላከያ መሣርያዎችን እንዳታገኝ፣ በእጇ የሚገኙት የጦርነት መሣርያዎችም በመለዋወጫ እጦትና በእርጅና ወደ ውድቅዳቂ ብረትነት አንዲቀየሩ ለማድረግ ያለመ ነውና፣ ኢራን የሯሷን የጦር መሣርያዎች ወደ ማምረቱ ፊቷንና ሀብቷን ያዞረችው ገና በጧቱ ነው፡፡ ከአምስትና ከስድስት ዓመታት በፊት ኢራን ሚሳይል ሠራሁ ብላ ሙከራ ስታካሂድ እነቢቢሲ በጣም ያሾፉ ነበር፡፡ አሁን ግን አሳሳቢ ነው ለማለት ተገድደዋል፡፡
ኢራን “ቬላያት 90” ብላ የጠራችው የበርካታ አዳዲስ መሣርያዎችን ሙከራን ያካተተው ይህ ልምምድ፣ በሰፊ የባሕር ክልል ላይ ነው የተካሄደው፡፡ ከኦማን ባሕረ ሰላጤ እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ የተዘረጋ፣ በምዕራብ የሶማሊያ ባሕርን በምሥራቅ ደግሞ የህንድ ውቅያኖስን ያካለለ ቦታን የሸፈነ ነው፡፡ ኢራን በአጭርና በመካከለኛ ርቀት የሚምዘገዘጉ ብቻ ሳይሆን እስከ 2,000 ኪሎ ሜትሮች የሚወነጨፉ ሚሳይሎችን ሠርታለች፡፡ ሚሳይሎቹ በዓይነት ሲዘረዘሩ ከአየር ወደ ምድርና ከምድር ወደ አየር፣ ከምድር ወደ ምድር፣ ከአየር ወደ አየር፣ በባህር ወደ ምድር፣ ከምድር ወደ ባህር ዘወትር የሚተኮሱ ናቸው፡፡ በዚህ ልምምድ ወቅት ኢራን የሠራቻቸውን የጦር መርከቦች፣ ባህር ሰርጓጅ መርከቦች፣ ቶርፒዶዎች፣ ፀረ ሚሳይል ሚሳይሎችና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሁሉ ተሞክረውበታል፡፡ ራዳር የማያያቸው ሚሳይሎችም መሞከራቸውም በኢራን በኩል ተነግሯል፡፡
የሚዲያዎች ጨዋታ የአሜሪካን የጦር በጀትና የኢራኑን በማወዳደር፣ የአሜሪካን የጦር መሣርያ ክምችትና የኢራንንን ጅምር መሣርያ የማምረት ዘመቻ በማነፃፀር ኢራን ጉዷ ይፈላል ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ የጦርነት ትርፋማነትና ኪሳራ በዚህ ሊሰላ ይችላል፡፡ የጉዳዩ አዋቂዎች ሊገመግሙትም ይችላሉ፡፡ ለጦርነት መኃይም የሆንን ሰዎች ግን የአሜሪካን የጦርነት በጀትና የታሊባንን እየገመትን የአፍጋኒስታን ጦርነት ለምን አሥር ዓመት ፈጀ ብለን እንጠይቃለን፡፡ አሜሪካ ከታሊባን ጋር ለመወዳጀት ዳርዳርታ እያሳየችና በኳታር ጽሕፈት ቤት ከፍተው ወደ ሥልጣናቸው የሚመለሱበትን መንገድ እያመቻቸች ነው፡፡ አከርካሪውን ሰባበርነው ሲሉት ባጅተው እንዲህ የሚደራደሩትና ጽሕፈት ቤት የሚከፍቱለት ታሊባን ከየት መጣ ብለን ማሰብ እንጀምራለን፡፡ ጦርነት በጦር መሣርያ ክምችት የሚሰላ ከሆነም የኢራቅ የቁርጥ ቀን ልጆችን ትጥቅና የፔንታጎንን የመሣርያ ክምር እያነፃፀርን ኧረ እንዴት ነው ነገሩ? ወደ ማለት እናዘነብላለን፡፡ የሆርሙዝ ሰርጥን ሰላምና ከነአካቴው መዝጋት በሚመለከትም ሚዲያዎች ለበጣ የበዛበት ትንተና በመሥራት የኢራንን ዛቻ ሲያቃልሉ ተሰምተዋል፡፡ ነገር ግን ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ 50 የጦር መርከቦች ለጥበቃ ተሠማርተው ባሉበት ጊዜ የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ምን ያህል እያስቸገሩ መሆኑን ማንም ሊዘነጋው አይገባም፡፡ እነዚህ የረባ ትጥቅ የሌላቸው ሰዎች በሶማሊያ ባሕር፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤና በህንድ ውቅያኖስ የሚደረገውን የባሕር ላይ እንቅስቃሴ አደገኛ ለማድረግ ችለዋልና በኢራን ላይ መሳቅ ነገሮችን ያለማመዛዘን ውጤት ነው የሚሆነው፡፡
ከሰሞኑ ዜናዎች መካከል የአፍሪካ ሚዲያዎች ጭንቀት ግራ አጋቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንግሊዝ ኑክሌር ቦምቦቿንና ኑክሌር አጥማጅ ባሕር ሰርጓጅ መርከቧቿን ማዘመን እንደሚገባት አስታውቃለች፡፡ ይህ ማንንም ያስጨነቀ አይመስልም፡፡ በተለይ የሚዲያ ሰዎችን፡፡ አሜሪካ አነስተኛ ኑክሌር ቦምቦችን (Mini-Nuke and Micro-Nuke) የመሥራትን አስፈላጊነት ደጋግማ ማስተጋባት የጀመረችው ቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሙ በታወጀ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በጆርጅ ቡሽ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ላይ ነበር፡፡ በአንድ ወገን ሚኒ ቦምቦቹን ለመሥራት ምርምር መጀመሩን የሚናገሩ ምንጮች ሲኖሩ፣ በሌላ ወገን ግን አሜሪካ በእነዚህ ቦምቦች መጠቀም መጀመሯንና በአፍጋኒስታንና በኢራቅ ጦርነት መንደሮችና ተራሮች በእነዚህ ቦምቦች ሳይደበደቡ እንዳልቀሩ ያላቸውን ጥርጣሬ ያስተጋባሉ፡፡ እነዚህ ማይክሮና ሚኒ ተብለው የተፈረጁ ኑክሌር ቦምቦች ከትልቁ ቡሽ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በሰፊው ጥቅም ላይ የዋሉትን በዩራኒየም የተቀመሙ ቦምቦች ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ እነፈረንሳይና እነጀርመን የተራቀቁ የጦር መሣርያዎችን ሳይቦዝኑ እያመረቱ ነው፡፡ ልምምድም ያደርጋሉ፡፡ ልምምዱ በቴአትር መልክ ቦምብና ሚሳይል ወደ ባዶ አየርና ወደ ምድረ በዳ በመተኮስ ወይም ጦርን ወደ አፍጋኒስታንና ኢራቅ ልኮ በሰው፣ በከተማና በሕንፃ ላይ እየተኮሱ መለማመድን ያካተተ ሊሆን ይችላል፡፡ አገሮችን ረግጠው የመግዛትና እጃቸውን በደም እያጠቡ የመዝረፍ ልማድ ያላቸው ጉልበተኛ አገሮች ያከማቹት ኑክሌር ቦምብና ሌላው ጅምላ ጨራሽ መሣርያ ችላ ብለው፣ የእነሱ መጠነ ሰፊ የመሣርያ ሙከራ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ተሞክሮ ያለቀለትን መሣርያ ተጠቅሞ እንዴት ማውደምና እንዴት መግደል እንደሚቻል ታስቦበት የሚደረግ ልምምድ ምንም ሳይመስላቸው፣ ማንንም ወርራና የማንንም ሀብት ዘርፋ የማታውቀው ኢራን ከአቅሟ በላይ ረባሽና የተለየ ዓላማ ያላት ተደርጋ በአፍሪካና በዓረቡ ዓለም ሚዲያዎች የምትወረፈው ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ ትናንት በኢራቅ ላይ ዛሬ ደግሞ ተመሳሳዩ ውንጀላ በኢራን ላይ ተሰምቷል፡፡ ነገስ? ከነገ ወዲያስ?
የሚዲያዎች ላይ አነጋገሮች ‘ወዮላት ኢራን’ የሚል መንፈስ ያጠላባቸው ይሁኑ እንጂ፣ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ጠበብቶች ጉዳዩን በጥንቃቄ መቃኘቱን ነው የመረጡት፡፡ የአሜሪካ የአየር ኃይል ዩኒቨርሲቲ ምሑር የሆኑት አዳም ሎውተር የአሜሪካ ፖለቲከኞች ከኢራን ጋር ለግብግብ ከመነሳታቸው በፊት ሊያስቡባቸው የሚገቡ ነገሮችን ጠቁመዋል፡፡ ከኢራን ጋር መፋጠጥ አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ገጥማው ከማታውቀው ከፍተኛ ብቃትና ትጥቅ ካለው ኃይል ጋር መጋጠም ማለት መሆኑን የተናገሩት ምሑሩ፣ አሜሪካ ከዚህ በፊት ጦርነት የከፈተችባቸው እነግሪናዳ፣ ፓናማ፣ ሶማሊያ፣ ሃይቲ፣ ቦስንያ፣ ሰርቢያ፣ ኢራቅና አፍጋኒስታን መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ በኢራቅ ሲሆን የነበረውን ነገር ሁሉ ቁጭ ብሎ ሲያይ የከረመው የኢራን ጦር ስለአሜሪካ ጦር ብዙ ነገር አውቆ የሚጠብቅ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል፡፡
አዳም ሎውተር የኢራን የስለላ መዋቅርም ችላ የሚባል እንዳልሆነ አውስተዋል፡፡ የኢራን የስለላ መዋቅር ከፍተኛ ብቃት ያለው መሆኑን ሊያሳዩ የሚችሉ በቅርቡ የተፈጸሙ ድርጊቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አብዱል ማሊክ ሪጊ የኢራን ሙጃሂድን (MKO) መሪ የነበረ ሰው ነው፡፡ አንዴ ለልዩ ሥራ ከዓረብ አገሮች አፍጋኒስታን ውስጥ ወደሚገኝ የአሜሪካ አየር ኃይል ካምፕ በመጓዝ ላይ እንዳለ፣ የኢራን የስለላ ድርጅት አውሮፕላኑን በጄቶቹ አስገድዶ ወደ ኢራን የአየር ክልል እንዲገባና እንዲያርፍ በማድረግ ሪጊን በቁጥጥሩ ሥር አውሏል፡፡ ከሳይንቲስቶቿ አንዱ ሳዑዲ ዓረቢያ ለስግደት ሄዶ ሲሰወር ጉዳዩን አነፍንፎ ሳይንቲስቱ ተጠልፎ አሜሪካ መግባቱን የደረሰበትና አሜሪካም ሳትወድ ነፃ እንድትለቀው ጉዳዩን ያጋለጠው ይኸው የስለላ መዋቅር ነው፡፡ ሳይንቲስቶቿን የገደሉና የሽብር ሥራዎችን የፈጸሙ በርካታ ቅጥረኞችንም ለቃቅሞ ለፍርድ አቅርቧል፡፡ በዚሁ ወርም አሜሪካ ወታደር አስመስላ ወደ አፍጋኒስታን ያስገባችውን፣ ከኢራናዊ ቤተሰቦች የተወለደ ኢራናዊ አሜሪካዊ፣ ድንበሯን ጥሶ በመግባት የከዳ የአሜሪካ ወታደር መስሎ የኢራንን የደኅንነት መዋቅር ለመሰርሰር ሲሞክር ክትትል ከተደረገበት በኋላ በቁጥር ሥር ውሎ ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ ከርሞ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ተሰምቷል፡፡
አዳም ሎውተር ወደ ኢራቅ ገባ ወጣ ሲል የነበረው የአሜሪካ ጦር ያለ በቂ እረፍት ወደ ሌላ ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ማድረግም የራሱ የሆነ አውዳሚ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አሳስበዋል፡፡ በቋሚነት ኢራቅ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የቆየው የአሜሪካ ጦር ከ150 ሺሕ እስከ 180 ሺሕ ይሁን እንጂ እዚያ ውስጥ ገብተው የወጡ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ወይም አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ወታደሮች ከአንድ ጊዜ በላይ ኢራቅ ውስጥ ገብተው ወጥተዋል ማለት ነው፡፡ የቀሩት ደግሞ በአፍጋኒስታን ጦርነት አንዳንዶቹ ሁለቱንም ጦርነቶች አይተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካ የመከላከያ ኃላፊ ሊዮን ፔናታ በቅርቡ ከአሜሪካው ሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የኢራን የኑክሌር ቴክኖሎጂ ዕድገት እያሳየ ቢሆንም ቦምብ ለመሥራት ብዙ እንደሚቀራት ገልጸው፣ አሁን ጊዜው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችንና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን ማድረጊያ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራቅን በኑክሌር ቦምብ ሠሪነት ወንጅለው መውረራቸው፣ አንድ ሰሞን ተመሳሳዩ ሰበብ ድርደራ በማይናማር (በርማ) ላይ ለመለጠፍም ዳርዳርታ ተጀምሮ ነበርና ሎረንስ ዴቪድሰን የተባሉ ታዋቂ አሜሪካዊ ፕሮፌሰርና ደራሲ የመከላከያ ኃላፊው ኑክሌር ቦምብ መሥራት የሚሉትንና ሐረግ በፅኑ ይቃወማሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ “consortiumnews.com.” ላይ ባሠፈሩት ጽሑፍ ሐሰተኛ ውንጀላዎችን በመጠቀም፣ በሐሰተኛ ውንጀላዎች ሌላውን ሰይጣን በማስመሰል፣ በሐሰተኛ ውንጀላዎች ሰበብ ወንጀሎችን በመፈጸም የአሜሪካ ፖለቲከኞች የሒትለሩን የጆሴፍ ጎበልስን መመርያ እየተከተሉ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ “.. If you tell a lie big enough and keep repeating it, people will usually come to believe it …” የሚለውን የናዚዎች አፈ ቀላጤ አባባል ማስታወሳቸው ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ግርግር መካከል የአፍሪካና የዓረቡ ዓለም ሚዲያዎች ውንጀላውንና ወዮልሽን አብረው አስተጋብተዋል፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ መጥቀስ ያስፈለገው የኃያላኑን ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ የዝርፊያ ሥራ ከማንም በላይ ያስተናገዱና በማስተናገድ ላይ ያሉም ሆነው ዞረው ለማሰብ ባለመቻላቸው ነው፡፡ የቅኝ ገዥነትን ጥቅም ያጣጣመ የአንድ አውሮፓዊ አገር ዜጋ የሆነ ጋዜጠኛና የአንድ የቅኝ ተገዥነትን ሰቆቃ ያስተናገደ የአፍሪካዊ አገር ዜጋ የሆነ ጋዜጠኛ ተመሳሳይ ፕሮፓጋንዳ ማስተጋባታቸው አስገራሚ ነው፡፡ የአፍሪካና የዓረብ አገሮች ሚዲያዎች ቢቢሲን፣ ሮይተርን፣ ኣዣንስ ፍራንስ ፕሬስን፣ ሮይተርን የመሳሰሉ ሚዲያዎችን እየጠቀሱ ዜና ማንበልበሉን የአዋቂነትና የዘመናዊነት ምልክት አድርገው የወሰዱት ይመስላል፡፡ ከግራና ከቀኝ ዜናዎችን ወስዶ ሚዛናዊ ትንታኔ ማቅረብ ኋላ ቀርነት እየሆነ ነው፡፡ በእርግጥ በእነዚያ ጉልበተኛ አገሮች ውስጥም የዚህ ዓይነት ዜናና ትንታኔ መሥራት ሽብርን ማበረታታት ተብሎ መብጠልጠልን የሚያስከትልና አደገኛ መዘዘ ለጋዜጠኛው የሚጋርጥ ሆኖ ታይቷል፡፡ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ ዓለማችንን ለማረጋጋት ምን ሚና ተጫውታለች? አንድ ሰሞን ጋብ ብሎ የነበረው ጦር መሣሪያዎችን ለማርቀቅ ምርምር ማካሄድና ማከማቸት ለምን እንደገና አገረሸ? የጋራና የተናጠል የጦርነት ልምምዶች ለምን እየተበራከቱ መጡ?’ ተብሎ ቢጠየቅ አሜሪካን ተጠያቂ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት የቀድሞው የዋርሶ ኃይል ከወጣባቸው የምሥራቅ አውሮፓና የቀድሞ የሶቪዬት ኅብረት ግዛቶች አዳዲስ የጦር ሠፈሮችን በመገንባት ሌላ ቀዝቃዛ ጦርነትን ሞኖፖላይዝድ አድርጓል፡፡ እነዚህ አገሮች ወደ ኔቶ እንዲገቡ በማድረግ የየአገሮቹን ጦር ኃይል እንደ ሚሊሻዎቹ አድርጎ ይገለገልባቸዋል፡፡ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ ጦርነቶችም አዝምቷቸዋል፡፡ በእነዚህ አገሮች ሚሳይሎችንና ሚሳይል አምካኝ የተባሉ ሚሳይሎችን እንዲሁም ራዳሮችን ወዘተ በመትከል ሌሎች አገሮች ጥርጣሬ ውስጥ ይገቡ ዘንድ በር ከፍቷል፡፡ በአንድ አገር ወስጥ ለውጥ ሲመጣ በተለይ ደግሞ ኢንቨስትመን ወይም ግሎባላይዜሽን በሚል ሽፋን የአሜሪካ ካምፓኒዎች የሚያካሂዱትን ዘረፋ ወይም ከልክ ያለፈ ብዝበዛ ለማስቆም ቆርጦ የተነሳ አገር ወይም መንግሥት ብቅ ባለ ቁጥር፣ በአጎራባች አገሮች አዳዲስ የጦር ካምፖችን በመክፈት አገሮችና ሕዝቦች የውስጥ ጉዳያቸውን በነፃነትና ባሻቸው መንገድ እንዳይቀይሱ ያስፈራራል፡፡ በዚህ ዘመን “አገሮች ወይም ሕዝቦች ነፃ ናቸው” ለሚለው ሐረግ አዲስ ትርጉም ሳያስፈለገው አይቀር!
በሰላም ያቆየን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻ This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it ማግኘት ይቻላል፡፡


