Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

አውሮፓና የሥራ አጥነት ማዕበል

  • PDF

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ባደጉ አገሮች የተከሰተው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ለአውሮፓውያኑም ስጋት እየሆነ ነው፡፡ የሥራ አጦች ቁጥር መጨመርና የኢኮኖሚው ዕድገት ማዝገም የአውሮፓ አባል አገሮች መሪዎችንና ፖሊሲ አውጪዎችን ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ በአውሮፓ በዩሮ ዞን አባል አገሮች ውስጥ እየታየ ያለውና ከወር ወር እያሻቀበ የሄደው የሥራ አጡ ቁጥር ስጋትን ፈጥሯል፡፡

ዩሮስታት ኤጀንሲ እንዳስታወቀው በ17ቱ የዩሮ ዞን አባል አገሮች እ.ኤ.አ በ2011 በህዳር የነበረው የሥራ አጥ ቁጥር 10.3 በመቶ ሲሆን፣ በታህሳስ 10.4 በመቶ አስመዝግቧል፡፡ የዩሮ ዞን የሥራ አጥነት መጠን ማሻቀብ አገሮቹ በአንድ ዓይነት ገንዘብ መገበያየት ከጀመሩ ወዲህ የመጀመርያው ተብሎለታል፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 በአባል አገሮቹ ውስጥ 16.5 ሚሊዮን ሰዎች ከሥራ የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2010 ከነበረው ጋር ሲነፃፀር 751 ሺሕ ልዩነት አሳይቷል፡፡

እንደ ኤጀንሲው መረጃ ከሆነ አባል አገሮቹ በሙሉ በሥራ አጥነት ማዕበል ይመቱ እንጂ፣ የስፔንን ያህል ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ያስመዘገበ አገር የለም፡፡ በስፔን የሥራ አጦች ቁጥር 22.9 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በብድር ቀውሱ ከፍተኛ ተጠቂ በሆነችው ግሪክ ደግሞ 20 በመቶ ሆኗል፡፡ ኦስትሪያ ደግሞ 4.1 በመቶ በማስመዝገብ ዝቅተኛውን የሥራ አጥ ቁጥር ይዛለች፡፡

በአውሮፓ የብድር ቀውሱ በማየሉ እ.ኤ.አ የ2011 ሙሉ ዓመት የሥራ አጦች ቁጥር እያሻቀበ የሄደበት ነበር፡፡ በታህሳስ 2010 የሥራ አጥ ቁጥሩ 10 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በ2011 ላይ በነበረው ተመሳሳይ ወር የ0.4 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 10.4 በመቶ አሻቅቧል፡፡ ይህ ዓይነቱ ታይቶ የማይታወቅ ሥራ አጥነት ወደ ፖለቲካ አለመረጋጋትና ኹከት ያመራል ተብሎ ተሰግቷል፡፡

ቢቢሲ የሲቲግሩፕ ኢኮኖሚ ባለሙያን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በዩሮ ዞን አባል አገሮች ያለው የሥራ አጥ ቁጥር በ2012ም ቢሆን እየቀነሰ አይሄድም፤ ይልቁንም ያሻቅባል እንጂ፡፡ ለዚህም ደግሞ የኢንቨስትመንቶች በጊዜያቸው አለመከናወን ትልቁን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ይህም በአውሮፓ ሥራ የማግኘት ዕድሉን በጣም ያጣበዋል፡፡ ይህንንም በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የደተረገ የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል፡፡ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም በጊዜያቸው እየተጠናቀቁ ወይም እየተሠሩ አይደለም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ቀድሞውንም ሆነ አሁን ትርፍ እየሰበሰቡ ባሉ ድርጅቶች የአዲስ ሠራተኞች ቅጥር ጉዳይ ቀዝቅዟል፡፡ በጭንቅና በኪሳራ ውስጥ ያሉ ድርጅቶችን ዕድሜ ለማራዘም ደግሞ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሠራተኞችን መቀነስ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ የሥራ አጡን ቁጥር የማብዛት ብቻ ሳይሆን፣ የአኅጉሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በመጐተትና የከፋ ቀውስ ውስጥ እንዳይከታት ተሰግቷል፡፡

በ17ቱ የዩሮ ዞን አባል አገሮች የሚታየው የሥራ አጥነት ቁጥር ማሻቀብ ዳፋው ለጠቅላላው ለ27ቱ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችም እየተረፈ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ህዳርና ታህሳስ በአውሮፓ አባል አገሮች የነበረው የሥራ አጥ ቁጥር በተከታታይ 9.8 በመቶ እና 9.9 በመቶ አስመዝግቧል፡፡ ከሥራ የተፈናቀለው ቁጥርም 23.8 ሚሊዮን ሕዝብ ነው፡፡

በጠቅላላው ከአውሮፓ አባል አገሮች ሲነፃፀርም ግሪክ፣ ቆጵሮስና ሰፔይን የሥራ አጥ ቁጥርን በከፍተኛ ሁኔታ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ኢስቶኒያ፣ ላቲቪና ሉቲኒያ ደግሞ ውድቀትን፡፡

ከሁለት ዓመታት ፅኑ የኢኮኖሚና የብድር ቀውስ በኋላ በተፈጠረው የበጀት ጉድለት ምክንያት በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አውሮፓውያን ከሥራቸው ሲፈናቀሉ፣ በታህሳስ ወር ብቻ 20,000 አውሮፓውያን ሥራቸውን ማጣታቸውን ፋይናንሻል ፖስት ዘግቧል፡፡ ከትናንት በስቲያ የአውሮፓ መሪዎች ባደረጉት ስብሰባ አውሮፓን ከብድር ቀውስ በማውጣትና ኢኮኖሚዋን በማሳደግ የዓለምን 16 በመቶ ድርሻ ለማበርከት ተነሳስተዋል፡፡ አሁን የተከሰተውን አስፈሪ ሥራ አጥነት ለመቅረፍም 82 ቢሊዮን ዩሮ ለማንቀሳቀስ ማሰባቸውን ዘገባው አስነብቧል፡፡

የአውሮፓ አባል አገሮች መሪዎች የሥራ አጥ ቁጥር እየጨመረ ባለበትና የኢኮኖሚው ዕድገት አደጋ በተጋረጠበት በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን ችላ አላልነውም እያሉም ነው፡፡ ኤቢሲ ኒውስ እንደዘገበው፣ የአባል አገሮቹ መሪዎች በብራሰልስ ተሰባስበዋል፡፡ በሚኖራቸው ቆይታም የሥራንና የኢኮኖሚ ዕድገት አጀንዳን ዋነኛ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ቁጥሮች እንደሚያሳዩት፣ የስፔይን ኢኮኖሚ ዕድገት በ2011 የመጨረሻው አራት ወራት በ0.3 በመቶ ቀንሷል፡፡ በመሆኑም በ2012 የመጀመርያው አራት ወራት ስፔይን የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገባለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፈረንሳይ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ የሚያሳየውም የ0.5 በመቶ ዕድገትን ብቻ ነው፡፡ ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ0.5 በመቶ ቅነሳን ያሳያል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በኢኮኖሚው ላይ የተጋረጠው አደጋ እንደሆነ ቢቢሲ አትቷል፡፡ ከሁሉም የተሻለች ናት የምትባለው ጀርመን በጥር ወር የሥራ አጥ ቁጥሯን ወደ 6.7 በመቶ ማውረዷ ይነገራል፡፡

የአውሮፓ መሪዎች በብራሰልስ በሚያደርጉት ውይይት በሥራ አጥነት ማዕበል የተመታችውን አውሮፓ ይታደጓት ይሆን? ሀብታሞቹ በሚባሉት የሰሜን አውሮፓና ምርታማ አይደሉም በሚባሉት ደቡብ አውሮፓ አገሮች መካከል የተፈጠረው ክፍተት በብራሰልሱ ስብሰባ ላይ ጥላውን አጥልቷል እየተባለ ነው፡፡