አቶ ፍፁም ገዛኸኝ፣ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ሊቀመንበር
አቶ ፍፁም ገዛኸኝ የኢትዮጵያ አስጐብኚ ድርጅቶች ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡
ሊቀመንበሩን በኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ እንዲሁም በአፍሪካ የኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታዎች (አይካሳ) ጉባዔ ወቅት ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ጋር በተያያዘ የተሠሩ ሥራዎችን በማስመልከት ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አይካሳን በመሳሰሉ ትልልቅ ጉባዔዎች ላይ ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ ምን ሊሠራ ይችላል?
አቶ ፍፁም፡- በአፍሪካ የኤችአይቪ/ኤድስና የአባለዘር በሽታዎች ዓለም አቀፍ ጉባዔ (አይካሳ) ተሳታፊዎች የተማሩ፣ በየአገሮቻቸው ትልቅ ሥልጣን ያላቸውና ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ የመስጠት ብቃትና ስለ ኢትዮጵያ ለማውራት ከሌሎች የተሻለ ሰፊ ዕድል ያላቸው ናቸው፡፡ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ጉባዔተኞች ትራንስፖርት በማቅረብና በአስጎብኝነት በመስኩ ባለሙያ ያላቸው የአስጐብኚ ድርጅቶች ቢሳተፉ፣ በእንግዶቹ ላይ ተቀርፀው የሚቀሩ ብዙ መልካም ነገሮችን መሥራት ይቻል ነበር፡፡
አይካሳን አስመልክቶ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ጉባዔተኞቹ ሲመጡ የሚጐበኙዋቸው ቦታዎችን እንዲያውቁ በድረ ገጽ ላይ በትክክል መቀመጣቸው ይገኝበታል፡፡ በእርግጥ የሚጐበኙ ቦታዎችን በድረ ገጽ ላይ ማስቀመጡ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የተለያዩ በርካታ አማራጮች፣ ለመጐብኘት የሚንቀሳቀሱባቸው ቀናትና ማንን ማግኘት (ኮንታክት) እንዳለባቸው የሚያመለክቱ ነጥቦች መካተት አለባቸው፡፡ ይህ ዓይነቱም አካሄድ እንግዶቹ የሚመቻቸውን መርጠው እንዲንቀሳቀሱ ይረዳል፡፡ የሚፈለገው ተግባር ግን አልተከናወነም፡፡ ፕሮግራሞችም አልተሠሩም፡፡ እንደ ጉባዔተኛ ወይም እንደ አገር ጐብኚ ሆነን ስንመለከተው የምንሄድበትን አገር በሙሉ አናውቀውም፡፡ ጉባዔተኛው ወይም ጐብኚው በራሱ ፕሮግራም እንዲሠራ የሚጠበቅ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ አስጎብኚ ድርጅት አያስፈልግም፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጅት የሚያስፈልገው እኮ ፕሮግራም ከመሥራትና የተለያዩ ነገሮችን ከማማከር ጀምሮ አስጎብኝቶ እስከመሸኘት ድረስ ያለውን ሥራ ለማከናወን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ግብር ከፋይ የሆኑና ባለሙያዎችን ያቀፉ እንደነዚህ ዓይነት ድርጅቶችን አገሪቱ በሚገባ መጠቀም ይኖርባታል፡፡
ሪፖርተር፡- ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ጋር በተያያዘ በአይካሳ ጉባዔ ምን ተገኝቷል?
አቶ ፍፁም፡- አይካሳን በተመለከተ ያለን መረጃ በጣም ውስን ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንድንሳተፍ አልተደረግንም፡፡ ከዚህ አኳያ እንደ ማኅበር ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ከጉባዔው መጀመር አስቀድሞ ግን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአዘጋጆቹ ጋር በመሆን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶን ነበር፡፡ የስብሰባው ዓላማ ብዙ ሆቴሎች በቱሪስቶች በመያዛቸው የተወሰኑትን አስለቅቁልን የሚል ጥያቄ ለማቅረብና በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ነበር፡፡
ማኅበሩም በዚህ ዙሪያ እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለበት ከአባል ድርጅቶቹ ጋር በሰፊው ከመከረበት በኋላ፣ በአዲስ አበባ ብዙ ጊዜ ይቆዩ የነበሩትን ቱሪስቶች ሌላ ቦታ እንዲጠቀሙና ፕሮግራሞቻቸውንም እንዲቀይሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት አስጎብኚ ድርጅቶቹ መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የያዙትን ፕሮግራም ወደ መጨረሻ እንዲያዛወሩት፣ መጨረሻ ላይ የነበረውን ፕሮግራም ደግሞ ወደ መጀመሪያ እንደቀየሩትና ሆቴሎች እንዲለቀቁ በማድረግ የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክተናል፡፡
ሪፖርተር፡- የቱሪስቶችን ፕሮግራም እንደዚያ መቀያየር አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳድርም?
አቶ ፍፁም፡- ከቱሪዝም ሥራ አኳያ ቱሪስቶች በተጻፈላቸው ወይም በተያዘላቸው ፕሮግራም እንዲጠቀሙ ለማድረግ ከመንቀሳቀሳቸው ከስድስት ወራት ወይም ከአንድ ዓመት በፊት ነው ዝግጅቶች መከናወን ያለባቸው፡፡ በዚህ መልኩ በተዘጋጀላቸው መሠረት የተያዙላቸው ሆቴሎች ሊከበሩላቸው ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሲፈጠሩ ቱሪስቶቹን በማስረዳትና የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር መቀየር ግድ ይሆናል፡፡ ይኼም የተለመደ ነገር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቅሬታዎች ሊቀርቡ እንደሚችሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ አስጎብኚ ድርጅቶችም ቅሬታዎችን ለማስተካከል የሚጠቀሙባቸው የራሳቸው የሆነ አካሄዶች አሏቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ ፍፁም፡- እንገናኛለን፡፡ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እንነጋገራለን፡፡ ችግሩ ግን ወደ ሥራ ሲገባ በሠራተኛ በኩል የሚፈጠር የአሠራር ችግር አለ፡፡ ከአይካሳ ጉባዔ በኋላ ግን ከአዘጋጁ አካል ጋር ተገናኝተን ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን ተነጋግረንበታል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ትልልቅ ጉባዔዎች ሲካሄዱ የምንሳተፍበት መንገድ ይኖራል፡፡ ትልቁ ነገር በአገራችን እስከዛሬ ድረስ የተከናወነው ኮንፈረንስ የአይካሳ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩም የሚመለከተው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች ትላልቅና ትናንሽ ኮንፈረንሶችን ያካሂዳሉ፡፡ ኮንፈረንሶችን ትናንሽ ናቸው ብለን መናቅ የለብንም፡፡ ውጤታማ የሚሆኑት ግን ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ሲዘጋጁ ወይም ሲሠሩ ነው፡፡ በዚህም አገሪቱ የበለጠ ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡
ሪፖርተር፡- ትልልቅ ጉባዔዎች ሲዘጋጁ ምን ዓይነት ዝግጅቶች ሊደረጉ ይገባል?
አቶ ፍፁም፡- ምንጊዜም ቢሆን ጉባዔዎች ሲዘጋጁ በሚገባ በተደራጀ ሁኔታ መሆን ይገባዋል፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹም ጉባዔዎች ከቱሪዝም አንፃር ኮንፈረንስ ቱሪዝም ይባላሉ፡፡ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ደግሞ ዝም ብሎ ስብሰባ ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ ወይም እንግዶች አገራችን መጥተው በሰላም ተሸኙ መሆን የለበትም፡፡ እነዚህ እንግዶች ወደ አገራችን ሲመጡ ብዙ የምናገኛቸው ጥቅሞች አሉ፡፡ ከጥቅሞቹም መካከል አንደኛው ይዘው የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡
ይህንን የውጭ ምንዛሪ እዚህ እንዲያወጡና አገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም የሚከናወነው ደግሞ የሚያዝናኑ ነገሮችን እያቀረቡ በማስደሰት፣ በማዝናናትና የአገሪቱን መልካም ገጽታ ይዘው እንዲሄዱ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገራችን ኮንፈረንሶች የሚዘጋጁበት መንገድ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ ነው?
አቶ ፍፁም፡- ብዙ ጊዜ በአገራችን ኮንፈረንሶች ሲዘጋጁ የኮንፈረንስ ጊዜውን በጠበቀ መንገድ ነው የሚከናወኑት፡፡ ይህም ማለት እንግዳው የመክፈቻው ቀን ይገባል፡፡ በመዝጊያው ወይም በመጨረሻው ቀን ይወጣል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን አካሄድ መከተል አያስፈልግም፡፡ ጉባዔው ከመጀመሩ ከስምንት ቀናት በፊት መግባት ወይም ከጉባዔው በኋላ ቢያንስ ለአሥር ቀናት ዘግይተው መሄድ አለባቸው፡፡ ይህም ለአየር መንገድ፣ ለሆቴሎችና በአጠቃላይ ለአገሪቱ ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ብዙ ገንዘብ እንዲያወጡና በዚህም ለብዙ ወገኖች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ ምን ያህል አባል ድርጅቶች አሉት?
አቶ ፍፁም፡- ማኅበሩ 163 አባል አስጐብኚ ድርጅቶች አሉት፡፡ እነዚህም ድርጅቶች የሚፈለግባቸውን መስፈርቶች አሟልተው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሕጋዊ ዕውቅናና የንግድ ፈቃድ አላቸው፡፡ አባል የሚሆኑት ድርጅቶች ምን ያህል ተደራጅተዋል? የተሟላ ቢሮና ባለሙያዎች አሏቸው? የሚለው ከታየና ከተጠራ በኋላ ነው አባል እንዲሆኑ የሚደረገው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ዓመት ብቻ በግምት ወደ 400 ሺሕ የሚጠጉ ቱሪስቶች እንደገቡ በተለያየ መንገድ ተገልጿል፡፡ እነዚህን ቱሪስቶች ተቀብለው ያስጐበኙት በማኅበሩ የታቀፉት አስጐብኚ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ለኮንፈረንስ የሚመጡትን እንግዶች ማስጎብኘት የድርጅቶቹ በጣም ቀላሉ ሥራ ነው፡፡
ምክንያቱም አስቀድሞ ለጉብኝት ብሎ የሚመጣውን ቱሪስት ለማስተናገድ ከአስጐብኚው ድርጅት ብዙ ይጠበቅበታል፡፡ ከሚጠበቅባቸውም ተግባራት መካከል ብዙ ፕሮፌሽናል የሆኑ አሠራሮች አሉ፡፡ ድንገት ጥፋት ቢፈጸም በተለያዩ አገሮች ሊያስከስሱ የሚችሉ ነጥቦችን ይዞ እንደሚመጣ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ጉብኝቱንም ከጨረሰ በኋላ ሥራችንን በተመለከተ እዚሁ ይገመግመናል፡፡ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ደግሞ ከላከው ድርጅት ጋር በመሆን በድጋሚ ከገመገመ በኋላ ነው ሥራው ተጠናቀቀ የሚባለው፡፡ በዚህ መልኩ ነው እስከዛሬ እየሠራን ያለነው፡፡
ከማስጎብኘት ሥራዎች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ቱሪስቶችን አሳምኖ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ሲባል ቀላል አይደለም፡፡ እኛ ብቻ ነን የአገራችን መልካም ነገር የሚታየን፡፡ በምዕራቡ ዓለም ግን የአገራችን መልካም ነገር በፍፁም አይታይም፡፡ ሁሉም የሚያስበው ድርቅ፣ ረሃብና ጦርነትን ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ አስቀይሮ ቱሪስቶችን ማምጣት ከሥራዎች 80 ከመቶ ያህሉን ይይዛል፡፡ እዚህ ከመጡ በኋላ ማስጎብኘቱ ምናልባት 20 ከመቶው የአስጐብኚው ድርጅት ተግባር ነው የሚሆነው፡፡ ይህንን ነው አሁን በኮንፈረንስ ቱሪዝም የምንሠራበት፡፡ ይህም ለእኛ በጣም ቀላል ነው፡፡ በአንፃሩ ግን ለእንግዶች የምንሰጣቸው አገልግሎትና ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታ የምናደርገው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡
ከአይካሳ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በራሳቸው ተንቀሳቅሰው አባል ድርጅቶቻችንን አነጋግረዋቸዋል፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለጋዜጠኞች ቀላል ጉብኝቶችን እዚሁ እንዳደረገ ሰምተናል፡፡ ከሙያ አንፃር ሲታይ ግን ይህንን ሚኒስቴሩ ማድረግ የነበረበት ሳይሆን፣ መደረግ ያለበት በአስጐብኚ ድርጅቶች ነው፡፡ መንግሥት ይህን ሥራ የሚያከናውን ከሆነ አስጎብኚ ድርጅቶች ለምን አስፈለጉ? ከየትስ አምጥተው ነው ግብር የሚከፍሉት? ስለዚህ በሩ ሊከፈትላቸው ይገባል፡፡
በአንድ በኩል ሲታይ ግን አይካሳም ሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለቀ ሰዓት ይህ ዓይነቱን የማስጐብኘት ሥራ መውሰዳቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሊመሰገኑም ይገባል፡፡ መልካም ጅማሮም ነው፡፡ ግን አይካሳም ሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ሥራ እንዲያከናውኑ በሕግ አልተፈቀደላቸውም፡፡ አይጠበቅባቸውም፡፡ ይህን ሥራ እንዲያከናውኑ በሕግ ለተፈቀደላቸውና ዕውቅና ላላቸው ድርጅቶች ሥራውን አሳልፈው መስጠት ይገባቸዋል፡፡


