Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

‹‹በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ የእንጀራ ፋብሪካ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ ነን››

  • PDF

አቶ ኃይሉ ተሾመ፣ የማማ ትኩስ እንጀራ ባለቤት

ከአሥር ዓመት በፊት ከአነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በወሰዱት አነስተኛ ብድር ወደ እንጀራው ንግድ የገቡት አቶ ኃይሉ ተሾመ፣ በአሁኑ ጊዜ ‹‹ከመንግሥት በሚያገኙት ያላሰለሰ ድጋፍ›› ከፍተኛ መጠን ያለው እንጀራ ወደ ውጪ በመላክ በዘርፉ ዋነኛ ላኪ ለመሆን ችለዋል፡፡ አቶ ኃይሉ የእንጀራውን ንግድ በጀመሩበት ወቅት ብዙዎች በዘርፉ ተሰማርተው የነበረ ቢሆንም፣ ምርታቸውን በየጊዜው በጥራትና በብዛት በማሳደግ በተወሰኑ ዓመታት በአገር ውስጥም ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ በቅተዋል፡፡ ማማ ትኩስ እንጀራ በተባለው ድርጅታቸው አዲስ አበባ ሒልተንና ሸራተን አዲስን ጨምሮ ለትላልቅ ኩባንያዎች አቅራቢ መሆናቸው ምርታቸው በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡ አቶ ኃይሉ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካን ጨምሮ ወደ ውጪ የሚልኩት የእንጀራ መጠን በሳምንት ዘጠኝ ሺሕ የደረሰ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት የሚገነቡት የእንጀራ ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር ወደ ውጪ የሚልኩትን እንጀራ መጠን በእጥፍ ለመጨመር አቅደዋል፡፡ ከእንጀራው ንግድ በተጨማሪ ሌሎች ምግቦችንም ወደ ውጪ ይልካሉ፡፡ ኃያል ዓለማየሁ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባገኘነው መረጃ መሠረት እርስዎ በባለቤትነት የያዙት ማማ ትኩስ እንጀራ በአገሪቱ ከፍተኛው የእንጀራ ላኪ ድርጅት መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የእንጀራ የውጭ ገበያ ምን እንደሚመስል ያብራሩልናል?

አቶ ኃይሉ
፡- በውጭ በተለይም በአሜሪካ ገበያ ለእንጀራ ያለው ፍላጎት በተለይ ባለፉት ሦስትና አራት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከተወሰኑ ወራት በፊት እኛ እንጀራ የምንልከው በሳምንት አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ ነበር፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ግን በሳምንት አራት ጊዜ መላክ የጀመርን ሲሆን፣ ከተወሰኑ ወራት በፊት በሳምንት ከአንድ ሺሕ እንጀራ የማይበልጠው ኤክስፖርታችን በአሁኑ ጊዜ 10 ሺሕ እየተጠጋ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በገና በዓል አካባቢ የውጪ ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ለደንበኞቻችን ከ10 ሺሕ እንጀራ በላይ በሦስትና በአራት ቀናት ውስጥ ለመላክ ተገደን ነበር፡፡ ይኸው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የውጪ ገበያ በምንታወቅበት በእንጀራው ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች በምንልካቸው የምግብ ዓይነቶችም ላይ እየታየ ነው፡፡ በቅርቡ በተለይ ወደ አሜሪካ ቆጮ መላክ ጀምረን በጥቂት ወራት ገበያው በመጨመሩ በአሁኑ ጊዜ በሳምንት ከ400 ኪሎ ግራም በላይ ቆጮ እየላክን እንገኛለን፡፡ በጥቅሉ በተለይ ባለፉት ሦስትና አራት ወራት የእንጀራውና ሌሎች የምንልካቸው ምግቦች ገበያ በጣም እያደገ ሲመጣ፣ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ገበያው በቀጣዩም እያደገ እንደሚሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማማ ትኩስ እንጀራስ እያደገ ከመጣው ከእንጀራና ከሌሎች ምግቦች የውጭ ገበያ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ያለው ዝግጁነት ምን ይመስላል?

አቶ ኃይሉ
፡- ሥራውን ከጀመርንበት ከአሥር ዓመት በፊት ጀምሮ ሥራችንን በጥራትና በመጠን እያሳደግን መጥተናል፡፡ አሁን ደግሞ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የውጪ የእንጀራ ገበያ ዕድል የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ የእንጀራ ፋብሪካ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንኑ ፋብሪካ ለመገንባት የአዲስ አበባ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ቢሮ 3,500 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ አዲስ አበባ ውስጥ በሊዝ እንዲሰጠን ጉዳያችንን እያስጨረሰልን ሲሆን፣ ለፋብሪካው ግንባታ የሚውል ብድርም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ  እንዲሰጠን ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራችንን ለማጠናከር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከሌሎች የመንግሥት መሥርያ ቤቶች እየተደረገልን ያለውን ያላሰለሰ ትብብርና ድጋፍ ሳልገልጽ ማለፍ ተገቢ አይሆንም፡፡ በዕቅዱ መሠረት የእንጀራ ፋብሪካው ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚጀምር ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ አዲስ የእንጀራና የሌሎች የምንልካቸው ምግቦች ማከፋፈያ ሱቅ ለመክፈት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ ወደ አሜሪካ የምንልካቸው ምግቦች የሚሰራጩት በወኪላችን በኩል ሲሆን፣ የኤክስፖርት መዳረሻችንንም እንደ አዲስ የተወለደችውን ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ወደ ሌሎች አገሮች ለማስፋፋት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የእንጀራ ፋብሪካው ምርታችሁን በምን ያህል እንደሚያሳድግና ለምን ያህል ሰዎችስ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ቢጠቅሱልን?

አቶ ኃይሉ
፡- በዕቅዱ መሠረት ፋብሪካው ለ400 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 350ዎቹ ሴቶች ይሆናሉ፡፡ ፋብሪካው በስምንት ወራት ውስጥ ሥራ ይጀምራል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ፋብሪካው ሥራ በሚጀመርበት ወቅት ምርታችንን በእጥፍ የምናሳድግ ሲሆን፣ የእንጀራ ኤክስፖርቱም በዚያው መጠን በእጥፍ፣ ብሎም አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሁለት እጥፍ ለማሳደግ ታጥቀን ተነስተናል፡፡ ሁሉም በዕቅዳችን መሠረት ከተከናወነ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቀን እስከ 25 ሺሕ እንጀራ የምናመርት ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ውጪ የምንልካቸውን ምርቶች መጠን 50 በመቶ እናሳድጋለን ብለናል፡፡

ሪፖርተር፡- የእንጀራ ገበያው እየጨመረ ለመምጣቱ እርግጠኛ ነን ይላሉ?

አቶ ኃይሉ
፡- አሁን ያለው የገበያ ሁኔታ በትክክል ያንን የሚያሳይ ሲሆን ፍላጎቱም የበለጠ እየጨመረ እንደሚመጣ ጥርጥር የለውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንጀራ የሚመገቡት በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ፈረንጆቹም ናቸው፡፡ በአሜሪካ እንጀራ ወይም ጤፍ ከጤነኛ ምግቦች ዝርዝር ውስጥ ከገባ ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ፣ እንጀራ ከኢትዮጵያውያንም አልፎ የፈረንጆችን ትኩረት ማግኘቱ አያስገርምም፡፡ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ እንጀራ ውስጥ ከሚገኘው ፕሮቲንና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ሌሎች ምግቦች ውስጥ ከሚገኙ ፕሮቲኖች ለሰው ልጆች ጤና የተሻለ መሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ እንጀራ ቶሎ ሊሻግት የሚችል ምርት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሌሎች እንደ አበባ የመሳሰሉት የኤክስፖርት ምርቶች እንደሚገጥማቸው ዓይነት የማጓጓዣ  ችግር አይገጥማችሁም?

አቶ ኃይሉ
፡- ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚደረግልን ትብብርና ድጋፍ ያላሰለሰ ነው፡፡ ይህም አነስተኛ የንግድ ሥራን በኢንዱስትሪ ደረጃ በማሳደጋችንና ለሌሎችም ምሳሌ እንድንሆን ለማበረታታት ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተደረገልን ያለው ትብብርም ተጠቃሽ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሳምንት አራት ጊዜ እንጀራ እየላክን የምንገኝ ሲሆን፣ ለዚህም አየር መንገዱ በፕሮግራማችን መሠረት ተገቢውን የአየር ጭነት አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ የማጓጓዣ ችግር አልገጠመንም፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ሌሎችንም ጨምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እያደረጉልን ያለው ትብብር ድርጅታችን ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሻገር ያስቻለው መሆኑን ብገልጽ ማጋነን አይሆንም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ከአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ጋር በተያያዘና በቀጣዩም ደረጃ ያወጣላቸውና እየተገበራቸው ያሉት ፖሊሲዎች ለዕድገታችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉና እያደረጉ እንደሚገኙ መግለጽም አግባብነት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ማማ ትኩስ እንጀራ በተለይ በእንጀራው የአገር ውስጥና የውጪ ንግድ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከእንጀራው በተጨማሪ ሌሎች ምግቦችን እየላከ እንደሆነ ገልጸውልናል፡፡ እነዚህ ተጨማሪ ምግቦች ምን ምን እንደሆኑና ወዴት እንደሚላኩ ቢያብራሩልን?

አቶ ኃይሉ
፡- በአሁኑ ጊዜ እንጀራውን ጨምሮ እንደ ወቅቱ ሁኔታ ከ15 እስከ 20 የምግብ አይነቶች ወደውጭ በመላክ ላይ እንገኛለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የቆጮ እንጀራ፣ የተለያዩ የወጥ ዓይነት ቁሌቶች፣ ሚጥሚጣና አዋዜ እንዲሁም የተለያዩ የቅመም ዓይነቶች ይገኙበታል፡፡ በቅርቡ የጀመርነው የቆጮ ኤክስፖርት በፍጥነት እያደገ የመጣ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በሳምንት ከ400 ኪሎ ግራም በላይ እያላክን እንገኛለን፡፡ የቆጮ ኤክስፖርቱን በመጪዎቹ ጥቂት ወራት በእጥፍ ወይም ከዚያም በላይ እንዲሆን ማሳደግ እንዳለብን የሚያመለክት የውጭ ገበያ በመኖሩ ለዚሁ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት የእንጀራ ኤክስፖርታችንን በሳምንት ወደ 15 ሺሕ ከፍ የምናደርግ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅት የቆጮውን ኤክስፖርት በእጥፍ የምናሳድገው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሚልኳቸው ምግቦች መካከል ‹‹የተለያዩ የወጥ ቁሌቶች›› የሚለው ያልተለመደ ይመስላል፡፡  ቁሌት እንዴት ነው ኤክስፖርት የሚደረገው?

አቶ ኃይሉ
፡- የተለያዩ የወጥ ዓይነቶች ለምሳሌ የቦዘና፣ የቀይ ወጥ፣ የዶሮ ቁሌቶችን ሠርተን በፍሪጅ አቀዝቅዘን እንልካለን፡፡ ይህን ከማድረጋችን በፊት እነዚህ ቁሌቶች በውጭ ገበያ ተፈላጊነት እንዳላቸው በላክነው የሙከራ ኤክስፖርት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በወኪሎቻችን አማካይነት እነዚህን ቁሌቶች በተለይ ለአሜሪካ ገበያ እያቀረብን ሲሆን፣ ገበያው ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ በመምጣቱ የእኛም ኤክስፖርት መጠን እንዲሁ እያደገ መጥቷል፡፡ በነገራችን ላይ ውጭ አገር ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥም የቁሌቱ ገበያም እያደገ በመምጣቱ፣ በአሁኑ ጊዜ ለተለያዩ ሱፐር ማርኬቶች አቅርቦታችንን በማቅረብ ላይ እንገኛለን፡፡