Thu05172012

Go to :English Edition

Back Home

“ቆሻሻን ወደ ገንዘብ በመቀየር መጠቀም ይጠበቅብናል”

  • PDF

አቶ ዘሩባቤል የማነብርሃን፣ የዳራ ብርኩዌቲንግ ፋብሪካ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ

አቶ ዘሩባቤል የማነብርሃን የዳራ ብርኩዌቲንግ ፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡

አቶ ዘሩባቤል በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን የገነቡት ፋብሪካ ቆሻሻዎችን በመጠቀም ብርኩዌት (ነጭ ከሰል) የተሰኘ ማገዶ ያመርታል፡፡ ይህ ማገዶ የድንጋይ ከሰልንና ፈርነስ ኦይልን የመተካት አቅም አለው፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ኃይሌ ሙሉ አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህንን ፋብሪካ ለመገንባት ያነሳሳዎት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ይህንን ሥራ የጀመርነው በ2002 ዓ.ም. ነው፡፡ ፋብሪካውን ያቋቋምነው የተጣሉ ቆሻሻዎችን በመጠቀም ወደማገዶነት ለመቀየር ነው፡፡ የተገነባውም በሲዳማ ዞን ዳራ በሚባል ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ ፋብሪካውን በተከልንበት አካባቢ የሚጣለው የቡና ገለባ አካባቢውን ይበክል ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ገለባ እየሰበሰብን ወደ ታዳሽ ኃይልነት መቀየር ጀምረናል፡፡ ይህንን ሥራ መጀመር እንዳለብኝ የወሰንኩት በህንድና በብራዚል ቆሻሻን በመጠቀም የሚያመርቱትን ማገዶ ወደ ውጭ እየላኩ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያገኙ ካወቅኩኝ በኋላ ነው፡፡ ቆሻሻን በመጠቀም ማገዶ ማምረት እንደሚቻል መጀመርያ ያየሁት ኬንያ ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ወደ ህንድ ሄጄ ማሽኑን ለመግዛት ችያለሁ፡፡ ኬንያ ውስጥ ቆሻሻን በመጠቀም ብርኩዌት የሚያመርቱ ድርጅቶች በርካታ ናችው፡፡ እኛ አገር ውስጥ ለጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉ ነገሮች ዝም ብለው በየቦታው ይጣላሉ፡፡ ቆሻሻን ወደ ገንዘብ በመቀየር መጠቀም ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ በማዘጋጃ ቤት ከሚሰበሰብ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚቻልበት ዘዴ አለ፡፡ ለቤት ውስጥ ማብሰያም መጠቀም ትችላለህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ በመምጣቱ የኢነርጂ እጥረት አለ፡፡ ስለዚህ ወደፊት ሰፊ ገበያ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በዚህና መሰል ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላት የሉም? ከሌሉስ ችግሩ ምንድን ነው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ሥራ ከጀመሩ በኋላ ተዘግተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ለምን ተዘጉ የሚለውን ሳጠና በወቅቱ የነበረው የገበያ ዋጋ ዋነኛ ችግር እንደነበር ለማወቅ ችያለሁ፡፡ እነኚህ ፋብሪካዎች በተከፈቱበት ወቅት የነበረው የፈርነስና ለማገዶ የሚያገለግሉ እንጨቶች ዋጋ ዝቅተኛ ነበር፡፡ ኢንዱስትሪዎችም አልተስፋፉም ነበር፡፡ ፋብሪካዎች ከነበረው ገበያ ጋር መወዳደር ስላልቻሉ ለመዘጋት ተገድደዋል፡፡ ትልቁ ነገር የዋጋ አለመመጣጠን ችግር ነበር፡፡ እኛ ይህንን ሥራ ከጀመርነው ወደ ስድስት ወር ገደማ ሆኖናል፡፡ ቀስ በቀስ ውጤቱን እያየን መጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ከቆሻሻ የሚሠራ ከሰል ከሌሎች ማገዶዎች የሚለየው በምንድነው? ምንስ የተለየ ጠቀሜታ አለው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- በአሁኑ ጊዜ እያመረትነው ያለውን ማገዶ በቤት ውስጥ መጠቀም አይቻልም፡፡ ልዩ ምድጃ ያስፈልገዋል፡፡ ይህንን የተለየ ምድጃ ጂቲዜድ እንዲሠራልን እየተነጋገርን ነው፡፡ አምስት ኪሎ ብርኩዌትስ ብትጠቀም 100 ኪሎ ሩዝ ማብሰል ትችላለህ፡፡ ወደ ፋብሪካዎች ስንሄድ ደግሞ የድንጋይ ከሰል ከውጪ ነው የሚመጣው፡፡ እዚህ አገር ያለው የድንጋይ ከሰል የካሎሪ መጠኑ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ የእኛ ብርኩዌት ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ በሙሉ መተካት ይችላል፡፡ ለረጅም ሰዓት ይነዳል፡፡ ከሦስት ሰዓት በላይ ይነዳል፡፡ አሁን ከሁለት ወር በኋላ የምንጀምረው ተጨማሪ ፋብሪካ አለን፡፡ ይህ ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር ቤት ውስጥ መጠቀም የሚያስችል ብርኩዌት ያመርታል፡፡ ጭስ አልባ ነው፡፡ ከካርቦን ነፃ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ካቀጣጠልከው ከሦስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ሊነድ ይችላል፡፡  ድንጋይ ከሰልና ፈርነስ ኦይል የሚባሉት በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች ናቸው፡፡ አሁን ባለን አቅም ሁሉንም ከውጭ የሚመጡትን ምርቶች ሙሉ በሙሉ መተካት ባንችልም፣ ለእነዚህ ምርቶች የምናወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ ማድረግ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ከእንጨት ማገዶ ጋር ብናነፃፅረው ከዋጋ አኳያ 40 በመቶ በላይ ይቀንሳል፡፡ እንጨት የሚነድበትና ብርኩዌት የሚነድበት ሰዓት ይለያያል፡፡ የመንደድ ኃይሉ ከእንጨት ሦስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ እንደ እንጨት መፍለጥና መቁረጥ አያስፈልገውም፡፡ ከካርቦንና ሰልፈር የፀዳ ነው፡፡ ብርኩዌት ስትጠቀም የሚገኘው አመድ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቡና ገለባና ከሰጋቱራ ውጭ ማገዶውን ለማምረት የምትጠቀሙት ቆሻሻ አለ?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ለጊዜው የምንጠቀመው ሁለቱን ነው፡፡ ግን ከሁለትና ከሦስት ወራት በኋላ ተጨማሪ ቆሻሻዎችን በጥሬ ዕቃነት ለመጠቀም አቅደናል፡፡ ማስፋፊያ ቦታ ጠይቀን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፋብሪካው በምን ያህል ካፒታል ተመሠረተ? ምን ያህል ሠራተኞችስ አሉት? ፋብሪካው አሁን ባለበት ቦታ እንዲገነባ የተመረጠው ለምንድነው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ፋብሪካው ሲገነባ ስድስት ሚሊዮን ብር ገደማ ወጥቶበት ነበር፡፡ አሁን ሰባት ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ወደ ሲዳማ የሄድኩበት ዋናው ምክንያት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ስላለ ነው፡፡ በቆሻሻ መልክ የሚጣለው የቡና ገለባ አካባቢውን እየበከለ ነበር፡፡ ይህንን ቆሻሻ ወደ ኢነርጂ ለመቀየር በማሰብ ነው ወደዚያ የሄድነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ 40 ያህል ሠራተኞችን አሉን፡፡ አዲሱ ማሽን ሲመጣ ደግሞ ተጨማሪ ሠራተኞች ይኖሩናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምርቶቻችሁን ለማን ነው የምታቀርቡት?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ምርታችን የድንጋይ ከሰልንና ፈርነስ ኦይልን ተክቶ ለማድረቂያነት ስለሚያገለግል በአሁኑ ጊዜ በቋሚነት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እናቀርባለን፡፡ የካሎሪ መጠኑ ከ3,800 በላይ ነው፡፡ ማዕድን ሚኒስቴር ማረጋገጫውን ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ ከድንጋይ ከሰል ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ይህንን ቢጠቀሙ ከዋጋም አንፃር ከአካባቢ ብከለትም አንፃር ተመራጭ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ “KFW” ከሚባል የጀርመን ድርጅት ጋር የካርቦን ፋይናንስ የምናገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የካርቦን ፋይናንስ ምንድነው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ካርቦን የሚለቁ አገሮች የሚከፍሉት ክፍያ ነው፡፡ ይህ ክፍያ ካርቦንን ለሚቀንሱ ድርጅቶች የሚሰጥ ነው፡፡ ህንድና ቻይና በዚህ ይጠቀማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ነው ያለው፡፡ ይህ ሰው ወላይታ ውስጥ ዛፎችን በብዛት በመትከሉ ነው የክፍያው ተጠቃሚ የሆነው፡፡ እኛም በዚህ ረገድ የካርቦን ፋይናንስ ለማግኘት እየጣርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በወር ምን ያህል ብርኩዌት ታመርታላችሁ?

አቶ ዘሩባቤል
፡- በወር 500 ቶን ብርኩዌት የማምረት አቅም አለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን 250 ቶን ገደማ ነው የምናመርተው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥሬ ዕቃውን የምታገኙት በግዢ ነው? እጥረትስ አያጋጥምም?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ቆሻሻውን የምንጠቀመው እየገዛን ነው፡፡ የቡና ገለባውን ገበሬዎቹ ሰብስበው አድርቀው ያመጡልናል፡፡ አንዱን ኩንታል በመቶ ብር ነው የምንገዛቸው፡፡ ስለዚህ በሥራው ሁላችንም ተጠቃሚዎች ነን፡፡ በአሁኑ ጊዜ የገነባነው ማሽን አንድ ነገር ብቻ ተጠቅሞ ነው ብርኩዌት የሚያመርተው፡፡ ከአሥር በላይ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም ብርኩዌት ማምረት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የእርሻ ተረፈ ምርቶችን መጠቀም ይቻላል፡፡ ስንዴ ታጭዶ የተረፈውን ገለባ መጠቀም ይችላል፡፡ ቆረቆንዳ መጠቀም ይቻላል፡፡ የበቆሎ አገዳም እንደ ጥሬ ዕቃነት ይውላል፡፡ ፋብሪካውን የተከልንበት ቦታ ከፍተኛ የቡና ምርት ያለው በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ ለፋብሪካችን የሚውል ጥሬ ዕቃ የማግኘት ችግር የለብንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእንጨት ፍቅፋቂን (ሰጋቱራ) በጥሬ ዕቃነት ስለምንጠቀም ብዙም ችግር አልገጠመንም፡፡

ሪፖርተር፡- ምርቱን የምታቀርቡበትን ገበያ ለማስፋፋት አላቀዳችሁም?

አቶ ዘሩባቤል
፡- እስካሁን እያደረግን የነበረው ባለን ምርት ገበያ መፈለግ ነው፡፡ እስካሁን ሦስት ትላልቅ ፋብሪካዎች ምርቶቻችንን ይወስዳሉ፡፡ አሁን ደግሞ ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለትምህርት ቤቶችና ለተለያዩ ተቋማት ምርቶቻችን ለማቅረብ አቅደናል፡፡ አዲሱ ማሽን ሲመጣ ማንኛውም ሰው ምርታችንን ቤቱ ውስጥ የሚጠቀምበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ወደ ውጭም የምንልክበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት አለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሥራውን ሲጀምሩ የገጠሙዎት ችግሮች ነበሩ?

አቶ ዘሩባቤል
፡- መጀመርያ ላይ ሐሳቡም አዲስ ስለነበር ከቦታ ማግኘት ጀምሮ ሥራውን ለማስፈጸም ትንሽ ይከብድ ነበር፡፡ አሁን ግን የአካባቢው ኃላፊዎች ጥሩ ድጋፍ እያደረጉልን ነው፡፡ ተጨማሪ ማስፋፊያ ስንጠይቅ በደስታ ነው የተቀበሉት፡፡

ሪፖርተር፡- ወደፊት ያለዎት ዕቅድ ምንድነው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ለጊዜው ያለን ዕቅድ ፋብሪካውን ማስፋፋት ነው፡፡ ምርቱ ሰፊ ገበያ አለው፡፡ ወደሱዳን ለመውሰድ ፍላጎት ያሳዩ ወገኖችም አሉ፡፡ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያና ሱዳን የመሳሰሉት አገሮች ምርታችንን ይፈልጉታል፡፡ ከእነዚህ አገሮች በቅርቡ የመጡ ሰዎች ለመፈራረም ፈልገው ነበር፡፡ ነገር ግን ምርቱን ማምረት ከጀመርን በኋላ ከእነሱ ጋር መነጋገሩ ይሻላል ብለን መፈራረሙን አቆይተነዋል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ልዩ ምድጃውን ማግኘት ከቻልን የምርታችንን ገበያ ማስፋፋት እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ትርፋማነቱስ እንዴት ነው?

አቶ ዘሩባቤል
፡- ትርፋማነቱ ትንሽ ትግል አለው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ትርፍ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከካርቦን ልቀት ጋር በተያያዘ ምን መሠራት አለበት ብለው ያስባሉ?

አቶ ዘሩባቤል
፡- እንደዚህ ዓይነት ፋብሪካ የሚገነቡና የካርቦን ልቀትን በመቀነስ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ፋብሪካዎች ቢበረታቱ ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን እኛ ተቀባይነት ብናገኝ በቶን ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ዩሮ እናገኛለን፡፡ የካርቦን ልቀትን ከመቀነስ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪም ያስገኛል፡፡ ብዙ መጠቀም የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ ከህንድና ከቻይና በተጨማሪ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮችም የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ዕድል መጠቀም ስላለባት እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን መንግሥት ቢያበረታታ ጥሩ ነው፡፡