አይኤፍሲ የዓለም ባንክ ግሩፕና በታዳጊ አገሮች ለሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት የብድር አገልግሎት የሚያቀርብ ተቋም ነው፡፡
በኢትዮጵያም አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት ግን ከ85 ሚሊዮን ዶላር በላይ አይዘልም፡፡ ይህም ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡ ሚስተር አዳሙ ላባራ በኢትዮጵያ የአይኤፍሲ ተጠሪ ናቸው፡፡ ተቋሙ የሚሰጠውን የፋይናንስ አልግሎት በተመለከተ ኃያል ዓለማየሁ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በመጀመርያ የአይኤፍሲ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ አሠራርና ዓላማውን ቢያብራሩልን?
ሚስተር አዳሙ፡- የተቋሙ ዋነኛ ዓላማ የግሉን ዘርፍ ማሳደግ ነው፡፡ ለዚህም አይኤፍሲ ኢትዮጵያ በሦስት ዋነኛ ምሶሶዎች ላይ የተመሠረተ ስልት ነድፏል፡፡ የመጀመርያው ምሶሶ በአገሪቱ ያለው የንግደና የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለግሉ ዘርፍ የተመቻቸ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ከመንግሥትና ከተለያዩ ሕዝባዊ ተቋማት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ስኬት ልንናገር የምንችለው የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ የጋራ መወያያ መድረክ ለማጠናከር እየሰጠን ያለውን የፋይናንስና የባለሙያ አገልግሎት ነው፡፡ በአገሪቱ ያለው የንግድና የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለግሉ ዘርፍ የበለጠ ምቹ እንዲሆን የሚያደርጉ አሠራሮችን ለመዘርጋት ከመንግሥት ጋር የምናደርጋቸውን ስምምነቶች በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን፡፡ ሁለተኛው አይኤፍሲ በተለያዩ ታዳጊ አገሮች ለዘመናት ሲተገብረው የቆየው አገልግሎት ሲሆን፣ ይህም በግሉ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ነው፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ የሰጠነው የፋይናንስ አገልግሎት 85 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ለሌሎች ታዳጊ አገሮች ከምንሰጠው፣ ከአገሪቱ ኢኮኖሚና እንዲሁም ከእኛም አቅም ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው፡፡
የአገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት አቅም ግምት ውስጥ ካስገባን በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የሰጠነውን የፋይናንስ አገልግሎት አሥር እጥፍ በአንድ ዓመት ውስጥ ማቅረብ እንችላለን፡፡ አሁን አገልግሎት ከምንሰጣቸው ጥቂት ኩባንያዎች በተጨማሪ ለአብዛኛዎቹ የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ ፍላጎት አለን፡፡ ፋይናንስ ያደረግናቸው ጥቂት ፕሮጀክቶች ከማዕድን ሲሚንቶና ወርቅ፤ ከእርሻ የቡና ምርት ሲሆን፣ ለአክሰስ ሊዝ ኩባንያም መጠነኛ የፋይናንስ አገልግሎት አቅርበናል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ለአነስተኛና ለመካከለኛ የንግድ ድርጅቶች ከምንሰጠው አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ዘርፍ ለእኛም ሆነ ለመንግሥት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በጣም ጠቃሚ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡ ለዚሁ ዘርፍ የፋይናንስ፣ የባለሙያና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- ለየትኞቹ ዘርፎች ቅድሚያ ትሰጣላችሁ?
ሚስተር አዳሙ፡- ለእርሻ፣ ለሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በወጪ ንግድ ላይ ለሚያተኩሩት፡፡
ሪፖርተር፡- የምትሰጡት የፋይናንስ አገልግሎት የብድር ነው ወይስ ብድር ከባንክ ማግኘት የሚያስችል የዋስትና አገልግሎት?
ሚስተር አዳሙ፡- እንደ ሁኔታው ነው፡፡ ሦስት ዓይነት የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንሰጣለን፡፡ አንደኛው የረዥም ጊዜ ቢያንስ የአምስት ዓመት ብድር አገልግሎት ነው፡፡ የብድር አገልግሎት ለምንሰጠው ድርጅት ባለአክሲዮን የምንሆንበትም አሠራር አለን፡፡ የአንድ ድርጅት ባለአክሲዮን በምንሆንበት ጊዜ የምንሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት የንብረት (Equity) ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባንክ ብድር ለማግኘት የሚያስችል ዋስትናም እንሰጣለን፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች የምንሰጠው የድርጅቶችን ወይም የፕሮጀክቶችን አሠራርና ገበያ በደንብ ካጠናንና ከመረመርን በኋላ ነው፡፡ ድርጅቶቹንም በምንገመግምበት ወቅት የድርጅቶችን ብቃት ለማጎልበት የምክርና የቴክኒክ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ድርጅት የእናንተን አገልግሎት ለማግኘት ማሟላት የሚጠበቅበትን መስፈርቶች ቢገለጹልን?
ሚስተር አዳሙ፡- በመጀመርያ ድርጅቱ የግል መሆን አለበት፡፡ ይህም ማለት ከ51 በመቶ በላይ የድርጅቱ ባቤትነት በግል የተያዘ ወይም ሙሉ በሙሉ የግል መሆን አለበት፡፡ ድርጅቱም በመስፋፋትና በትርፍ ላይ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዝርዝር የንግድ ዕቅድ ማዘጋጀትም ግዴታው ነው፡፡ የድርጅቱ ፕሮጀክት በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ የማይፈጥር መሆን ያለበት ሲሆን፣ ለዚህም አስፈላጊውን የቴክኒክና የሙያ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ፕሮጀክቱ ነዋሪዎችን የሚያፈናቅል ወይም ተመሳሳይ እክሎች ካሉበት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በጥቅሉ ለአንድ ድርጅት የፋይናንስ አገልግሎት የምናቀርበው ፕሮጀክቱ ዓለም ዓቀፍ የንግድና የኢንቨስትመንት አሠራር መመዘኛዎችን ሲያሟላ ነው፡፡ የሠራተኞች አያያዝና ፕሮጀክቱ በኅብረተሰቡ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ፣ እንዲሁም የድርጅቱ የምርት ጥራት ከግምት ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡ ስማችን ከፕሮጀክቱ ጀርባ ስለሚውል የፋይናንስ አገልግሎት ከመስጠታችን በፊት እነዚህ ሁሉ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መሟላታቸውን እናረጋግጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል እንደገለጹት አይኤፍሲ ለሁለት ዓመት ተኩል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣ ተጠቃሚ የሆኑት ጥቂት ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ተቋሙ የሰጠውም የፋይናንስ አገልግሎት አናሳ ነው፡፡ ድጋፍ ወይም ብድር ማግኘት አንደኛው ፈተና በሆነበት አገር ውስጥ ተጠቃሚውና የተሰጠው ብድር አነስተኛ የሆነው ለምንድነው?
አቶ አዳሙ፡- እንደማየው ከሆነ የግሉ ዘርፍ ብዙ ዕድሎች አሉት፡፡ በአሁኑ ጊዜም በተሻለ ሁኔታ በመንቀሳቀስም ላይ የሚገኝ ይመስለኛል፡፡ [ያ እንዳለ ሆኖ] ብዙዎቹ ግን በደንብ የሚያውቁን አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ወደኛ የሚመጡት ጥቂት ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ አይኤፍሲ የዓለም ባንክ ግሩፕ አባል ነው ሲባል የሚሰጠውን አገልግሎት ለማግኘት የማይቻል ዓይነት እንደማይመስላቸው ሰምተናል፡፡ ነገር ግን በእርግጥ ለመናገር ለሁሉም በራችን ክፍት ነው፡፡ ፕሮጀክት ያላቸው ወደኛ ቢመጡ በፕሮጀክቶቹ ላይ በመምከር የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት እንችላለን፡፡ ካልሆነም ወደ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ልንመራቸውም እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ችግሩ የግንዛቤ ችግር ብቻ ነው?
አቶ አዳሙ፡- ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን አንዳንድ ግንዛቤው ያላቸውም ከአይኤፍሲ የፋይናንስ አገልግሎት ለማግኘት ያለው ቢሮክራሲ ተስፋ የሚያስቆርጥና የተቋሙም የሥራ ቋንቋ (ኮድ) አስቸጋሪ እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ስለዚህስ ምን ይላሉ?
አቶ አዳሙ፡- ያ የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ ሲጀመር እኛ አገልግሎታችንን ለማግኘት የሚመጡትንና የመጡትን ደንበኞች ሳይሆን አጋር ብለን ነው የምንጠራቸው፡፡ የምናያቸውም እንደዚያ ነው፡፡ የአምስት ዓመት ብድር ወይም የብድር ዋስትና ስትሰጥ በእርግጥም ፕሮጀክቱን በሚገባ ማጤን አለብህ፡፡ ይህም የተወሰነ ጊዜ መውሰዱ የማይቀር ነው፡፡ ጊዜ ብቻም ሳይሆን በደንብ የተጠና የቢዝነስ ዕቅድም አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህም ብድሩን ለማግኘት የሚጠየቁት መስፈርቶች ይመስሉኛል ከተቋሙ የፋይናንስ አገልግሎት ለማግኘት ብዙ ነገር እንደሚጠየቅ፣ ወይም ብድሩን ለማግኘት ከባድ እንደሆነ የሚያመለክት አመለካከት በአገልግሎት ፈላጊዎች ላይ እንዲቀረፅ የሚያደርጉት፡፡ የምንሰጠው ብድር የስድስት ወር ወይም የዓመት ባለመሆኑ መስፈርቶቹን ማሟላታቸውን ማረጋገጥ፣ ማጤንና መገምገም የግድ ይላል፡፡ እንደሁኔታው ለተወሰኑ ፕሮጀክቶችም የአሥር ዓመት የብድር ወይም የብድር ዋስትና የምንሰጥበት ሁኔታም አለ፡፡ የሥራ ቋንቋን በተመለከተ ደግሞ በበርካታ አገሮች ለሚሠራ እንደ አይኤፍሲ ያለ ተቋም ወጥ የሆነ የሥራ ቋንቋ መጠቀሙ ስራውን ከማፋጠን አንፃር የግድ የሚል ነው፡፡ የሥራ ቋንቋው ግን ሁልጊዜ ለተጠቃሚዎች ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ለዚህም ነው በዋነኝነት ከምናገለግላቸው አነስተኛና መካከኛ የንግድ ድርጅቶች ይልቅ ከባንኮች ጋር የምንሠራበት አጋጣሚ የሚበዛው፡፡ በየአገሩ ያሉ ባንኮች ደግሞ ከድርጅቶቹ ጋር በቀላሉ ይግባባሉ፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ያሉ የንግድ ድርጅቶች የእናንተን አገልግሎት ለማግኘት ያሉባቸው ዋነኛ ድክመቶች ምንድን ናቸው?
ሚስተር አዳሙ፡- እንደሚመስለኝ ዋነኛው ድክመት ግልጽና ተጨባጭ የሆነ የንግድ ዕቅድ ማውጣት አለመቻል ነው፡፡ አንዳንዴ ጥሩ የንግድ ሐሳብ ያላቸውና የእኛንም አገልግሎት የሚያገኙ ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ያንን ጥሩ አዋጭ ሐሳብ በዕቅድ ለማስፈር ወይም ወደ ቢዝነስ ዕቅድ መለወጥ ትልቁ ራስ ምታት ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- እንዳሉት ጥሩ የሆነ የቢዝነስ ሐሳብ ያላቸው ሆኖም ያን ሐሳብ ወደ ዕቅድ ለመቀየር ወይም በግልጽ በዕቅድ ለማስቀመጥ የሚቸገሩትን ልትረዱ የምትችሉበት አሠራርስ የለም?
ሚስተር አዳሙ፡- ያን አሠራር ለመዘርጋት ጥናት እያካሄድን ነው፡፡ ይህንንም በየዘርፉ የምናይበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህን ዘርፎች ወይም ንዑስ ዘርፎች በሚገባ መለየት ከተቻለ የብድር አገልግሎቱን ማመቻቸት ይቻላል፡፡ ትላልቆቹ ኩባንያዎች በቢዝነስ ዕቅድ የሚመሩ ስለሆነም ይህ የሚያስፈልገው ለአነስተኛና ለመካከለኛ የንግድ ፕሮጀክቶች ነው፡፡ በመሆኑም ለጊዜው መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጠውና የታዳሽ የኃይል ምርቶችን በማምረት ዘርፍ ለተሰማሩ ከአገር ውስጥ ባንኮች ብድር የሚያገኙበትን ዋስትና ለመስጠት ፍላጎት አለን፡፡
ሪፖርተር፡- የፋይናንስ አገልግሎት ከሰጣችኋቸው ጥቂት ድርጅቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ የውጭ አገር ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ለውጭ አገር ኩባንያዎችም የፋይናንስ አገልግሎት ታቀርባላችሁ ማለት ነው?
ሚስተር አዳሙ፡- በትክክል፡፡ ኩባንያው እዚህ አገር የተመዘገበና የሚያካሂደው ኢንቨስትመንት እዚህ ከሆነ የአገልግሎታችን ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- አይኤፍሲ ኢትዮጵያ እስካሁን የሰጠው የ85 ማሊዮን ዶላር የፋይናንስ አገልግሎት ከሌሎች አገሮች ተሞክሮው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ በሚሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት የተጠቃሚው ቁጠር እየጨመረ የሚሄድበት ሁኔታ ቢኖር የብድሩ አገልግሎት እስከ ምን ያህል ከፍ ሊል ይችላል?
ሚስተር አዳሙ፡- አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ወይም አራት መቶ ሚሊዮን ዶላር (በዓመት) ልናቀርብ እንችላለን፡ በእርግጥ ይህ የሚወሰነው ባለው ፍላጎት መጠን ነው፡፡ ፍላጎቱ ከጨመረ በዚያው መጠን የአገልግሎቱን መጠን ከፍ ማድረግ እንችላለን፡፡ በሁለት ዓመት ተኩል የሰጠነውን የ85 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ አገልግሎት አሥር እጥፍ በአንድ ዓመት እስከ 850 ሚሊዮን ዶላር ማበደር እንችላለን፡፡ ገደብ ሊኖርብን የሚችለው በዓመት የምንሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ከበለጠ ነው፡፡ ያኔ ለተወሰኑ ዘርፎች ወይም ፕሮጀክቶች ብቻ ቅድሚያ ለመስጠት ልንገደድ እንችላለን፡፡ ለዜው ግን ገደብ የለብንም፡፡
ሪፖርተር፡- የምትሰጡት የፋይናንስ አገልግሎት መጠንስ መጨመር እያሳየ ነው? ወይስ አሁንም አናሳ ነው?
ሚስተር አዳሙ፡- አሁን ከፍ እያለ ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች አገልግሎታችንን ለማግኘት እየሞከሩ ነው፡፡ ትንበያችን እንደሚያመለክተው በሁለት ዓመት ተኩል የሰጠነው የ85 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ አገልግሎት በዚህ ዓመት ብቻ እንደምናቀርብ ነው፡፡ ከድርጅቶች ውጪም ለማኅበራት የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ እየሞከርን ነው፡፡ ይህም ብዙዎች እንዲመጡ እንደሚያደርግ እምነታችን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለአንድ ፕሮጀክት የምትሰጡትስ የፋይናንስ ወይም የብድር አገልግሎት መጠን የፕሮጀክቱን ወጪ ምን ያህል የሚሸፍን ነው?
ሚስተር አዳሙ፡- እኛ የምንሰጠው የብድር አገልግሎት የፕሮጀክቱን 30 ወይም 35 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ወጪ 30 በመቶ ከፕሮጀክቱ አቅራቢ የሚጠበቅ ሲሆን ቀሪውን በሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በኩል የምናሟላው ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአንድ ፕሮጀክት የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት በአማካይ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?
ሚስተር አዳሙ፡- አንድ ድርጅት አንድ ፕሮጀክት ይዞ ወደኛ ሲመጣ ስለ ፕሮጀክቱ በድፍኑ እንወያያለን፡፡ ፕሮጀክቱ እኛ ትኩረት ከምንሰጥባቸው ዘርፎች አንዱ ከሆነ ድርጅቱ ዝርዝርና ግልጽ የሆነ የአዋጪነት የንግድ ዕቅዱን እንዲያቀርብ እንጠይቃለን፡፡ የንግድ ዕቅዱን ካየን በኋላ ፕሮጀክቱን በእርግጥም እኛ ፋይናንስ ለማድረግ የምንፈልገው ፕሮጀክት ዓይነት ከሆነ፣ ምን ምን ነገሮችን በዝርዝር እንደምናይና የፕሮጀክቱም ባለቤት ብድሩን መቼ ማግኘት እንደሚፈልግ የሚገልጽ የመጀመርያ የመግባቢያ ሰነድ ከባለቤቱ ጋር እንፈራረማለን፡፡ የመጀመርያው የመግባቢያ ሰነድ (Mandate Letter) የሚፈረምበትና ብድሩም ወይም የብድር ዋስትናው የሚለቀቅበት ጊዜ በአማካይ አራት ወራት ይወስዳል፡፡ ለምንሰጠው የፋይናንስ አገልግሎትም እንደ ማስያዣ (Collateral) የምንወስደው ፕሮጀክቱን እንጂ ቤትና ሌሎች ንብረቶች የሚያዙበት ሁኔታ አይኖርም፡፡


