በደነቀ ፀጋዬ አባይሬ
ንጉሥ በዙፋኑ ብቻ ሳይሆን በክብሩ፣ በዝናው፣ በፀጋውና በግርማ ሞገሱ ከፈጣሪ አምላክ በታች ያለ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ ንግሥና በቀላሉ የሚገኝና የሚቀመጡበት አይደለም፡፡ ንጉሥ ልዕለ ሕዝብ ነው፡፡ በምድር ላይ ካለው ሰዋዊ ክብር፣ ሥልጣን፣ ሞገስና ዝና በሙሉ ቀደምትነትን ይይዛል፡፡ ከንጉሥ በላይ አንድም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ንጉሥ ከሉዓላዊነቱ የተነሳ ‹‹ንጉሥ አይከሰስም፣ ሰማይ አይታረስም›› ተብሎለታል፡፡ በዚህም መሠረት ይመስላል የንጉሥ ክብርና ፀጋ በቀላሉ የማይደፈር፣ የማይገሰስና ግርማ ሞገስን ተጎናጽፎ የሚኖረው፡፡ ንጉሥን የቅርብ ቤተሰቡ ካልሆነ በስተቀር ውስጠ ገመናውን ማንም ቢሆን ጠንቅቆ ሊያውቀው አይችልም፡፡ አንዲት የንጉሥ ባለሟል አንድ ቀን በንጉሡ ክፍል ውስጥ መደበኛ ባለሟልነቷ የሚጠይቀውን አገልግሎት ለመስጠት ቀና ጎንበስ በማለት ለንጉሡ የሚገባውን ታላቅ ክብርና የእጅ መንሳት ሥነ ሥርዓት ከፈጸመች በኋላ፣ ወደ ንጉሡ ክፍል ትዘልቃለች፡፡ በንጉሡ ክፍል ውስጥም ገብታ ተገቢውን ሥራ ሠራርታ ልትወጣ ስትል፣ ንጉሡ የልጅቷ ውበትና ቁንጅና ያማልለዋል፡፡ በዚህም ውበትና ቁንጅና የተረታው ንጉሥ ባለሟሊቱን ድንገት ሳያስበው እጇን አፈፍ ወገቧን እቅፍ ካደረገ በኋላ ከንፈሯን ከከንፈሩ በማዋሃድ ምጥጥ አድርጎ ስሞ ይለቃታል፡፡ ባለሟሊቱም ከዚያን በፊት ባለው የዕድሜ ዘመኗ ውስጥ ንጉሥ እንዲህ ያለ ነገር ይሠራል ብላ አስባ ስለማታውቅ፣ ነገሩ ይገርማትና ‹‹እንዴ! ንጉሥም ይስማል እንዴ?›› ብላ ባለችበት ፈዛ ቀረች ይባላል፡፡ይህ አባባል አባባል ሆነ እንጂ እንዳሁኑ የዓለማችንና የአገራችን ሕግ ቢሆን ኖሮ ‹‹እንዴ! ንጉሥም ይስማል እንዴ?›› ተብሎ የሚታለፍበት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ታላላቆቹ የዓለም ሰዎች ማለትም እንደ ዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት፣ እንደ የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ወዘተ ‹‹ደፍሯል›› ወይም ‹‹የመድፈር ሙከራ አድርጓል›› ተብሎ የሕግ ተጠያቂነት ሊኖርበት በቻለ ነበር፡፡ ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን እኔም አንዳንድ ነገሮችን ረጋ ብዬ ስመለከት ልክ እንደ ንጉሡ ባለሟሊት ፈዝዤ እየቀረሁ ነው ብል ማጋነን አይደለም፡፡ ከወርኅ ጥቅምት 2004 ዓ.ም. መጀመርያ ጀምሮ ሊዝ የሚለውን ጉዳይ በብዙ አቅጣጫ ስመለከተው ዝም ብሎ ግራ ይገባኛል፡፡ ከዚህም መሠረታዊ እውነታ ላይ በመነሳት ይመስለኛል፡፡
- እንዴ! ፓርላማም ይሳሳታል እንዴ?
- እንዴ! መንግሥትም ይሳሳታል እንዴ?
- እንዴ! ሚኒስትርም ይሳሳታል እንዴ?
- እንዴ! መስተዳድርም ይሳሳታል እንዴ?
- እንዴ! ሰብሳቢም ይሳሳታል እንዴ? . . . እያልኩ ራሴን መጠያየቅ ጀምሬአለሁ፡፡
የሊዝ አዋጁ መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ሲታወጅ በመንግሥት በኩል አዋጁ መቶ በመቶ ትክክል ነው አንድም ስህተት የለበትም የሚል ዓይነት ድምዳሜ ተደርሶበት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ‹‹አዋጁ ለፓርላማው የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ አልተመራም፡፡ በቂ ውይይት አልተደረገበትም፡፡ ሕዝቡ አልተወያየበትም . . . ወዘተ፣ ወዘተ›› ሲባል ይደመጥ ነበር፡፡ በርካታ ጥቆማዎችና አስተያየቶችም በስፋት ይሰነዘሩ ነበር፡፡ መንግሥት ግን ይህንን ሁሉ እውነታ በምንም ዓይነት መንገድ ሊቀበለውና ሊያስተውለው አልቻለም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ከሁለትና ከሦስት ወራት በኋላ በተለይም ከብዙ ውዝግብና ንትርክ በኋላ ማለት ይቻላል መንግሥት ‹‹አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ሊደረግበት ይገባ ነበር፤ ይህም ባለመደረጉ ትንሽ ክፍተት አለ፤›› እያለ በተለያዩ መድረኮች ላይ እያመነ መምጣት ጀምሯል፡፡ ለመሆኑ ሕዝቡ አስቀድሞ ቢወያይበትስ ኖሮ አዋጁ ምን ሊሆን ይችል ነበር?
ይህን ጉዳይ አሁንም በአግባቡ ማየትና ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ‹‹መንግሥት ሕዝቡን ማወያየት ነበረብኝ፤ ባለማወያየቴ ትንሽ ክፍተት አለ፤›› ብሎ ማመኑ በራሱ እጅግ በጣም ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ ትልቅ ቁምነገርም ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥትንም የሚያግባባና የሚያቀራርብ ጉዳይ ነው፡፡ መግባባት ካለ ደግሞ ሁሉም ነገር ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን አንጂ መንግሥት ስለሊዝ አዋጁ ኅብረተሰቡን አስቀድሞ ቢያወያይ ኖሮ አዋጁ ይፀድቅ ነበር ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም በበሰለ ውይይት ሊሻር ወይም ሊሻሻል ይችል ነበር፡፡ የዚህ ዓይነት ውዝግብና ክርክርም አይፈጠርም ነበር፡፡ በአጠቃላይ አገላለጽ መንግሥት ‹‹ትንሽ ክፍተት ነበር›› ብሎ ካመነ የዚህ ትንሽ ክፍተት ቀጥተኛ ትርጓሜ አዋጁ ትክክል አልነበረም፤ ሕዝብ ያልመከረበት አዋጅ ነው፡፡ ስለዚህም አዋጁ ስህተት ነበር ማለት ነው፡፡ መንግሥት የአዋጁ አፀዳደቅ ላይ ‹‹ትንሽ ክፍተት ነበረው›› ሲል አዋጁን በውይይት ላሻሽለው ይገባል ማለቱ ነው፡፡ ምክንያቱም አዋጁ መላው ኅብረተሰብ ሳይወያይበት የፀደቀ ስለሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት አዋጁ በሥራ ላይ ሊውል አይገባውም፡፡ ምክንያቱም አሁንም መላው ኅብረተሰብ እየተወያየበት አንጂ እያፀደቀው ስላልሆነ ማለት ነው፡፡
በቀጥተኛው አገላላጽ አዋጁ የመላው ኅብረተሰብ ውይይት ሳይደረግበት መፅደቁና ‹‹ክፍተት ነበረው›› መባሉ አዋጁ ስህተት ነው ሲባል ነው፡፡ ስህተት ነው ማለት ደግሞ ስህተቱ የግድ መታረም ወይም መስተካከል አለበት ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት አዋጁ በቀጥታ ሥራ ላይ ቢውል መልሶ ሌላ ስህተት መፍጠር ይሆናል ማለት ነው፡፡ መንግሥት አገርንና ሕዝብን ያለምንም ስህተት የመምራት ከፍተኛ ኃላፊነትም እንዳለበት በአግባቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ መንግሥት ማለት የተባበረ የሕዝብ ውክልና ማለት ነው፡፡ መንግሥት እንደሰው ሊሳሳት ይችላል፡፡ ስህተትን ማረምና መቀበል ደግሞ ትልቁ ብልህነት ነው፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥትነት አዋጁን ‹‹ትንሽ ክፍተት ነበረው›› ብሎ መቀበሉ እጅግ በጣም ተገቢ ነው፡፡ ሊለመድም ይገባል፡፡ ምክንያቱም የስህተት ትንሽ የለውምና ማለት ነው፡፡ ‹‹ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ›› የሚባለውም አባባል ይህንን እውነታ ግልጽ አድርጎ ሊያሳይ ይችላል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገሪቱ የፓርላማ አባላት የሁለት ወር እረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀው ገና ወደ ፓርላማ ሥራቸው እንደተመለሱ፣ በመጀመርያው ሳምንት አዋጁን በጥልቀት ሳይመረምሩትና ሳያብላሉት ማፅደቃቸው ለክፍተቱ ትልቅ መነሻ ይመስለኛል፡፡
በመጀመርያ ደረጃ አንድ አዋጅ ከመታወጁ በፊት በብዙ አቅጣጫ ሊታይና ሊጤን ይገባዋል፡፡ አዋጅ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ መላውን ኅብረተሰብ የሚመለከት አዋጅ በመላው ኅብረተሰብ ሊመከርበት ይገባል፡፡ አዋጅ ሁሉ አንድ ዓይነት ይዘት የለውም፡፡ አንዳንድ አዋጆች የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን ብቻ የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መላውን ኅብረተሰብ በቀጥታ ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን ብንመለከት የሚመለከተው አሠሪና ሠራተኛውን ክፍል ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ የመሬት ሊዝ አዋጅ ግን መላውን ኅብረተሰብ የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ አዋጅ ከመታወጁ በፊት ግራና ቀኙ ኋላና ፊቱ በብዙ አቅጣጫ ሊታይና ሊጤን ይገባዋል፡፡ ለዚህ እውነታ አንዳንድ የሙያ ዘርፎችን አባባሎች እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ ጤና ባለሙያ፣ ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ››፤ እንደ ፍትሕ አካል፣ ‹‹ሰርቆ ከማሰብ እጅን መሰብሰብ››፤ እንደ ምህንድስናና ግንባታ ባለሙያ ደግሞ ‹‹አሥር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ›› የሚሉትን አባባሎች ማለት ነው፡፡ የእነዚህ ሙያዎች አባባሎች ዋነኛ ዓላማ በሙያው ረገድ ስህተት እንዳይፈጸም ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ ነው፡፡ ይህም ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራርን መከተል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ታዲያ መንግሥት ከሁሉም በበለጠ ሁሉንም ወገን ባቀፈና ባማከለ ሁኔታ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ሊሠራ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ምንም ዓይነት ስህተት ሊሳሳት አይገባውም፡፡ በዚህ የሊዝ አዋጅ ዙርያ አሁንም አንዳንድ ጭብጥ ነገሮችን እያነሱ በምሳሌነት መመልከት ይገባል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የሊዝ አዋጁ በምንም ዓይነት መንገድ ሕገ መንግሥቱን የሚጋፋ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 7ን እንመልከት፡-
- ንብረት የማፍራት፣
- ንብረት የመሸጥ፣
- ንብረት የማውረስ፣
- ንብረት የመለወጥ፣
- ንብረት የማስተላለፍ ሙሉ መብት ለዜጎች እንደተሰጠ በግልጽ ይደነግጋል፡፡ እነዚህ መብቶች እኩል የሆነ ዋጋና ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናም አላቸው፡፡
ይሁን እንጂ አዲሱ የሊዝ አዋጅ አንቀጽ 6/3ን ብቻ ብንመለከት እነዚህን እኩል ዋጋ ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን በግልጽ ሲሽራቸው ይታያል፡፡ ለምሳሌ የአዋጁ አንቀጽ 6/3 ‹‹በነባር ይዞታ ላይ የሠፈረ ንብረት ባለቤትነት ከውርስ በስተቀር በማናቸውም መንገድ ለሌላ ሰው ከተላለፈ ንብረቱ የተላለፈለት ሰው የቦታው ባለይዞታ ሊሆን የሚችለው በሊዝ ሥሪት መሠረት ይሆናል፤›› ይላል፡፡ ለምን? ይህ ጉዳይ በአግባቡ መታየት አለበት፡፡ ‹‹ንብረት ማፍራት፣ ንብረት መሸጥ፣ ንብረት ማውረስ፣ ንብረት መለወጥና ንብረት ማስተላለፍ›› የሚባሉት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እኩል የሆነ ሕገ መንግሥታዊ ዋጋና ዋስትና አላቸው፡፡ ይህም በአግባቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከዚህም ሌላ የሊዙ አዋጅ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 9/1 ማለትም ‹‹ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፤›› የሚለውን በግልጽ በመተላለፍ፣ እነዚህ እኩል ዋጋ ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን በመሻር ‹‹ማውረስ›› የሚለውን መብት ብቻ ለይቶ ያስቀራል፡፡ ለምን?
ለመሆኑ ሌሎቹ መብቶች ተሸረው ‹‹ውርስ›› የሚለው መብት ብቻስ ለምን ሳይሻር ቀረ ይሆን? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እጅግ በጣም ቀላል ሊሆን ይቻላል፡፡ ግን ግን ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የሰጠውን መብት የሊዙ አዋጅ ሊሽረው እንደማይችል በግልጽ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ስለሆነ ማለት ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ማንኛውም ወገን በአግባቡ ሊያስተውለውና ሊረዳው የሚገባ አንድ ዓብይ ነጥብ አለ፡፡ ይህም ዓብይ ነጥብ የሕዝባችን የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የሕዝባችን የአኗኗር ዘይቤ በሦስት ዋና የኅብረተሰብ ክፍል (ካታጎሪ) የተከፈለ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከመሬታቸው ያለመነቀል ወይም ያለመፈናቀል ሙሉ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 በግልጽ ተደንግጓል፡፡ መሆንም አለበት፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት በግልጽ ያልተቀመጠው አንቀጽ ግን ‹‹የከተማ ነዋሪ›› የሚለው ነው፡፡ ‹‹የከተማ ይዞታ ወይም የከተማ ነዋሪን›› የሚመለከት በአንቀጽ 40 በየትኛውም ንዑስ አንቀጽ ሥር በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40/6ም ቢሆን የግል ባለሀብቶች (ኢንቨስተሮች) በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ይደነግጋል እንጂ ለግል መኖርያ ቤት የሚል የለም፡፡ መሬት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚባሉት ደግሞ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና የከተማ ነዋሪው በአንድ ላይ ተጣምረው ነው፡፡ ይህም በአግባቡ የታየ አይመሰለኝም፡፡ መሬት የሁሉም ሕዝቦች መሆኑ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ከሚባሉት አንዱ መኖርያ ነው፡፡ ቤትና መሬት ደግሞ እጅግ በጣም የተቆራኘ የተፈጥሮ መስተጋብር እንዳላቸው በአግባቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ቤትና መሬት በምንም ዓይነት መልኩ ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡ የሰው ልጅ በዋሻ ውስጥ በኖረበት ዘመንም ቢሆን መሬትን ለመጠቀም የግድ ተገዷል፡፡ ቤትና መሬት የአንድ ሳንቲም ገጽታ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ቤቱን ሸጠ ሲባል የቤቱን ጣሪያና ግድግዳ ማቴሪያል ሸጠ ማለት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሬት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብቻውን ተሸጠ የሚባልበት አንድም ዘመን የለም፡፡ በዘመነ ምኒልክ መሬት የከተማና የጠፍ እየተባለ ለሹማምንቱ ብቻ እየተለየ በነፃ ይሰጥ ነበር፡፡ በዘመነ አፄ ኃይለ ሥላሴም ቢሆን የከተማ ቦታ በምሪት ይሰጥ ነበር እንጂ የመሬት ሽያጭ አልነበረም፡፡ በዘመነ ደርግ ደግሞ መሬት የሚባለው ነገር ቀርቶ ቤትም የሚሸጥበት የሕግ አግባብ አልነበረም፡፡ ደርግ ምናልባት መሬትን ለነዋሪዎች በማኅበርና በራስ አገዝ ስም በምሪት ይሰጥ ነበር፡፡ በአሁኑ በዘመነ ኢሕአዴግም ቢሆን መሬት የሚሸጥበት የሕግ አግባብ የለም፡፡
ይሁን እንጂ ባዶ መሬት ከሕግ አገባብ ውጭ መኖርያ ቤት ያለው በማስመሰል መሬትን በሽያጭ መልክ ለገበያ ማዋሉ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ይህንን ግብይት ያከናውኑ የነበሩት ደግሞ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ሆነው ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ነው፡፡ የመሬት ወረራ፣ የመሬት ሽያጭ፣ ሕገወጥ ግንባታ፣ ሕገወጥ ደላላ፣ ወዘተ የሚባሉት ሕገወጥ ክንውኖች ሁሉ የበቀሉት በጥቂት ግለሰቦች አማካይነት እንጂ የመሬት ሽያጭ ሕግ በመኖሩ አልነበረም፡፡ ይህም ሕገወጥ ክንውን ሌብነት መኖሩን እንጂ የመሬት ሽያጭ መኖሩን አያሳይም፡፡ ሌብነትን ደግሞ መንግሥት ጠንክሮ ሊዋጋው ይችል ነበር፡፡ መንግሥት ይህንን ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ዝም ብሎ ሲመለከተው ኖሯል፡፡ ምንም ዓይነት አሠራርና ቁጥጥር አልነበረውም ማለት ይቻላል፡፡ በጥቅል አገላለጽ ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት ለዚህ ዋነኛ ችግር መነሻ ሆነው ከመቆየታቸውም በላይ፣ ከፍተኛ የሥራ አፈጻጸም ድክመትና ቁጥጥር ማነስ ችግርም ነበር፡፡
ለምሳሌ የሪል ስቴት አልሚዎችን የማልማት ፈቃድ አሰጣጥ ማየት ይቻላል፡፡ በአንድ ወቅት ላይ ሁሉም ሰው የሪል ስቴት ፈቃድ አውጭ ነበር፡፡ ለሪል ስቴት አልሚነት ፈቃድ ሲሰጥ እጅህ ከምን አይባልም ነበር፡፡ የሪል ስቴት አልሚው ምን ያህል ካፒታል ይዞ እንደተነሳ ወይም እንደሚነሳ የሚያስረዳ ጭብጥ መረጃ ላይ ትኩረት አይሰጥም ነበር፡፡ በባንክ የሚያዝ ገንዘብም ላይ ትኩረት አይደረግም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ማለት ይቻላል የኋላ ኋላ ሪል ስቴቶች መሬት አጥረው አስቀመጡ፣ የመንግሥት መሬት አደባልቀው ወሰዱ፣ ያልተጨረሰ ቤቶችን ሸጡ፣ በወሰዱት መሬት ላይ ማልማት አልቻሉም፣ ወዘተ እየተባለ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ሲገባ ታይቷል፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ሌሎች የመሬት ችግሮችና ጣጣዎች ላይ በመንተራስ መሬት ያለአግባብ በግለሰቦች እየተሸጠ የግለሰቦች መክበሪያ ሆኗል፡፡ ይህንንም ሕገወጥ ክንውን ለመከላከል የሊዝ አዋጅ መታወጅ አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰና የሊዝ አዋጁ ሊታወጅ ችሏል፡፡
በአጠቃላይ አገላለጽ የሊዝ አዋጁ የከተማ ነዋሪውን አቅም ያገናዘበ አይደለም፡፡ የነዋሪውን ሕዝብ አቅምና ችሎታ በፍፁም አላጣጣመም፡፡ አዋጁ ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ሊመልስ አይችልም፡፡ አዋጁ ነዋሪውን ሕዝብ የሚያፈናቅል መስሎ መታየት የለበትም፡፡ አዋጁ ለነዋሪውም ሆነ ለልማቱ ተስፋ ሰጭ መሆን አለበት፡፡ ልማቱን ብቻ ለማሳለጥ ታስቦ ነዋሪዎችን ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆን የለበትም፡፡ አዋጁ በብዙ ዓይነት መንገድ መቃኘት አለበት፡፡ የግል መኖርያዎችም ከሊዝ ሥርዓት ነፃ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻ በ This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it ማግኘት ይቻላል፡፡


