Skip to main content
x
ሁለተኛው የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ለተግባር የቀረበ ይሆን?

ሁለተኛው የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ለተግባር የቀረበ ይሆን?

የበፊቷን ኢትዮጵያ ገጽታ ከመሠረቷ ይቀይራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሕገ መንግሥት ተረቅቆ በ1987 ዓ.ም. መፅደቁ ይታወሳል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ የተተገበረውና በፌዴራሊዝም የመንግሥት ሥርዓት አወቃቀር ላይ የተመሠረተው ሕገ መንግሥት ይዘት፣ አንድ ሦስተኛው በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል፡፡

ይህ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀደቀውና የቬና ዲክላሬሽን እየተባለ የሚጠራውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በመቀበል ለተግባራዊነቱ ቃል የገባው ሕገ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን አካቷል፡፡ ከመሠረታዊ የሰው ልጆች መብት ጀምሮ እስከ ፖለቲካና ሲቪል መብቶች ይገኙበታል፡፡ በዚህም መሠረት በተለይ የሰው ልጅ መሠረታዊ የመኖር፣ የመበልፀግ፣ ሐሳቡን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና የመቃወም መብቶችን አጠቃልሎ ይዟል፡፡

ሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ ለሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ተገዢ ካለመሆኑም በላይ ራሱ በተደጋጋሚ ይጥሳል ተብሎ በተቃዋሚዎችና በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲተች የሚስተዋል ቢሆንም፣ የዜጎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለማሻሻል የተለያዩ ዕርምጃዎች ሲወስድ እንደሚታይም ይነገራል፡፡

ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ለማጠናከር የትግበራ ዕቅድ ማውጣት አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ብሔራዊ መርሐ ግብር ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ሆኗል፡፡ የውይይት ፕሮግራሙን በይፋ የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ለተጋባዥ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

በመርህ ደረጃ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶች ተፈጥሮአዊና በሕይወት መኖር ተነጥለው የማይታዩ ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን፣ እስካሁን አንዳንድ ተቋማትን በማደራጀት፣ ዜጎች በማስተማርና ንቃተ ህሊናቸውን ከፍ ያለ እንዲሆን በማድረግ አንዳንድ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ከተመሠረቱት የመንግሥት ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና እምባ ጠባቂ ተቋም ይገኙባቸዋል፡፡ ኮሚሽኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶችን ጨምሮ አንዳንድ ወሳኝ ክስተቶችን በመፈተሽ፣ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ተበታትነው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች እንዲሰባሰቡና የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ በማድረግ ብዙ ሥራዎች ሲሠራ ይስተዋላል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በየአራት ዓመቱ ለተመድ የሚቀርበው የእርስ በርስ መገማገምያ ሪፖርትም በመንግሥት ደረጃ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡

ሆኖም እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሒውማን ራይትስዎች፣ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትና የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ድርጅት የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን መንግሥት ገጽታ የመጠበቅ እንጂ፣ የዜጎችን መብት ለመጠበቅ የተቋቋመ አይደለም በማለት ተቃራኒ ሪፖርቶች ሲያወጡ ይስተዋላል፡፡

መንግሥት የእነዚህን ትችት ፈጽሞ የማይቀበልና ግንኙነቱን ለማሻሻል ያልቻለ ሲሆን፣ ከተመድና ከአውሮፓ ኅብረት ጭምር አወዛጋቢ ጉዳዮች በገለልተኛ አካላት እንዲመረመሩ የሚቀርብለትን ጥያቄ አይቀበልም ሲሉ የሚሞግቱ ወገኖች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዳይሠሩ ከተከለከሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን የማረጋገጥ ጉዳይ መንግሥት የግሉ አድርጎ የያዘው እንደሚመስል የሚተቹ አሉ፡፡

መርሐ ግብር እንደ ግብ

በየአራት ዓመቱ በመደበኛነት ለተመድ የሚቀርበው የሰብዓዊ መብት የእርስ በርስ መገማገሚያ መድረክ ለአንዳንድ አገሮች ምክረ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም ባቀረበችው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ከተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አንዱ ብሔራዊ ሰነድ ማዘጋጀት ነበር፡፡ በተለይ የፖለቲካና የሲቪል መብት አያያዝን እንዲያሻሽል ምክረ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ መንግሥት የድርጊት መርሐ ግብር ለማዘጋጀት የተሰጠው ምክረ ሐሳብ ላይ አተኩሮ ሲሠራ ይስተዋላል፡፡

በዚህም መሠረት በ2006 ዓ.ም. የመጀመሪያው ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር እንዲፀድቅ ሲደረግ፣ ተፈጻሚነቱ እስከ 2009 ዓ.ም. ለሦስት ዓመታት እንዲሆን ታስቦ የተረቀቀ ነበር፡፡ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ ስለመሆኑ ግን አጠያያቂ ነው፡፡

ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ማዘጋጀት መንግሥት በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች አቀናጅቶ በመሄድ፣ የዜጎች የሰብዓዊ መብት ግንዛቤ ከፍ ለማድረግና የሰብዓዊ መብት ጥቃቶችን ለመከላከል ያለመ እንደሆነ በራሱ በሰነዱ ሰፍሯል፡፡ የመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር በተለይ የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ከመጠበቅና ከመከላከል አንፃር መሬት ላይ ጠብ ያለ ነገር እንዳለ በርካቶች ጥያቄ ያነሱበታል፡፡

የአንድ አገር የሰብዓዊ መብት አያያዝና መከበር በአጠቃላይ ከአገሪቱ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ነፃነት ተነጥሎ ማየት የማይቻል ነው፡፡ አምስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ተካሂዶ አዲሱ መንግሥት በተቋቋመ ማግሥት በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ሁከት፣ ከዜጎች ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶች መታፈን ጋር አገናኝቶ ለመፈተሽ ፍላጎት የለም ተብሎ ትችት ይቀርባል፡፡

የመጀመሪያው የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር መጠናቀቅ ላይ የተከሰተውን አመፅ ተከትሎ የደረሰውን የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት መርምሮ፣ መነሻው በአብዛኛው የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት መሆኑ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የገለጸው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከአንደኛው የድርጊት መርሐ ግብር ዓላማ ተፈጻሚ ከመሆን አለመሆን አንፃር ግን አልተመለከተውም፡፡ እሱም ብቻ ሳይሆን፣ በቅርቡ ሁለተኛው ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ይፋ በሆነበት ወቅትም፣ የአስተባባሪው ጽሕፈት ቤት የመጀመሪያው መርሐ ግብር ከሞላ ጎደል ግቡን የመታ እንደነበር ነው ሪፖርት የቀረበው፡፡ እንደ መጀመሪያው ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ሁሉ ሁለተኛው መርሐ ግብርም ይፋ የሆነው፣ በጣም ትልቅ ትኩረት በተሰጠውና በርካታ እንግዶች ታዳሚ በሆኑበት ሰፊ መድረክ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በይፋ መከፈቱን አብስረው ነበር፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተጠናቅሮ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው ይኸው ዕቅድ፣ ከመጀመሪያው መርሐ ግብር እምብዛም በይዘት ልዩነት ያለው አልነበረም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በዚሁ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ባደረጉት ንግግር ዕቅዱ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻልና የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት እንደ አንድ መሣሪያ ተመልክተውታል፡፡

በተለይ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በአዲሱ ዓመት መግቢያ ንግግራቸው ለሁከቱ መከሰት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአስተማማኝ ደረጃ መገንባት አለመቻል መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የገዢው ፓርቲ ብሔራዊ አባል ፓርቲዎችም በውስጣቸው ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት መንገሡና የሥልጣን አተያይ መዛባት (ሕዝብን ከማገልገል ፋንታ ራስን መጥቀም) መፈጠሩ በግልጽ ታምኖበት ድርጅቶቹ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ስብሰባ ባደረጉት ንግግራቸው፣ ‹‹አንዳንድ የእኛ ዴሞክራሲና ልማት የማይዋጥላቸው በሚሉት ደረጃም ባይሆንም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ጀማሪና በሽግግር ላይ በመሆኑ አንዳንድ ጉድለቶች አሉበት፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ንግግር መንግሥት ቀደም ሲል ለሕዝቡ ከገባው ቃል ጋር አብሮ የሚሄድ አይመስልም በማለት የሚተቹ አሉ፡፡

መርሐ ግብሩ ሁለተኛውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አድርጎ የተነሳ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ናቸው፡፡ ዕቅዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመጣው ለሕዝቡ የመልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ትርጉም ያለው ምላሽ ይሆናል ብለዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣ ስለመርሐ ግብሩ አሳጥረው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለቀረቡ አንዳንድ አስተያየቶችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ የመንግሥትን ቁርጠኝነት አድንቀው፣ መሬት ላይ ተግባራዊ እንዲሆንና ሰነድ ከማዘጋጀት ባለፈ ሥራ እንዲሠራ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በተለይ በክልሎች በዓመት አንድ ጊዜ የአፈጻጸም ሪፖርት ያደርጋሉ መባሉ፣ ለአተገባበሩ ትኩረት አላነሰም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የራዕይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ተሻለ ሰብረ በበኩላቸው፣ መርሐ ግብሩ እንዲህ መዘጋጀቱን አድንቀው ጥላቻንና የግለሰቦችን መልካም ስም ማጥፋት በተመለከተ በሰነዱ መካተቱን በመቃወም ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ሰበብ የሰዎች የመናገር ነፃነት ላይ እንቅፋት እንዳይሆን ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የክልል መስተዳድሮች ተወካዮች በመድረኩ ከተገኙት መካከል ነበሩ፡፡ ከአንዳንድ ክልሎች በአብዛኛው ሰነዱንና መርሐ ግብሩን በማድነቅ አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመጡ ተወካይ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ዘርዘር ያለ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ቢካተትበት የሚል አስተያየት አቅርበዋል፡፡ ተቀባይነትም አግኝተዋል፡፡

ሌላ ስማቸውን ያልጠቀሱ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ጠንከር ያለ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ የዕቅዱን ዋና ዓላማ የሰብዓዊ መብት ግንዛቤ ማሳደግና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መከላከል (Human Rights Promotion and Protection) መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንደኛው መርሐ ግብር በተጨባጭ የትኛው ተግባራዊ መሆኑን ግልጽ መደረግ አለበት የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት፣ እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ግንዛቤ ማሳደግና ማስተማር ከፍ ብሎ ይሆናል እንጂ፣ ሁለተኛውና ዋናውን ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥበቃና የመከላከል ሥራ እምብዛም የተሳካ አይደለም ብለዋል፡፡ ብሔራዊ መርሐ ግብር ማዘጋጀት፣ ማርቀቅና መሰነድ በራሱ የመጨረሻ ተግባር ተደርጎ እየታየ እንዳይሆንም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በክልሎችና በፌዴራል መርሐ ግብሩን የማስፈጸም ሒደት በተመለከተ የተለየ ሐሳብ ያንፀባረቁ ሲሆን፣ በተለይ ሪፖርት ሲቀርብ ዓመታዊ ሆኖ የተለየ ክፍለ ጊዜና ራሱን የቻለ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ቢቀርብ ይሻላል በማለት አማራጭ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

የአስተባባሪው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ምላሽ ሲሰጡ፣ በተለይ ዕቅዱ ወደ መሬት መርዶ ተግባራዊነቱ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ በሚለው አስተያየት ላይ ተስማምተዋል፡፡ መንግሥት በሩን ዘግቶ ያዘጋጀው ሪፖርት እንዳልሆነና አፈጻጸሙን በተመለከተም በየደረጃው ከሕዝብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ ምክክር እንደተደረገበት ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ደግሞ ከጥላቻ ንግግር ጋር ተያይዞ የቀረበውን ሥጋት በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ጉዳዩ ሆን ተብሎና ጥናትን መሠረት አድርጎ የተካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ ጋር ግንኙነት እንደሌለውም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ግለሰቦች በብሔራቸው፣ በሃይማኖታቸውና በመሳሰሉት የጥላቻ ቅስቀሳ እየተደረገባቸው ነው፤›› በማለት፡፡ አስተባባሪው ጽሕፈት ቤት በርከት ያሉ የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አባል የሆኑበት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዋና ጸሐፊነት ያገለግላል፡፡ ኮሚሽነሩ አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) የመርሐ ግብሩ አጠቃላይ መንፈስ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡበት ጠይቀዋል፡፡

በድርጊት መርሐ ግብሩ ሥር አራት ዋና ዋና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች በቀዳሚነት፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የባህል መብቶች፣ በመብት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በአካባቢ ደኅንነትና የመልማት መብት ሥር በርካታ የሰብዓዊ መብት ዝርዝሮች ሰፍረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ ተሳታፊዎች ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሰብዓዊ መብት ዕቅድ ከማዘጋጀት በተጨማሪ ለተግባራዊነቱ እንዲሠራ ይጠይቃሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ራሱ ከበቂ በላይ ለሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ከለላ መስጠቱን ዋቢ በማድረግ፡፡