Skip to main content
x

ለሴቶች የሀብትና የቤት ዕድል ተጠቃሚነት ተግባራዊ ሥራ ያስፈልጋል!

የመንግሥት ቤቶች ፕሮግራም ከተጀመረ ጀምሮ ሴቶች በራሳቸው 30 በመቶ፣ ከወንዶች ጋር በመጋራት 70 በመቶ ዕድል አግኝተው በፕሮግራሙ ተካፍለዋል ፡፡ እንደ  ታዳጊ እንዲሁም እንደ ዴሞክራሲ  ጀማሪ አገር፣ ይህ ለሴቶች የተደረገው ማበረታቻ በእውነቱ መልካም የሚሻል  ነው፡፡  ይህንን   በገሀድ  የተጎናጸፉት  ሕገ መንግሥቱ  የሰጣቸው መብት በመሆኑ ሲሆን፣ በዕድሉ ግን በቤት ላይ ብቻ ሳይሆን  በሥልጠና፣ በትምህርት፣ በሥራ መስክ አነሰም በዛ ተጠቃሚ  ሲሆኑ ይታያል፡፡ አካል ጉዳተኞችም  በተመሳሳይ መልኩ  ተጠቃሚ  የሚሆኑበት  መንገድ እየተመቻቸ  ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ መንግሥት  ሊመሰገን ይገባዋል፡፡

የሴቶችን  ጉዳይ ስንመለከተው  እውነታው  ይህ ሆኖ ሳለ  በተለይ በቤቱ  ፕሮግራም አማካይነት ዕጣ  ቢወጣላቸውም  በተግባር እንደሚታየው ግን የቤቱን ዕድል የሚጠቀምበት ገንዘብ ያለው፣ ባለሀብት የሚባለው አካል  መሆኑ  በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ  ሴቶች  አስቀድሞ ያፈሩት ገንዘብ  ባለመኖሩ፣ ያፈሩት የራሳቸው ሀብትና ጥሪት ስለሌላቸው  ዕጣ ከወጣላቸውና የቤት ባለቤትነት ዕድሉን ካገኙ ከጥቂት  ጊዜ በኋላ በዚያ ቤት ነዋሪ የሚሆነው ሌላ ሰው እየሆነ መታየቱ  አስገራሚ   ነው፡፡

 ስለዚህ  በሴቶች መብት ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት ፣ ስለሴቶች ተቆርቋሪ ነን  የሚሉ  የመንግሥት ወይም የበጎ አድርጎት ድርጅቶች፣  ከከተማ ዳርቻ ለሚኖሩና ተጋላጭ ለሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች መደጎሚያ የሚሆን  ገንዘብ ማፈላለግ  እንደሚገባቸው፣ ተጠቃሚነታቸውን እንዳያጡ በማሰብ ሊደግፏቸው እንደሚገባ ማጤን አለባቸው፡፡  በእኔ እምነት  መንግሥትም ቢሆን ለአካል ጉዳተኞች ና ለሴቶች የቅድሚያ ክፍያ በብድር መልክ በማመቻቸት ማቅረብ እንዳለበት አስባለሁ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አሁንም  የሀብት  ሥርጭቱ  እኩልነት እያጣና እየሰፋ ይመጣና  ሴቶችን ዳር በማውጣት የእኩል ተጠቃሚነት ዕድሉን ሊያሳጣቸው ይችላል፡፡ ሌሎችም የኅብረተሰቡ ክፍሎች  የእኩል ተጠቃሚነት ድርሻ ላይኖራቸው ይችላል  የሚል ሥጋት አለኝ፡፡   በሌላ መልኩ  የሴቶች ማኅበራት  ወይም  እንደ ሴቶች እና ሕፃናት ጉዳዮች ሚኒስቴር  ያሉ አካላት  በዚህ  ዘርፍ ከወሬ ባሻገር ለሴቶች የሀብት ተጠቃሚነት ተግባራዊ  ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሌላው የቤቶች ፕሮግራምን በተመለከተ ከሴቶች ተጠቃሚነት አኳያ የማነሳው በ40/60 ፕሮግራም ውስጥ ሴቶች ያላቸው ድርሻ ምንድነው? የሚለውን ነጥብ ነው፡፡ እዚህም ላይ  የሴቶች ተሳትፎ እንደሚባለው አይደለም፡፡ ላለው  ይጨመርለታል የሚለው አባባል  በሕገ መንግሥቱ  አይሠራም፡፡ በአንቀጽ 35 መሠረት  ሀብት ላለው ፣ የሚጠበቅበትን ሒሳብ በቅድሚያ ለዘጋው ሰው በቅድሚያ ቤት ይሰጠው  ብሎ ነገር  የለም፡፡  ሕገ መንግሥቱ  በዚህም ላይ መሥራት  አለበት፡፡  የእንግሊዝኛው ትርጉም ላይ የሕገ መንግሥቱ  አንዳንድ ዓረፍተ ነገሮቹ ሲጀምሩ   ‹‹if clause or conditional sentence›› ቅድመ ሁኔታዎችንና ውጤቶቹን አመላካች በሆኑ ቃላት ይጀምራሉ፡፡

 ለምሳሌ  ‹‹ አንድ ሰው የቤቱን  ሒሳብ  ከዘጋ፣ ቤቱን  በቅድሚያ ያገኛል  በሚለው አንቀጽ ውስጥ  ‹‹አንድ ሰው የቤቱን ሒሳብ ከዘጋ የሚለው›› ቅድመ ሁኔታን አመላካች ወይም ‹‹if clause›› ነው፡፡  ቀጣዩ ዓረፍተ ነገር ‹‹ቤቱን በቅድሚያ ያገኛል›› በማለት የሚጠቀልለው ውጤቱን አመላካች ነው፡፡ በሌላ አባባል   ለምሳሌ  አንድ   ተማሪ ትምህርቱን ካጠና፣  ፈተናውን በአስተማማኝ ውጤት ያልፋል ማለት እንችላለን፡፡  በሕገ መንግሥቱ ግን አንድ  ተማሪ ቢያጠናም ባያጠናም ሕጉ  እስከፈቀደለት ድረስ  ወደ ሚቀጥለው ክፍል  ይገባል እንደማለት ይሆናል፡፡ መሆን ያለበት ግን አንደኛ ተማሪ መሆን ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ፈተናውን መፈተን  ነው፡፡  ይህ  ጥሩ ምሳሌ ላይሆን  ይችላል፡፡ ይህም ሆኖ ለማለት የተፈለገው ግን አንዲት ሴት ለ40/60  ቤቶች ፕሮግራም እስከተመዘገበች ድረስ እንዲሁም የመጀመሪያውን መስፈርት እስካሟላች  ድረስ የ30/70 ዕድሏ  የሕገ መንግሥት  ጥያቄ ስለሆነ  ቅድሚያ ታገኛለች፡፡   የቅድሚያ ክፍያ መሥፈርቱ 40 በመቶ ከሆነ፣  የ30  የብቸኛ ዕድል ተጣቃሚነቷ እዚህም ላይ ሊሠራ ይገባዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ጥያቄ በትናንሹ ነገር የሚሠራ በትላልቁ ላይ ግን የማይሠራ  መሆን የለበትም፡፡  ምሁራን በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት አለባቸው፡፡ ሴቶችም ለመብታቸው መከራከር አለባቸው ፡፡ በ20/80 ላይ የሚሠራው፣ በ10/90 ላይ የሚሠራው  በ40/60 ላይ ግን የማይሠራ ከሆነ   የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35  አስፈላጊነት አጠያያቂ ይሆናል፡፡  መብት ሲደረፈር ሲጣስ መታገል የሁሉም  ዜጋ ጉዳይ ነው፡፡  ለማለት የፈለግሁት  የሕገ መንግሥት  ጥያቄ ጉዳይ በመሆኑ መታየት አለበት ነው፡፡

ስለሆነም  በዚህች አገር  የሴቶች  ጉዳይ  በቤት ተጠቃሚነት፣ በሥልጠና፣ በትምህርትና  በሥራ ዕድል ተጠቃሚነት  ዙሪያ በደንብ መታየት አለበት፡፡ መድረክ ባገኘ ቁጥር እየተወናጨፈ  የሚያወራው  የመሥሪያ ቤት ኃላፊ ፣ ቢሮው ወይም እቤቱ ሲሄድ የሚያወራውን በተግባር  አለመተግበሩ ያስቆጫል፡፡ እንደውም የሴት ነገር እያለ የሚዘብትም ኃላፊ ነኝ ባይ በርካታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሴቶች  ግን  እናቶቻችን፣ እህቶቻችን፣ የትዳር አጋሮቻችን  ናቸው፡፡ እኔ ግን  እናቴ ከእኔ በላይ ሁሉም ነገሬ በመሆኗ ከእኔ በላይ ተጠቃሚ ብትሆን  በምን ዕድሌ፡፡  ስለሆነም  የአፍ  ብቻ ሳይሆን፣ የተግባር ሰዎችም እንሁን፡፡ የሴቶችን ጉዳይ በሁሉም አቅጣጫ  እንመልከተው፡፡

 (ወልዴ በፍርዱ  ከአ.አ፣ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያ)