Skip to main content
x
ለ20 ኪሎ ሜትር ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ መንገዶች ግንባታ ተጀመረ

ለ20 ኪሎ ሜትር ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ መንገዶች ግንባታ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡና እየተገነቡ ከሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ የሚጠበቀው ዘመናዊ መንገድ ግንባታ ሥራ ማክሰኞ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም.  በይፋ ተጀመረ፡፡

መነሻውን ቃሊቲ የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ አደባባይ በማድረግ በሁለት ኮሪደሮች የሚጓዘውና ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀውን የመንገድ ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥበት ሥራውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

አዲስ አበባን መነሻና መድረሻ በማድረግ የአገሪቱን የወጪ ንግድ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚያስተናግደው ይህ መንገድ ሲጠናቀቅ፣ ከተማዋን የባለሦስት ተሻጋሪ መንገዶች ባለቤት እንደሚያደርጋት ይጠበቃል፡፡

 የመንገድ ግንባታውን የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት ከንቲባ ድሪባ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ ዘመናዊ ከተማ እንድትሆን ለማድረግ አንዱ ማሳያ የዚህ መንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡ የመንገዱ ግንባታ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያነሷቸውን ቁልፍ ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ከሚከናወኑ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታና በከታማዋ ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ከተዘረጋው ፕሮግራም ጋር  ተያያዥነት አለው ብለዋል፡፡

 በአሁኑ ወቅት በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላትና በከተማዋ ነዋሪ ሰፊ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን ለከተማዋ ዘመናዊነት አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት ከተያዙ ፕሮግራሞች አንዱ የሆነው የመንገድ ግንባታ ሥራ በከተማዋ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ጉልህ ድርሻ በመያዝ ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡ ሰኞ፣ የካቲት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ግንባታቸውን ለማስጀመር የመሠረት ድጋይ የተጣለባቸው የቃሊቲ፣ ቱሉ ዲምቱ አደባባይና የቃሊቲ - ቡልቡላ - ቂሊንጦ መንገድ ፕሮጀክቶችም የከተማዋን የመንገድ ሽፋን በማሳደግ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የአዲሱ መንገድ ግንባታ የአገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በማስተናገድ፣ የትራፊክ ፍሰቱን በማቀላጠፍ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዲሻሻል ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከቃሊቲ ቀበለት መንገድ አደባባይ - በቡልቡላ በኩል አድርጎ ወደ ቂሊንጦ የሚገነባው መንገድ ቀደም ሲል በአካባቢው ምንም ዓይነት የመንገድ መሠረተ ልማት በሌለበት ሥፍራ እንደሚገነባም አስታውሰዋል፡፡ አዲስ የመንገድ መሠረተ ልማትና የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በይፋ ግንባታቸው የተጀመረው እነዚህ ፕሮጀክቶች በዓይነታቸው እስካሁን ከተገነቡት ይልቅ ዘመናዊ ሲሆኑ፣ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድርና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጀት በአጠቃላይ ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የሚገነቡ ናቸው፡፡

የፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ ርዝመት 20.6 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች እንደመንገዶቹ ሁኔታ የ40፣ የ50 እና የ60 ሜትር ስፋት ኖሯቸው የሚገነቡ ናቸው፡፡ ግንባታውን የቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ተረክቧል፡፡

ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት የተሰጠው ሲሆን፣ የሚለከታቸው ባለድርሻዎች ድጋፍ ከተጨመረበት ከዚህ ጊዜ ቀድመው የሚጠናቁቀበት ተስፋ  እንዳለ ኢንጂነር ሀብታሙ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ መውጫና መግቢያ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሲያገለግል የቆየው ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ በመነሳት ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የሚደርሰው አንደኛው የመንገድ ፕሮጀክት፣ አጠቃላይ የፕሮጀክት ወጪው 2.45 ቢሊዮን ብር ሆኖ 11 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 50 ሜትር ስፋት የሚኖረው ትልቁ መንገድ ነው፡፡ 11 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው በአንደኛው መንገድ ይካተታሉ ከተባሉት ውስጥ የአቃቂ ድልድይን ጨምሮ አምስት ዋና ዋና የተሻጋሪ ድልድይ ግንባታዎች ተጠቅሰዋል፡፡ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ሥራውን ኢንጂነር ዘውዴ እስክንድር አማካሪ ኩባንያ ተረክቦታል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሁለተኛው ክፍል የቃሊቲ ቡልቡላ ቂሊንጦ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ አጠቃላይ ርዝመቱ 5.4 ኪሎ ሜትር በ50 ሜትር ስፋት፣ 3.5 ኪሎ ሜትር በ40 ሜትር እንዲሁም 16 ሜትር በ60 ሜትር ስፋት የሚገነባ ሆኖ በልዩ ሁኔታ ዲዛይን መደረጉ ተነግሮለታል፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ 2.33 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በዚህ ግንባታ ክፍል ውስጥ ከላይና ከታች የትራፊክ ፍሰቱን የሚያስተናግድ አንድ አደባባልይ፣ ሁለት ተሻጋሪ ድልድዮችና ሁለት 125 ሜትር ርዝመት ያላቸው ድልድዮች ግንባታን አካትቶ የሚካሄድ ውስብስብ ፕሮጀክት እንደሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ የቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በቃሊቲ ቡልቡላ፣ በቂሊንጦ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሸጋገሩ አንቀሳቃሾች ማምረቻዎችና በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች በሙሉ ከፍተኛ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ አዲስ የሚገነባ መንገድ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የዚህን ፕሮጀክት የዲዛይንና የቁጥጥር ሥራ ሄክ የተባለ ሌላ አገር በቀል አማካሪ ድርጅት የሚያከናውን ሲሆን፣ 11 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ ደግሞ ኢንጂነር ዘውዴ እስክንድር የተባለው አማካሪ ድርጅት ተረክቧል፡፡

የዚህ መንገድ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን፣ መንገዱ በሚያልፍበት አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ኢንተርፕራይዞችና ለቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የንግድ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ኢንጂነር ሀብታሙ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የዚህ መንገድ ግንባታ በኮዬ ፈጩ አካባቢ እየተገነቡ ለሚገኙ 70 ሺሕ ያህል ኮንዶሚኒየም ቤቶችና ወደፊትም የሚገነቡትን ጨምሮ ከ300 ሺሕ ላላነሱ ነዋሪዎች ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገለግሎት ለማቅረብ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ አክለዋል፡፡

በአካባቢው እየተገነቡ የሚገኙትና የአንድን ከተማ ያህል ብዛት ያለው ሕዝብ ሊኖርባቸው የሚችሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው ሲጠናቀቅ፣ በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ከመሐል ከተማው ጋር የሚኖረውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ጠቀሜታቸው የላቀ እንደሚሆን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለወጣቶች፣ ለአምራቾችና ለተቋራጮች እንዲሁም በመንገድ ኮንስትራከሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም ብዙ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

ለመንገድ መሠረተ ልማት ዕድገት መንግሥት ትኩረት እንደሰጠ የገለጹት ከንቲባ ድሪባ፣ ለአዲስ አበባ የመንገድ ልማት የሚውል ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማፅደቅ የተለያዩ የግንባታና የጥገና ሥራዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ መንገዶችን ለተጠቃሚዎች ምቹ ለማድረግ አስተዳደሩ ለጥገና ከ267 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ለጥገና ሥራው ትኩረት መሰጠቱንና በጥቂት ወራት ውስጥም በአዲስ አበባ ከተማ ለውጥ ስለመመዝገቡ የከተማው ነዋሪ ምስክር ይሁነኝ ብለዋል፡፡ ከጥገና ሥራው ጎን ለጎን አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች እንደሚተገበሩ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የግንባታ ሥራቸው የተጀመሩት መንገዶች 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ቢሆኑም፣ ለግንባታ የሚጠይቁት ወጪ 4.7 ቢሊዮን ብር መሆኑ ብቻም ሳይሆን በአንድ ኪሎ ሜትር ከ235 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ መሆናቸው ከሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች የተለዩ አድርጓቸዋል፡፡