Skip to main content
x
ሕዝብን አለማዳመጥ አገርን ለጥፋት መዳረግ ነው!

ሕዝብን አለማዳመጥ አገርን ለጥፋት መዳረግ ነው!

ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላማ መመራቱ ይታወሳል፡፡ ፓርላማው ሕዝቡን በጉዳዩ ላይ በየደረጃው ካወያየ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚፀድቅ ተገልጿል፡፡ ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ የሕዝብን ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት ተሰምሮበታል፡፡ እንደተባለው የሕዝብ አስተያየት በይፋ እስከሚሰማ ድረስ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ አሁን አቋም ይዞ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚታዩ አሳሳቢ ጉዳዮችን ግን መቼም ቢሆን ችላ ማለት አይገባም፡፡ ሕዝብና መንግሥትን ከሚያቃቅሩ ዋነኛ አጣዳፊ ጉዳዮች መካከል ለአሁን አጣዳፊ የሆኑትን ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት ሕዝብን ሲያስተዳድር የተለያዩ ችግሮች ማጋጠማቸው አይቀሬ ቢሆንም፣ ሁልጊዜ እየተደጋገሙ የሚመጡ ችግሮችን ለመፍታት አለመቻል ግን ማስጠየቅ አለበት፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዳይፈጠር ማድረግ፣ ፍትሕ ማዛባት፣ ሕግ አለማክበር፣ ሕዝብን አለማዳመጥና የመሳሰሉት ጠንቀኛ ችግሮች ሕዝብንና መንግሥትን እየለያዩ ናቸው፡፡ ይኼ ደግሞ አደጋ አለው፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ኅብረትን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ አካላትን፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና የበርካታ አገሮችን ኤምባሲዎች የምታስተናግድ ናት፡፡ ከኒዮርክና ከጄኔቫ ቀጥላ የምትታወቅ የዓለም  አቀፉ ማኅበረሰብ መናኸሪያ ናት፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የምትገኝ ከተማ ፍትሐዊ የታክስ ሥርዓት፣ ዘመናዊ የተሽከርካሪና የባቡር መንገዶች፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓት፣ ፅዳትና ውበት፣ አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ ለነዋሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡ ማዘጋጃ ቤቶች፣ የነዋሪዎችን ደኅንነት ነቅተው የሚጠብቁ የፀጥታ መዋቅሮች፣ በትምህርትና በሥራ ልምድ ራሳቸውን ያበቁ የከተማ መሪዎች፣ ወዘተ. ያስፈልጋሉ፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢሕአዴግ የከተማውን ቢሮክራሲ ከፖለቲካ ተሿሚነት አላቆ በሙያተኞች እንዲመራ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን እየቀረ ግን ከተማዋ ከስሟ ጋር አልመጣጠን ብላለች፡፡ እርግጥ ነው ባለፉት አሥር ዓመታት የከተማዋ ገጽታ ጉልህ ለውጥ ቢታይበትም፣ ከቁሳዊው ግንባታ በተጨማሪ ሰብዓዊ ጎኑ ብዙ ይቀረዋል፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጀምሮ በክፍላተ ከተሞችና በወረዳዎች የተሰማሩ አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ከተማዋን እንዴት እየመሩ ነው የሚለው በጥልቀት መፈተሽ አለበት፡፡ የእነሱና የሕዝቡ ግንኙነት ምን ይመስላል የሚለውም እንዲሁ፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ማዶ ለማዶ ሆነው እየተያዩ ነውና፡፡

ወቅቱ ክረምት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር አውራ ጎዳናዎች በጎርፍ ይጥለቀለቃሉ፡፡ የመኖሪያ መንደሮች በጎርፍ ይወረራሉ፡፡ ጎርፍ ሲመጣ ደግሞ ብቻውን አይደለም፡፡ ደረቅ ቆሻሻዎችና የመፀዳጃ ቤት ፍሳሾች ከየአካባቢው ይለቀቃሉ፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች በአግባቡ ባለመሠራታቸው ወይም ባለመኖራቸው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ ከከፍታ ቦታ በከፍተኛ ፍጥነት የሚወረወር ጎርፍ ያገኘውን እየጠራረገ በአስፋልት መንገድ ላይ ተጉዞ ተዳፋት ላይ ያሉ መንደሮችን ሲያጥለቀልቅና የሰው ሕይወት ሲያልፍ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ከፍተኛ የሆነ ንብረት ሲወድምም እንዲሁ፡፡ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው አስፋልት መንገዶች እየፈራረሱ ነው፡፡ ሰሞኑን የከተማው አስተዳደር የዘንድሮ ክረምት ከባድ ስለሚሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ ለክፍላተ ከተሞችና ለወረዳዎች ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ እነሱም በየደረጃው ሕዝቡን ለማነጋገር ስብሰባ ጠርተዋል፡፡ በስብሰባ አዳራሾቹ የተገኘው ነዋሪ ሕዝብ ቁጥር ግን እጅግ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ ለምን? ሕዝቡ ከዚህ ቀደም ይህንን ችግር በተደጋጋሚ አቅርቦ የሚሰማው በማጣቱ ብቻ ጊዜዬን በመዳረቅ ለምን አጠፋለሁ ብሎ ነው፡፡ በተለይ በወረዳ ደረጃ ያሉ ሹማምንት ችግሩ ሲነገራቸው ከማስፈጸም ይልቅ፣ ጊዜያቸውን በማይረባ ነገር ስለሚያጠፉ ሕዝብ ተሰላችቷል፡፡ በዘንድሮ ዝናብ ሥጋት የገባቸው ዜጎች ችግሩን ከነመፍትሔው ቢያቀርቡም የወረዳዎቹ የማስፈጸም ፍጥነት በጣም ቀርፋፋ ነው፡፡ የበላይ አካል ትዕዛዝ ሲመጣ ብቻ ይንቀሳቀሳሉ እንጂ ዳተኞች ናቸው እየተባለ በአደባባይ ተነግሯል፡፡ ከተማው ይህንን ችግር ተገንዝቦ ፈጣን ዕርምጃ ይወስዳል? ወይስ እንደ ወረዳዎቹ ያንቀላፋል? የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት ለፈጣን ዕርምጃ ይነሳል? ወይስ ሕዝቡ እንደሚለው ጊዜያዊ የዘመቻ ሥራ ነው?  መልስ ያስፈልጋል፡፡  ያውም በተግባራዊ ዕርምጃ የታጀበ፡፡

የፀጥታ ችግርን በተመለከተ ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊሶችና የደንብ አስከባሪዎች ቢሰማሩም፣ በጠራራ ፀሐይ ሰዎች ይዘረፋሉ፡፡ በዝርፊያው ወቅት በደረሱባቸው ጉዳቶች ለሕልፈት ይዳረጋሉ፡፡ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች ላይ በኃይል የታጀቡ ዝርፊያዎች ይፈጸማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አስከፊ ድርጊቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገጽታቸውን እየለወጡ ወደ ተደራጀ ወንጀል እያመሩ ነው፡፡ ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች ከሕዝብ ጋር ሆነው ወንጀልን መከላከል ባለመቻላቸው ብቻ ሕገወጦች የከተማዋ ሥጋት ሆነዋል፡፡ ጀንበር ከጠለቀች በኋላ ለብቻ በእግር የማይገባባቸው መንደሮች እየተበራከቱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሕዝቡን ለማስተባበር የተሳናቸው የወረዳ አስተዳደር አካላት የበላይ አካል ትዕዛዝ ሲጠብቁ ይውላሉ፡፡ ለማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ የተዘጋጁ ቤቶች ክፍት ሆነው ያዛጋሉ፡፡ ደንብ አስከባሪ ተብለው የተሰየሙት ደግሞ አልፎ አልፎ ጎዳና ላይ ከሱቅ በደረቴዎች ጋር ሲሯሯጡ ከመዋል ባለፈ በመንደሮች ውስጥ ቅኝት አያደርጉም፡፡ ደረቅ ቆሻሻ የሚሰበስቡ ዜጎች የቆሻሻ ያለህ እያሉ እየለመኑ የነዋሪዎችን በር በሚያንኳኩበት በዚህ ጊዜ፣ ሕገወጦች ደረቅ ቆሻሻ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ውስጥ ሲደፋ መከላከል ሲገባቸው በሚፈለጉበት ቦታ አይገኙም፡፡ ሥምሪታቸው እንዴት እንደሆነም ለሕዝቡ ግልጽ አይደለም፡፡ ወንጀል ተበራክቶ ሕዝብ ሲያስመርር የእነሱ ሚና ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በቅርብ የሚያውቋቸው ወረዳዎች እንዴትና መቼ እንደሚያሰማሯቸው፣ ለምን እንደሚያሰማሯቸው ለሕዝብ ግልጽ አይደለም፡፡ ሕዝቡም ይህንን በግልጽ ይናገረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትም ሆነ ካቢኔው፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ሕዝቡ ለምን ከክፍላተ ከተሞቹና ከወረዳዎቹ ጋር ያለው ግንኙነት እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚለውን ለማወቅ ታች መውረድ አለባቸው፡፡ ወረዳዎቹ ከሕዝብ ጋር ለመነጋገር ስብሰባ ሲጠሩ ሕዝብ በምልዓት ካልወጣ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ ወረዳዎቹ ለበላይ አካል በግልጽና በሀቅ አብራርተው ስለማያስረዱ ብቻ ሳይሆን፣ ከላይ ያለው አካል በጠንካራ ክትትልና ግምገማ ለማየት ተነሳሽነት በማጣቱ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በጎርፍ ሥጋት ላይ የተጠራው የሕዝብ መድረክ ተሳታፊዎችን ለምን አጣ ቢባል መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝቡ እምነት በማጣቱ ነው፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት መላ ይፈለግለት የተባለ የፍሳሽ ማስወገጃ መፍትሔ ሳይበጅለት ዛሬ እንደ አዲስ ሲቀርብለት ይበሳጫል፡፡ በፀጥታ ሥጋት ላይ ያነሳው የዓመታት ጥያቄ ዝም ሲባል ይናደዳል፡፡ ከዓመት ዓመት ጎርፍ አካባቢውን እያጥለቀለቀ ሲያጠፋው ኖሮ አሁንም ያው ሥጋት ሲነገረው ይከፋል፡፡ ችግሩ ታውቆ ብዙ የተባለበት ጉዳይ እንደ አዲስ መፍትሔ ይፈለግለት ሲባል ይቀየማል፡፡ ከሕዝብ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ችላ እየተባሉ ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡ በቅርቡ ቆሼ በሚባለው አካባቢ የደረሰው ዘግናኝ አደጋ ለዓመታት ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ውጤቱ ምን እንደሆነ ደግሞ ከአስከፊ ገጽታው ጋር ታይቷል፡፡

በአጠቃላይ ሕዝብን አለማዳመጥ የሚያመጣውን አስከፊ መዘዝ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ደም አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ግጭት በሚገባ ለማየት ተችሏል፡፡ ስህተቶች በስህተት ላይ እየተደመሩ በመሄዳቸው ምክንያት ብቻ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነዋል፡፡ አገር የሚያስተዳድረው ኢሕአዴግ በዚህ ሳቢያ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ለማድረግ ከከተተ ሰንብቷል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን አሁንም ብልጭ ድርግም የሚሉ አጥፊዎች ይታያሉ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ነውር የሆነባቸው አጥፊዎች፡፡ ከራሳቸውና ከቡድን ጥቅም በላይ አርቀው ማሰብ የተሳናቸው አጥፊዎች አሁንም ሕዝብን እንደናቁ ናቸው፡፡ ለእነሱ ሥራ ማለት በጠባብ የቡድን ስሜት ውስጥ የተወሸቀ ራስ ወዳድነት ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝብ የሥልጣን ትልቁ ባለቤት መሆኑን በማመን ከታች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ አገልግሎት መስጠት የመንግሥት ወግ መሆን ነበረበት፡፡ ይህ አልሆን እያለ ትናንት ሲያወዛግቡ የነበሩ ጉዳዮች ዛሬ ጥሬ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብን ብስጭት ያንረዋል፡፡ ሕዝብና መንግሥት እንዳይተማመኑ ያደርጋል፡፡ ተሃድሶው ይህንን መፍታት ካልቻለ ፋይዳው ምንድነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሕዝብን አለማዳመጥ አገርን ለጥፋት መዳረግ ይሆናል!