Skip to main content
x
ሕዝብ ይከበር!

ሕዝብ ይከበር!

ሕዝብ የሚከበረው የአንድ አገር የፖለቲካ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ስለሆነ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት በምርጫ ሥልጣኑን መያዙን የሚያምን ከሆነ፣ ከምንም ነገር በፊት የሚያስቀድመው ሕዝብን ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ ስለሆነም ለምርጫ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚገዙት ለሕዝብ ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ መሆን አደጋ ስላለው ግለሰብ ፖለቲከኛም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሽርጉድ የሚሉት የሕዝብ አጀንዳ ይዘው ነው፡፡ አምባገነኖች ደግሞ ራሳቸውን ከማንም በላይ ስለሚያዩ፣ እንኳን ለሕዝብ ፈቃድ ሊገዙ ይቅርና ሕዝቡን ራሱን መከራ ያበሉታል፡፡ በየትኞቹም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በገነቡ አገሮች በመንግሥት ውሳኔዎች ላይ የሚንፀባረቁት የሕዝብ ይሁንታዎች ብቻ ናቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ የመንግሥት ተሿሚዎች የሕዝብ አገልጋይ ሲሆኑ፣ ሕዝብ ደግሞ አለቃቸው እንደሆነ ስለሚታመን ነው፡፡ ይኼ ዓይነቱ ወግ ማዕረግ በሌለባት አገራችን ግን ከምኞት የዘለለ እውነታ የለም፡፡ በሕዝብ ስም እየተማለ ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ይበዛሉ፡፡ ለታይታና ለይስሙላ የሕዝብ ስም በተደጋጋሚ ቢጠራም፣ የሚታየው ግን ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ነው፡፡ ሕዝብ ባለመከበሩ ብቻ በርካታ ጉዳቶች እየደረሱ ነው፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው፣ አገር በብልፅግና ጎዳና የምትገሰግሰው፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚረጋገጠው፣ ዜጎች በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹትና የሚደራጁት፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል የሚኖረው፣ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩትና በሥርዓት መኖር የሚቻለው የሕግ የበላይነት ሲከበር ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ሕግን መሠረት ያደረጉ ተግባራት ሲከናወኑ ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ ሕዝብ በነፃነት የፈለገውን ይመርጣል፡፡ የመንግሥት አሠራርም ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ ሕገወጥነት በሕግ ፊት ያስጠይቃል፡፡ ገደብ የሌለው ሥልጣን ሥፍራ አይኖረውም፡፡ የሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነት ይረጋገጣል፡፡ ይኼንን የመሰለ በሕገ መንግሥት ላይ የሠፈረ ፀጋ ተይዞ ግን አገር ሁሌም የንትርክ መድረክ ትሆናለች፡፡ ሕዝብን የሚያዳምጠው እየጠፋ ከየአቅጣጫው ብሶት ይሰማል፡፡ አገርን ለትርምስ የሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ሥጋት ይፈጠራል፡፡ ይኼንን ችግር መገላገል አዳጋች እየሆነ ነው፡፡

የመንግሥት ሹማምንት ከላይ እስከ ታች መናበብ እያቃተቸው ትርምስ ሲፈጠር ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ስለማይቻል፣ አገርን ቋፍ ውስጥ የሚከቱ አሳሳቢ ሥጋቶች ይደቀናሉ፡፡ ለይስሙላና ከአንገት በላይ ከሕዝብ ጋር በመነጋገር ተማምነናል ተብሎ ዲስኩር በተነገረ ማግሥት የሕዝብ እሪታ ይሰማል፡፡ ‹‹አንዳንድ›› ከሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች መፍትሔ እንደማያመጡ እየታወቀ፣ ግብረ መልሳቸው በቅጡ የማይታወቁ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ይለፈፋሉ፡፡ ‹‹አንዳንድ›› የሚባለው ፈሊጥ እርባና እንደሌለው በተለያዩ ጊዜያት ታውቋል፡፡ ሕዝብ የሚናገረው ሌላ ‹‹አንዳንድ›› የሚባሉት የሚያወሩት ሌላ፡፡ መደማመጥ ጠፍቶ ሁሉም ባሻው መንገድ ሲነጉድ 100 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት አገር ትረሳለች፡፡ ሕዝብን የሚያህል ክቡር ፍጡር ይዘነጋል፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርቶችና በለብለብ ጥናቶች ላይ የተመሠረቱ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞከር ከሰፊው ሕዝብ ጋር ጠብ ይፈጠራል፡፡ ሕዝቡን የሚያዳምጠው በመጥፋቱ ብቻ የማንም አድርባይና አስመሳይ ሲያነኩረው የከረመው ሥራ ተመልሶ ጥሬ ይሆናል፡፡ ከፍሬ ይልቅ ገለባ እየበዛ ሕዝብ እየተናቀ ነው፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባቃታቸው ዳተኞች ምክንያት ብቻ ሕዝብ እየተሳቀቀ ነው፡፡ ሕዝብን ለቁጣ ማነሳሳት ትርፉ ምን እንደሆነ በቅርቡ በግልጽ ታይቷል፡፡ ያውም ከፍተኛ መስዋዕትነት ያስከተለ አደጋ፡፡

የሃያ ሁለት ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረውን ሕገ መንግሥት ያላነበቡ ተሿሚዎች እንኳን ሕዝብ ሊመሩ የሚናገሩትን አያውቁም፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶች የተባበሩት መንግሥትታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችና አገሪቱ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች አካል መሆናቸውን ያልተገነዘቡ ተሿሚዎች፣ ዜጎች በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸውን ሲጠይቁ ዱላ ይቀናቸዋል፡፡ ሕጋዊ ሆኖ መብትን መጠየቅ እንደ በደል እየታየ ወደ ሕገወጥነት የሚገፉ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች ከታችኛው የወረዳ መዋቅር ጀምሮ በብቃት ሳይሆን፣ በፓርቲ አባልነትና ወገንተኝነት የተኮለኮሉ ሹማምንት በሚፈጥሩት ጦስ አገር ይተራመሳል፡፡ ሕዝብን ማክበር የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ እንደ ተራራ የሚገዝፍባቸው፣ እንደ በቀቀን መፈክር ከማስተጋባት ውጪ ምንም አያውቁም፡፡ ካሰፈሰፉበት የግልና የቡድን ጥቅም በላይ ሕዝብ የሚባል ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት እንዳለ አይገነዘቡም፡፡ ለማስመሰል ግን ለሕዝብ እንደቆሙ ሲናገሩ ደግሞ አያፍሩም፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝብ ጠልቷቸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ መንግሥት በሚባለው ተቋም ላይ ያለው እምነት ተሟጧል፡፡ በእነሱ ሳቢያ ከፍተኛ ጥፋት ከደረሰ በኋላ የሚደረገው መሯሯጥ ፋይዳ ቢስ ስለሆነ ውጤቱ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ሆኗል፡፡

ሕዝብ ፍትሐዊ የግብር ሥርዓት ይኑር፣ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ይሁኑ፣ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ይኑረው፣ በመንግሥት ውሳኔዎች የምለው ይደመጥ፣ በአገር ጉዳይ ያለኝ ተሳትፎ የባዕድነት ሳይሆን የባለቤትነት ይሁን፣ ሕገወጥነትና ብልሹ አሠራሮች ይወገዱ፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ይቁም፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፣ አገር በሕግ የበላይነት ሥር ትተዳደር፣ ወዘተ እያለ ሲጠይቅ ምላሹ ፈጣንና የማያወላዳ መሆን አለበት፡፡ በተቃራኒው ግን ግብር ሊገምት የተሠማራው ኃይል ግንዛቤ ሳያስጨብጥ ተንደርድሮ ይሄድና ሕዝቡን እንደ ድንገተኛ መብረቅ ያተራምሰዋል፡፡ ግብር መክፈል መብትም ግዴታም እንደሆነ እየታወቀ አሠራሩን ሰይጣናዊ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ሕዝብ ግራ ተጋብቶ ጥያቄ ሲያቀርብ ጆሮ ዳባ ልበስ ይላል፡፡ መንግሥት አያዳምጥም ተብሎ ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እንዲገባ ምክንያት ይሆናል፡፡ ጥፋት በጊዜ መታረም ሲገባው የዘመቻ ሥራ ውስጥ ይገባና በርብርብ ለማስተካከል ይሞከራል፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ አስከፊ ድርጊት መገለጫው ይህ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› በማለት ነጋ ጠባ ሲያነበንበው የነበረው በአጭር ጊዜ ተረስቶ፣ አገርን ዳግም ለትርምስ የሚጋብዝ ድርጊት ይፈጸማል፡፡ ያ ሁሉ መሃላና ግዝት ተረስቶ ለግጭት የሚዳርጉ እንቅስቃሴዎች ለምን ተከሰቱ ብሎ የሚጠይቅ የለም? ወይስ እንደተለመደው ‹‹እንቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው›› የሚባለው ጀብደኝነት እንደገና አቆጥቁጧል? የአገር ዘላቂ ሰላምና ህልውናን ከመጤፍ በማይቆጥሩ የሹም ዶሮዎች ምክንያት ሕዝብ ሲታመስ ዳተኛ መሆን በዝቷል፡፡ በሕዝብ ስም እየተማለ ሕዝብን ማስለቀስ ጊዜ ያለፈበት አደገኛ ድርጊት መሆኑን አለመገንዘብ ወይም ችላ ማለት ለአገር አይጠቅምም፡፡ ሕዝብ ሹማምንቱ በየቀኑ ምን እንደሚያደርጉ ያውቃል፡፡ ማን ለሕዝብ እንደሚሠራ ማን ደግሞ የሕዝብ ደም እንደሚመጥ ከማንም በላይ በሕዝብ ዘንድ ግልጽ ነው፡፡ በሕዝብ ላይ ቢሮአቸውን እየቆለፉ የሚጠፉ፣ በጉቦ አላስወጣ አላስገባ የሚሉ፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን የሚነፍጉና በአገር ላይ የሚያላግጡትን ያውቃቸዋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሌለ ብቻ እንዳሻቸው የሚፈነጩ በዝተዋል፡፡ ተሃድሶውን የይስሙላ ያደረጉ ኃይሎች ሕዝብ ቢንቁ ምን ይገርማል? ዋናው ጉዳይ ግን ሕዝብ አለመደመጡና አለመከበሩ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ለሌላ ዙር ችግር ያጋልጣል፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚባለው የሕግ የበላይነት ከሌለና አጥፊዎች ለሕግ ካልቀረቡ ችግሩ ይቀጥላል፡፡ አገር እያስተዳደረ ያለው መንግሥት ቃል አባይ እየሆነ እስከ መቼ ይቀጥላል? ውስጥን አጥርቶ ሕዝብን ማስተዳደር አለመቻል እኮ ሌላው ቢቀር በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ እስከዚያው ግን ለአገር ዘለቄታ ሰላምና መረጋጋት ሲባል ሕዝብ ይከበር!