Skip to main content
x
ሕይወት አዳሽ ዛፎች

ሕይወት አዳሽ ዛፎች

የለበሱት በዝናብ ርሧል፡፡ ችግኝ ለመትከል በተመረጠው በእንጦጦ ማርያም ጋራ ላይ የተገኙት ማልደው ነው፡፡ በግምት ሁለት መቶ የሚሆኑ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በቦታው የተገኙት የድርጅቱን 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አስመልክቶ በተዘጋጀ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ለመሳተፍ ነው፡፡

በረዶ ቀላቅሎ በሚወርደው ዝናብ እንጦጦ ጋራ ላይ ወጥቶ ችግኝ መትከል አዳጋች ቢሆንም፣ ሠራተኞቹ በስፍራው ተገኝተዋል፡፡ አንዳንዶች አልፎ አልፎ ከሚታዩት ዛፎች ሥር ለመጠለል ሞክረዋል፡፡ የቀረ ይቅር ብለው ያመጣቸውን ኮስተር መኪና ፍለጋ የሄዱም ነበሩ፡፡

ከአሁን አሁን ያባራል በሚል ተስፋ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ቢጠብቁም እልህ የተያያዛቸው ይመስል ዝናቡ በማባራት ፈንታ በተቃራኒው እየበረታ ሄደ፡፡ ነገሩ ያላማራቸው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ መሃል ገብተው ስለ ፕሮግራሙ ገለፃ ይሰጡ ጀመር፡፡ ሰዎቹም በሞራል ወደ ሥራ አስኪያጁ ተጠግተው አዳመጡና የተሰጣቸውን ችግኝ መትከል ያዙ፡፡ በዝናብ የራሰው መሬት እያዳለጣቸው የሚወድቁ ነበሩ፡፡ አንዱ አንዱን ለማትረፍ ሲሞክር በዚያው ይወድቃል፡፡ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ሳይቀሩ ወድቀዋል፡፡

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ችግኝ መትከል ቀርቶ ከቤት መውጣት ከባድ ቢሆንም የነበረው መነሳሳት ደስ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ባለፈው ዓመት ክረምት ነበር፡፡ ክረምት በገባ ቁጥር በዘመቻ ችግኝ መትከል የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ እንደ አንድ የማኅበራዊ ግዴታ መወጫ አድረገው በየዓመቱ ችግኝ መትከልን ልምዳቸው ያደረጉ ድርጅቶችም ጥቂት አይባሉም፡፡ የክረምቱ ዝናብ ሳይበግራቸው በየጋራው ችግኝ መትከል የሚጠይቀውን ጥንካሬና ሞራል መንከባከቡም ላይ ካልታከለ ነገሩ ውሀ ቅዳ ውኃ መልስ አይነት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በየዓመቱ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል የሚበቅሉት ሰባት ከመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ይህንን የተመለከቱ አንዳንዶች የችግኝ ተከላ ፕሮግራሞችን ‹‹ችግኝ ቀበራ›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡

ከምድር ወገብ በዜሮና በ23 ዲግሪ መካከል የምትገኘው ኢትዮጵያ ሞቃት የአየር ንብረት ካላቸው አገሮች ተርታ ነች፡፡ አማካይ አመታዊ የዝናብ መጠኗም ከ1,000 እስከ 2,200 ሚሊ ሜትር ሲሆን፣ ለግብርናና ለኑሮ የተመቸች መሆኗ ይነገርላታል፡፡ ልምላሜ ሌላኛው የአገሪቱ መገለጫ ስለመሆኑም ብዙ ተብሏል፡፡ ተዘምሮላታልም፡፡ ከሶስቱ የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አንዱ አረንጓዴ የሆነውም የአገሪቱን ልምላሜ በተምሳሌትነት በመወከል ነው፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ለአየር ንብረት ለውጥ በእጅጉ የተጋለጠች ስለመሆኗ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን፣ በየአስር አመቱ የሚከሰተውና ብዙዎችን ለከፋ ረሀብ እንስሳትን ደግሞ ለእልቂት የሚዳርገው ድርቅ፣ ጊዜውን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ጎርፍና ሌሎችም አገሪቱ በድህነት እንድትታወቅ እያደረጉ ያሉ ቤተኛ ችግሮች ናቸው፡፡

በአገሪቱ የሚታዩ የአካባቢ ችግሮች ዘርፈ ብዙ ሲሆኑ፣ የአፈር መሸርሸር፣ የደን መመናመን/መጨፍጨፍ፣ የውኃ መበከል፣ የአየር መበከል፣ የተፈጥሮ ሀብትና የብዝኃ ሕይወት መመናመን ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ የፎረም ፎር ኢንቫይሮመንት ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ገብሩ ይናገራሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ አገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ችግር ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ለአየር ንብረት ለውጡ መከሰት ያደረጉት አስተዋፅኦ ከቁጥር የሚገባ ነው ባይባልም የችግሩ ዋነኛ ተጠቂዎች መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ትልቁ የዓለም ሥጋት ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ ከሆኑት መካከል የደን መመንጠር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ለችግሩ ያለው ድርሻም 20 በመቶ ነው፡፡ እንደአሁኑ የህዝብ ቁጥር ባልጨመረበት እርሻ ባልተስፋፋበት ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ክፍል በደን የተሸፈነ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ በተለይም የቡናና ሻይ፣ የቅባት እህሎች ማገዶና ከሰል፣ የሰደድ እሳት፣ ልቅ ግጦሽና የመሠረተ ልማት መስፋፋት የአገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመናመን አድርጓል፡፡

የደን መጨፍጨፍ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረባቸው አመታት በየአመቱ ከ150 እስከ 200ሺሕ ሄክታር ደን ይመነጠር ነበር፡፡ የአገሪቱ ጠቅላላ የደን ሽፋንም ወደ 3 በመቶ ወርዶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በደን መመንጠር ምክንያት ይፈጠር በነበረው የአፈር መሸርሸርም በየአመቱ አንድ ቢሊዮን ሜትር ኩብ አፈር ታጥቦ ወደ ጎረቤት አገሮች ይሄድ እንደነበር ከአለም የምግብ ድርጅት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ግብርናን መሠረት ላደረገው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ምን ያህል ከባድ ቀውስ እየፈጠረ እንደሚገኝ ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአለም አገሮች ዘግይተውም ቢሆን የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው ለአረንጓዴ ልማት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፈው ከመመንጠር ለተረፉት የጥበቃ፣ የተመናመኑትን ደግሞ መልሶ የማልማት ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ አባል በመሆን ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት የአገሪቱ መንግሥትም ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 44 ላይ ስለአካባቢ ደህንነት መብት ከተቀመጠው ድንጋጌ በተጨማሪ የተለያዩ የአካባቢና ደን ጥበቃ ላይ ያተኮሩ አዋጆችና የፖሊሲ ግቦችን በማስቀመጥ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ የደን ጥበቃና ልማት ፕሮግራሞችን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በሥነ ምህዳር ጥበቃ ረገድ የሚሰጡትን ጥቅም ማጎልበት፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል ናቸው፡፡

የደን ሀብትና አካባቢን ለማልማት፣ ክጥፋት ለመከላከልና ለመንከባከብ ማህበረሰቡን ማደራጀት፣ በደን እርሻ ልማት እንዲሳተፍና ከደን ልማትና ከተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ከሚገኘው ጥቅም ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የደን ልማትን ለማስፋት እየተተገበሩ ከሚገኙ እስትራቴጂዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የተለያዩ የጥበቃና የልማት ስራዎች እየተሠሩ ባለበት በአሁኑ ወቅትም በየአመቱ የሚመነጠረው የደን መጠን ቀላል አይደለም፡፡ ከ1993 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ 92,000 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ደን በየዓመቱ እንደሚመነጠር፣ በእነዚህ ዓመታት በደን ልማት መጨመር የተቻለው የደን መጠን ግን ከ19000 ሄክታር እንደማይበልጥ ከአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እየተሠራ ያለው ሥራ አዝጋሚና ከውጤቱ ይልቅ የሚደርሰው ጥፋት ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡

   በአዲሱ የደን ትርጓሜ መሰረት፣ ደን በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ዛፎች ያሉበት፣ ቢያንስ የቦታው 20 በመቶ በዛፍ የተሸፈነ እንዲሁም የዛፎቹ ቁመት ከሁለት ሜትር የማያንስ ማለት ነው፡፡ ትርጓሜው ከዚህ ቀደም ከደን የማይቆጠሩ እፅዋት በደን ስም እንዲያዙና በአገሪቱ የደን ድርሻ ላይ መጠነኛ ጭማሪ እንዲኖር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የደን ሽፋን 15.5 በመቶ ሲሆን፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በጀት ዓመት ወደ 20 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይህም ሆኖ ቁጥሩ የተጋነነ እንደሆነና ትክለኛውን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የማይወክል እንደሆነ በመከራከር መረጃውን የማይቀበሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡

አገሪቱ በየአመቱ ከምታሳየው የደን ልማት ይልቅ የሚመነጠረው ትልቅ ድርሻ እያለው የደን ሽፋኗ ጨምሯል ብሎ ሪፖርት ማድረግ መሠረተ ቢስና ከእውነታው ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመግለፅ የአገሪቱ የደን ሽፋን አላደገም የሚሉ አሉ፡፡ 15.5 በመቶ ደርሷል በሚለውም አይስማሙም፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የአገሪቱን የደን ሽፋን በተመለከተ የሚሰጡት ቁጥርም የተለያየ ነው፡፡

የደን ሽፋን መጨመር ለአገሪቱ ከሚሰጠው ሥነምህዳራዊ ጥቅሞች ባሻገር ያደጉት አገሮች አረንጓዴ ልማትን ለመደገፍ ባዘጋጁት የካርበን ፋይናንሲንግ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገሮች ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት ከፍተኛ የበካይ ጋዝ መጠን የኦዞን ንጣፍ እንዲሳሳ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲፈጠር፣ ሙቀት እንዲጨምር፣ ግግር በረዶዎች እንዲቀልጡ፣ የባህር ከፍታ እንዲጨምር፣ የተበከለ ዝናብ እንዲዘንብና ሌሎችም ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ነው፡፡

የችግሩ መነሻ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት አገሮች ቢሆኑም፣ መጠኑ ይለያይ እንጂ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እነሱን ጨምሮ አገሮችም ናቸው፡፡ ካርበን ፋይናንሲንግ በአገሮቹ የሚለቀቀውን የበካይ ጋዝ መጠን ማመቅ የሚችል ደን ለሚያለሙ አገሮች ገንዘብ የሚሰጥበት አሠራር ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ካደጉት አገሮች የሚሰጡ ድጋፎች ሁሉ በካርበን ፋይናንስነት የሚያዙ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ በ2000 ከተጀመረ እስካሁን 187 ሚሊዮን ቶን የካርቦን ልቀት ወደ ከባቢ አየር እንዳይገባ መከላከል ተችሏል፡፡ ከአገሮችና ትልልቅ ተቋማት በሚገኝ ፈንድ የሚታገዘው የካርበን ፋይናንሲንግ ፕሮግራም የሚያስተገብረው  የዓለም ባንክ ሲሆን፣ 15 የካርበን ፕሮጀክቶችን ወስዶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለመሆን የደን ምንጣሮና መሳሳትን ማስቀረት ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን የሚሠሩ  የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትም አሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል ሬድ ፕላስ አንዱ ነው፡፡

ሬድ ፕላስ 70 አባል አገሮች ሲኖሩት፣ ኢትዮጵያ አባል ከሆነች አራት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ብሔራዊ አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ አንድ አገር በካርበን ፋይናንሲንግ ተጠቃሚ ለመሆን ሦስት ምዕራፎችን ማለፍ አለባት፡፡ እነዚህም የዝግጅት፣ የኢንቨስትመንትና የክፍያ ምዕራፎች ናቸው፡፡ አገሪቱም ከዓለም ባንክና ከኖርዌይ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የመጀመሪያውን የዝግጅት ምዕራፍ ጨርሳለች፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ መሟላት ካለባቸው ዋናዋና ተግባራት መካከል ስትራቴጂ ማዘጋጀትና የአገሪቱን የካርበን ልቀት መለካት ይጠቀሳሉ፡፡

በደን ምንጣሮ ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ከባቢ አየር የምትለቀው ዓመታዊ የካርበን ልቀት 18 ሚሊየን ቶን ሲሆን፣ 4.7 ሚሊየን ቶን ወደ ከባቢ አየር እንዳይገባ ተከላከላለች፡፡ ‹‹ይህንን ለክቶ ማሳወቅ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ከአፍሪካ አገሮችም እኛ የመጀመሪያ ነን፡፡ የልቀት መጠኑን ለማውጣት መረጃዎች ስንሰበስብ የነበረው በሳተላይት በመታገዝ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክቱ ከመተግበሩ በፊት የነበረው የካርበን ልቀትና ፕሮጀክቱ መተግበር ከጀመረ በኋላ የሚኖረውን የልቀት መጠን ለመለየትና ምን ያህል ውጤታማ መሆን እንደተቻለ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ ወደ ፊት ሥራ እየሥራን በየሁለት ዓመቱ የልቀት መጠኑን የምንለካበት የልኬት ሥርዓትም ዘርግተናል፤›› በማለት ወደ ክፍያ ሥርዓቱ ለመግባት የመጀመሪያውንና ከባዱን መስፈርት ማሟላት መቻሉን ይገልፃሉ፡፡ እንዲሁም ዓለም ባንክ ያስቀመጣቸውን 34 መመዘኛዎች ማሟላት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የደን ጥበቃ ሥራውን ለማከናወን ተመራጩ መንገድ ማኅበረሰቡን መደገፍ የሚችል የተለያዩ የቢዝነስ ይዘት ያለው አሳታፊ የደን ጥበቃ አስተዳደር ነው፡፡ ‹‹ይህ ደንን ለመጠበቅ ዋና መሳሪያችን ነው፡፡ በዚህ የ15 ዓመት ልምድ ያለን ሲሆን፣ ይህንኑ ማስፋት እንፈልጋለን፤›› ይላሉ ዶ/ር ይተብቱ፡፡ ላሉት ደኖች ጥበቃ ማድረግ፣ የጠፉትን ደግሞ መልሶ መተካት የተያዘው ስትራቴጂ ዓላማ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ተራራማ አገሮች ደን ወሳኝ ፋይዳ አለው፡፡ በደን ውስጥ ውኃ፣ ብዝኃ ሕይወት፣ ንፁህ አየር፣ ውበት፣ ቱሪዝም ሌሎችም በርካታ ጥቅሞች አሉ፡፡ ድርቅን በመከላከል ረገድም የማይናቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ይሁንና ባለው የግንዛቤ ችግር በርካታ ደኖች ተመንጥረው አልቀዋል፡፡ በአገሪቱ ካለው 17 ሚሊዮን ሄክታር ደን፣ በየዓመቱ ግን 92000 ሄክታር ደን ይመነጠራል፡፡ ‹‹ከዓመት ዓመት ብዙ ደን እናጣለን፡፡ የደን ጥቅም የገባን ቀን ለእያንዳንዱ ደን ስስት ይኖረናል›› የሚሉት አስተባባሪው፣ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል በአማራና በትግራይ እንዲሁም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል በሀረርጌ የነበሩ ደኖች ተጨፍጭፈው ማለቃቸውን ይናገራሉ፡፡

እነዚህን ደኖች ወደ ነበሩበት ለመመለስና ላሉት ደግሞ ጥበቃ ማድረግ አገሪቱ በደን ልማት ከምታገኛቸው ጥቅሞች ባሻገር በካርበን ፋይናንስ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ በካርበን ፋይናንስ ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው በተሰራ ስራ መጠን ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሄክታር የሚለማው ደን ምን ያህል በካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ከመግባት እንደሚያግድ ተሰልቶም ክፍያ ይታሰባል፡፡

እንደ ዶ/ር ይተብቱ ገለፃ፣ አንድ ሄክታር ደን ከ300 እስከ 400 ቶን ካርበን የመያዝ አቅም አለው፡፡ ክፍያው የሚፈፀመውም በቶን እየተሰላ ነው፡፡ በቶን የሚታሰበው ዋጋ ግን ከጊዜ ጊዜ ይዋዥቃል፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረ አካባቢ ዋጋው በቶን እስከ 30 ዶላር ድረስ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በጣም አሽቆልቁሏል፡፡ ‹‹ዓለም ባንክ በቶን አምስት ዶላር እከፍላችኋለው እያለን ነው፡፡ ነገር ግን በጣም ትንሽ በመሆኑ እንደራደራለን፡፡ ገበያው ግን በሳንቲም ቤት ሁሉ ወርዷል፡፡ ፖሊሲው ጠንከር ሲል ዋጋው ይጨምራል፡፡ ሲላላ ደግሞ ይቀንሳል፤›› በማለት የካርበን ገበያውን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

በአገሪቱ በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ መተግበር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ተስፋ ሰጭ ጅምሮችም እየታዩ ነው፡፡ በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የማጃንግና በደቡብ ክልል የሚገኘው የሸካ ደን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ የተመዘገቡ የአገሪቱ ኩራት ናቸው፡፡ ሌሎችም በርካታ ጥብቅ ደኖች ይገኛሉ፡፡ በ23000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈው የሸካ ደን ከትሮፒካል ፎረስት ይመደባል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙና ዝርያቸው በመመናመን ላይ ያሉ እንደ ቀረሮ ያሉ ዛፎች መገኛ ነው፡፡ በከፋ ማኅበረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሉላ ዛፍም የደኑ አካል ነው፡፡

ከኢሉአባቦራ ተነስቶ እስከ አኝዋክና ቤንች ማጂ የተዘረጋው ማጃንግ ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን ነው፡፡ ከ500 እስከ 2500 ሜትር ከባህር ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ከሞቃት እርጥበታማ የደን ዝርያ የሚመደብ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ 35 ብርቅዬ ዕፅዋትና እንስሳት መኖሪያ እንደሆነ ከመልካ ኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

እነዚህ ደኖች አገሪቱ በካርበን ፋይናንስ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያደርጓት ናቸው፡፡ ይሁንና በደን ሽፋናቸው ከሚታወቁ የዓለም አገሮች አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ‹‹አነስተኛ ደን ካላቸው አገሮች አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ በካርበን ፋይናንስ የተሻለ ተጠቃሚ ነች፡፡ ነገር ግን የአገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ መጠን መጨመር ግድ ያላል፤›› ብለዋል ዶክተር ይተብቱ፡፡

የካርበን ፋይናንስ ውጤታማነትና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች የሚኖረው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚሉ የተለያዩ መከራከሪያ ነጥቦችን  ይደረድራሉ፡፡ በፕሮግራሙ የሚገኘው ገቢ ከወጪው ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ባለሙያ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ሲያልፍም የአገሪቱ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት የተዘበራረቀና ‹‹ይሄ ለግጦሽ ይሄ ለግብርና ተብሎ የተደለደለ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ ስለዚህም የእርሻ ቦታዎች ለደን የሚውሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል በመግለፅ፣ ካርበን ፋይናንስ ከዚህ አንፃር ሲገመገም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ፡፡

እሳቸው ይህንን ቢሉም የሬድ ፕላስ አስተባባሪው ዶ/ር ይተብቱ፣ ከደን ልማት የሚገኘው ጥቅም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ያህል እንደሆነ፣ ‹‹የደን ሽፋን መጨመሩ የአገሪቱን የሥነ ምህዳር ሚዛን ማስጠበቅና በዚያው መጠን ደግሞ ገቢ የሚገኝበት ነው፡፡ አዋጭ ነው አያዋጣም የሚል ጥያቄ የሚያስነሳም አይደለም፤›› በማለት ተደራራቢ ጥቅም እንጂ ጉዳት ሊኖረው እንደማይችል በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡

አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው የአየር ንብረት ለውጥ የአለም አገሮች ወቅታዊ የመወያያ ርእስ ነው፡፡ የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ያወጣው አንድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በከባቢ አየር ውስጥ ሚገኘው የካርበንዳይኦክሳይድ ክምችት ከቅድመ ኢንዱስትሪ ጊዜ ጀምሮ ሲሰላ በ30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም እስከ ሞት ለሚያደርሱ የተለያዩ የጤና ችግሮች መከሰት ምክንያት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት ባላቸው አደጋዎች 600,000 ሞት ተመዝግቧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ አገሮች የተከሰቱ ናቸው፡፡

ናሽናል ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽንን ዋቢ አድርጎ የፃፈ አንድ ፀሐፊ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእንስሳትና ዕፅዋት ዝርያዎች ከምድረ ገፅ ሊጠፉ እየጨመረ በሚሄደው የሙቀት መጠን ሳቢያ እ.ኤ.አ በ2040 የአርክቲክ ግግር በረዶዎች ሙሉ ለሙሉ ሊቀልጡ እንደሚችሉ አብራርቷል፡፡ በሚደርሰው የከባቢ አየር ብክለት ኦክስጅን ቢጠፋ፣ ዓለምን ለስድስት ወራት በአርቲፊሻል ኦክስጅን ለማቆየት 38 ትሪሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅም የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ይህም የአየር ንብረት ለውጥ በዋዛ የሚታይ ሳይሆን ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ሁሉ የተቃጣ እልቂት እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ይህንን አደጋ ለመቀነስ የሚደረግ ርብርብ ሁሉ ተገቢና ዓለምን መታደግ ነው፡፡ ካርበን ፋይናንስም የዚሁ ተግባር አካል ነው፡፡ ድጋፍ የሚያደርጉ አገሮችም ተግባራቸው በለጋስነት ብቻ የሚታይ ሳይሆን በከባቢ አየር ላይ ላደረሱት ብክለት እንደ ካሳ ነው፡፡ ይህ የብዙሃኑ እምነት ቢሆንም፣ ከሰሞኑ አሜሪካ የአየር ለውጥ ስምምነትን እንደማታፀድቅ ማሳወቋ ግርታ ፈጥሯል፡፡