Skip to main content
x

ሕገ መንግሥቱና የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረክርስቶስ

በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሲናገሩ ‹‹እኔ ለአዲስ አበባ ጉዳዬም አይደል፣ ለሐዋሳ ጉዳዬም አይደል፣ ለአዳማ ጉዳዬም አይደል፣ እኔን የሚያሳስበኝ የገጠሩ ሕዝብ ኑሮ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህንን የተናገሩት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የሥልጣን ዘመናቸው ላይ ነበር፡፡

ከላይ የተጠቀሰው አባባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሩት በርካታ ዓመታት በኋላ፣ ዛሬ በተጨባጭ በመላው ኢትዮጵያ በክልልም ሆነ በከተማ ደረጃ የሚታየው ዕድገት በየጊዜው በመንግሥትም ሆነ በምሁራን መገምገሙ ለሰላምም ለሁሉም ነገር በእጅጉ ጠቃሚ ነገር ይመስለኛል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት በአዲስ አበባ የታየው ዕድገት ከመላው አገሪቱ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል? ወደፊትስ እንዲህ መቀጠል አለበት ወይ? የሚለው ጉዳይ በእኔ እምነት ከሁሉም በላይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ አበባን ልዩ ከሚያደርጋት ባህርይዋ አንዱና ዋነኛው ከአምስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደሚኖርባት መታመኑ ሲሆን፣ የሚቀጥለው ትልቁ ከተማ አዳማ ደግሞ የሕዝብ ቁጥሩ ከ400 ሺሕ ያልዘለለ ነው፡፡ ሌሎች በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች የሕዝብ ቁጥራቸው ከአዲስ አበባ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡

በተለይ ከላይ እንደተጠቀሰው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ መሪ እንዳስቀመጡት ሳይሆን፣ የተገላቢጦሽ አዲስ አበባ እንዴት ልታድግ ቻለች የሚለውን ጉዳይ ማንሳት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የአዲስ አበባ ዕድገትና የገንዘብ እጥበት

በአገራችን የተለያዩ ክልሎች ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና በእጅጉ እንደተስፋፉ መንግሥትም ያመነው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በክልል ከተሞችና መስተዳድሮች ያሉ ሙሰኞች በተለያዩ መንገዶች ጤነኛ ባልሆነ መንገድ እጃቸው የገባን ገንዘብ እዚያ ክልላቸው መልሰው ወደ ልማት ቢቀይሩት በቀላሉ የኅብረተሰቡን ትኩረት መሳባቸው ስለማይቀር፣ ገንዘቡን ይዘው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሰፊና ምንም በማያውቃቸው ከተማ ወደ ቋሚ ሀብትነት ይለውጡታል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚከሰተው ችግር በርካታ ነው፡፡ አንደኛ ያ ገንዘብ የተሰረቀበት ማኅበረሰብ ውስጥ ቢሽከረከር በተለያየ መንገድ ለማኅበረሰቡ ጠቀሜታ መስጠቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ከዕይታ ለመራቅና ለመደበቅ አዲስ አበባ ውስጥ ወጪ ከተደረገ እነዚህ ሰዎች ከተጠያቂነት ለመዳን ሰፊ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ሁለተኛ ተገቢ ያልሆነ የካፒታል ፍልሰት ይፈጥራል፡፡ ሦስተኛ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ አላስፈላጊ የኑሮ ውድነት ይፈጠራል፡፡ በተለይ በቋሚ ገቢ ለሚተዳደሩ ደመወዝተኞች ኑሮ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አራተኛ የአዲስ አበባ መስተዳድርም ይህ ጤነኛ ያልሆነ ገንዘብ በተለያየ መንገድ እጁ ስለሚገባ፣ ለመንገድና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ስለሚጠቀምበት የከተማዋ ዕድገት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ዜጎች ጤነኛ ባልሆነ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ወደ ቋሚ ሀብትነት ስለሚቀይሩ ገንዘቡ ታጠበ ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አዲስ አበባ የገንዘብ እጥበት ማዕከል ሆናለች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት አፋጣኝና ተገቢ ዕርምጃ ካልወሰደ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ዜጎች ላይ ቅሬታ ማስነሳቱ ስለማይቀር የመጨረሻ ውጤት ጥሩ አይሆንም፡፡

በአዲስ አበባ ሀብት ያፈራ የሚኖረው መብት

በአዲስ አበባ ሀብት ያፈራ ሰው ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ለንብረቱ መተማመኛ የሚፈጥርለት ከመሆኑም በላይ፣ ዋጋው በየጊዜው የማደግ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ደግሞ ይህ ዜጎች ገንዘባቸውን ወደ አዲስ አበባ ይዘው እንዲፈልሱ የሚገፋፋ ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች የተገነባ ቋሚ ሀብት ዋጋ የመጨመር ዕድሉ ከአዲስ አበባ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፡፡

አዲስ አበባ ያለ ቋሚ ሀብት ጥበቃ የማግኘት ዕድሉ

አዲስ አበባ ያለ ሀብት ከተማዋ የማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ በመሆኗና በርካታ ሕግ አስከባሪ ተቋማት ስላሉ፣ ለቋሚ ሀብት የሚገኘው ጥበቃ በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች ያሉ ባለንብረቶች ንብረታቸውን የሚጠብቅላቸው የተጠናከረ የፀጥታ ኃይል ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ በብዙ አገሮች እንደሚደረገው ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ በቂ ትጥቅ የላቸውም፡፡ ቢኖራቸውም ትጥቁን በመጠቀም በሌሎች ላይ ጉዳት ቢያደርሱም ተጠያቂነቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ እስከ አሁን ራሱን ከጥቃት (ያለ ሕግ አስከባሪ አካላት) በበቂ ሁኔታ የተከላከለ ባለሀብት የለም፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳታገኝ ትልቅ ፈተና ሊሆን  የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ምክንያቶች እንውሰድና ወደ ሕገ መንግሥቱ ስንመጣ ዜጎች በማንኛውም ክልል ሀብት ማፍራት እንደሚችሉ የሚደነግግ ቢሆንም፣ ይህ ሁኔታ ግን መሬት ላይ ወርዶ በተግባር በበቂ ሁኔታ መታየት አልቻለም፡፡ እውነቱን ለመናገር አዲስ አበባ ማንኛውም ዜጋ እንደ ልቡ መሬት አግኝተው ወደ ልማት መግባት እንደተቻለው ሁሉ፣ በገጠሪቷ ኢትዮጵያም ያለ ገደብ ዜጎች መሬት እያገኙ በልማት ቢሰማሩ ዛሬ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተናገሩት በዋናነት የገጠሩ ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆን ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አንዳንድ ዕድለኛ  የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በደርግ ዘመን በነፃ ያገኙትን መሬት በአሥር ሚሊዮኖች ሸጠው የንጉሥ ኑሮ መኖር የቻሉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፣ መንግሥት ቆም ብሎ ይህ ገንዘብ ከየት መጣ ብሎ አፋጣኝ እርምት መውሰድ ባለመቻሉ ነው፡፡

አዲስ አበባ ቱሪስቶች በብዛት የማይታዩባትና ከፍተኛ የሆነ ምርት እያመረተች ወደ ዓለም ገበያ በመላክ ገንዘብ ማግኘት ያልቻለች ከተማ ሆና፣ ይህ ሁሉ ሀብትና ግንባታ ከየት መጣ ብሎ መጠየቅ ማንኛውም ጤነኛ አዕምሮ ያው ሰው ሊያደርገው የሚገባ ተግባር ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ከተማዋ ምንም ዓይነት የፌዴራል ድጎማ ስታገኝ ሌሎች ክልሎች  ደግሞ ከፍተኛ  የሚባል ድጎማ እያገኙ፣ አዲስ አበባ ከክልል ከተሞች በላቀ ሁኔታ እንዴት ልታድግ ቻለች ብሎ መጠየቅ ደግሞ ሌላው ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡

አንድ ከውጭ አገር የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች እያስመጣ የሚሸጥ ነጋዴ ሸቀጡን የሚሸጠው በመላው አገሪቱ ሆኖ ሳለ፣ ያገኘውን ትርፍ እዚህ አዲስ አበባ ብቻ ወደ ቋሚ ሀብትነት የሚለውጠው ከሆነ ይህ ጤነኛ ነገር ነው ወይ? ያገኘውስ ትርፍ ሌሎች ክልሎች ሄዶ ወደ ቋሚ ሀብትነት ለመለወጥ ችግሩ ምንድነው፡፡

አንድ አንደኛ ደረጃ ኮንትራክተር በርካታ ሚሊዮኖች በሚያወጡ የልማት ሥራዎች ይሳተፋል፡፡ ከዚያ የሚያገኘውን የተጣራ ትርፍ ወደ ቋሚ ሀብትነት ሲለወጥ በመላው አገሪቱ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ኢንቨስት ለማድረግ ምን አገደው? አገሪቷ የምታውቀው በዋናነት የእርሻ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝ ነው፡፡ ከዚህ የሚገኘው የተጣራ ትርፍ ወደ ቋሚ ሀብትነት የሚለወጠው የት ነው?

እነዚህንና ሌሎችም ጥያቄዎችን በማንሳት ተገቢውን እርምት ለማድረግ የምንቆጥበው ጊዜ መኖር የለበትም፡፡ እኔ እንደ አንድ ዜጋ እንኳን ግለሰቦች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያከናውነው የኢንቨስትመንት መጠን ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ሳነፃፅር በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡

በጣም የሚገርመው ጉዳይ አዲስ አበባ ውስጥ አንዱ የገነባው ሕንፃ እስከ ሦስተኛ ፎቅ ድረስ ብቻ ተከራይቶ ሌላው ፎቅ ባዶውን ሆኖ፣ ከጎኑ ሌላ ባለሀብት ረጅም ሕንፃ ሲገነባ ይታያል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ሌላ ከተማ ሄዶ የልማት ሥራ አያከናውንም፡፡ ይህ ጉዳይ ሰፊ ምርምርና ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ አገራችን ያላትን ውስን የገንዘብ ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ ካላዋልን ዕድገት እንዴት ሊመጣ ይችላል?

በእኔ እምነት ለዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ (ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደተሞከርኩት) የሕገ መንግሥት ክፍተቶች በመሆናቸው፣ ይህ ጉዳይ በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያለፈውን ሩብ ክፍለ ዘመን እንዳሳለፍነው፣ ሌላ ሩብ ክፍለ ዘመን ይህንን ችግር ይዘን ከቀጠልን የሚፈጠረው ማኅበራዊና አገራዊ ቀውስ ጥሩ አይመስለኝም፡፡

እዚህ ላይ አንድ ጥሩ ነገር አለ ብሎ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በአገራችን እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ መንደሮችና የባቡር መሠረተ ልማቶች ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ በመሠረቱ የመቀየር አቅም አላቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ የኢንዱስትሪ መንደሮች በከፍተኛ ደረጃ ከተሞች እንዲያድጉ የሚያስችሉ በመሆናቸው፣ በዚህ ዘርፍ ተግተን ከሠራን በአገራችን ባሉ ከተሞች ተቀራራቢ ዕድገት እንዲኖር ይረዳል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ ተግባር ጋር በተጓዳኝ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የዚህ ሒደት አካል ለመሆን በራስ መተማመናቸውን እንዲያሳድጉ ተገቢውን ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የክልል ባለሥልጣናትም የክልል ሕጎችም ከዚህ በጎ ተግባር ጋር አብረው መራመድ መቻላቸው በበቂ ሁኔታ መመርመር አለበት፡፡ የክልል ባለሥልጣናት በምንም ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙሪያ ሊደረግ የነበረውን የልማት ሥራ የማደናቀፍ ውሳኔ እንዳይወስኑ ተገቢው ሥራ መሠራት አለበት፡፡

ሌላው ለከተሞች ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚደረገው አሁን የተጀመረው የባቡር ልማት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ደጋግሜ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት ከባቡሩ ልማት ጎን ለጎን ሌሎች የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን በተገቢው ፍጥነት ማድረግ ከተቻለ፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ያለ ችግር እየተንቀሳቀሱ የሚሠሩ ከሆነ ከተሞች ያድጋሉ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይፋጠናል፣ ባቡር ካሉት በርካታ ጥቅሞች ቀጥሎ ያለው ማኅበራዊ ፋይዳ በእጅጉ የጎላ ነው፡፡ እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ዜጋም ሩቅ ቦታ በባቡር መጓዝ ስለሚችል ከተሞች እንዲያድጉ ይረዳል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው አዲስ አበባ የፌዴራል በጀት ሳይመደብላት በራሷ ገቢ ብቻ እንዴት በከፍተኛ ፍጥነት ልታድግ ቻለች? እንዴት እንደ ሸንበቆ ፈጣን ዕድገት አመጣች? የሚለው ጉዳይ ሰፊ ምርምር የሚሻ ቢሆንም፣ ሌሎች ክልሎች የራሳቸውን ገቢ እያመነጩና የፌዴራል በጀት እያገኙ እንዴት ዕድገታቸው አዝጋሚ ሆነ የሚለውም  ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም. በተከሰተው ሕዝባዊ አመፅ መሠረቱ ከአዲስ አበባ ውጪ መሆኑ ሌላው ምርምር የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ በተለምዶ በአመዛኙ ባለፉት ሥርዓቶች ላይ አመፅ ከዋና ከተማ ነበር የሚመነጨው፡፡ የ2008 አመፅ የተካሄደበት ጊዜ ደግሞ በክረምት ወቅት ተማሪዎች ትምህርት ቤት በሌሉበት፣ ገበሬው በከፍተኛ ሥራ ተወጥሮ ባለበት ጊዜ መካሄዱ ደግሞ በኢትዮጵያ የአመፆች ታሪክ ልዩ ያደርገዋል፡፡ አመፅ በአመዛኙ የሚካሄደው በየካቲት ወር ገደማ ሲሆን፣ ይህም ምክንያቱ አንደኛ ተማሪዎች በበቂ ሁኔታ የሚተዋወቁበት ጊዜ በመሆኑ፣ ሁለተኛ በገጠር ደግሞ ገበሬው የግብርና ሥራውን አጠናቆ ፋታ የሚገኝበት ወቅት ስለሆነ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለማንሳት እስከ አሁን ተመራጭ ወቅት ነበር፡፡

ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ እንመለስና ሕገ መንግሥቱ በእኔ እምነት ለአዲስ አበባ (ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች) ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በክልል የሚኖሩ ሕዝቦች የአዲስ አበባን ምሥል በቴሊቪዥን ባዩ ቁጥር ወይም ወደ አዲስ አበባ ብቅ ብለው ሲመለከቱ ይህ ዕድገት እኛ ዘንድ ለምን አልመጣም የሚል ጥያቄ እያነሱ ያለበት ወቅት እንደሆነ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይቶች ሲደረጉ በየጊዜ የምንሰማው ነው፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች በሕንፃ ሲታጠሩ የክልል ከተሞች ደግሞ የቢጫ ጄሪካን ሠልፍ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አሀዳዊ ያልሆነ የአስተዳደር ሥርዓትና አሐዳዊ የሆነ የገንዘብ ሥርዓት በተገቢው ላጠናው ሰው ትልቅ ቀውስ እየፈጠረ ነው፡፡ ክልሎች በክልላቸው የተገኘን ገንዘብ ከክልላቸው እንዳይወጣ ለመከላከል የሚችሉበት ምንም ዓይነት አሠራር አልተዘረጋም፡፡

አሁንም በድጋሚ ለማሳሰብ የምፈልገው ዜጎች ያለ ገደብ እንደ ፍላጎታቸው፣ በመሉ በራስ መተማመን ከቦታ ቦታ ሄደው ሥራቸውን መሥራት ካልቻሉ ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ ዕድገት መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያሳለፈው 26 የሥልጣን ዓመታት የትኛው ተግባር ጥሩ እንዳልሆነ፣ የትኛው ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ መለየት ከተሳነው በራሱ ላይ ችግር መጋበዙን መገንዘብ አለበት፡፡

ከተሞች ደግሞ ማደግ ካለባቸው ትልቁ ፍጆታ ምግብ በመሆኑ ከአነስተኛ ማሳ ወጥተን በሰፋፊ እርሻዎች፣ ዋጋው ርካሽ የሆነ የምግብ ምርት በበቂ ሁኔታ ከከተሞችና ለኢንዱስትሪ መንደሮች ማቅረብ ካልተቻለ አሁንም ብዙ የተደከመለት ግንባታ ተንገራግጮ ነው የሚቆመው፡፡ አሁን ያለውን የአዲስ አበባ ሁኔታ ብንመለከት ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋጋ ውድነት በስፋት ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ አብዛኛው ገበሬ የሚያመርተው አሁንም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ አሠራር በመሆኑ፣ ለከተሞች የሚቀርበው የምግብ ምርት በእጅጉ አናሳ ነው፡፡ ለዜጎች መቅረብ የሚገባቸው ግን ልክ እንደ ቅንጦት ምርት ለዓመት በዓል ዕለት ብቻ ነው የምናያቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ የዶሮ ምርት እዚህ አካባቢያችን ባሉ የአፍሪካ አገሮች እንኳን በየመንገዱ እየተጠበሰ (እንደኛ አገር ቆሎ ማለት ነው) የሚሸጥ ሆኖ ሳለ፣ እኛ አገር ዶሮ ለመብላት የግድ ሁለት ወር ሙሉ መፆም ይጠበቅብናል፡፡ ለኢንዱስትሪ ሠራተኞች ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነና ኃይል ሰጪ የሆኑ ምግቦችን ማግኘት ካልቻሉ ምርታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በጤናቸው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ግንባታ በሚከናወንበት ቦታ ከፍተኛ የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች ምሳቸውን ዳቦ በሙዝ በልተው ነው ጉልበት ወደሚጠይቁ ሥራዎች የሚሄዱት፡፡ ይህ ሁኔታ የግድ መለወጥ አለበት፡፡

በአጠቃላይ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በከተሞችና በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ያለው ግንኙነት በምንም ሁኔታ ጤነኛ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ ካልተስተካከለ ዕድገትን መመኘት  የዋህነት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡