Skip to main content
x

ሕጉና አተገባበሩ የተራራቁበት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሕግ አስፈጻሚው ግንኙነት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ ተግባራት አሉት፡፡ ሕግ ማውጣት ዓይነተኛ ተልዕኮው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን የሕዝብን ቅሬታ ይሰማል፤ መፍትሔም ይዘይዳል፡፡ አስፈጻሚውን ይቆጣጠራል፡፡ አሳሳቢ የሆኑ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም ውይይት ያደርጋል፡፡ እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚሽከረከረው ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚው አካል ዴሞክራሲያዊ ይሆን ዘንድ እንደምን አድርገው መቆጣጠር እንዳለባቸው ማሳየት ነው፡፡ ነገሩን የበለጠ ለማብራራት እንዲረዳ ባሳለፍነው ሳምንት የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ለሕዝብ ይፋ ያደረገውን ጥናትና በ1994 ዓ.ም. የወጣውን ‘በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች’ የሚለው የኢሕአዴግ የፖሊሲ ሰነድ በመመርኮዝ ሕገ መንግሥቱን ደግሞ ዋና የመገምገሚያ መሥፈረት በማድረግ ነው፡፡ እንደ ነገሩ ሁኔታ የተለያዩ አገሮችን ልምድና ተገቢ መርሆችን የእኛኑ ሕግና አሠራር ለማንጠር እንጠቀማለን፡፡

ፓርላሜንታዊ አሠራርን በሚከተሉ አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ በኢትዮጵያም ቢሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ጥቅል መርሆዎችን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ ሕጎችን ያጸድቃሉ፡፡ ፖሊሲዎችን ያወጣሉ፡፡ በጀት ያጸድቃሉ፡፡ የሕግ አስፈጻሚውም ምክር ቤቱ ባወጣቸው ሕግጋትና ፖሊሲዎች መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ስለሚጠበቅ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ እነዚህም በትክክል ስለመፈጸማቸው ክትትል ማድረግ ተግባራቸው ነው፡፡ ሕግ አስፋጻሚው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣቸውን ሕግና ፖሊሲ ዘወትር መከተል አለበት፡፡ በ1994 ዓ.ም.  የወጣው ‘በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች’ የሚለው የኢሕአዴግ የፖሊሲ ሰነድም ይኼንኑ በሚያጸድቅ መልኩና በጣም በጠንካራ አገላለጽ ሕግ አስፈጻሚው ሁልጊዜም ለምክር ቤቱ ስለሚኖርበት ተጠሪነት  ‹‹ከዚህ ውጭ አንድ ጋት መንቀሳቀስ አይችልም፤ አይገባውምም፤›› ይላል፡፡ በመቀጠልም፣ ዴሞክራሲን የበለጠ ለማጎልበት ሕጎች ሲወጡም ሆነ ከወጡ በኋላ ሕዝቡ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸትም ማረጋገጥም አንዱ ኃላፊነታቸው እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ምክር ቤቶች ከሕግ አውጭነታቸው ባሻገር የሕግ አስፈጻሚውን አካል ይሾማሉ፤ ይሽራሉ፡፡ አስፈጻሚው የሚሠራቸውን በሕጉና በፖሊሲዎቹ መሠረት እየፈጸመ ስለመሆኑ የመከታተል ሥልጣንም ኃላፊነትም ያለባቸው መሆኑን ከላይ አይተናል፡፡ በዋናነትም የሕግ አውጭው ክትትልና ቁጥጥር የሚመነጨው ያወጣቸው ሕጎች፣ ያጸደቃቸው ፖሊሲዎች በትክክል ሥራ ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ካለበት ኃላፊነት ነው፡፡ በሹመት ጊዜም ይሁንታውን የቸራቸውና ቃለ መሃላ ያስገባቸው ባለሥልጣናት ግዴታቸውን ስለመወጣታቸው በቅርበት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሕግ አውጪው ባስቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ያልሠራን ሚኒስተር ወይም ሹመኛ የማባረር ሥልጣን አለው፡፡ ይህም ቢሆን በሕገ መንግሥቱም ከላይ በተጠቀሰው በኢሕአዴግ ፖሊሲ ላይ የተረጋገጠ ነገር ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ስላለመሆኑ ብዙም ጥናትና ምርምር ማድረግ ባይጠበቅም፣ በቅርቡ መንግሥት ይፋ ያደረገው ጥናት በግልጽ ያሳያል፡፡ ከ1994 ዓ.ም. በፊት ስለነበሩት ጊዜያት ግምገማ ያደረገው የኢሕአዴግ ፖሊሲ መደምደሚያው ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምክር ቤቱ ድክመት ፖሊሲው በምክንያትነት ያነሳው የአባላቱ የብቃት ማነስን፣ የቋሚም ይሁን ሌሎች ኮሚቴዎች ሥራቸውን በአግባቡ መምራት በሚያስችላቸው ሁኔታ አለመደራጀታቸውን እንዲሁም ኮሚቴዎቹ በሥራቸው የተለያዩ ባለሙያዎችን በመቅጠር ስለተለያዩ ጉዳዮች  ማብራሪያና የፖሊሲ አማራጮችና ጥናት ማቅረብ የሚያስችል አሠራር አለመዘርጋታቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአስፈጻሚው አካል የሚቀርቡላቸውን ረቂቅ አዋጆች በቅጡ መረዳት እንዳይችሉ ሳንካ ሆኖባቸዋል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሥራቸውን መሥራት የሚችሉት በኮሚቴ ብቻ ሳይሆን በአባል ደረጃም ምክርና ድጋፍ የግድ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው፡፡ ከላይ የተገለጸው ፖሊሲ ከወጣ ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላም ቢሆን በቅርቡ ይፋ የሆነው መንግሥታዊው የጥናት ውጤት እንደመሰከረው (በእርግጥ አገር ያወቀው ጉዳይ ቢሆንም!) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁንም ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በተለይም ደግሞ የአስፈጻሚው አካልን ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ አንፃር በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡

ይኼው ከላይ የተጠቀሰው ፖሊሲ ከ1994 ዓ.ም. በፊት ኢሕአዴግ ለምክር ቤት የሚያቀርባቸውን ሕጎችም ይሁን ፖሊሲዎች ተንትኖ ስላለማቅረቡ፣ ስለምን እንደወጡም ብዙም የሚያብራራ አሠራር ስላለመከተሉ ንስሐ ቢጤ ገብቶ ነበር፡፡ በአባላት አቅም ማነስ፣ በኮሚቴ አደረጃጀት፣ ለምክር ቤቶች ሚና ፓርቲው ይሰጠው የነበረው አነስተኛ ትኩረት ምክንያት ምክር ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል አለመሥራታቸውን ከ15 ዓመታት በፊት አምኗል፡፡

ይሁን እንጂ ፖሊሲው የምክር ቤት አባላት ከፓርቲያቸው ፖሊሲ ያፈነገጠ አስተያየት መስጠትም መያዝም ስለማይችሉ ተጨማሪ አስተያየት መስጠትና ሙያዊ ትንታኔ ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎችን መጋበዝ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጾ ነበር፡፡ የፓርቲውን ፖሊሲ የማይደግፉ የምክር ቤት አባላት በምክር ቤት መቀመጥ አይችሉም የሚል አሠራርና መርሕ ይከተላል፡፡ ነገር ግን አስፈጻሚው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ሊከታተሉ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ የምክር ቤት አባላት የፓርቲያቸው ፖሊሲ ከኅሊናቸው ጋር የሚጋጭባቸው ከሆነ አማራጫቸው ምክር ቤቱን ጥለው መሄድ ብቻ ነውም ይላል፡፡ ፖሊሲው በመቀጠልም ከሕግ ውጭ የሚሠራውን አካል (ባለሥልጣንም ይሁን ሌላ)  በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲያልፍ የማድረግ አስፈላጊነትን ይገልጻል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዜጎች በሥርዓቱ ላይ አመኔታ የሚያሳድሩት እንዲህ ሲሆን ብቻ እንደሆነ በማስረዳት ነው፡፡ ከ15 ዓመታት በኋላ ግን ከዚያው ብዙም ፎቀቅ አለመባሉን ስናስብ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን መገንዘብ አይከብድም፡፡

እንደሚታወቀው፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የሚፈታተን ተግባር በዋናነት   የሚመነጨው ከአስፈጻሚው ነው፡፡፡ ይህንን ባሕርዩን በማረቅ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያስገድዱ ተቋማትን ማቋቋምና ሥርዓትን ማስፈን ደግሞ ከሕግ አውጭው የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው የሕግ አወጣጥ ሒደት በዋናነት ሕጎችን የሚያረቅቀው ወይም የሚያመነጨው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመሆኑ ነገሩ ቀላል ሊሆን አይችልም፡፡

ቢሆንም ግን በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ፓርላማው በተለያዩ ዘዴዎች አስፈጻሚውን ሊቆጣጠር ይችላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አራቱን ብቻ እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ፓርላማው በሚያቋቁማቸው ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች አማካይነት ነው፡፡  የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን በማቋቋም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችንና የሌሎች ተቋማትን ሥራ በመከታተል፣ ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ ወዘተ ቁጥጥር ሊያደረግ ይችላል፡፡ በቅርቡ የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ መንበርን የተረከቡት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከሩሲያ መንግሥት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት የፌዴራል የምርመራ ቢሮና የብሔራዊ ደኅንነት ጉባዔ ኃላፊዎችን በመጥራት የሴኔት ኮሚቴ አባላት ሲጠይቁ እንደነበረው ማለት ነው፡፡ ፓርላማው በኮሚቴም ይሁን በምክር ቤት ሊያደረጋቸው ስለሚገባ ጥያቄዎች የተወሰኑ ነጥቦችን እንጨምር፡፡

በኢትዮጵያ የምክር ቤት አባላት ሚኒስትሮች ሪፖርት በሚያቀርቡበት ወቅት ጥያቄ ሲያነሱ እናያለን፡፡ የተለመደው አሠራር የምክር ቤት አባላት ጥያቄ ለሚመለከተው ሚኒስትር አስቀድመው ጥያቄ ይልኩና ሚኒስትሩ ተዘጋጅቶ፣ ጥያቄዎቹም ተስተካክለውና ማን እንደሚጠይቃቸው ተወስኖ ሚኒስትሩ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ ይጠይቃሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ሚኒስትሮችን በመጥራት መጠየቅ፣ ምርመራ ማድረግ ይችላሉ ሲል በዚህ መንገድ የሚደረገውን ዓይነት ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፡፡ በጀርመን ፓርላማ በሳምንት ለሦስት ሰዓት ያህል የምክር ቤት አባላት ሹመኞችን በመጥራት የሚጠይቁበት የጥያቄ ጊዜ አለ፡፡ በካናዳ ደግሞ ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ ጧት 45 ደቂቃ ምክር ቤቱ አስፈጻሚውን እየጠራ የሚጠይቅበት የጥያቄ ሰዓት አለ፡፡ በእንግሊዝ ደግሞ እያንዳንዱ ሚኒስትር ለሚመለከተው ኮሚቴ በየአራት ሳምንታቱ የአንድ ሰዓት ጥያቄ አለበት፡፡ ምክር ቤቱ ወይም ኮሚቴዎቹ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ነገሮች ብቻ ለሚኒስትሮቹ ሊያሳውቋቸው ይችላሉ እንጂ ቀደመው በተነገሯቸው ጥያቄዎች ላይ ተወስነው መልስ መስጠትና አባላቱም ከእነዚያ ጥያቄዎች  ሳያፈነግጡ መጠየቅ ላይ አይወሰኑም፡፡ የጥያቄዎቹ ዓይነትም ብዙ ጊዜ የመስቀለኛ ጥያቄ ቅርጽ ያላቸው እንጂ በቅርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሊቀመንበር ሪፖርት ሲያቀርቡ ተነስቶ እንደነበረው ‹‹ሥራችሁን ስታከናውኑ የገጠማችሁ ችግር ካለ ቢገልጹልን›› የሚል ዓይነት አይደለም፡፡ የጥያቄዎቹ ዓላማ አስፈጻሚው ሥራውን በትክክልና በሕግ መሠረት እያከናወነ መሆኑን ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ ሪፖርት ከመቅረቡ አስቀድሞ ጥናት ማከናወንና መረጃ መሰብሰብ ይገባል፡፡ ከዚያ የምርመራ ጥያቄው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

ሌላው የቁጥጥርና ክትትል ዘዴ ደግሞ ፓርላማው እንደ ተቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ሌላ ባለሥልጣንን በመጥራት ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ማብራሪያ እንዲሠጥ ወዘተ በማድረግ ነው፡፡ ይህ በመደበኛ የሪፖርት ወቅት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያትም በመጥራትም ይከናወናል፡፡ ለአብነት ከሳምንት በፊት ሎንደን ከተማ ላይ በደረሰው የሽብር ጥቃት ድርጊቱ በተፈጸመ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ምክር ቤት በመቅረብ ማብራሪያ እንደሰጡትም እንደተጠየቁት ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ ይህን የማድረግ ልምዱ ከአገር አገር ይለያያል፡፡ በየአገራቱ ያለውን የቁጥጥርና የክትትል ባህል ልዩነት ለመረዳት ያህል ግን፤ በእንግሊዝ (ሎንደን) በደረሰው ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈው አራት ሰዎች ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ አርባ ያህል ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ፣ በቆሼው የቆሻሻ ክምር መናድ ምክንያት ሕይታቸውን ያጡት ግን ከአንድ መቶ አሥር በላይ ናቸው፡፡ ምክር ቤታችን ግን ማንንም ጠርቶ ማብራሪያ አልጠየቀም፡፡ በቅርብ ጊዜ የሆነውን ብቻ ብናነሳ እንኳን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ደንበር አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ቢያልፍም፣ በጋምቤላ ክልል ደግሞ ድንበር ጠባቂ ሠራዊት ወይም ሚሊሻ ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ ዜጎች በተደጋጋሚ ለጥቃት ቢጋለጡም የፌደራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች አልበለዚያም የመከላከያ ሚኒስትሩ ስለጉዳቱ ሁኔታ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አልጠየቀም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ ግን መቀመጡን ተቀምጧል፡፡

ሦስተኛው የቁጥጥር ሥልት ደግሞ ተቆጣጣሪ ተቋማትን በማቋቋም አስፈጻሚውን በተጨማሪነት መቆጣጠርና መከታተል ነው፡፡ ለዚህ ተግባር እንዲያገለግሉ ሲባል ከሚቋቋሙት ውስጥ ለአብነት ኦዲተር ጀነራል፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂና የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ተቋማትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ለእነዚህ ተቋማት አፈጣጠር ምክንያቱ አስፈጻሚው አካል በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕግጋት የተቀመጡለትን አሠራር ተክትሎ  ስለመሥራቱ በመቆጣጠር  ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ ሲባል ነው፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ በተወሰነ መልኩ በጥንካሬው የሚታወቀው የኦዲተር ጀኔራል መሥሪያ ቤት ቢሆንም በሚያቀርበው ሪፖርት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከታተለ ዕርምጃ ማስወሰዱን ላይ ግን አልተዘወተረም፡፡ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ተቋማት አገሪቱ አስቸጋሪ የመልከም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች ውስጥ በምትገኝበት ወቅት እንኳን  የተነሳውን ችግር ከመቅረፍ አኳያ እምብዛም የጎላ ድርሻ ነበራቸው ማለት ያስቸግራል፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተወሰነ መልኩ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እስከተወሰነ ጊዜያት ድረስ የተፈጸሙትን መንግሥታዊ ችግሮች ያጣራ ስለመሆኑ ሰምተናል፡፡ የእንባ ጠባቂው ተቋም ግን አገሪቱ በመልካም አስተዳደር እጦት ባጋጠማት ችግር ብዙው ሰው ‹‹በጥልቅ ተሃድሶ›› ውስጥ ሲገባ ምን እያደረገ እንደሆነ አላወቅንም፡፡ የእነዚህ ተቋማት ተጠሪነት ለራሱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ቢያንስ እነዚህን ተቋማት እንኳን በመጥራት ሲጠይቃቸው አልተስተዋለም፡፡ ኢትዮጵያም እንደሌሎች አገሮች ሁሉ እነዚህ  የዴሞክራሲ ተቋማት ግን አቋቁማለች፡፡

አራተኛው የአስፈጻሚውን አሠራር የሚያርቁ፣ ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን የሚገልጹና የሚገድቡ ሕጎችን ማውጣት ነው፡፡ የተወሰኑ ሕግጋትን ማንሳት ቢቻልም በዋናነት ግን የአስተዳደር ሕግ በማውጣት አስፈጻሚው ሊከተላቸው የሚገባውን የአሠራር መንገዶች ማስቀመጥን ይመለከታል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በኢትዮጵያ ዋና ረቂቅ ሕግ አቅራቢው ራሱ አስፈጻሚው ስለሆነ በራሱ ላይ ቀንበር መጫን የፈለገ ስለማይመስል እስካሁን ለማውጣት አልተፈለገም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ፣ ወጥነት የሌላቸው፣ በየጊዜው የሚቀያየሩ አሠራሮችን ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡  ሕግ አውጭውም ጭምር ሥራ ላይ ሲያውላቸው ይታያል እንኳንስ ሌላ ነገር ሊፈጽም ቀርቶ፡፡ መንግሥት፣ አስተዳዳራዊ እንከኖችን፣ የአገልግሎት አሠጣጥ ጉድለቶችን ለማስተካከል ከተጠቀመባቸው ሥልቶች ውስጥ የተወሰኑት ሙስናን መከላከል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት፣ በጥልቀት መታደስ፣ ሂስና ግለ ሂስ ማድረግ፣ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ መተግበር፣ የዜጎች ቻርተር ሥራ ላይ ማዋል፣ ካይዘንንን መተግበርና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ  በየጊዜው ሥራ ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌሎች የአስተዳደር ሕግና የመሳሰሉትን አሠራሮች ማውጣት ይገባው ነበር፡፡ ይህንን ባለመፈጸሙ ደግሞ ለአስፈጻሚው አካል ማበረታቻ ሰጥቶታል ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም፣ ፓርላማው (ሕግ አውጪው) አስፈጻሚውን ከሚቆጣጠርበት ዘዴ አንዱ ሕግ የሚያስፈጽምበትን ሥርዓት በማስቀመጥ ነው፡፡ የሚያስፈጽምበትን አሠራር አለማስቀመጥ ወይም በተለያየና በተበጣጠሱ ሕጎች ማስቀመጥ ተገልጋዩ ብቻ ሳይሆን ፈጻሚውም በአግባቡ እንዳያውቃቸው ማበረታታት ነው፡፡

የሕግ አውጭው ቁጥጥርን ውጤታማነት የሚገዳደሩ በርካታ ሁኔታዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የመጀመሪያውና ዋነኛው የተጠናከረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጥፋት ነው፡፡ በአጠቃላይ እንደ አገርም ሆነ በፓርላማው መድበለ ፓርቲያዊ ሥርዓት በመጥፋቱ ቁጥጥሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው ማሳደሩ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት ደግሞ ከአገራችን ፓርላማ ይልቅ በግልጽነታቸው ቅርብ የሆኑንን የአሜሪካንና የእንግሊዝን ምክር ቤቶች ዋቢ ማድረግ እንችላለን፡፡ በአሜሪካ ሴኔት ዴሞክራቶቹ፣ በእንግሊዝ ሌበር ፓርቲው በተቃዋሚነት ባይኖሩ አሁን ባለው መጠን ቁጥጥሩና ክትትሉ ሲበዛም የማጋለጥ ተግባሩ ሊኖር ይችል ነበር ማለት ይከብዳል፡፡

ሌላው እንቅፋት ደግሞ ኢሕአዴግ ለሕግ የበላይነት ሳይሆን ለፓርቲ የበላይነት ቅድምና መስጠቱ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ተጠሪነታቸውን ሲያስቀምጥ ለሦስት ነገሮች ብቻ ነው ይላል፡፡ እነዚህም ሕገ መንግሥቱ፣ የመረጣቸው ሕዝብና ሕሊናቸው ብቻ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከእዚህ በተቃራኒው ተጠሪነታቸው ለፓርቲው ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከፓርቲው ፖሊሲ ውጭ በፓርላማ መናገርም አስተያየትም መስጠት አይችሉም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን በፓርላማ በሚሰጡት አስተያየት ምክንያት አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንኳን ሊወሰድባቸው እንደማይችል እንደማይገባም አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም፣ ከእነዚህ ድንጋጌ የምንረዳው  ከፓርቲው የተለየ አቋም ቢይዙ እንኳን የሚፈቅድ መሆኑን ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ ፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት አባላት የፓርቲያቸውን አቋም ብቻ እንዲደግፉ ይጠበቃል፡፡ ይህንን የሚያስተባብርም ተጠሪ ይኖራቸዋል፡፡ የእኛ ሕገ መንግሥት ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁልጊዜም ማሰብ ያለባቸው አድራጎታቸው ሕገ መንግሥታዊ ስለመሆኑ፣ የመረጣቸውን ሕዝብ ፍላጎት ስለማንጸበረቃቸውና ስለ ኅሊናቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው፣ ከላይ የተገለጸው ፖሊሲ ላይ እንደተገለጸው የምክር ቤት አባላት የፓርቲው አቋም ከኅሊናቸው ጋር የሚጋጭባቸው ከሆነ መፍትሔው ጥለው መውጣት ብቻ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ለኅሊናቸው ታማኝ እንዲሆኑ ነው የሚጠይቀው፡፡ በመሆኑም ቁጥጥሩ የላላና ሁልጊዜም የፓርቲውን ፖሊሲ በማሰብ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል ማለት ነው፡፡

የደንቦችንና መመሪያዎችን ሕጋዊነት ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት አለማበጀት ደግሞ ሌላው ሳንካ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ዝርዝርና የማስፈጸሚያ ሕጎች እንዲያወጣ ውክልና መስጠት የተለመደ ነው፡፡ ከመርህ አንፃር መውጣት አለመውጣታቸውን እንዲሁም ከአዋጆቹ ጋር የማይጋጩ መሆናቸውን መከታተልና ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አደረጃጀትን ማስተካከል፣ አቅምንም ማጎልበት ይጠይቃል፤ ደንቦችና መመሪያዎች ከአዋጆች ጋር እያገናዘቡ ለመመርመር ይረዳ ዘንድ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ማሳያ ብቻ እንጥቀስ፡፡ የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መመሪያዎችን ያወጣሉ፡፡ እነዚህ መመሪያዎች ደግሞ ሕግ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ይሁን እንጂ፣ መመሪያዎቹ በነጋሪት ጋዜጣ አይወጡም፡፡ በሌላ መንገድ አይታተሙም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህንን ሁኔታ አይጠይቁም፤ አይከታተሉም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የመንግሥት ትጥናትም አስፈጻሚው አካል የሚከተላለቸው የአሠራር ሒደት ግልጽ አለመሆን በማለት የገለጸው ይኼንኑ የሚጠናክር ነው፡፡ በተጨማሪም የክትትል ጉድለትም እንዳለ እንዲሁም ላወጧቸው ሕግች ማስፈጸሚያነት የሚውሉ ደንብና መመሪያ መውጣት አለመውጣቱን አለመከታተል የምክር ቤቶቹ ጉድለት እንዳለባቸው መግለጹን ልብ ይሏል፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ የሚመነጨው ከመንግሥት አወቃቀር ነው፡፡ ሕግ ተርጓሚው ከአስፈጻሚው ጋር የሚኖረው የግንኙነት ሚዛን ላይ ተፅዕኖ ከሚያደርሱት ጉዳዮች አንዱ መንግሥታዊ አወቃቀር ነው፡፡ ከፕሬዚዳንታዊ ይልቅ መንግሥታዊ አወቃቀሩ ፓርላሜንታዊ መሆኑ በራሱ ለሕግ አስፈጻሚው ጉልበተኛነት እንደ አንድ ጥሩ አጋጣሚ መውሰድ ይቻላል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ተፅዕኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሥልጣን የያዘው አሸናፊ ፓርቲ የሚወስናቸውን ፖሊሲዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ለፓርላማ በማቅረብ ለማስፀደቅ ቀላል ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አመራር የሚሰጥ ፓርቲ ሲሆን ደግሞ የአስፈጻሚውን ጥረት  የበለጠ ያቀልለታል፡፡

በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚው አካልና በተመሳሳይ ጊዜ የፓርላማ አባል ስለሚሆኑ በፓርቲም፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤትም እንዲሁም በፓርላማም ውስጥ ስለሚሳተፉ የፈለጉትን ከማስወሰን የሚያደናቅፋቸው አካል አይኖርም፡፡ ይህ ዓይነቱ የሕግ አወጪና አስፈጻሚ መቀላቀል የሕግ አውጪውን በቀላሉ ያሻውን እንዲፈጽም ሊያደርገው ይችላል፡፡ በፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት ሁልጊዜም አስፈጻሚው ለፓርላው ተጠሪነት አለበት፡፡ አስፈጻሚው የበታች፣ ሕግ አውጭው ደግሞ የበላይ ነው፡፡ አስፈጻሚው በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን ሕግ አውጭውን ሊቆጣጠረው አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ግን በተግባር እየሆነ ያለው በተገላቢጦሹ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በአንዲት አገር ውስጥ ሕገ መንግሥታዊነት አለ ወይም የለም ለማለት የመጀመሪያው ነጥብ የሕግ የበላይነት መስፈኑን ወይም ያለበትን ደረጃ የሚመለከት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ባልሰፈነበት ወይም የገዥዎች ፍላጎት በነገሠበት፣ ሥርዓት አልበኝነት በሰረጸበት ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊነት አይኖርም፡፡ ውጤታማ የሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ግቦችንና ድንጋጌዎችን የሚያስፈጽሙ ተቋማትን ማጠናከር ግድ ነው፡፡ አፍሪካንና ሌሎች ታዳጊ ዴሞክራሲዎችን ሕገ መንግሥታዊነት በመገዳደር ላይ የሚገኘው የፓርቲዎች አምባገነንነት ነው፡፡ በፓርቲ ደረጃ የሚፈጸም ሕገወጥ ድርጊት ብሎም ሕገ መንግሥታዊነትን እንዳይሠርጽ የሚያደርግ እንቅፋትን በማስተካከል ለሕገ መንግሥታዊነት ዋጋ መስጠት ይገባል፡፡ ይህንን ግብ ለማሳከት ከሚረዱት ተቋማት ዋነኛው ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ አስፈጻሚው እየተገራ ይሄዳል፡፡ አስፈጻሚው በተራው ደግሞ ፓርቲውን ይገራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ካልሆነ፣ በ1994 ዓ.ም. የታወቀው ችግር ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላም እዚያው ላይ ከሆነ ዘፋኝ ‹‹ዛሬም እዚያው ነሽ፤ ወይ መካሪም የለም ወይ፡፡›› እንዳለው መሆኑ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡