Skip to main content
x
መንግሥት ራሱን አያታል!

መንግሥት ራሱን አያታል!

ሕዝብን በአግባቡ ማስተዳደር ያለበት መንግሥት በሕዝብ አመኔታ የሚያሳጡት ድርጊቶችን በተደጋጋሚ ሲፈጽም አገርን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሥጋት ይፈጠራል፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት ለሕዝብ በበርካታ ጉዳዮች ኃላፊነት ሲኖርባቸው፣ ከነዚህም መካከል ዜጎች ግብር እንዲከፍሉ፣ ለሕጋዊነት ተባባሪ እንዲሆኑና ለአገራቸው በተለያዩ አገልግሎቶች እንዲሰማሩ ማድረግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሕዝብ ደግሞ በምላሹ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብርና ደኅንነቱን እንዲያስጠብቅ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖርበት የግድ ይላል፡፡ መንግሥት የሕዝብ ተቀጣሪ በመሆኑም ብዙ አገሮች ይህ አሠራር ግዴታ ነው፡፡ እዚህ አገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ አልሻሻል እያለና እያስቸገረ ያለው መሠረታዊ ጉዳይ፣ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል አለመቻሉ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት እየጎደለው በአዋጅ የወጣ ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ሲያቅት ይታያል፡፡ ሕዝብ ቅሬታ ሲኖረው ቅሬታን ማስተናገድ የዳገት ያህል እያቃተ ነው፡፡ እውነቱን አውቆ ከመታረም ይልቅ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ውስጥ እየተገባ ራስን ማታለል ተለምዷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ክፍተት ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች ጩኸቶች እየተሰሙ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች አመፅ የሚያነሳሱ ድርጊቶች ተስተውለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ግብር መክፈል የዜግነት መብትም ግዴታም ነው፡፡ የግብር ሥርዓቱ ፍትሐዊ ሆኖ ሁሉም ዜጋ በታክስ መረብ ውስጥ መግባት እንዳለበት መቼም ቢሆን አጠያያቂ አይሆንም፡፡ አገር በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ከተሰማሩ ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በሚሰበሰብ ግብር ልማቷን ማቀላጠፍ እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይልቁንም የመንግሥት ፀሎት መሆን የነበረበት አንድም ዜጋ ከግብር ሥርዓቱ ውጪ እንዳይሆን ነው፡፡ ይኼም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ የቀን ገቢ ግብር ግምት የሚመለከታቸው ወገኖች ቅሬታዎች በሕጋዊ መንገድ ቀርበው መስተናገድ ሲገባቸውና የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ ማቅረብ ሲኖርበት ለምን ትርምስ ይፈጠራል? በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጠው በግልም ሆነ በቡድን አቤቱታ የማቅረብ መብት ተከፋፍሎ ለምን ይከለከላል? በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ከገቢያችን ጋር የማይመጣጠን ግብር ተጭኖብናል ሲሉ በፍጥነት ማስተናገድ ይሻላል? ወይስ የምን መንጫጫት ነው እያሉ ወደ አመፅ መግፋት? በተለያዩ አገልግሎቶች አሰጣጥ ላይም ችግሩ የባሰ ነው፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መኖር የሚገባውን መተማመን የበለጠ የሚደረምሱ አደገኛ ክስተቶች እየታዩ ነው፡፡ እነዚህን ማረም ሲያቅት ደግሞ በፕሮፓጋንዳ የተቀባቡ ማስፈራሪያዎችን ይዞ መቅረብ ሕዝብን እንደገና ለሁከት መቀስቀስ ነው፡፡ መንግሥትም ችላ ብሎ ተቀምጧል፡፡ ራስን ማታለል ነው፡፡

በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው ከሕዝብ በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ሕዝብን ከማገልገል በላይ የተሻለ ፀጋም አይኖርም፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ባነሳ ቁጥር እውነትን እየተጋፉ የፀረ ልማትና የፀረ ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ነው ማለት ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሕዝብ ታጋሽ ማንም የለም፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ ሕግ አክብሮና አስከብሮ የሚመራው ቢያገኝ ተዓምር መፍጠር እንደሚችል በተግባር ያረጋገጠ ነው፡፡ ከመጠን በላይም ታጋሽ ነው፡፡ ትዕግሥቱም ገደብ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ጀምሮ ትዕግሥት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ትዕግሥት ሲያበቃ ደግሞ ይገነፍላል፡፡ ከዚህ ቀደም ገዥውን ፓርቲ ከላይ እስከ ታች ድረስ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ውስጥ ያስገባው የሕዝብ ብሶት መከማቸት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል አገሪቱን አደጋ ውስጥ የከተተ፣ ለበርካታ ወገኖች እልቂትና ለንብረት ውድመት ምክንያት የነበረ ሁከት መከሰቱ መቼም አይዘነጋም፡፡ በዚህም ሳቢያ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ናት፡፡ አንፃራዊ መረጋጋት ቢፈጠርም አሁንም አገርንና ሕዝብን ችግር ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ በቀን  ገቢ ግምት ምክንያት በየቦታው የሚሰሙ ማጉረምረሞችና የሁከት ብልጭታዎች ወዴት ያመሩ ይሆን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥትን እንደገና ሆድና ጀርባ የሚያደርጉ ድርጊቶች ካልተገቱ አደጋ እየሸተተ ነው፡፡ እንደ ሰጎን አንገትን አሸዋ ውስጥ ለመቅበር መሞከር አያዋጣም፡፡

መንግሥት ከሕዝብ ጋር በየእርከኑ በግልጽ ተነጋግሮ ችግሮችን አጥርቶ የማወቅ ግዴታ እያለበት፣ አሁንም በሐሰተኛ ሪፖርቶችና በተድበሰበሱ ፕሮፓጋንዳዎች ውስጥ ተወሽቋል፡፡ ቅሬታ ሲቀርብለት አይሰማም፡፡ በየመዋቅሩ የተሰገሰጉ አስፈጻሚዎች ሕዝብን ንቀው እንዳሻቸው ሲፈነጩ ሃይ ባይ አጥተዋል፡፡ የትናንቱን አደጋ የዘነጉ ሹማምንት ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ እየወሰኑ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጥልቅ ጉድጓድ እየቆፈሩ ነው፡፡ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሳይሆን በደመነፍስ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ሕዝብን ለአመፅ ሲያነሳሱ አይደነግጡም፡፡ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መዋቅር ድረስ በስብሰባ ስም ቢሮአቸውን እየዘጉ ይጠፋሉ፡፡ በጉቦና በመማለጃ ሕዝብ ያስመርራሉ፡፡ ቅሬታ ለመቀበል የተከፈቱ ቢሮዎች በስም እንጂ በሥራቸው አይታወቁም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሕዝብ መሮት ሲነሳ በሌላ ኃይል እንደተገፋ በእነሱ ፕሮፓጋንዳ ይነዛል፡፡ መንግሥትም ራሱን እየሸነገለ የፕሮፓጋንዳው ሰለባ ይሆናል፡፡ ይህንን ሁሉ ጉድ የሚያየው ሕዝብ ደግሞ ተንገሽግሾ ለመንግሥት የነበረችው እንጥፍጣፊ አመኔታ ትጠፋለች፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ይኼው ነው፡፡

ከትምህርት ተቋማት የተመረቁና በዚያ አውዳሚ ሁከት ተሳትፈዋል የተባሉ ወጣቶች የተሃድሶ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ከተፈቱ በኋላ ሥራ ፈጥረው ኑሮአቸውን ሊያቀኑ ሲታገሉ፣ ያላሰቡት የግብር ጫና እየመጣባቸው እንደገና ለምን ወደ አመፅ እንዲገቡ ይገደዳሉ መባል አለበት፡፡ ትናንት በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ዕጦት የተማረረ ሕዝብ የተሻለ ነገር ሲጠብቅ ወደ ሁከት የሚከተው ችግር ለምን ያጋጥመዋል መባል አለበት፡፡ የመብት ጥያቄዎች ሲነሱ የሌሎች ዓላማ ተሸካሚ ሆናችኋል የሚባሉ ዜጎች ይከፋቸዋል ለምን አይባልም? የራስን መብት መጠየቅ በሕግ በተረጋገጠበት አገር ውስጥ ለምን ትጠይቃለህ የሚሉ ትናንሽ አምባገነኖች ማነው እንዲህ ዓይነት መብት የሰጣቸው አይባልም ወይ? የሕዝብን ቁጣ እያናሩ አገርን ዳግም አደጋ ውስጥ መክተት ምን ማለት ነው? ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ጠፍቶ አገርን አደጋ ውስጥ የሚከት ችግር እንዲፈጠር ለምን ይፈቀዳል? መንግሥትም ሁልጊዜ ለችግሮች በራሱ መንገድ ብቻ በመሄድ ፈውስ ለመፈለግ እያለ ትርምስ እየፈጠረ ነው፡፡ አሁንም አደገኛ ምልክቶች አሉ፡፡

አገር በሕግና በሥርዓት መመራት አለበት፡፡ ሁሌም እንደምንለው የሕግ የበላይነት የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ መሆን አለበት፡፡ ሕግ የበላይ ሆኖ ሲከበር የሕዝብ ጥያቄዎችም ምላሽ ያገኛሉ፡፡ አሁን ግን መንግሥት ራሱን እየሸነገለ ነው፡፡ በፕሮፓጋንዳና በቅስቀሳ አገር እንዳይመራ ማወቅ አለበት፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት እየሻከረ ነው፡፡ ሕዝብን ወዳልሆነ አቅጣጫ የሚገፉ ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡ ሕግን የማስከበር ሥራ በግልጽነትና በተጠያቂነት መንገድ መከናወን ሲገባው የዘፈቀደ ሥራዎች እየበዙ ነው፡፡ መንግሥት በራሱ አንደበት ሕዝቡ እንደተመረረና በእጁ ጭምር ‹‹ወዲያ በል›› እንዳለው መናገሩ እየተዘነጋ፣ ራሱን በራሱ ሲሸነግል ይታያል፡፡ ከሕዝብ ጋር ታች ድረስ ወርጄ እመካከራለሁ እንዳላለ፣ ሹማምንቱ ተጠያቂነት የሌበት ድርጊት ሲፈጽሙ አይቶ እንዳላየ ይሆናል፡፡ ትናንት በግምገማ ከኃላፊነታቸው የተባረሩ ሌላ ሹመት ተደርቦላቸው በሌላ ሥፍራ ተሹመው ይገኛሉ፡፡ ሕዝብ ይህንን እያየ ምሬቱ ጣሪያ ይነካል፡፡ ከምንም ነገር በላይ መከበር የነበረበት ሕዝብ እየተረሳ ብሶቶች እንዲጠራቀሙና ሁከት እንዲቀሰቀስ ምቹ መደላድል ይፈጠራል፡፡ ጊዜ ባለፈበት የፕሮፓጋንዳ ሥልት ሕዝብን ለማታለል ጥረት ይደረጋል፡፡ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት የሚያደፈርሱና ሕዝብን ለአመፅ የሚጋብዙ ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ቋፍ ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ይህ ግን አደጋ አለው፡፡ መንግሥት ራሱን ባያታልል ይሻላል!