አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

መንግሥት የሚያስተላልፋቸውን መመርያዎች ለኦነግ ያቀብል ነበር የተባለ የወረዳ ሥራ አስፈጻሚ ተከሰሰ

  • የኦሕዴድን እንቅስቃሴና የሕዝቡን የፖለቲካ አዝማሚያ ሲያሳውቅ እንደበር ተጠቁሟል

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስብሰባ ውስጥ በመሳተፍና መንግሥት የሚሠራቸውን ሥራዎችና የሚያስተላልፋቸውን መመርያዎች፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ለተፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ሲያቀብል ነበር የተባለው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ መረጃዎቹን የኦነግ ከፍተኛ አመራር መሆኑ በክሱ ለተገለጸው ዳውድ ኢብሳና ለሌሎች አመራሮች በኢሜይል አድራሻቸው አማካይነት ያስተላለፉ እንደነበር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ አቶ አየለ በየነ በክፍለ ከተማው ውስጥ መንግሥት የሚያስተላልፋቸውን መመርያዎች፣ በስብሰባ የሚተላለፉት ውሳኔዎችና የፀጥታ ሁኔታዎችን ለኦነግ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት በስልክ ያስተላልፍ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ በተለይ በግሉ በሚጠቀምበት ኢሜይል አድራሻው ለቡድኑ መረጃ ማስተላለፉን አክሏል፡፡ ለኦነግ ትግል እንቅፋት ናቸው በማለት ያሰባቸውንና ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው ዜና የሚሠሩ ጋዜጠኞችን፣ አገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዳለ የሚገልጹ ግለሰቦችን፣ የፀጥታ አካላትና ካድሬዎችን በመለየት ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ለኦነግ አመራሮች ሪፖርት ማድረጉን ክሱ ያብራራል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ውስጥ የሚሠሩ ስማቸው የተገለጸ ጋዜጠኞችን ‹‹በኦነግ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው›› በማለት ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ለአመራሩ ዳውድ ኢብሳ ሪፖርት ማድረጉንም አስረድቷል፡፡

ከአቶ አየለ በተጨማሪ ሌሎቹም ተከሳሾች ማለትም መልካሙ ክንፉ፣ ቦንሳ በየነ፣ ይማም መሐመድ፣ ለሜሳ ግዛቸው፣ ኩመራ ጥላሁን፣ መያድ አያናና ሙሉና ዳርጌ የኦነግ አባል በመሆን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የሽብር ተግባር ወንጀል ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ በኦሮሚያ ክልል ያለው የሕዝብ ሁኔታ፣ የፖለቲካ አዝማሚያና በኦሕዴድ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ አጣርተው ሪፖርት እንዲያደርጉ በአቶ ዳውድ መመርያ እንደተሰጣቸውና እነሱም ሪፖርት ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ከኦሕዴድ ጋር አብረው የሚንቀሳቀሱት አባላት ሥልጣንና ጥቅም ፈላጊዎች መሆናቸውን፣ ሕዝቡ ከኦነግ ጋር መሆኑን፣ በኦሕዴድ ውስጥ ጥርጣሬ እንዳለና እርስ በርስ የጎሪጥ እየተያዩ መሆናቸውን ተከሳሾቹ ሪፖርት ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ተከሳሾቹ በሴል በመደራጀትና በጋራ ኢሜይል በመጠቀም ለኦነግ ሪፖርት ሲያደርጉ እንደነበር፣ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ወልመራ ወረዳ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው ሥራ ያላገኙ ወጣቶች፣ እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የግል ሠራተኞችና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳ ማሊባ ወረዳ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች በሴል የተሳሰሩ የኦነግ አባል መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር አቅርቧል፡፡

ተከሳሾቹ በሱዳን በኩል የሚገቡ የኦነግ ታጣቂዎችን በመቀበል የሚያስፈልጋቸውን የምግብ፣ የመኝታና የመሣሪያ መግዣ ገንዘብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እየተላከላቸው ሲያስተናግዱ እንደነበርም አክሏል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ 7(1) እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀእናለ) እንዲሁም አንቀጽ 38 ተላልፈው በመገኘታቸው የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ መመሥረቱን ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ገልጾ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ለተከሳሾቹ በመስጠት መቃወሚያ ካላቸው ለግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡