Skip to main content
x
ሙያ በየፈርጁ

ሙያ በየፈርጁ

ነግሻለሁ

የምሽት ጨረቃ ከደመናው ስትፈልቅ፣

የማለደ ፀሐይ በመስኮቴ ስትሠርቅ፣

በአምላኬ እጅ ሥራ ልቤ ስትደነቅ፣

በቤቱ ጉልላት ወፎች ከዘመሩ፣

ውብ ቢራቢሮዎች በቅፅሬ ካደሩ፣

ጠጅ ሳር፣ አሪቲ ደጄ ላይ ካማሩ፤

ይህ እውነት በርቶላት

ሞራው ተገፎላት፤

የደስታ ወይኗን ትጎንጭልኝ ነፍሴ፣

ንጉሥ ነኝ ማለት ነው በቃ እኔው ራሴ፡፡

በሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) ‹‹የተገለጡ ዓይኖች›› (2009)

* * *

ውሻዎ ፊትዎን ሲልስ እስከ ሞት በሚያደርስ ባክቴሪያ ሊጠቁ እንደሚችሉ ያውቃሉ?

ውሾች ከሰው ልጆች ጋር ካላቸው የቅርብ መስተጋብር የተነሳ፣ አብረው ለሚኖሯቸው ሰዎች የተለየ ፍቅርና ታማኝነት አላቸው፡፡ በመሆኑም አንድ ሰው ከቤት ሲወጣ መሸኘት፣ ሲመለስ ደግሞ በፈንጠዝያ፣ ድምፅ በማሰማት፣ ዘሎ እስከ ትከሻ በመውጣትና በመላስ የደስታ አቀባበል ማድረግም ልማዳቸው ነው፡፡ ሆኖም ውሾች የቱንም ያህል በንፅህና ቢያዙ፣ የበሰለ ምግብ ብቻ ቢመገቡ፣ ክትባትም ሆነ የሕክምና ክትትል ቢደረግላቸው ከአፋቸው የሚወጣው ባክቴርያ ለሰው ልጅ ጤና ጎጂ ከመሆኑም ባለፈ ለሞት ያደርሳል፡፡ በተለይ ውሾች ፊትዎን ማለትም አፍና አፍንጫዎ ላይ እንዳይልስዎት መጠንቀቅ ይገባል፡፡

ሚረር እንደዘገበው፣ የውሾች አፍና አፍንጫ በተለያዩ ዓይነት ባክቴሪያዎች፣ ጀርሞችና ቫይረሶች የተሞላ ነው፡፡ ይህም ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች በማጋለጥ ሰዎችን እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በመሆኑም ለውሾች ፍቅርን መስጠቱ እንዳለ ሆኖ፣ ፊት አካባቢ እንዳይልሱ መከላከሉ ተገቢ መሆኑን በለንደን ኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ የቫይሮሎጂና ባክቴሪዮሎጂ ፕሮፌሰሩ ጆን ኦክስፎርድ ይመክራሉ፡፡

* * *

ምግብ ማቁለጭለጭ ያስከፈለ ዋጋ

አንዳንዶች ምግብ ይዘው እንስሳትን በማቁለጭለጭ ይጫወታሉ፡፡ ሳር ይዘው ከብቶች ከእጃቸው እንዲነጥቋቸው በማድረግ ሲጫወቱም ይስተዋላሉ፡፡ ለድመትና ውሻ ሥጋ በእጅ ይዞ በማሳየትና በመሯሯጥ እንስሳቱ እንዲነጥቋቸው የሚያደርጉም አሉ፡፡ ይህ ግን እንስሳትን ሊያስቆጣ የሚችልበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሜትሮ እንደሚለው፣ በታይላንድ ገጠራማ ሥፍራ የሚገኝ ቤተ መቅደስን ለመጎብኘት ከሄዱ አምስት ጓደኛሞች፣ የ36 ዓመቱ ናፊም ፕሮምራቴ በግቢው ውስጥ የሚገኘውን ድብ ምግብ እያሳየ ማቁለጭለጭ ይጀምራል፡፡ በዚህ የተቆጣው ድብ፣ ፕሮምራቴ ላይ ዘሎ በመውጣትና በመጣል ልብሱን ቀድዶ ቆዳውን ይቦጫጭረዋል፡፡ በአንገቱ፣ በእጁና በእግሩ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ፕሮሞራቴ፣ በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከድቡ መላቀቅ የቻለ ቢሆንም፣ ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ሕክምና እየተደረገለት መሆኑን በሳምንቱ ማብቂያ ላይ ሜትሮ ዘግቧታል፡፡

* * *

የባንክ ብድር ላለመክፈል ፊቷን በፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያስቀየረች

በማዕከላዊ ቻይና ውሃን ከተማ የሚኖሩት የ59 ዓመቷ ወይዘሮ ከባንክ 25 ሚሊዮን የን (3.71 ሚሊዮን ዶላር) ተበድረዋል፡፡ ሆኖም ይህንን ብድር ላለመክፈል በፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ፊታቸውን ቀይረው ሌላ ሰው ይመስላሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ባንኩ ካለው ፎቶና መረጃ ጋር የሚመሳሰል ባለዕዳ ያጣል፡፡ ባንኩ ጉዳዩን ለፖሊስ ያሳውቅና ፖሊስ ክትትሉን ይጀምራል፡፡ ዥንዋ ኒውስ ኤጀንሲ እንደሚለው፣ ወይዘሮዋ በፊታቸው ላይ ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከማድረግና መልካቸውን ሙሉ ለሙሉ ከመቀየራቸው ባለፈም ስማቸውንና አድራሻቸውን ጭምር ለውጠዋል፡፡ ጉዳዩን የያዘው ፖሊስ ‹‹በጉዳዩ ተገርመናል፡፡ በእጃችን በያዝነው የወይዘሮዋ ፎቶና መልኳን ከቀየረች በኋላ ያለው የተለያየ ነው፡፡ አሁን ላይ በሰላሳዎቹ ውስጥ የምትገኝ መስላለች፤›› ብሏል፡፡

ዘ ናጁዋን የተባሉት ወይዘሮ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የሌላ ሰው መታወቂያ ተጠቅመው በባቡር ሲጓዙ ነው፡፡ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናውን ያደረጉትም የባንክ ብድር ካርድ ተጠቅመው መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

* * *