Skip to main content
x
ማሳለፍ እያለ መጋጨትን ምን አመጣው?

ማሳለፍ እያለ መጋጨትን ምን አመጣው?

እነሆ መንገድ። ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። መንገዱ በደመናው እንባ ረጥቧል። የሰው ኮቴ ተነባብሯል። አላፊ አግዳሚ ለሚያልፍ ቀን በክፉና ደግ ይሞነጫጨራል። አመሉን አይረሳም። የድመትን ያህል ባይሆንም ይኼ ተራማጁ ሰው አመለኛ ነው። ጎርምሶም፣ ጎልምሶም፣ ጃጅቶም ጥቂት በጥቂት እርስ በእርሱ ሲሸራረፍ ያልፋል። ጉስቁልናችን ከመንገዱ ቢከፋ እንጂ አይሻልም። ያ ከሹፌሩ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ በወያላው የውስጥ ሱሪ አለማጥለቅ ተናዶ፣ “እንዲያው ዘንድሮ። ብለን ብለን ነገረ ሥራችን ሁላ የዝንጆሮ ይሁን?” እያለ ያጉረመርማል። ምን ማለት እንደሆነ ሲጠየቅ፣ “አታየውም እንዴ መቀመጫው እርቃኑን ተገልጦ ሲመናቀርብን። ዛፍ የሚወጣ ጭላዳም እንደዚህ እንትኑን አይጥልም፤” ይላል። “ዓይን የተፈጠረው ሁሉን ለማየት ነው አልተባለም እንዴ?” ይለዋል ከጎኑ የተየመው አስለፍላፊ። “ተው በዓይናችን አትምጣ። ባይሆን በመንገዱ አሳብ፤” ይላል ጎልማሳው። ከጀርባ መሀል መቀመጫ፣ “አሁን እስኪ በወዛደሮች ቀን ስለወዝና ምንዳ አለመመጣጠን ማውራት ሲኖርብን እንዲህ ይባላል? ደግሞስ በሰው መቀመጫ ምን አገባን?” የምትል ጠይም  ተሰይማለች።

“የወዙንና የደመወዙን ነገርስ አታንሺው። ቀንና ሰው አልተገናኝቶም። በበኩሌ ከወዛደሮች ቀን ያተረፍኩት ነገር ሥ አለመግባት ብቻ ነው። 30 ዓመት አንድ ፋብሪካ ስሠራ ነው የምልሽ ይላታል፤” ገብስማ ፀጉር ከፋይ ጃኬት ለባሽ። ሦስተኛው ረድፍ ከጎኔ የተሰየመ ወጣት ደግሞ፣ “አቦ ጃኬትህ ይከይፋል። የት ነው የገዛኸው እባክህ?” ብሎ ትከሻውን ዳሰሰው። ገብስማው በመገረምና በድንጋጤ መለስ ብሎ አይቶት አንገቱን እየነቀነ፣ “የዛሬ ልጆች ምን እንደሚሻላቸው እንጃ። ይቅርታ ወንድሜ ጤና ይስጥልኝ ምናምን ብሎ ቢጠይቀኝ ምን አለበት? ቅጡ ጠፋን እኮ እህቴ፤” ብሎ ለጠይሟ ዓይናማ ሲያማው ወጣቱ ሰምቶ “ዋት?” አለ በለሆሳስ። ዘመንና ዘመነኛ አልስማማ ሲል መንገድ መሀል ገብቶ እንደማስታረቅ፣ በዋጋ እያወዳደረ ያለዋጋው የሚያኖረው በዛና ያየነውን ዓይተን የሰማነውን መተረክ ሥራችን ሆኖ ቀረ። ዓይን የማያየው የለም ብቻ? የጆሮንስ ኧረ ማን ሰማ?!

አብረውን የተሳፈሩት ባርኔጣ የደፋ አዛውንት ታዘብኩትን ያሉትን ነገር ጮክ ብለው ሁላችንም እየሰማናቸው ያወሩናል። “አቤት! እንዲያው እንዲህ ሕዝብ ብቻ ይሁን አገሩ? እግዚኦ! አይ ስምንተኛው ሺሕ? ማንም ያልነበረበት ቦታ ሁሉ ጫካ እኮ ነበር!” አጠገባቸው ለተቀመጠው ወጣት ዞረው ይነግራታል። “ይገርምሀል ያኔ እትዬ እከሊት፣ እከሌ፣ ጋሽ እንትና በቃ! ሌላ አልነበረም እኮ!” ይላሉ እንዳሻቸው ትዝታና ትዝብት መሀል ተወራጩ። ከወደኋላ መቀመጫ፣ “ለማንኛውም መንግሥት ቢያስብበት ጥሩ ነው። የእስካሁኑ ይበቃል!” ትላለች አንዷ። “የእስካሁኑ ምን ነበር?” ይጠይቋታል አጠገቧ የተቀመጡ ተሳፋሪዎች። “በቂ የመኖሪያ ቤት መሥራት አለመቻል፣ ዘርፈ ብዙ የሥራ ዕድሎች በአጥጋቢ ሁኔታ አለመፈጠር፣ ይህን ተከትሎም ስደት በአስከፊ ሁኔታ ጣራ መንካቱ ነዋ! መንግሥት መዘጋጀት ያለበትን ያህል የሕዝቡን ቁጥር ዕድገት ዓይቶ፣ አጥንቶ፣ ገምቶ ቀድሞ ስላልተዘጋጀ እኮ ነው ዛሬ እንዲህ እኛም ሆንን እሱ የምንጫጫ፤” ስትል፣ “ቁጥራችን እንዲህ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ግን ኢትዮጵያ አትጠበንም?” ይላል ሌላው። የማንሰማው የለም እያልን እኛም ወሬ እንኮመኩማለን። ወግ የማያልቅበት አገር!

“አትጠበንም?” ስትለው አጠር ቀጠን ያለች ኮረዳ፣ “ሁሉም ቦታ ከሞላ ነዋ። ቁጠባው፣ መንገዱም፣ የዋጋ ግሽበቱ እንዲያው ምን አለፋሽ በቃ ምንም ሥርዓት ያለው አካሄድ አይታይ፤” ይላል ወጣቱ ጫን ባለ ድምፅ። “አዬ!” ብለው አዛውንቱ ባርኔጣቸውን አንስተው ጉልበታቸው ላይ አስቀመጡ። “እንዲያው የሚገርመኝ ድሮ እኛ ‘ልጅ በዕድሉ ያድጋል’፣ ‘ልጅ ፀጋ ነው’፣ ‘ልጅ ምንም ቢሆን ሥጋ ነው፣ አይከዳም!’  እያልን ካለማወቅ ፈለፈልነው። እኛስ ባለማወቅ ነው! ዘመኑም ደግ ነበር ኧረ። የአሁን ዘመን ሰው ግን ምን እንደሆነ አላውቅም፤” ብለው ቁጭት አድሮባቸው ተብሰለሰሉ። ከኋላ መቀመጫ ፊት የተመጡት ቆንጅዬዋ ልጅና ጎልማሳው ሰውዬ ናቸው። “እኔን የሚገርመኝ?” ትላለች እሷ። “ለመቆጠር አስቸግረን በ‘ነው!’ ‘አይደለም!’ አኃዛችን እስኪያጨቃጭቅ የምንሮጠው የት ለመድረስ ነው?” ስትለው፣ የፌዝ ሳቀና ጎልማሳው፣ “ህንድና ቻይና ጋ!” አላት። በኢኮኖሚ ይሁን በሕዝብ ብዛት የታወቀ ነገር አልነበረም። ጠያቂዋ ቆንጆ ሳትወድ በግዷ ፈገግ ስትል አየናት። እንዲህ ነው የዚህች አገር እውነት፣ ሳይወዱ በግድ ፈገግ ያሰኛል!

መሀል መቀመጫ በአዛውንቱ የሚብሰከሰኩ ጎልማሳና ወይዘሮን አልፎ አጠገቤ በስልክ ጨዋታ የያዘ ወጣት ተቀምጧል። ከሴት ጓደኛው ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደሚገኝ ያትታል። “ምን አልኳት እኔ? ዕድሜ መጠየቅ ያስኮርፋል?” ይላል። መጨረሻ ወንበር ላይ በተመሳሳይ የዕድሜ እርከን ውስጥ የሚገኙት አራት ተሳፋሪዎች ከአፍ ከአፉ እየነጠቁ ይተርቡታል። አንዱ፣ “ዕድሜ መደበቅ በሰው አልተጀመረ፣ እግዜርስ መች ተናገረና? አቤት የዘንድሮ አፍቃሪና የፖለቲካ ፓርቲ ግን። ‘ቫላንታይንስ ዴይ’ አበባ በመግዛትና ምርጫ ሲደርስ በመቀስቀስ ይወሰን? ምነው ይኼን ያህል ጥበብ ራቀን?” ይላል። ከአጠገቡ ተቀብላ፣ “ዝም ብላ 23 አትለውም? ምን አስጨነቃት? ስንትም ብትሆን የገዢው ፓርቲ ልጅ ነኝ ብላ ድርቅ ማለት ነው፤” ትላለች። አንድምታዋን ሊያስፈታ፣ “እኮ ምን ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ?” አጠር ቀጠን ያለ ተሳፋሪ ሲጠይቃት፣ “ያለ ልማትና ዴሞክራሲ አላውቅም ነው ሲፈታ። በአጭሩ ‘ገዴ ብልፅግና ነው’ ነው። አይ ካለ አሸባሪና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ነው ብላ ሳይቀድማት መቅደም፤” ስትለው ሳቀ። ሌሎቻችንም ፈገግ።

ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ሆኖ ልጁ በዕድሜሽን ንገሪኝ ቀሽም ጥያቄ ላከሸፈው መግባባት ለምን እጠየቃለሁ እያለ ይደነፋል። አራተኛው ተሳፋሪ ደግሞ፣ “እውነቱን ነው፣ እንኳን የኖሩትን መኖር አለመኖራቸውን አጣርተው የማያውቁትም 40 ወይም 60 ዓመት እንገዛለን ብለው ያስወራሉ። ምናለበት ብትነግረው?” ይላል። ወደ ደራው የወጣቶቹ ጨዋታ ጆሮውን የጣደው ጎልማሳ፣ “መቼ ልጅቷ የባርነት ዘመን ተጠየቀችና ነው መግዛትና መገዛትን እዚህ መሀል የምታመጡት?” ሲል በከፊል ዞሮ ጠየቀ። ጥያቄው ጥያቄ ወለደ። “አንተስ ማንን ለማስወንጀል ባርነትን እዚህ የምትደነጉረው?” የሚል። ጫን ያለው መጣ አለ ሰውዬው!

ጉዟችን ቀጥሏል። አጠገቤ የተሰየመው ወጣት የስልክ ጨዋታ ወላ በኔትወርክ ወላ በአንዳች መላ ሊደመደም አልቻለም። ይኼን የታዘበው ጎልማሳ፣ “ይኼኔ እንደገና ዛፍ መብራት ቦግ እልም እያለ ስላንገላታን የኃይል መቆራረጥ እየጮህን ቢሆን ኖሮ አይደለም ከኔትወርክ ቀጣና ከሲም ካርድ ባለቤትነትም በተፋቅን ነበር፤” ብሎ አዲስ ብሶት ያራግፍብን ጀመር። “የመብራትንስ ነገር ተወው…” አጠገቡ የተቀመጠች ወይዘሮ አገዘችው። “ምኑን ተውኩት ይኼን እንደ አቦ ሸማኔ የሚምዘገዘግ የለውጥ ጊዜ ወይ ወገቡን ወይ ጭራውን ሳልይዘው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እያስተጓጎለኝ፤” ይላታል። ጋቢና የተቀመጡት ተሳፋሪዎች በበኩላቸው፣ “ሳይናጡ ቅቤ ሳይታሹ ምጣድ ይሆናል እንዴ? ይኼው ዛሬ ጅቡቲ ካልተዋሀድኩ የምትለው እኛ በሻማ ራት በልተን ብንተኛ መስሎኝ?” ይባባላሉ።

ሾፌሩ፣ “ከይቅርታ ጋር የበላተኛው ቁጥር ትንሽ አልተጋነነም? እኛ ማለት ለመሆኑ እነማን ነን?” ብሎ ይጠይቃል። ሰዎቹ ይመልሳሉ፣ “ለዘለቄታው ከሚያጠግበን ስትራቴጂና ፖሊሲ አንፃር ዛሬ ዓይኔ ካልበራ ሙግትስ አልበዛም?”  ጥያቄውን በጥያቄ። “ጉድ እኮ ነው በዚህ የፀሐይ ንዳድ ስለጨለማ ማውራት ግፍ ነው፤” ብላ ልትገላግል ከአዛውንቷ አጠገብ ያለቸው ቀዘባ ስትገባ ጎልማሳው፣ “ያደለው ስለኑክሌር ኃይል ያወራል እኛ እዚህ በፈረቃ ብርሃን እንታደላለን፤” አለና ደነፋ። “መቻል ነው ወንድሜ እዬዬም ሲደላ መሆኑን ከታሪክ መማር ይበጃል፤” ትላለች ከመጨረሻ ወንበር። ከጎኗ ያለው ደግሞ “ምን ይደረግ? እኔም ይኼው ሳላስበው ድርግም ባለበኝ ቁጥር የዕድሜ ማራዘሚያዬን ይዤ ቁጭ እላለሁ፤” አለ። “ምንድነው ደግሞ የዕድሜ ማራዘሚያ?” ሲለው ሁሉም፣ “በርጫ ነዋ! መብራት እስኪመጣ ተብሎ ይጀመራል መጥቶ እስኪሄድ እኛ በምርቃና የራሳችንን መብራት አብርተን ዕድሜ እናራዝማለን፤” ከማለቱ፣ “የእብድ ቀን ቶሎ አይመሽ’ አሉ። እስኪ ሾፌር ቶሎ ቶሎ ንዳው…” እያለ የሚያጉረመርመው በዛ። አጉረምራሚ ሁላ!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ቀበናን እንዳለፍን ወያላችን ሦስት ብላቴና የተቀዳደደ ካናቴራ የለበሱ ሴት ልጆች ጫነ። “መጨረሻ ወንበር ላይ ግቡ። ብርዳም። ደግሞ በእናንተ ትራፊክ ያስቁመኝ?” ብሎ ቀልባቸውን ገፈፈው። ሾፌሩ ደግሞ፣ “ይከፍላሉ? ካልከፈሉ አውርዳቸው፤” እያለ ይደነፋል። “ተዋቸው እንጂ። እንዴ? ምንድነው እናንተ ትንሽ ትንሹ ላይ የምትፈረጥሙት? የስንቱን ላብ የሚያልብ አከማች እያየ እንዳላየ እያለፋችሁ የደሃ ልጆች ላይ ሲሆን ትበረታላችሁ?” ብሎ ጎልማሳው ሲጮህ ከሁለቱ ሞሳ ሕፃናት ከፍ የምትለዋ፣ “የደሃ ልጅ አይደለንም። የሠራተኛ ልጆች ነን፤” ብላ ሳግ በተናነቀው ድምፅ ተናገረች። ጎልማሳው አመድ መስሎ ዞሮ አይቷት ወፍራም ምራቅ ዋጠ። ይኼኔ ከጎናቸው የተሰየመው ወጣት፣ “እህትማማቾች ናችሁ?” አላት። በአዎንታ ራሷን ነቀነቀነችለት።

“አባትሽ ምን ይሠራሉ?” እያባበለ ንዴቷን ማብረድ ይዟል። “አናጢ ነው። ጎበዝ ነው። ግን አሁን አሞት ቤት ተኝቷል፤” ብላ ቀና ብላ አየችው። “አይታከሙም? ለምን ቤት ይተኛሉ?” ሲላት የሚያሠሩት ሰዎች ክፍያውን ገና አልሰጡትም፤” ብላው እንባዋ ሲያቀር ወጣቱ ክንዱን ትከሻዋ ላይ ጠምጥሞ በታላቅ ወንድም መንፈስ አቀፋት። ይኼኔ ደግሞ ጎልማሳው ብሶበት፣ “ወዝና አዳር የማይገጣጠምባት ዓለም። ‹ወዝ አደር› የላቡን የልፋቱን ተነጥቆ መጨረሻው አልጋ ላይ መውደቅ ሲሆን፣ ወዙንም ደሙንም የሚመጡት ከበርቴዎች ግን በአልጋ ላይ አልጋ፣ በቤት ላይ ቤት፣ በመኪና ላይ መኪና ሲያግተለትሉ ይኖራሉ። አሁን ለዚህ ዓለም ናት? መንግሥታት ናቸው? ወይስ ፈጣሪ ነው የሚወቀሰው?” ብሎ ከኪሱ ሳንቲሞች አውጥቶ የሦስቱን የወዝ አደር ልጆች ሒሳብ ከፈለ። ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ወያላው “መጨረሻ” ሲለን ተስፋ አይሞትምና ቁዘማችንን ረስተን ወዝ ለማፍሰስ እየተጋፋን ወረድን። ምንዳና ምንደኛ ተፈላልገው የሚገናኙት መቼ ይሆን ግን? እንዲያው ለነገሩ ማሳለፍ እያለስ መጋጨትን ምን አመጣው ብንባባልስ? መልካም ጉዞ!