Skip to main content
x
ሥራ አጥነትና ድህነት የወለደው ስደት

ሥራ አጥነትና ድህነት የወለደው ስደት

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተወለዱበትን አገርና ቀዬ እየለቀቁ በልዩ ልዩ  አገሮች የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር በ1992 ዓ.ም. 173 ሚሊዮን ነበር፡፡ ይህ መጠን በዚህ ዓመት 41 በመቶ አድጎ ወደ 244 ሚሊዮን  ደርሷል፡፡ ይህም ከዓለም ሕዝብ 3.3 በመቶ ያህል መሆኑን የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡

የማኅበራዊ ጥናት መድረክ የሶሾዮ ኢኮኖሚ ተመራማሪው ዘሪሁን መሐመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአፄ ኃይለሥላሴና በደርግ ሥርዓቶች ሰዎች የሚጓዙት ወደ ምዕራብ አገሮች ነበር፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት የነበረው ፍልሰት ትምህርት ፍለጋ ሲሆን፣ በደርግ ሥርዓት ደግሞ በብዙ መቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩት ወገኖች የተሰደዱት ሥርዓቱንና የፖለቲካ ሁኔታውን ጥላቻ ነበር፡፡

በአሁን ሥርዓት ደግሞ የሥራ አጥነትንና ድህነትን ለመወጣት በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና ደቡብ አፍሪካ ይሰደዳሉ፡፡

እንደ ዓለም ባንክ መረጃ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የድህነት መጠን በ1996 ዓ.ም. በነበረበት 38.9 በመቶ በ2009 ዓ.ም. ወደ 26.6 በመቶ ዝቅ ቢልም በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አሁንም ከድህኅነት ወለል በታች እንደሚገኝ ዶ/ር ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በትግራይ ክልል ብቻ የድህነት መጠኑ 23.4 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላዩ ሕዝብ መካከል ሩብ ያህል ይሆናል፡፡ በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለወጣቶች የስደት መንስዔ አንበሳውን ድርሻ የያዘው ደግሞ ሥራ ማጣት ነው፡፡ ዶ/ር ዘሪሁን የማዕከላዊ ስታትስቲክስን መረጃ ዋቢ አድርገው እንዳብራሩትም፣ በብሔራዊ  ደረጃ የሥራ አጥ መጠን 17 በመቶ ደርሷል፡፡

ዋነኛው የሥራ አጥ ተጠቂ ወጣቱ ክፍል እንደሆነ፤ በገጠሩ አካባቢም በመሬት እጦትና ጥበት፣ አማራጭ የኑሮ ሁኔታ በማጣት፣ በሕዝብ ብዛት በተለይ በከተማ በቅርቡ  የተከሰተው የኑሮ ውድነትና በሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሳቢያ ስደት እንደ ብቸኛ አማራጭ ተደርጎ  እየታየ መጥቷል፡፡ ከዚህ አንጻር በአጠቃላይ ስደት እንደ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ክስተት ተቆጥሯል፡፡ ይህም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን አትርፏል፡፡

ወጣቱ የራሱን ቢዝነስ ለማካሄድ የሚያስችል የካፒታል እጥረትና እጦት፣ የልምድና የብቃት ማነስ፣ ገበያው ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን አለመቻልና ሌሎችም ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ ከዚህ የአኳያ ትምህርትና የኢንዱስትሪያል ልማት ፖሊሲዎች እንዲሁም የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ልማት ስትራቴጂ የሥራ አጥ ወጣቱን ለመቅረፍ ዋንኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ሆኖም፣ የሥራ አጥ ወጣት ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ፣ ችግሩም የዛኑ ያህል ውስብስብ እየሆነ፣ ስደትን እንደብቸኛ አማራጭ አድርጎ የሚገነዘብ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

የወጣቱን ሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍና ሕገ ወጥ ስደትንም ለመግታት በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማተኮርና መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው የትምህርት ፖሊሲው ሲሆን፣ ሁለተኛው አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ልማት ስትራቴጂ ነው ብለዋል፡፡

የክርስቲያን ችልድረንስ ፈንድ ኦፍ ካናዳ ካንትሪ ዳይሬክተር ፈለቀ ታደለ (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ መካከለኛ ገቢ ለማደግ የምታካሂደው እንቅስቃሴ ላይ ሦስት እንቅፋቶች ተጋርጠዋል፤›› ብለዋል፡፡

እንቅፋቶቹም ሰባት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለምግብ ዕርዳታ መጋለጡ፣ የማይማን ቁጥር ከሌሎቹ የዓለም  ክፍሎች አንፃር  ሲታይ  ከፍተኛ መሆኑንና 26 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ሆኖ መገኘቱ ናቸው፡፡

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ መንግሥት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከተግባራቱም መካከል አንዱ ብሔራዊ የሶሻል ፕሮቴክሽን ፖሊሲ ማውጣቱ ይገኝበታል፡፡ ፖሊሲው ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ 12 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ እንዳወጣና እነዚህንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዴት አድርጎ እንደሚታደጋቸው የሚገልጽ ፕሮግራም እንደቀረጸ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

18 ሚኒስቴሮችን ያካተተና በአካል ጉዳተኞችና በአረጋውያን ዙሪያ ያለመ የድርጊት መርሐ ግብርም ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መሆን ከተጀመረ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

እንደ ዶ/ር ፈለቀ አገላለጽ፣ በመርሐ ግብሩ ከተካተቱ ሚኒስቴሮች መካከል ሦስቱ ብቻ በጥሩ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ የቀሩት ግን መዋቅርና እንቅስቃሴውን የሚመራ አካል የላቸውም፡፡ ሥራውን የሚያከናውኑት በአስታዋሽነት እንጂ በሥራ ሒደት ዴስክ እየተመራና ስትራቴጂ ወጥቶለት አይደለም፡፡

ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ 4.7 በመቶ ወይም 4.2 ሚሊዮን  አረጋውያን እንዳሉና አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ ስትደርስ ይህ መጠን ወደ ዘጠኝ በመቶ እንደሚያድግ፣ ካሉትም አረጋውያን መካከል 51 በመቶ የሚሆኑት የቤተሰብም ሆነ የመንግሥት ድጋፍ እንደሌላቸው፣ ሕይወታቸውን የሚያቆዩት በልመና እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መሥፈርት መሠረት፣ የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው ወገኖች 15 ሚሊዮን ይሆናሉ፡፡ ከእነዚህ 95 ከመቶው ከድህነት ወለል በታች ያሉ ናቸው፡፡ አካል ጉዳተኛ ከሆኑ ሕፃናት መካከልም በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት አራት ከመቶ አይበልጡም፡፡

ተመራማሪውና ዳይሬክተሩ ይህንን ያመላከቱት የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ሰሞኑን ባካሄደው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ‹‹ዩዝ፣ ኢምፕሎይመንት ኤንድ ማይግሬሽን›› እና ‹‹ቨርነረብል ግሩፕስ ኤንድ ሶሻል ፕሮቴክሽን›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎቻቸ ነው፡፡