Skip to main content
x
ስሜን ብሔራዊ ፓርክ ከአደጋ ዝርዝሩ ከወጣ በኋላ

ስሜን ብሔራዊ ፓርክ ከአደጋ ዝርዝሩ ከወጣ በኋላ

ስሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክን ተከትሎ በአዋጅ የተቋቋመ የኢትዮጵያ ፓርክ ሲሆን፣ ብዝኃ ሕይወቱ ብዙዎችን ከመላው ዓለም ስቧል፡፡ በ1958 ዓ.ም. ከለላ ተበጅቶለት የተቋቋመው ፓርኩ የኢትዮጵያ ረዥሙ ተራራ ራስ ዳሽንን ከማካተቱም በላይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መኖሪያም ነው፡፡ ዋልያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮ እንዲሁም ከ1,200 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች በፓርኩ ይገኛሉ፡፡ ስሜን ብሔራዊ ፓርክን መጠለያ ካደረጉት ከ200 የሚበልጡ አዕዋፋት አምስቱ ከኢትዮጵያ በስተቀር በየትኛውም አገር አይገኙም፡፡

የፓርኩን አስገራሚ ተፈጥሯዊ አቀማመጥና አስደናቂውን ብዝኃ ሕይወት ያስተዋለው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ፓርኩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ መሆን እንዳለበት በማመን እ.ኤ.አ. በ1978 በቅርስነት መዝግቦታል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ከሚጎበኙ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ የሆነው ፓርኩ፣ በዓለም ቅርስነት በተመዘገበበት ወቅት የነበረውን ገፅታ እንደያዘ መዝለቅ ግን አልቻለም፡፡ የዓለም ቅርስ በተባለ በ18 ዓመቱ እንስሳቱና የተፈጥሮ ሀብቱም አሥጊ ሁኔታ ውስጥ ወደቁ፡፡

በዓለም ቅርስነት ሲመዘገብ በዋነኛነት የዩኔስኮ መሥፈርት ሰባትና አሥርን ያሟላ ነበር፡፡ በመሥፈርት ሰባት መሠረት፣ የፓርኩ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ልዩ መሆን በዓለም ብቸኛ ያደርገዋል፡፡ መሥፈርት አሥርን ያሟላው ደግሞ የፓርኩ የብዝኃ ሕይወት ስብጥር ከሌሎች ተፈጥሯዊ አካባቢዎች የላቀ በመሆኑ ነበር፡፡ ያለፉት ሁለት አሠርታት የፓርኩ ገጽታ ግን እነዚህን መሥፈርቶች የሚፃረር ነው፡፡

ፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ ዋልያዎች ቁጥር ተመናምኖ ወደ 100 ሲወርድ የቀይ ቀበሮዎች ቁጥርም ከ20 አይበልጥም ነበር፡፡ በፓርኩ ሕገወጥ የሰዎች ሰፈራ ንሮ ወደ 412 አባወራዎች በፓርኩ ይኖሩ ነበር፡፡ የነዋሪዎቹ ሕይወት የተመሠረተው ግብርና ላይ እንደመሆኑ፣ የፓርኩን ተፈጥሯዊ ሀብት በሚጎዳ መልኩ ሲያርሱ፣ የቤት እንስሳቶች ቁጥርም ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር፡፡

በነዚህ ችግሮች የተሸበበው የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ የአገሪቱ ፓርኮች አደጋ ያንዣበባቸው መሆናቸው ቸል ከተባለ ሰነባብቷል፡፡ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተፈጥሮ ቸር ሆና የለገሰችንን ሀብቶች መጠበቅ ተስኖን፣ ከሕልፈታቸውም መታደግ ተስኖን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ፓርኮች በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎች ሳቢያ ለሰው ሠራሽ አደጋ የተጋለጡ ሲሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላትም አፋጣኝ ዕርምጃ ከመውሰድ ታቅበዋል፡፡ ዳግም ሊገኙ የማይችሉ ሀብቶች ሲጠፉ ቸል ማለት የኋላ ኋላ የታሪክ ተጠያቂ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡

ስሜን ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ የአደጋ መዝገብ ውስጥ መግባቱ የፓርኩን ህልውና ለመጠበቅ የተደረገውን እንቅስቃሴ ያፋጠነው ይመስላል፡፡ ፓርኩን ወደ ዩኔስኮ ቅርስነቱ ለመመለስ የተደረገው ጥረት ተፈጥሯዊ ሀብቱ እንዲያገግም በር ከፍቷል፡፡ በዩኔስኮ 20ኛው ጉባዔ በአደጋ መዝገብ የሰፈረው ፓርኩ፣ ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በተቋሙ 41ኛ ጉባዔ ከመዝገቡ እንዲወጣ ተወስኗል፡፡  

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ኢዱልጥባ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ሐምሌ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ቢሮ እንዳስታወቁት፣ ስሜን ብሔራዊ ፓርክ ከአደጋ ዝርዝር እንዲወጣ የተወሰነው የዓለም የተፈጥሮ ንብረት ማኅበር (አይሲኤን) ተወካዮች በፓርኩ ቅኝት ካደረጉ በኋላ ነበር፡፡

ፓርኩ የአደጋ መዝገብ ውስጥ ከገባባቸው ምክንያቶች መካከል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ላስቻለው የተፈጥሮ ሀብት ተገቢው ጥበቃ አለመደረጉ ይገኝበታል፡፡ የፓርኩ አስተዳደር አካላት ፓርኩን በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣታቸው በላይ፣ ፓርኩ እንዲያገግም የተደረገው ጥረት ዓመታት ወስዷል፡፡ ፓርኩ የተጋረጡበት ሰው ሠራሽ ጫናዎች ማለትም ሕገወጥ ሠፈራ፣ እርሻ፣ የግጦሽ ከብቶች መሰማራት፣ የቤት እንስሳት በፓርኩ መበራከትና ፓርኩ ውስጥ መንገድ መኖሩ ከዝርዝሩ እንዳይወጣ ምክንያት ሆነው ቆይተዋል፡፡

ዩኔስኮ ፓርኩ ከአደጋ መዝገብ እንዲወጣ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች የፓርኩን 136 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይዞታ ማስፋትን ያካትታል፡፡ እንደ ዋልያ አይቤክስ ያሉ ብርቅዬ እንስሳትን ቁጥር ከመጨመር ጎን ለጎን የሰዎች ሥፍራና ልቅ እርሻን ለመቆጣጠር ሥልት መቀየስንም ይጠይቃል፡፡

አቶ ኩመራ እንደሚናገሩት፣ ባለፉት ዓመታት ፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን አስወጥቶ መልሶ የማስፈር እንዲሁም የጠፋውን ብዝኃ ሕይወት ዳግም የመመለስ ሥራዎች ሲከናወኑ ነበር፡፡ ፓርኩን ዳግም በመከለል ረገድ ከ136 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ወደ 412 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንዲሸፍን ተደርጓል፡፡ ከፓርኩ ድንበር ውጪ የነበሩ ብርቅዬ እንስሳት የፓርኩ አካል እንዲሆኑ ማስቻሉንም ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡ አዲሱ የፓርኩ ድንበር በሚኒስትሮች ደንብ ቁጥር 337/2007 ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ መደረጉንም ያክላሉ፡፡

ስሜን ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የነበሩ ሰዎችን አስወጥቶ በሌላ አካባቢ ማስፈር ከሁሉም ሥራዎች ከባድ እንደነበረ የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹አድካሚና እልህ አስጨራሽ የነበረው በፓርኩ የሚኖሩ ሰዎችን ማስወጣት ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ፓርኩ ውስጥ ወደ 418 የሚጠጉ የግጭ ማኅበረሰብ አባወራዎችና እማወራዎች ይኖሩ ነበር፡፡ ከፓርኩ ወጥተው ደባርቅ ከተማ እንዲሰፍሩ ለማድረግ 156 ሚሊዮን ብር ተመድቦ፣ መልሶ ማስፈሩ በ2007 ዓ.ም. ተጀምሮ በያዝነው ዓመት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

ሰዎቹ ከፓርኩ ወጥተው አዲስ ቦታ ሲሠፍሩ እንደ ውኃ፣ መንገድ፣ መብራት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ መሠረተ ልማቶች ሊሟሉላቸው ይገባል፡፡ ሕይወታቸውን ያለ መሰናክል እንዲመሩ የሥራ አማራጮች ሊቀርቡላቸውም የግድ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ዋና ዳይሬክተሩ ሲመልሱ፣ መልሶ ሠፈራ የተካሄደው የነዋሪዎቹ ፈቃደኝነት ተመርኩዞ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

ነዋሪዎቹ ከፓርኩ ከወጡ በኋላ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ሕይወታቸውን የሚመሩበትን መንገድ የሚያመላክቱ ፓኬጆች ተዘጋጅተው፣ ጉዳዩን እንዲከታተል በተቋቋመ ኮሚቴ በኩል እየተተገበሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከአርሶ አደርነት ወደ ከተሜነት አኗኗር ሲመጡ የሚጠብቃቸው የተለየ ኑሮ ስለሆነ የዕውቀት ክፍተት እንዳይኖር አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ቅሬታዎች ቢኖሩም ጥሩ ጅማሮ ላይ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

በተያያዥም 69 በመቶ የፓርኩ ክፍል ከቤት እንስሳት ንክኪ ውጪ እንደተደረገ ይናገራሉ፡፡ የስሜን ብሔራዊ ፓርክን የሚያቋርጠው መንገድ ከፓርኩ ውጪ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ የመንገድ ግንባታው ቢያንስ በዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የዓለም የተፈጥሮ ንብረት ማኅበር ተወካዮች ፓርኩን ከገመገሙ በኋላ ፓርኩ በ41ኛው የዩኔስኮ ጉባዔ ከአደጋ ዝርዝር ከሚወጣ ይልቅ፣ የተጀመሩ ሥራዎቹ ሲጠናቀቁ ወደ ቀደመ ቦታው ቢመለስ ይሻላል የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ፓርኩን ወደ ቀደመ ቦታው ቢመለስ ይሻላል የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ፓርኩን ወደ ቀደመ ይዘቱ ለመመለስ ያደረገችው ከፍተኛ ጥረት ከግምት እንዲገባላት በማሳሰቧ፣ ከአደጋ ዝርዝሩ እንዲወጣ ተወስኗል፡፡ ኢትዮጵያ ፓርኩ ከዝርዝሩ እንዲወጣ በ35ኛው፣ በ39ኛውና በ40ኛው ጉባኤ ጠይቃ ፓርኩ የሚጠበቀውን ያህል ባለማገገሙ ጥያቄው ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ፓርኩን የገመገመው አካል፣ ፓርኩ ከአደጋ ዝርዝሩ ቢወጣም እንኳን አሁንም ሥጋቶች እንዳሉት ገልጿል፡፡ የቤት እንስሳትን ለመቆጣጠር የተቀመጠውን ስልት በተግባር ለማዋል እንደሚከብድ ተጠቁሟል፡፡ ባለሥልጣኑ የቤት እንስሳትን ቁጥር ከ69 በመቶ ወደ ዜሮ የማድረስ ዕቅዱ ምን ያህል ስኬታማ ይሆናል የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም ከፓርኩ ውጪ እየተሠራ ያለው መንገድ ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀቁም ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ፓርኩ ከነበረበት ይዞታ ስለሰፋ ቀድሞ ለዩኔስኮ ከቀረበው ሰነድ የተለየና ወቅታዊ ይዘቱን የሚገልጽ አዲስ ሰነድ መዘጋጀትም ይኖርበታል፡፡

በእርግጥ የተመናመነውን የዋልያ አይቤክስ ቁጥር ወደ 950 ማድረስ ተችሏል፡፡ የቀይ ቀበሮ ቁጥር ወደ 140 ሲያድግ፣ ከ20 ሺሕ በላይ ጭላዳ ዝንጅሮዎችም ይገኛሉ፡፡፡ ሆኖም ፓርኩን በጥንቃቄ በመያዙ ካልተገፋ፣ ያገገመው የተፈጥሮ ሀብት ዳግም መጥፋቱ አያጠያይቅም፡፡ በዚህ ረገድ የእንስሳትን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡

አካባቢው ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለበት እንደመሆኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አስፈላጊነት አያጠያይቅም፡፡ ቢሆንም በአካባቢው የሚካሄዱ ግንባታዎች የተፈጥሮ ሀብቱን ታሳቢ ያደረጉ ካልሆኑ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቱም ይሁን የቱሪስት ፍሰቱ ከአካባቢው አቅም በላይ መሆን የለበትም፡፡ ‹‹ብዙ ባለሀብቶች በአካባቢው ሎጆች መገንባት ቢፈልጉም አካሄዱ ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ተደርጎ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ መሠራት አለበት፤›› ይላሉ፡፡

የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ከዩኔስኮ የአደጋ መዝገብ መውጣቱ አሁን የተሰጠውን ትኩረት እንዳይቀንሰው የሚሉ ሥጋቶች አሉ፡፡ ፓርኩ በከፍተኛ ሁኔታ ሥጋት ካጠላባቸው ፓርኮች አንዱ እንጂ ብቸኛው አለመሆኑም ተያይዞ ይነሳል፡፡ ኢዱልጥባ የተቀሩት የአገሪቱ ፓርኮች ጥበቃ ተደርጎላቸው ወደ ቀደመ ይዞታቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል በቀጣይ ስለያዛቸው ዕቅዶች ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦም ነበር፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ ከሁሉም ፓርኮች የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ሁኔታ አስጊ ሲሆን፣ ፓርኩ እስኪያገግምም ከባድ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ችግር በሚቀጥለው ዓመት እልባት ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡ የአብጃታ ጉዳይም ውስብስብ ከሆኑት አንዱ ሲሆን፣ ሐይቁ እየሸሸ ደኑም እየተመናመነ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ያሻዋል፡፡

ባሌ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በሦስት መንደሮች ነዋሪዎች የሰፈሩ ሲሆን፣ ከስሜን ብሔራዊ ፓርክ የተገኘውን ተሞክሮ በመመርኮዝ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ አስረግጠዋል፡፡ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሰዎች ሰፈራና ልቅ እርሻ ባይኖርም ከ200 ሺሕ በላይ ጥገኛ የቤት እንስሳት ይኖራሉ፡፡ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች በመጠበቅ ረገድ የሁሉም አካል ርብርብ እንደሚያስፈልግ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡