Skip to main content
x

በሕዝቦች እቅፍ ውስጥ የሚሞሸር ፖለቲካ አላችሁ?

ቴሌቪዥን እንደ ዛሬው 24 ሰዓት ሙሉ የማይጠፋ አምፖል ሳይሆን ገና በልጅነቱና በሙሉ የሕይወት ዘመኑ ከመብራት ጋር (መብራት ባለበት ቦታ) ይበራ ይጠፋ በነበረበት ወቅት ልማዳችን የተመሠረተ ሰዎች፣ የዜና ሰዓታችን አሁንም የምሽቱ የሁለት ሰዓቱ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ ፈርዶብን የጠዋት ዜና ይኑር አይኑር አላውቅም፡፡ በራሱ በቴሌቪዥኑ የሰባት ሰዓቱ ዜና ሲሉ ብንሰማም እኔና የእኔ ቢጤዎች ለዚያ ሰዓት ዜና ገና ‹‹ፕሮግራምድ›› አልሆንም፡፡ በዚህ ሰዓት ላይ የሚነሳብን የወሬ ሱስ፣ ወይም የዜና አመል ወይም የ‹‹መረጃ›› ወልፍ እስካሁን የለብንም፡፡ ከቆየው ልማድ ጀምሮ አሁንም ከቀጠለውና ካልቀረው አሠራር ተምሮ አዲስ ነገር ካለ ብሎ ዜና ልስማ የሚለው ከመሸ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ግን ዜና የለም፣ አዲስ ነገር የለም፡፡ ብቻ ግዴታችንን ለመወጣት፣ ምሳችንን ለመክፈል የአገር ቤቱ ብሔራዊ ቲቪ ይከፈታል፡፡ ግማሽ ሰዓት ለመንግሥት ቴሌቪዥን እንከፍላለን፡፡ ይኼ ቴሌቪዥን አሁን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ይሰኛል፡፡ አጭር ስሙ ሳይቀር ኢቢሲ ነው፡፡ ኢብኮ እንኳን አይደለም፣ ይገርማል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእንግሊዝኛ "ETV" ይባል በነበረበት ጊዜ፣ በአማርኛ ኢቲቪ ሳይሆን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአማርኛ ማሳጠሪያ ኢቴቪ ነው ብሎ እንዳልፎከረና ያዙኝ ልቀቁኝ እንዳላለ፣ ዛሬ ደግሞ እንደ ቀድሞዎቹ የብሪታንያ ቅኝ ግዛቶች ምንትሴ ቢሲ ሆኗል፡፡

የብሔራዊ ቴሌቪዥናችንን የመጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. (ሰኞ) የምሽት ዜና የግድ የሰማሁት ቀድም ብሎ በገለጽኩት ስሜት ነው፡፡ ግዴታዬን ልወጣ ነው፡፡ ባጋጣሚ የተለመደው የምሽት ሁለት ሰዓት የግማሽ ሰዓት (ሲደመር)  ዜና ሙሉ ሽፋን ‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስድስተኛ ዓመት መሠረት ድንጋይ የተጣለበት የሚሊንየም አዳራሽ አከባበር ሥነ ሥርዓት›› ላይ ነው፡፡ አብዛኛው ዜና ከሞላ ጎደል ሁሉም ዜና በዕለቱ በራሱ በዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ሥርጭት ሲተላለፍ የነበረው የአከባበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡

የደነቀኝና የልማዴን ባልወጣ ኖሮ ሊያመልጠኝ የነበረው ግን እዚህ ዋና ሽፋን የተሰጠው ጉዳይ ውስጥ የተወሸቀው ‹‹የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የሕዝብን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥናት ይፋ አደረገ፤›› የሚለው ዜና ነው፡፡ ድራሹ እስኪጠፋ ድረስ በስድስተኛ ዓመቱ አከባበር ሥነ ሥርዓት ውስጥ የተወሸቀው ዜና በቴሌቪዥን ጣቢው የዕይታና የምሪት ልክና ለሪፖርተሩ ተሰፍሮ የተሰጠው ግዴታን የመወጣት አቅም መጠን በእጅጉ ተጎሳቁሏል፡፡ ይኼን በመሰለ ‹‹ፖሊሲ›› እና አቀራረብ ውስጥ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከሉ ያቀረበው ጥናት ይዘት ቅምሻውና ጭማቂው ‹‹አልተገለጸልንም››፣ እንዲገለጽልን አልተደረገም፡፡ የጥናቱ ኮፒ ለተሳታፊዎች ስለመስጠቱም፣ በዚያውም ‹‹ተሳትፎውን ለማረጋገጥ›› ለተፈለገው ሕዝብ እንዲደርስ ስለመደረጉ በጭራሽ አናውቅም፡፡

ዕርም ታህልና በጣም ትንሽ ከምናውቀው ከቴሌቪዥኑ ዜና እንደተረዳነው ግን፣ የጥናትና የምርምር ማዕከሉ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕዝብን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ጥናት ማካሄዱን፣ ጥናቱንም ‹‹ይፋ›› ማድረጉን፣ ‹‹የአመራር ብቃት ማነስ፣ የሕዝብ ተሳትፎ የሚፈለገውን ያህል አለመሄድና በሚዲያ ሥራ ላይ ጣልቃ መግባት በጥናቱ የተገለጹ ችግሮች›› መሆናቸውን ሰምተናል፡፡ በተለይም የፖሊሲ ጥናት ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ‹‹በተፈለገው ደረጃና በተፈለገው ፍጥነትና ጥልቀት እንዳይሄድ፣ የሕዝብ ወሳኝነት ሚና፣ የሕዝብ ጫና ፈጣሪነት ድርሻ፣ የሕዝብ የበላይነት ሚና ወደ ማረጋገጥ ደረጃ ግን እንዳንደርስ ያደረጉን ማነቆዎች አሉ፡፡ በዋነኛነት በአስፈጻሚው አካል በኩል የሚፈጠሩ እንቅፋቶች፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በራሱ በአደራጃጀቶች፣ በምክር ቤቶች፣ በሕዝብ አደረጃጀቶች፣ በመገናኛ ብዙኃን ያሉ የራሳቸው እጥረቶች . . . ›› ሲሉ ሰምተናል፡፡

የአቶ ዓባይ ፀሐዬ የተቀነጨቡ የንግግር ፍላጮች (ሳውንድ ባይትስ) በገነኑበትና አራት ደቂቃ በፈጀው በዚህ ዜና ውስጥ፣ የጥናቱ ሪፖርት ለፌዴራልም ሆነ ለክልል አመራር አካላት እንደሚቀርብ፣ እነሱም ሐሳብ እንደሚሰጡበት መፍትሔውም ላይ አቋም እንደሚወስዱበት በአቶ ዓባይ አንደበት ሲነገር አድምጠናል፡፡ ‹‹በሕዝብና በምክር ቤት የሚሠራው ደግሞ›› እንደዚሁ በእነሱ በራሳቸው እንደሚሠራ፣ ለዚህም ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ይመጣ ዘንድ የተወሰነ ሒደት ይጠይቃል ብለውናል፡፡ ‹‹ግን መጀመር አለበት፣ መፍጠን አለበት፣ ዳር መድረስ አለበት፣ በቃ እንደዚህ ብለን መቀጠል አንችልም፡፡ ሕዝብ እያለቀሰ መልስ እያጣ ምንም ማድረግ የማይቻልበት ዓይነት ሁኔታ ደግሞ እየተፈጠረ . . . [ይህ] መሆን ያለበትም ሲሉም ሰምተናል፡፡ እንዲህ የተባለበት ጉዳይ ዜና ነው እንዲህ የተድበሰበሰውና የተሸፋፈነው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የተጎሳቆለው፡፡

ከዚህ በላይ እንደገለጽነው ዋናው ዜና የሕዝብ ወሳኝነት ሚና፣ የሕዝብ ጫና ፈጣሪነት ድርሻ፣ የሕዝብ የበላይነት ሥፍራ አልተረጋገጠም የሚለው ነው፡፡ እንዲያውም የመንግሥት ሚዲያ ቢችልበት ኖሮ በአሁኑ ቋንቋና አባባሉ የሕዝብ ወሳኝነት፣ ጫና ፈጣሪነት፣ የበላይነት ብሎ ነገር የለም ‹‹ብሎ መውሰድ ይቻላል›› ባለ ነበር፡፡ ግን ይኼን ማለት አይችልም፡፡ ሁለት ምክንያቶችን እንሰጣለን፡፡ የመጀመሪያው የአገራችን የመንግሥት ሚዲያ የገዢው ፓርቲ አፈ ቀላጤ መሆኑ በጭራሽ አልቀረም፡፡ የየትኞቹም ፓርቲዎች ፕሮፓጋንዳ ያልተጣባው የሕዝብ አገልጋይ ሚዲያ አልሆነም፡፡ እንዲያውም ሽግግሩ እንኳን አልታሰበም፡፡

ሁለተኛው ሚዲያው የተካነበት፣ ፖለቲካውም የተዘፈቀበት የቋንቋ ነገር ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የ‹‹ጥሪ ዋጋ›› ቋንቋ ነው፡ በአገራችን ውስጥ የተለመደ በግብይይት ውስጥ የሚታወቅ የጥሪ ዋጋ የሚባል ነገር አለ፡፡ ሻጭ የሚፈለገው የመሸጫ ዋጋ ላይ ለማረፍ መጀመሪያ በጣም ትልቅ ዋጋ ይጠራል፡፡ በጎዳና ላይ ግብይይትማ ሻጭ የጠራውን ትልቅ ቁጥር እጅግ በጣም ጎምዶ፣ እሺ መባል እንኳን ዋስትና ሊሆን አልችል ብሎ አስቸግሯል፡፡ በውሸትም ረገድ የዚህ ዓይነት የጥሪ ታክቲክ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ ስብሰባ እንድትመጣ ፈርም እሺ፣ የቤተሰብ ፖሊስ ተጠሪ ምረጥ እሺ፣ የቀበሌ (አሁን የወረዳ) የበር ማንኳኳት እንኳ የአድራጊ ፈጣሪነት ኃይለ ቃልን በሚያስተጋባበት አገር፣ ዴሞክራሲ ባህል እየሆነ ስለመምጣቱ ማውራት፣ ኧረ ባህል አልሆነም የሚል ክርክር ውስጥ ይከተንና ሳይታወቀንም ሆነ እየታወቀን ‹‹ዴሞክራሲ ተጀመረ እንጂ . . . ›› ወደሚል ማስማሚያ ላይ እንድንወድቅ ያደርገናል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ስምንት እየተጠቀሰም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊነት የሚገለጸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው ብቻ ሳይሆን ‹‹በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት›› ጭምር ነው ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች የፖሊሲ መጽሐፍም (1994) የሚመካው በዚሁ ነው፡፡ በዚህና በሌሎች ጽሑፎችና መግለጫዎች በየትኞቹም ዴሞክራሲዎች ውስጥ ያልተለመደውን የሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎን (ቀጥተኛ ዴሞክራሲን) ለማረጋገጥ ረዥም ርቀት ሄደናል የሚባለውም ተመሳሳይ ጠቀሜታ ላለው ‹‹የጥሪ ዋጋ›› ቋንቋ ነው፡፡ ዜናው ውስጥ ተደጋግመው ያየናቸው ‹‹የሕዝብ ተሳትፎ የሚፈለገውን ያህል አለመሄድ››፣ ‹‹በተፈለገው ደረጃ፣ በተፈለገው ፍጥነትና ጥልቀት›› አልሄደም ማለትም ተመሳሳይ ዋጋ ያለው ‹‹ጥሪ›› ነው፡፡

የሕዝብ ተሳትፎ ችግራችን ምንድነው? ወዘተ የሚለውን ጥናቱ አነሳው የተባለውን ጉዳይ ወደምናይበት ሙከራ ከመግባታችን በፊት፣ የፖሊሲ ጥናቱ ዜና የተወሸቀበትን፣ የግድቡን ጉዳይና ፋይዳ በአጭሩ እንቃኝ፡፡ የዓባይ ውኃን የመጠቀም መብታችን ጫጫታ የማያስፈልገው የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ይኼን መብት ማስከበር ተገቢ ኃላፊነት መሆኑም በጭራሽ አያከራክርም፡፡ ዋናው ጉዳይ በብልህ አካሄድ ማንንም ለመጉዳት እንዳልታለመ፣ አካሄድና መንገዱም ማንንም እንደማይጎዳ ሳይታክቱ በማረጋገጥ የጠብ መንገድን መዝጋት መቻል ነው፡፡ በዚህ በኩል ከሁሉም አገሮች ጋር ያለውን የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነት የማጠናከሩ ጥረት ከንቁነት ጋር አግባብ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ጠላትነትን የሰረዘ፣ ‹ወይ እኔ› ‹ወይ አንተ› የሚለውን የአንደራረስም ፖለቲካን የሚያፈርስ፣ የእርቅና የመግባባት ፖለቲካዊ ሁኔታን መፍጠር ባለ ብዙ ጎን ወሳኝ ጠቀሜታ አለው፡፡ የዚህ ሁኔታ መሟላት ከውጭ በተዘዋዋሪ የመተራመስን ዕድል የሚዘጋና ልማትንና ሰላምን ነቅቶ የሚጠብቅ፣ ከዳር እዳር በአንድ ላይ የመቆም፣ ምልዓተ ሕዝባዊ ዘብ (ወታደራዊ ኃይል የማይተካው መከላከያ) አገሪቱን ያቀዳጃታል፡፡ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲም መሠረት ለመያዝ የሰፋ ዕድል ይፈጠርለታል፡፡ በዚህ የውኃ መብታችን መከበር ምክንያት ከድሮ ጀምሮ ገና ለገና የአገራችንን የኢትዮጵያን መጠንከር ከሥጋት የሚቆጥሩት፣ ከዚህ ቀደምም የኤርትራን ትግል ጭምር በማዳከሚያነት ሲጠቀሙበት ለነበሩት ሰሜናዊ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ አገሮች፣ የውስጥ መናጨታችን ሠርግና ምላሻቸው እንዳይሆን ሁሉም ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራም ግንኙነትም 20 ዓመታት ሊሞላው ከተቃረበው ከዚህ ጠንቀኛ አረንቋ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ተቃዋሚነትንና የጎረቤት አገር ቀውስን መጠቃቂያና መጠፋፊያ እስከማድረግ እሳትና ጭዳቸው መውጣቱ ከባድ ጠንቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሐሳብ መለያየትና በተለያዩ ሰላማዊ የተቃውሞ ጎራ ውስጥ መሠለፍ ሞት አለመሆኑን ካረጋገጥንና ተቃውሞ የሚፈታበት ሰላማዊ አሠራር ከመሠረትን፣ የውስጥ ተቃውሞ ከጎረቤት ባለጋራነት ጋር አይሸራረብም፡፡ ይኼ ራሱ ‹‹ለሕዝብ ተሳትፎ›› መሪ መንገድ ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎም ጥረትና ውጤት ነው፡፡

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከሉ ይፋ አደረገው ከተባለው ጥናት ዜና በስሚ ስሚና በጭላንጭል እንደተረዳነው፣ የሕዝብ ወሳኝነትና የሕዝብ የበላይነት ሚና፣ የሕዝብ ጫና ፈጣሪነት ድርሻ ማረጋገጥ ያልተቻለው አንድም በአስፈጻሚው አካል እንቅፋቶች፣ ሌላው እንዲያውም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአደረጃጀቶቹና በመገናኛ ብዙኃን የገዛ ራሳቸው እጥረት ነው ተብለናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሉዓላዊነት መገለጫ መንገድም እንደ ሌላው አገር ዴሞክራሲ በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ተሳትፎ ጭምር መሆኑን፣ በዚህም ረገድ ረዥም ርቀት መጓዛችን ሲነገረን ኖሯል፡፡ የሚገርም ነው፡፡

ገዢው ፓርቲ ዛሬም ከአምስት ምርጫ በኋላ፣ ከምርጫ 2007 ዓ.ም. ወዲህም፣ ከ2008/2009 ዓ.ም.  ሁከት አሁን ድረስ ፀንቶ ያለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላም ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አለኝ ማለቱን አልተወም፡፡ ኢሕአዴግና ‹‹አጋሮቹ›› የተቀራመቱትን ምርጫ ለድጋፉ ምስክር አድርጎ ማቅረቡ ዛሬም አልቀረም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የድጋፍ ኪሳራውን መደበቅ አልቻለም፡፡ እየተስፋፋና እየጨመረ የመጣበት ተቃውሞና ቁጣም በእጅጉ አሳጥቶታል፡፡ የአገራችን ኅብረተሰብ ብዝኃነት ያለው ነው፡፡ ብዝኃነቱም በብሔርና በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚና በፖለቲካ ፍላጎቶቹም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህም በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊወከል እንደማይችል ኢሕአዴግ በጥብቅ  ያምናል፡፡ ይኼ በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊወከል የሚችል ኅብረተሰብ አይደለም የተባልነው ገና አሁን በ2009 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነው፡፡

ዕድሜ ለኢሕአዴግ እንጂ የምርጫ ድምፅና ድጋፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና አልተግባቡም፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን አገሪቷ ውስጥ ያጠላው ደመና ሌላ አመለካከት እንዳይወስድብኝ፣ ችግር እንዳይገጥመኝ ተብሎ ወደ ምርጫ የግድ መውጣትና ያልወደዱትን መምረጥ በአዲስ አበባ ሳይቀር ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ኢሕአዴግን መደገፍና መምረጥ፣ በጥቅልም ሆነ በግል ሳይጠመዱ ከመኖር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለዚህ ተመዝጋቢዎችን ወይም መራጮችን አንድ በአንድ ለመለየትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘዴና ይኼን የሚከታተል የቅርብ አስተዋይና አስታዋሽ/ተመልካች መኖር አለመኖሩ የግድ መረጋገጥ የለበትም፡፡ ፍርኃቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ አዲስ አበባን በሚያህል ሰፊ ከተማ ውስጥ በየቤቱ እየተሄደ ያልተመዘገበን የመቀስቀስና ስም የመልቀም ሥራ ይካሄዳል፡፡ ምዝገባም ካለቀ በኋላ ማን እንደቀረ ይለያል፡፡ ከዚህ ጋር ማን ምንድነው? የሚለው ጉዳይም መኖሩ ግልጽና የግድ ነው፡፡

በማኅበራትና ‹‹በአደረጃጀት›› የሕዝብ ተሳትፎ የሚባለውም የእስካሁኑ ማስመሰል እንኳን የሌለበት ድርቅና ነው፡፡ ኢሕአዴግ በየተቋማቱ፣ በየማኅበራቱ፣ በመላ ቢሮክሲው ውስጥ እስከ መጨረሻው የከተማና የገጠር ቀበሌ መዋቅር ድረስ በወጣት፣ በሴት፣ በመምህራን፣ በማኅበራት ውስጥ ጭምር ሥርና ጅማት ሆኖ የተሠረጫጨ፣ ራሱን ሥጋና ደም አድርጎ የዘረጋ፣ ተማሪውን፣ ገበሬውን፣ ሴቱን፣ የመንግሥት ሠራተኛውን፣ ነጋዴውን፣ ሥራ አጡን ሁሉ የተበተበ ‹‹አደረጃጀት›› አለው፡፡

ኢሕአዴግ ለእሱ የማይታመኑትን አካባቢዎችና ማኅበራት የተቃዋሚዎች ምርጥ ምሽግና የጠላት ወረዳ አድርጎ ያያቸዋል፡፡ የእሱ ምርኮና ወረዳው ውስጥ የገቡትን ከፖለቲካ ነፃ የሚሆን ነገር የለም ሲል ለእሱ ፊት የማይሰጡትን ትምህርት ቤቶች ማኅበራት ግን ከፖለቲካ እንዲርቁ ይፈልጋል፡፡ ሥራቸው ጥናትና ምርምር ነው፡፡ ፖለቲካ ከተፈለገ ከዩኒቨርሲቲና ከትምህርት ቤት ውጪ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሞ ማካሄድ ይቻላል ይላል፡፡ የተማሪ የመመራመርና የማወቅ ጉዳይ ፖለቲካን የሚጨምር መሆኑን ኢሕአዴግ ባይክድም፣ በሌሎች የዕውቀት መስኮች የሚሠራባቸው የኮንፈረንስ፣ የውይይትና የሌክቸር (ገለጻ) መንገዶች በፖለቲካ ጉዳይ ላይ እንዲፈጸሙ አይፈልግም፡፡ በተለይ እሱ ባላስገበረው መድረክ ውስጥ ከመደበኛ ትምህርት ተግባር ውጪ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መነጋገርም ለኢሕአዴግ አይመቸውም፣ ነውርም ነው፡፡

የተማሪዎች ማኅበር ለተማሪው፣ የመምህራን ማኅበር ለመምህራን፣ የሠራተኛው ማኅበር ለሠራተኛው ጥቅምና መብት መታገል ባህሪያቸው ነው፡፡ ይኼ ግን ኢሕአዴግ እንዲታሰብ እንደሚፈልገው ከፖለቲካ በመለስ ያለ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሙያ ጥቅምና መብት ከመንግሥት ፖሊሲዎች ጋር ይገናኛል፡፡ ከአንዳንዱ ማኅበር የውስጥ ጥቅም ያለፈና ማንኛውንም የሙያና የብዙኃን ማኅበር የሚያገናኝ ጥቅምም አለ፡፡ ማንኛውም ማኅበር በነፃ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጽና የመቃወም፣ አድማ የመምታት መብቶች፣ በአጠቃላይ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከጥቃት ከመከላከልና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባትና መቀጠል ከመዋደቅ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ያለውን መንግሥት መደገፍም ሆነ መቃወም ሊመጣ ይችላል፡፡ ከአንዱ ፓርቲ አቋም ጋር መጣጣምና ከሌላው ጋር መቃረን ይከሰታል፡፡ የጋዜጠኛም ሆነ የተማሪ፣ የመምህራንም ሆነ የሠራተኛ፣ የመሐንዲስም ሆነ የሐኪሞች ነፃ ማኅበርነት የሚገለጸው የፓርቲ አቋምን በመደገፍና ባለመደገፍ ሳይሆን፣ ከድርጅታዊ ቁጥጥርና ትዕዛዝ ውጪ ሆኖ በወደዱት ለመንቀሳቀስ መቻልን ነው፡፡ የብዙኃን ማኅበራትን ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚለያቸው ፖለቲካ ውስጥ አለመግባት ሳይሆን፣ በፖለቲካ ፕሮግራም ዙሪያ የመሰባሰብና ለሥልጣን የመታገል ዓላማ አለመያዛቸው ነው፡፡ ለኢሕአዴግ ይኼ አይጠፋውም፡፡ እንዲያውም በወረቀት ላይ (የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ሰነዱ) የሙያና የብዙኃን ማኅበራት በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ከጠባብ ጥቅም ያለፈ ልዩ ቦታ እንዳላቸው ይነግረናል፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ትግላቸው ኢሕአዴግን ሲፈታተን ግን ትርጉሙ ሌላ ይሆናል፡፡

ኢሕአዴግ የሕዝብን ተሳትፎ የሚታገልበት ሌላም ዘዴ አለ፡፡ ሕዝብ ጥቅሙን ያውቃል፡፡ ሕዝብ የሚበጀውን ራሱ ያውቃል ይባላል፡፡ ይኼ ሕዝብን የመገበዝና ድጋፍን የመሻማት ተራ ዘይቤ ነው፡፡ በማንኛቸውም ጥያቄ ሕዝብ ጥቅሙን ካወቀ የፖለቲከኞች መጫጯህ ለምን አስፈለገ? ጥቅም ሁሉ ፈጥጦና ተሰጥቶ ላይገኝ፣ መወሳሰቡና በብዥታ መታጠር ሊኖር ይችላል፡፡ የፖለቲከኞች፣ የምሁራን፣ የጋዜጠኞች አንዱ ሥራም አጥርቶ፣ ፈልቅቆ፣ ፈልፍሎ፣ አበልፅጎ ማውጣት ነው፡፡ ሕዝብ ጥቅሙን ያውቃል፣ የሚበጀውን ያውቃል ባይነት ፋይዳ የሚኖረውም አማራጮች እየወጡ በአግባቡ እንዲብላሉና እንዲፋጩ ተደርጎ ሕዝብ በጉዳዮች ላይ ፍላጎቱንና ምርጫውን እንዲገልጽ ከማስቻል ጋር ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ፍላጎትና ጥቅምን ማወቅ ላይጣጣሙ የሚችሉበት ጊዜ አለ፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ያለ ኢንፎርሜሽን ሚዲያ፣ አካዳሚ ነፃነት የማይታሰበው ለዚህ ነው፡፡

አገር ስለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እየተናገረ ነው፡፡ የማንኛውም ሥር ነቀል ማኅበራዊ ለውጥ ስኬት ዋና ሚስጥር የሕዝብን ልብ የመርታት፣ የእሱን ፈቃድ የማግኘትና ወደ ታላቅ የተግባር ጎርፍ የመምራት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የሚሰምረው ብዙኃኑ በለውጡ መጪ ልማታቸውን እስካዩበትና እስከተማመኑበት ድረስ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግገው አማራጭ ሆነው ወጥተው በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ይዘው ሊያስተዳድሩን የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ መሠረታዊ ሀቆች ላይ የተፈተለ የፖለቲካ አቋምና ምግባር ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ እውነታቸውን ከውሸታቸው፣ የምራቸውን ከቀልዳቸው፣ የለበጣውን ከሁነኛው መለየት ይቻል ዘንድ የፖለቲካ መኃይምነት ዳስ የድብብቆሽ ጉሮኖ መናድና መፍረስ አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፣ ሥልጣን ላይ ያለውም ጭምር በኅብረተሰቡ መሠረታዊ ሀቆች ላይ የተፈተለ የፖለቲካ አቋም ወደ ሕዝብ የሚደርሰው፣ በሕዝብ ድጋፍ የሚታቀፈው፣ ሰፊ የፖለቲካ ጉልበትም የሚያገኘው ነፃ መደራጀት፣ ነፃ ንግግር፣ ነፃ መድረክ ሲፈጠር ነው፡፡

የሆነ ባለሙያ ወዳጄ ሙሽራ ታውቃለህ? አለኝ፡፡ ለካስ እሱ የሚያወራው እንደ እንሰት፣ ሙዝና ዘንባባ ባሉ ተክሎች አናት ላይ አዲስ እየወጣ ያለውና የተጠቀለለው ወይም የተሸበለለው መሀከለኛውን ቅጠል ነው፡፡ ይህም ራሱ የመዝገበ ቃላቱ ትርጉም ነው፡፡  ለካስ እኛ የምናውቀው ሁለተኛውን የሙሽራ ትርጉም ነው፡፡

ባለሙያው ወዳጄ እንዳስተማረኝ ሁልጊዜ አዲስነትንና ዕድገትን የሚወክለው የእንሰት ተክል ሙሽራ፣ ያለንብርብር አቃፊው ሙቀትና ከለላ በቀላሉ ጠውላጊ ነው፡፡ ይኼ እንዳይሆን ሁልጊዜ በሰፊ ዕቅፍ ውስጥ ተሞሽሮ ዕድገትን ይፈለቅቃል፡፡ እያደገም ሞሻሪውን ያሳድጋል፣ ያሰፋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲም የፈለገ የአቋም ጥራት ቢኖረው፣ የፈለገውን ያህል ቡድኖችን ቢያሰባስብ በሕዝቦች እቅፍ እስካልተሞሸረ ድረስ እንኳንስ ለለውጥና ለአገር ዕድገት፣ ራሱንም ለማዳን የሚበቃ ፖለቲካዊ አቅም አይኖረውም፡፡ ሕዝብ አቀፍ ፖለቲካዊ ጉልበት ለመገንባት በሕዝቦች እቅፍ ውስጥ መሞሸር ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡