Skip to main content
x
በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የ5 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የ5 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ወርልድ ቪዥን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል ዓላማው ያደረገና በዘመቻ መልክ የሚተገበር የአምስት ዓመታት አገር አቀፍ ፕሮግራም ይፋ አደረገ፡፡ ለዘመቻው በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል፡፡ 

ፕሮግራሙ፣ በሕፃናትና በሴቶች ላይ የሚደርሱ የኃይል ጥቃት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋና የመሳሰሉት ችግሮችን በተመለከተ ለኅብረተሰቡ ግንባቤ መስጠት፣ ለሴቶች የሙያ ሥልጠና፣ የብድርና ቁጠባ ዕድሎችን በማሻሻል የኢኮኖሚ ድጋፍ ማድረግ፣ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ የማይታወቁ የሴቶችና ሕፃናት ጥቃትን አስመልክቶ በመንግሥት የወጡ ሕጎችና ፖሊሲዎች ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ መዋቀር በመዘርጋት የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት ላይ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ያለ ዕድሜ ጋብቻና ሌሎችም በሕፃናትና በሴቶች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል ‹‹ዓለም አቀፍ ርብርብ ይጠይቃል›› በሚል መርህ የተዘጋጀው ይህ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ፕሮግራም ሰኔ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በይፋ ተጀምሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 የተደረገ የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ቅኝት እንደሚያመለክተው፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ 15 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የሚዳሩት ከ18 ዓመት በታች ሳሉ ነው፡፡ በአገሪቱ ከ15 እስከ 19 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 13 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ሴቶች በልጅነታቸው የልጅ እናት እየሆኑ ነው፡፡ ይህ ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን 23 በመቶ በአፋር፣ 19 በመቶ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ 17 በመቶ  በኦሮሚያና በሐረሪ፣ 16 በመቶ በጋምቤላና 8 በመቶ ደግሞ በአማራ ክልል ናቸው፡፡ ሴቶች የሚያገቡበት አማካይ ዕድሜም 16.5 ዓመት ነው፡፡ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው የሚያረግዙም ሴቶች ቁጥር ከአፋርና ሶማሌ ክልል ቀጥሎ በኦሮሚያ ከፍተኛ ሥርጭት መኖሩንም ናሙናው ያመለክታል፡፡

የኦሮሚያ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አዚዛ አብዲ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ በክልሉ ሁለት ዞኖች በደቡብ ሸዋና በሰሜን ሸዋ ትልቅ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ኦሮሚያ ላይ እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች መቀነሳቸው ሲሆን፣ በሁለቱ ዞኖች ላይ በዘመቻ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ክልላችን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ይሠራልም፤›› በማለት ከ18 ዓመት በታች ያሉ ልጃገረዶች እንዳይዳሩ ክልሉ የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሃይማኖታዊ አመለካከት፣ የባህል ተፅዕኖ፣ የኢኮኖሚ ችግርና የአቻ ግፊት ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲዘወተር እያደረጉ የሚገኙ መሠረታዊ ችግሮች ናቸው፡፡ አለመማርም ሌላው ትልቁ ችግር ነው፡፡ ‹‹አንዲት ልጅ ያለ ዕድሜ እንድታገባ ማድረግ ድህነት እንዲቀጥል ማድረግ ነው›› ያሉት አቶ ፀጋአብ ታደሰ በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ያለ ዕድሜ ጋብቻን የሚከለክለው ዘመቻ አስተባባሪ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ ላይ ለብቻው ትኩረት ተደርጎበት አለመሠራቱ ችግሩ እስካሁን እንዳይቀረፍ አድርጓል፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሚለው ተካትቶ ሲሠራበት ነው የቆየው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ከባህልና ከሃይማኖት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ወንድ ድንግል ማግባት አለበት የሚል ሃይማኖታዊ መርህ አለ፡፡ የአንዲትን ልጃገረድ ድንግልና እርግጠኛ መሆን የሚቻለው ደግሞ የመጀመሪያ የወር አበባዋን ከማየቷ በፊት ነው የሚል እምነት መኖር፣ ‹‹እኛም በተመሳሳይ ዕድሜያችን አግብተን ምን ሆንን›› የሚሉ እናቶች መኖር ሴት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው እንዲዳሩ እያደረገ ይገኛል፡፡

‹‹መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያለ ዕድሜ ጋብቻን በተመለከተ መረጃ ከመስጠት ባሻገር ከበስተጀርባው ያሉ ችግሮችን ማስወድ ላይ ትኩረት አድርገው አለመሥራታቸው ሌላው ችግር ነው፤›› የሚሉት አቶ ፀጋአብ የኢኮኖሚ ችግር ትኩረት የሚሰጠው ሌላው ግፊት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት አይልኩም፡፡ ትምህርት ቤት ያልገባች ልጃገረድ ደግሞ ያለ ዕድሜዋ የመዳር ዕድሏ በጣም ሰፊ ነው፡፡