Skip to main content
x
በአውሮፓ ኅብረት ህልውና ላይ ሪፈረንደም እንደማካሄድ የሚቆጠረው የፈረንሣይ ምርጫ

በአውሮፓ ኅብረት ህልውና ላይ ሪፈረንደም እንደማካሄድ የሚቆጠረው የፈረንሣይ ምርጫ

በፈረንሣይ የወደፊት ዕጣ ፈንታና በአውሮፓ ህልውና ላይ ለውጥ ያመጣል የተባለው የፈረንሣይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረ ወዲህ፣ በፈረንሣይም ሆነ በአውሮፓ ኅብረት ውጥረት ነግሷል፡፡ በተለይ ከዕጩዎቹ አንዷና የፕሬዚዳንትነት መንበሩን ሊይዙ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁት የቀኝ አክራሪ ፓርቲ ብሔርተኛዋ ማሪን ለፔን፣ ፈረንሣይን ከአውሮፓ ኅብረት የመነጠል ፍላጎታቸውና በስደተኞች ላይ ያላቸው አቋም ለኅብረቱም ሆነ ለፈረንሣይ ሥጋት ሆኗል፡፡

ሆኖም እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ሕዝበ ውሳኔ ካሳለፈች በኋላ የመበታተን ሥጋት ያንዣበበትን ኅብረቱን ይበታትኑታል የተባሉት ዕጩዋ ለፔን፣ ባለፈው እሑድ በተካሄደው የፈረንሣይ ፕሬዚዳንታዊ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ የመሪነቱን ሥፍራ አላገኙም፡፡ ይልቁንም የፔንን ያህል ያልተጠበቁትና ለዘብተኛው መሀል ዘመም ኢማኑኤል ማክሮን በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከፔን ልቀው ተገኝተዋል፡፡

በመጀመርያው ዙር ምርጫ ከቀረቡት 11 ዕጩዎች ኤማኑኤል ማክሮን 23.75 በመቶ ድምፅ ሲመሩ፣ ማሪ ለፔን 21.53 በመቶ ድምፅ በማግኘት ተከትለዋል፡፡ በመሆኑም ሚያዝያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚካደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ የሚስተር ማክሮንና የሚስ ለፔን ወደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው መምጣት ለፈረንሣይ ታሪካዊ የተባለ ነው፡፡ ከ60 ዓመታት በላይ እየተፈራረቁ አገሪቱን ሲመሩ የነበሩት የሶሻሊስትና የግራ ዘመም ተቃዋሚ ሪፐብሊካን ፓርቲዎች በዘንድሮ ምርጫ አልቀናቸውም፡፡ ይልቁንም የኤን ማርቼው ኢማኑኤል ማክሮንና የናሽናል ፍሮንቷ ማሪን ለፔን ለፈረንሣይ ፕሬዚዳንትነት ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋለማሉ፡፡

የሌሎች አገር ዜጎችን ያገላል ለሚባለው ለናሽናል ፍሮንት ፓርቲ ለፔን ያስመዘገቡት ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጡ ሲሆን፣ ከሶሻሊስትና ከሪፐብሊካን ፓርቲዎች የድጋፍ ቃል ለተገባለት ኤን ማርቼ ደግሞ ድንቅ ነው፡፡ ሆኖም የሁለቱም ፓርቲ መሪዎች ለፈረንሣይ የወደፊት ጉዞ ያላቸው ዕቅድ ጽንፍ ለጽንፍ ከመሆኑም ባሻገር፣ በአውሮፓ ኅብረት መኖርና አለመኖር ላይም ያላቸው አቋምም የተለያየና ኅብረቱን ውጥረት ውስጥ የከተተ ነው፡፡

ኢማኑኤል ማክሮን ማን ናቸው?

የ39 ዓመቱ ማክሮን ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው ሁለተኛው ዙር የፈረንሣይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ካሸነፉ የመጀመሪያው የፈረንሣይ ወጣት ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በምርጫ ተወዳድረው ባያውቁም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፖለቲካዊ ብቃትን አስመዝግበዋል፡፡ የልማት ባንክ ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2014 ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ከመሆናቸው አስቀድሞ ለፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንዴ የኢኮኖሚ አማካሪ ነበሩ፡፡ እሳቸው ያረቀቁት ‹‹ማክሮን ሎው›› የተባለው ቢል ዘወትር እሑድ ሱቆች እንዲከፈቱና አንዳንድ ኢንዱስትሪዎችም ከቁጥጥር ጫና እንዲላቀቁ የፈቀደ ነው፡፡ ‹ዲጂታል ስታርት አፕን› አስተዋውቀዋል፡፡ ሆኖም ፖሊሲዎቻቸው በግራ ዘመም ሶሻሊስቶች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ግራም ሆነ ቀኝ ዘመም ያልሆነውን ‹‹ኤን ማርቼ›› ፓርቲ እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2016 ያቋቋሙ ሲሆን፣ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊነታቸው የለቀቁትም ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር ከመጀመራቸው አስቀድሞ ነው፡፡

በሶሻሊስቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ዋልስ ድጋፍ ያላቸው ሚስተር ማርኮን፣ በ20 ዓመት ከሚበልጧቸው የቀድሞ መምህራቸው ብሪጌት ትሮንዣ ጋር ትዳር የመሠረቱ ቢሆንም ልጅ አላፈሩም፡፡ ሆኖም ከባለቤታቸው ከሚወለዱ ልጆች ለተወለዱ ሰባት ልጆች የእንጀራ አባት ናቸው፡፡

የማክሮን ዕቅዶች

ማክሮን በ35 የተለያዩ ሥርዓቶች የተዋቀረውንና ውስብስብ የተባለውን የፈረንሣይ የጡረታ ሥርዓት አንድ ማድረግ ዓላማቸው ነው፡፡ በአገሪቱ የሚታየውን የበጀት ጉድለት ማስተካከል፣ 120 ሺሕ የሕዝብ አገልግሎት ሥራዎችን ማቋቋምና የኮርፖሬሽን ታክስን አሁን ካለበት 33 በመቶ ወደ 25 በመቶ ዝቅ ማድረግም ፍላጎታቸው ነው፡፡ ካምፓኒዎች በሳምንት 35 ሰዓታት እንዲሠሩ መደራደር፣ መምህራን በብዛት በማይገኙባቸው የአገሪቱ ክፍሎች መምህራንን መላክና ከ15 ዓመት በታች ያሉ ተማሪዎች ሞባይል ስልኮችን ትምህርት ቤት ውስጥ እንዳይጠቀሙ ማድረግም ይገኝበታል፡፡ አሥራ አንድ ሺሕ ፖሊሶችን በመቅጠር ሽብርተኝነትን ለመፋለም አስበዋልሸ፡

ፈረንሣይ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከርና በዩሮ ዞን አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማጥበቅም ፍላጎታቸው ነው፡፡ የሥራ ላይ ልምምድን ለማጠናከር 50 ቢሊዮን ዩሮ ለመመደብ ያቀዱ ሲሆን፣ የአገሪቱን የኃይል አጠቃቀም ወደ ታዳሽ ኃይል የመቀየር ግብ አላቸው፡፡

ማሪን ለፔን ማን ናቸው?

የ48 ዓመቷ ሚስ ማሪን ለፔን የፍሮንት ናሽናሊስት ፓርቲን መንበር ከአባታቸው ላይ የነጠቁት እ.ኤ.አ. በ2011 ነበር፡፡ በ2012 በነበረው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ሦስተኛ ሰው ሆነው ነበር፡፡ በ2015 በተካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ለፓርቲው ትልቅ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ በ2010 ሙስሊሞች በጎዳና ላይ የሚያደርጉትን ፀሎትና የናዚ ጀርመን ወረራን በማነፃፀራቸው ትችት የገጠማቸው ለፔን፣ ለ2017 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲቀሰቅሱም ሁሉንም ስደተኞች እንደሚያግዱ አሳውቀዋል፡፡

ፓርቲው ሌሎችን ያገላል የሚባለውን በመለወጥ መልካም ዝና መልሰው ገንብተዋል የሚባሉት ለፔን፣ አሁን ደግሞ ስደተኞችን የሚያገል ንግግር በማድረግ ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ የፓርቲውን የሕግ ክፍል ይመሩም ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ሰሜን ምዕራብ ፈረንሣይን ወክለው ለአውሮፓ ፓርላማ ተመርጠው በማገልገልም ላይ ናቸው፡፡ ሁለት ጊዜ ትዳራቸውን የፈቱ ሲሆን፣ የሦስት ልጆች እናት ናቸው፡፡

የለፔን ዕቅዶች

ሚስ ለፔን ፈረንሣይን ከአውሮፓ ኅብረት ለመነጠልና በዩሮ መገበያየትን ለማስቆም ሪፈረንደም ለማካሄድ አቅደዋል፡፡ ሕገወጥ ስደተኞችን ሙሉ ለሙሉ የሚያስወጡ ሲሆን፣ ሕጋዊ የስደተኞች ቅበላቸውንም በዓመት በ10,000 ይቀንሳሉ፡፡

ቤት የማግኘት መብት ለፈረንሣይ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን፣ አክራሪ የሚባሉ አስተምህሮ የሚከተሉ መስኪዶችን ይዘጋሉ፡፡ የሃይማኖት መገለጫ የሆኑ አለባበሶችና ሴት ሙስሊሞች ራሳቸውን የሚከናነቡበትን ቡርቃ አድርጎ በመንገድ መታየትም ይታገዳል፡፡ የጡረታ መውጫ ዕድሜን 60 እንደሚያደርጉ ያስታወቁት ለፔን፣ ከፈረንሣይ ውጭ ከሚገኙ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የ35 በመቶ ታክስ ይጥላሉ፡፡

የአውሮፓውያኑ ምልከታ

በተለያየ ጽንፍ ከቆሙት ማክሮንና ለፔን፣ የአውሮፓ ኅብረት ምልከታ ለማክሮን ያደላ ነው፡፡ ማክሮን የአውሮፓ ኅብረት መኖር እንዳለበትና እንዲጠናከር የሚፈልጉ ሲሆን፣ ለፔን ግን በኅብረቱ ላይ ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ ይህም የአውሮፓ ኅብረት አስፈላጊነትን በሚያቀነቅኑት ጀርመን፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቤልጂየምና ሌሎችም የኅብረቱ አባል አገሮች ተቀባይነትን አሳጥቷቸዋል፡፡

የመጀመሪያውን ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ በፈረንሣይና በአውሮፓ ኅብረት ባንዲራ ታጅበው ንግግር ላደረጉት ማክሮን የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ከኅብረቱ አገሮች ተችሯቸዋል፡፡ የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ቻርለስ ሚሼል የደስታ መልዕክታቸውን ሲገልጹ፣ የአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክትን ወደፊት የማራመድ ብሩህ ተስፋ ሰንቀው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የቼክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንትም፣ ‹‹የማክሮን ድል በብሔርተኛነትና በአክራሪነት የታመሙትንና የደከሙትን ለመለወጥ ተስፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትን ከእንግሊዝ ጋር በዋናነት የሚያደራድሩ ፈረንሣያዊው ሚሼል ባርኒየር፣ ‹‹ማክሮን ጀግናና አውሮፓዊነትን የሚያቀነቅን በመሆኑ እደግፈዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቀመንበር ፍሬድሪካ ሞግህሪኒ፣ ‹‹ማክሮን የወደፊቱ ትውልድ ተስፋ›› ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ጂን ጃንከር የኅብረቱን ፕሮቶኮል በመጣስ ለማክሮን ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ባልተጠናቀቀ ምርጫ ላይ አስተያየት የማይሰጥ ቢሆንም፣ የአውሮፓ ኅብረትን መፈራረስ የሚመኙትን ለፔን ሚስተር ማክሮን በመጨረሻው ምርጫም እንዲያሸንፉ ተመኝተዋል፡፡ ‹‹የፈረንሣይ መራጮች ውሳኔ መሠረታዊ ነው፡፡ የአውሮፓ የጋራ እሴቶችን በማጠናከር ወይም በማፈራረስ ላይ የተመሠረተ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ለማክሮን ምንም ዓይነት የቅስቀሳ ድጋፍ የማያደርግ መሆኑን ቢገልጽም፣ የቀድሞው የፈረንሣይ የገንዘብ ሚኒስትርና በብራሰልስ የኅብረቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር፣ የፈረንሣይ ምርጫ በአውሮፓ ኅብረት ላይ ሪፈረንደም ከማካሄድ ይወዳደራል ሲሉ ምርጫው ለኅብረቱ መኖር ወይም መፈራረስ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ‹‹አጓጊ ምርጫ›› ብለውታል፡፡

በመጀመርያው ዙር ምርጫ ሽንፈት የተጎናፀፉት ለፔን፣ ‹‹የፈረንሣይ ሕዝብ ፍላጎትን ለመሙላት የእስልምና አክራሪነትና ሽብር ላይ አነጣጥሬያለሁ፡፡ ሚስተር ማክሮን በዚህ ጉዳይ ደካማ ነው፡፡ የፈረንሣይ ሕዝብን ከሽብር ለመከላከል ፕሮጀክት የለውም፡፡ ማክሮንን መምረጥ ቁጥጥር በሌለበት ሉላዊነት (ግሎባላይዜሸን) ላይ ሪፈረንደም ማካሄድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ሕዝበ ውሳኔ ካደረገች በኋላ የአውሮፓ ኅብረት ራሱን አጠናክሮ ለመጓዝ ጥረት ቢያደርግም፣ የፈረንሣይ ምርጫና የዕጩዋ ለፔን አቋም ሌላ መዘዝ ይዞበት ብቅ ብሏል፡፡ የለፔን መመረጥ ፈረንሣይ ከኅብረቱ እንድትወጣ ጫና መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ኅብረቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲበታተን ሊያደርግም ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ መገበያያ ገንዘባቸውን በዩሮ ላደረጉት፣ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመሠረቱት፣ ተዘዋውሮ የመሥራት መብትን ላጎናፀፉት አባል አገሮች ሌላ ፈተና ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ፈረንሣይ ፕሬዚዳንቷን የምትመርጥ ሲሆን፣ ማክሮን ካሸነፉ የኅብረቱ ህልውና የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ለፔን ካሸነፉ ደግሞ የኅብረቱ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞችም የፈረንሣይ ምርጫ ውጤት የኅብረቱን መኖር ወይም አለመኖር ጭምር የሚወስን ነው ብለውታል፡፡ የምርጫው ውጤት በኅብረቱ ላይ ሪፈረንደም ከማካሄድ መሳ ለመሳ ይሆን እንደሆነ ወደፊት ይታያል፡፡