Skip to main content
x
በኦሊምፒክ የተወዳዳሪነት አቅም የሚያጎለብት መድረክ ተዘጋጀ

በኦሊምፒክ የተወዳዳሪነት አቅም የሚያጎለብት መድረክ ተዘጋጀ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቀጣይ በሚደረጉት አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል መድረክ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ መድረኩ አገሪቱ በውድድር ከሚኖራት ውጤታማነት በተጨማሪ በተቋሙና በአገር አቀፍ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መካከል ያለውን የግንኙነት መስተጋብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው፡፡

ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ ኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በሚዘጋጀው በዚህ መድረክ ‹‹የአሸናፊነት ስልት›› በሚል ለውይይት በሚቀርበው አጀንዳ፣ አገሪቱ በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ የምትሳተፍባቸው ስፖርቶች ቅድሚያውን ይይዛል ተብሏል፡፡ በዚሁ መሠረትም በ2010 ዓ.ም. አልጀርስ ላይ በሚካሄደው ሦስተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና፣ በዚያው ዓመት በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ላይ ሦስተኛው የበጋ የወጣቶች ሻምፒዮና፣ በ2011 ዓ.ም. ኬፕ ቨርዴ ላይ በሚካሄደው የአፍሪካ ቢች ጨዋታዎችና፣ በ12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች እንዲሁም ከሦስት ዓመት በኋላ ቶኪዮ ላይ የሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በመድረኩ ከሚነሱ ዋና ዋናዎቹ ስለመሆናቸው ኦሊምፒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴው በተጨማሪም በትግራይ አስተናጋጅነት በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ላይ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው 6ኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ዝግጅትና ተሳትፎን አስመልክቶ ግምገማዊ ውይይት ይደረጋል ብሏል፡፡