Skip to main content
x
በኦሮሚያ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ 600 ሰዎች ታስረው ክስ ተመሥርቶባቸዋል

በኦሮሚያ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ 600 ሰዎች ታስረው ክስ ተመሥርቶባቸዋል

የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2009 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት፣ 600 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ክስ እንደመሠረተ አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ክስ ከመሠረተባቸው ውስጥ 93 የሚሆኑትን ከስድስት ወራት ቀላል እስር እስከ 13 ዓመት ከባድ እስር ድረስ እንዳስፈረደባቸውም ገልጿል፡፡

በገንዘብ ቅጣትም እንዲሁ 62 ሰዎች ከአንድ ሺሕ ብር እስከ 50 ሺሕ ብር ድረስ እንዲቀጡ ያደረገ መሆኑን፣ የተቀሩት ክሶች በሕግ ሒደት ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ሒሩት ቢራሳ ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ የኮሚሽኑን የዘጠኝ ወራት ሥራ አፈጻጸምና ከግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ ኦሮሚያ የሚካሄደውን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮንፈረንስ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነሯ እንደገለጹት፣ ቅጣቱ በእስራትና በገንዘብ መቀጮ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ በሙስና ያካበቱትን ሀብት መልሰው ሊያገኙ እንደማይገባ፣ ጥፋተኞቹ ሀብቱን መልሰው ካገኙ የተወሰደው ሕጋዊ ዕርምጃ አስተማሪነቱ ጥያቄ ውስጥ እንደሚወድቅ አመልክተዋል፡፡

‹‹ከዚህ አንፃር 96,200 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ 21.2 ሚሊዮን ብርም እንዲሁ እንዲመለስ ተደርጓል፤›› ሲሉ ኮሚሽነር ሒሩት ገልጸው፣ ‹‹ከዚህ በተጨማሪ ያላግባብ ሊባክን የነበረ 30.6 ሚሊዮን ብርና ሊጠፋ የነበረ 51.8 ሚሊዮን ብር በአስቸኳይ በተወሰደ ዕርምጃ ተመልሷል፤›› ሲሉ ኮሚሽኑ የወሰደውን ዕርምጃ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሰባት ሚሊዮን ብር፣ 230,919 ካሬ ሜትር መሬት፣ 40 የተለያዩ ቤቶችና ስድስት ተሽከርካሪዎች እንዲታገዱ መደረጉን ኮሚሽነር ሒሩት ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመትና በዚህ ዓመት መጀመሪያ በኦሮሚያ ክልሎች ለተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በተለይ ሙስና ለመልካም አስተዳደር ዕጦት ዋነኛ ምክንያት እንደነበር በተለያዩ መድረኮች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በተለይ የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከፀረ ሙስና ትግሉ በተጨማሪ በሥነ ምግባር ላይ እየሠራ መሆኑን ኮሚሽነር ሒሩት ገልጸው፣ የግንቦት 20 በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች ከግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ ተከታታይ ኮንፈረንሶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡