Skip to main content
x
በፈተናዎች የታጠሩት ሶሻል ኢንተርፕራይዞች

በፈተናዎች የታጠሩት ሶሻል ኢንተርፕራይዞች

መውለድ ወይም እናትነት የመጀመሪያ ሲሆን እርግዝናም ማሳደጉም ከበድ ይላል፡፡ በሆርሞን ለውጥ ከሚፈጠረው የባህሪ ለውጥ ባሻገር ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ተገቢውን እንክብካቤ መስጠትና ለሕፃኑ ጤናማ ዕድገት የሚያስፈልጉ ምግቦችን አዘጋጅቶ መመገብም እንግዳ ይሆናል፡፡ ይህም በወላጆች ላይ የሚፈጥረው ፈተና ቀላል አይደለም፡፡

በችግሩ ከተፈተኑ እናቶች መካከል ወይዘሮ ሜላት ዮሴፍ አንዷ ናቸው፡፡ ‹‹ልጆቻችን ምግብ በሚጀምሩበት ጊዜ ለአካላቸውና ለአዕምሯቸው ዕድገት የሚጠቅሙ ምግቦችን በቀላሉ በቤት ውስጥ እንዴት ማዘጋጀትና መመገብ እንደምንችል አናውቅም፡፡ በአጋጣሚ የሥነ ምግብ ባለሙያ ጓደኛ ስለነበረችኝ እንዴት ማዘጋጀት እንዳለብኝ ሐሳብ ትሰጠኝ ነበር፤›› በማለት በቂ የምግብ አቅርቦት ቢኖርም አዘገጃጀቱን አለማወቅ ለብዙዎች ፈተና መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ለልጃቸው ዕድገት የሚጠቅሙ የምግብ  ምጥኖችን ከሥነ ምግብ ባለሙያ ጓደኛቸው ጋር በመተጋገዝ ያዘጋጁም ነበር፡፡ ለጎረቤቶቻቸውና ለሌሎች  በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ሙያውን ያጋሩ ጀመር፡፡ ‹‹የወለዱ ሁሉ ስለምግብ አዘገጃጀት ሲጠይቁን ስናይ የሁሉም ሰው ችግር መሆኑን ተረዳን፡፡ ገዝቶ ለመብላት አቅም ቢኖርም እንዴት አድርጎ ማዘጋጀት እንዳለብን ካላወቅን የችግሩ አካል ነን፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ለጉዳዩ መፍትሔ መስጠት እንዳለባቸው ይሰማቸው ጀመረ፡፡

ቲታ ባይት የተባለ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የሚሠራውን ድርጅት እንዲያቋቁሙም ምክንያት ሆናቸው፡፡ በ2007 ዓ.ም. የተቋቋመው ቲታ ባይት ሥራውን የጀመረው ጣዕም ያላቸው ምግቦች ለመጀመርያዎቹ 1,000 ቀናት የሚል የሕፃናት የምግብ አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ መጽሐፍ በማሳተም ነው፡፡

ከ53 በላይ የምግብ አዘገጃጀት ዓይነቶችን ይዞ የወጣው መጽሐፉ በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረው ተቀባይነት ጥሩ እንደነበረም ያስታውሳሉ፡፡ በተለያዩ ድርጅቶች ስፖንሰር አድራጊነት የታተመው መጽሐፍ ከምገባ ጋር የተያያዙ ችግሮች ጎልተው ለሚታዩበት ለታችኛው የማኅበረሰቡ አካል ከዋጋው አንፃር ተደራሽ አልነበረም፡፡  

ስለዚህም ለአብዛኛው ኅብረተሰብ ተደራሽ በሆነ መልኩ አገልግሎቱን በኤስኤምኤስ፣ በሞባይል አፕልኬሽንና በስልክ ጥሪ አገልግሎቱን ለማቅረብም ሐሳብ አላቸው፡፡ ከዚህም ሲያልፍ ሰዎች መጠነኛ ገንዘብ ከፍለው በአጭር ጊዜ የምግብ አዘገጃጀት የሚማሩበትን ዕድል ለመፍጠር ዓላማ እንዳላቸው ወይዘሮ ሜላት ይናገራሉ፡፡ ይሁንና እነዚህን ውጥኖች ዕውን ለማድረግ የተለያዩ በተለይም ከገንዘብ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ተጋርጠውባቸዋል፡፡

ድርጅቱ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ ከሚያገኘው ገቢ በስተቀር ቋሚ ገቢ የለውም፡፡ ‹‹ቢዝነሳችን ይቀጥላል? አይቀጥልም? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ እንደዚህ ዓይነት የባህርይ ለውጥ ላይ ያተኮሩ አገልግሎቶች ጥቅምን ላይረዳ ይችላል፡፡ ለዚህም ድጋፍ ያስፈልገናል፤›› ይላሉ፡፡

ከበጎ አድራጎትና ከንግድ ድርጅት ጋር የሚመሳሰል ባህርይ ያላቸው እንደ ቲታ ባይት ያሉ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ሶሻል ኢንተርፕራይዞች) ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ተቋማቱ የተለያዩ አገልግሎቶችንና ምርቶችን በአነስተኛ ትርፍ በመሸጥ ገቢ የሚያገኙ ሲሆን፣ የሚያገኙት ትርፍ ሥራውን ለማጠናከር አልያም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለመሥራት የሚውል ነው፡፡

ይህ ከሌሎች የቢዝነስ ተቋማት የሚለያቸው ቢሆንም፣ እነሱን የሚያስተዳደር የተለየ ሕግ ባለመኖሩ በበጎ አድራጎት፣ በንግድ ተቋማትና በግል ድርጅትነት ተመዝግቦ ለመሥራት እንደሚገደዱ፣ ይህም ሥራቸውን እያደናቀፈ እንደሚገኝ፣ ለዚህም ተቋማቱን የሚያስተዳድር ፖሊሲ እንዲወጣ ጥያቄ መቅረቡን  ከወራት በፊት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣነው ዘገባ ማንሳታችን የሚታወስ ነው፡፡

ሰፖርት ፎር ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ኢን ኢስት አፍሪካ የተባለውና በብሪትሽ ካውንስል የሚተገበረው የሁለት ዓመታት ፕሮጀክት በአገሪቱ ለሚገኙ መሰል ተቋማት ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ያለባቸውን ችግሮችና ተስፋ ሰጪ ዕድሎችን በጥናት በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረክ ያዘጋጃል፡፡

ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል አዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር 55,000 መድረሱን፣ አንድ አራተኛ የሚሆኑትም በሴቶች የሚመሩ መሆናቸውን በእለቱ ይፋ ባደረገው ጥናቱ ተመልክቷል፡፡

መነሻ ካፒታል የማግኘት ጉዳይ የተቋማቱ ዋናው ችግር ሲሆን፣ የሚተዳደሩበት ፖሊሲ አለመኖርና ሌሎች የገንዘብ ችግሮች የተቋማቱን ህልውና እንደሚፈታተኑ በጥናቱ ተካቷል፡፡

ከተጀመረ 12 ዓመታትን ያስቆጠረው ‹‹የፀሐይ መማር ትወዳለች›› የቴሌቪዥን ፕሮግራም መሥራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ፣ በዕለቱ ተገኝተው ልምዳቸውን ካካፈሉ ሶሻል ኢንተርፕሩነሮች መካከል ናቸው፡፡

ሰፊውን የኅብረተሰብ ክፍል መድረስ የሚያስችሉ አዳዲስ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለመሸፈን ብዙ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ማገልገል የምንፈልገው ገንዘብ ከፍሎ አገልግሎቶችን ማግኘት የማይችለውን የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ለመሰል ፕሮጀክቶች ከባንኮች ብድር ማግኘት የሚቻለው እንደ አንድ ቢዝነስ አትራፊ መሆን ሲቻል ነው፤›› በማለት የሚቋቋሙበትን ዓላማ ለመፈፀም የገንዘብ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡    

በጤና፣ በእርሻ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎትና በመሳሰሉት ሴክተሮች የተሠማሩት ተቋማቱ፣ በአብዛኛው በወጣቶች የተያዙ ናቸው፡፡ ሴቶቹን በማሣተፍ ረገድም በመስኩ የተሰማሩና ተቀጥረው የሚሰሩ ሴቶች 32 በመቶ እንደሆኑና ከሌሎቹ የሥራ መስኮች አንፃር የተሻሉ መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም በአማካይ 21 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ብሪቲሽ ካውንስል በሚያደርገው ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ27 አገሮች የሶሻል ኢንተርፕራይዝ ፕሮግራም በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡