Skip to main content
x
ተቃውሞ የቀሰቀሰው የቁርጥ ግብር ከፋዮች አቤቱታ

ተቃውሞ የቀሰቀሰው የቁርጥ ግብር ከፋዮች አቤቱታ

የፌዴራል መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ በይበልጥ ለመሰብሰብ ባለፈው ዓመት አዋጅ ቁጥር 929/2008 አውጥቷል፡፡ ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችም ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት፣ ይህ አዋጅ በሚፈቅደው መሠረት ገቢያቸውን ለመሰብሰብ ካለፈው ወር ጀምሮ በሰፊው መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡

አዋጅ ቁጥር 929/2008 ቀደም ሲል ሲሠራበት የቆየውን የግብር ከፋዮች ደረጃ ቀይሮታል፡፡ ቀደም ሲል ደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፍዮች ከ500 ሺሕ ብር በላይ፣ አሁን በተቀየረው አሠራር ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ሆኖ ተመድቧል፡፡ ቀደም ሲል ደረጃ ‹‹ለ›› ከ100 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር በላይ ነበር፡፡ አሁን ባለው አሠራር ከ500 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ሆኖ ተመድቧል፡፡ አወዛጋቢው ደረጃ ‹‹ሐ›› ቀደም ሲል እስከ አንድ መቶ ሺሕ ብር ድረስ ሽያጭ ያላቸው የሚመደቡበት ነበር፡፡ አሁን ባለው አሠራር የደረጃ ‹‹ሐ›› ቁርጥ ግብር ከፋዮች እስከ 500 ሺሕ ብር ድረስ ሽያጭ ያከናውናሉ ተብሏል፡፡

ይህ አዋጅ መነሻ ተደርጎ ከሚያዝያ እስከ ግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. ድረስ በደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የዕለት ገቢ ቅኝት ሲካሄድ ቆይቶ፣ ሰሞኑን ውጤቱ ለእያንዳንዱ ነጋዴ ተገልጿል፡፡

በዚህ ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ ነጋዴዎች ቅሬታ በማሰማት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ቅሬታ በኦሮሚያ ክልል በአምቦ፣ በወሊሶ፣ በጊንጪና በሌሎች ከተሞች ግጭት እስከ መቀስቀስ ድረስ ዘልቋል፡፡

የአነስተኛ ነጋዴዎችን ቅሬታ በተገቢው ለመግለጽ ያህል በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የቁርጥ ግብር ምጣኔ ከተገለጸላቸው 927 አነስተኛ ነጋዴዎች መካከል፣ ከ700 በላይ የሚሆኑት ቅሬታ ማቅረባቸውን የወረዳው ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ጥናት የተካሄደባቸው 148 ሺሕ አነስተኛ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 47 ሺሕ የሚሆኑት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ከመቶ ሺሕ በላይ የሚሆኑት የሚያቀርቡት ቅሬታ ቢኖራቸውም፣ ግምቱ ተቀራራቢ መሆኑን በመረዳት ግምቱን መቀበላቸው ተገልጿል፡፡

በደረጃ ‹‹ሐ›› ሥር የተደለደሉ ቁርጥ ግብር ከፋዮች የግብር አተማመን ሒደቱ በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙት አቶ አሰፋ መኮንን፣ በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ የሚገኙት ወ/ሮ ጌጤ ፈይሳና በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኙት አቶ ፈቃዱ ዘገዬ ይገኙበታል፡፡

የወ/ሮ ጌጤና የአቶ ፈቃዱ ስም ለደኅንነታቸው ሲባል የተየቀረ ነው፡፡ አቶ አሰፋ መኮንን ለረዥም ዓመታት በውጭ አገር ሲኖሩ ቆይተው ወደ አገራቸው የተመለሱ ናቸው፡፡ እኚህ ግለሰብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ሃና ማርያም አካባቢ ‹‹ሕገወጥ›› የተባሉ ቤቶች ሲፈርሱ የእሳቸውም አብሮ ፈርሷል፡፡

በዚህ ምክንያት ለችግር የተዳረጉት አቶ አሰፋ፣ ከዘመድ በመጠጋት ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ አነስተኛ የመጠጥ ግሮሰሪ ከፍተው በመሥራት ላይ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ አቶ መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቀን ገቢየቸው እስከ 240 ብር ድረስ እንደሆነ አሳውቀው ነበር፡፡ ነገር ግን የክፍለ ከተማው ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ያሳወቃቸው የቀን ገቢ ግምት 2,000 ብር እንደሆነ ነው፡፡

ይህን ያህል ገቢ በፍፁም ሊያገኙ እንደማይችሉና ተመኑ በዚህ ከፀና ሕይወታቸው የተመሰቃቀለ እንደሚሆን አቶ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በቁርጥ ግብር ምክንያት ግጭት በነበረበት አምቦ ከተማ ውስጥ በአነስተኛ ንግድ የሚተዳደሩት ወ/ሮ ጌጤም መረር ያለ ቅሬታ አላቸው፡፡

ወ/ሮ ጌጤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተሰማሩበት የንግድ ሥራ በለስላሳ መጠጦችና በቡና ችርቻሮ ነው፡፡ በዚህ ንግድ ሥራ በቀን ከ250 ብር እስከ 300 ብር ድረስ እንደሚያገኙ የተናገሩት ወ/ሮ ጌጤ፣ ነገር ግን የገቢዎች ጽሕፈት ቤት በቀን 4,500 ብር ሽያጭ እንደሚያከናውኑ አድርጎ አሳውቋቸዋል፡፡

‹‹እኔ በቀን ይህን ያህል ገንዘብ ሠርቼ አላውቅም፤›› በማለት ግምቱ ጭራሽ ለእውነታ ቅርብ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ አቶ ፈቃዱም ተመሳሳይ ሐሳብ አላቸው፡፡ አቶ ፈቃዱ በሚኖሩበት ቡሬ ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ይተዳደራሉ፡፡ አቶ ፈቃዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቀን ቢበዛ እስከ 800 ብር ድረስ ይሠራሉ፡፡ ይህንንም ለመንግሥት አሳውቀዋል፡፡ ነገር ግን የቡሬ ከተማ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት 1,600 ብር በቀን እንደሚሠሩ አድርጎ ግምት ጥሎባቸዋል፡፡

‹‹ይህን ያህል ገንዘብ በቀን መሥራት የሚያስችል መደብር የለኝም፤›› ሲሉ አቶ ፈቃዱ ይናገራሉ፡፡ አዲሱ ግምት በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ፣ ከደረጃ ‹‹ሐ›› ወደ ደረጃ ‹‹ለ›› የሚያሸጋግራቸው በመሆኑ በኋላ ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመት እንዳልቻሉ እነዚህ አነስተኛ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከራስ አቅም በሚሰበሰብ ገቢ ላይ እንዲመሠረት ይፈልጋል፡፡ ለቀጣዩ 2010 ዓ.ም. ከተያዘው 320.8 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ 190 ቢሊዮን የሚሆነው ከአገር ውስጥ ምንጮች እንዲሰበሰብ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ክልሎችም በአብዛኛው የሚይዙት በጀት ከራስ ገቢ ሳይሆን በፌዴራል መንግሥት ድጎማ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ባሉት ዓመታት የራሳቸውን ገቢ እስከ መጨረሻው ጥግ መሰብሰብ እንዳለባቸው ከየምክር ቤታቸው ጋር መተማመን ላይ ደርሰዋል፡፡  

የፌዴራል መንግሥት ለበጀት ዓመቱ ከያዘው በጀት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የክልሎች ድጎማ ነው፡፡ ክልሎች 117 ቢሊዮን ብር በድጎማ፣ ሰባት ቢሊዮን ብር ደግሞ ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ተመድቦላቸዋል (የ2010 ዓ.ም. ድጎማ አዲስ አበባ ከተማንም ይጨምራል)፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓመት 40 ቢሊዮን ብር የማመንጨት አቅም ላይ መድረሱን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን በ2008 ዓ.ም. የተሰበሰበው 22.1 ቢሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. 11 ወራት ውስጥ 31.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ የተሰበሰበው ግን 26.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማው የሚፈልገውን አገልግሎት በይበልጥ ለማሳካት የከተማው ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን በሙሉ የመሰብሰብ ፍላጎት አለው፡፡ ይህንንም ለማሳካት በቀድሞው ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ጊዜ የከተማው ገቢዎች ባለሥልጣን፣ በፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር እንዲታቀፍ ተደርጓል፡፡

በእርግጥ ከዚህ ወቅት ጀምሮ የከተማው ገቢ የመሰብሰብ አቅም ያደገ ቢሆንም፣ የአሁኑ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከዚህም በላይ እንዲያድግ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ሌሎቹ ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማም ለሚካሄደው ልማት የፋይናንስ መሠረት ከግብር የሚሰበሰበው ገቢ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም በ2003 ዓ.ም. ላይ የቆመውን የቀን ገቢ ግምት፣ እንደ አዲስ ከስድስት ዓመት በኋላ ለማንቀሳቀስ ተሞክሯል፡፡

በአማራ ክልልም በተመሳሳይ የክልሉን ገቢ በይበልጥ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ስብሰባ ክልሉ ለ2009 ዓ.ም. ከያዘው 32 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከራስ ምንጮች መሰብሰብ የቻለው 8.5 ቢሊዮን ብቻ ነው፡፡ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ ለምክር ቤት አባላት እንዳብራሩት፣ መሰብሰብ የተቻለው የበጀቱን 20 በመቶ ያህል ብቻ ነው፡፡ ይህንን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አበክረው ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ለቀጣዩ 2010 በጀት ዓመት 37.6 ቢሊዮን ብር በጀት አፅድቋል፡፡ የኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ የክልሉ የወጪ ፍላጎት 56 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ ከግብር የሚገኘው ግን ከአሥር ቢሊዮን ብር እንደማይበልጥ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ለማሻሻል የተጀመረው የገቢ ግብር ግምት ግጭት የተስተናገደበት ሲሆን፣ አቶ አዲሱ በዕለት ገቢ ግምት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲቀርቡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ከገቢ ግምት ጋር ተያይዞ የተነሳውን ቅሬታ ምክንያት በማድረግ፣ ሌላ ዓላማ ይዞ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሞከር ፍፁም ተቀባይነት የለውም፤›› ያሉት አቶ አዲሱ፣ ክልሉ ይህንን እንደማይታገስ አጥብቀው አስታውቀዋል፡፡ የቁርጥ ግብር ተመን ይፋ ከተደረገ በኋላ በኦሮሚያ ክልል አምቦ፣ ወሊሶና ጊንጪ ከተሞች አመፅ የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ በእነዚህ ከተሞች የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች መሰባበራቸውና መቃጠላቸው ተገልጿል፡፡ ሱቆችም እንዲሁ ተዘግተው የዋሉባቸው ጊዜያት መኖራቸው፣ እንዲሁም በቡሌ ሆራ (ሀገረ ማርያም) አመፅ ቀስቃሽ ጽሑፎች እየተበተኑ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ከወሊሶና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገው ነበር፡፡ የክልሉ መንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለዕረፍት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች መንግሥት ግብር መሰብሰብ እንዳለበት፣ ነገር ግን የቀን ገቢ ግምቱ ፍትሐዊነት የጎደለው እንደሆነ ነግረዋቸዋል፡፡ አቶ ለማ በሰጡት ምላሽ ተጋነነ የተባለው የዕለት ገቢ ግምት በመተማመን እንደሚፈታ፣ የሚቀርቡ ቅሬታዎችም እንደሚጣሩ ገልጸዋል፡፡ ነጋዴዎችም በአቅማቸው መጠን ለመንግሥት ግብር መክፈል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን የነበረው ክፍያም እስከ ሐምሌ 15 ቀን ያለቅጣት መደረጉንና ነጋዴዎችም በጊዜው ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ክልልም በቀጣዩ በጀት 10.23 ቢሊዮን ብር ከራሱ ምንጮች ለመሰብሰብ ማቀዱም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገልጿል፡፡ ይህም ተግባራዊ የሚሆነው በሦስቱም ደረጃዎች ከሚገኙ 183,136 ግብር ከፋዮች መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሤ አስረስ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ክልሎች የወጪ ፍላጎታቸው እስከ 60 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ቢሆንም፣ በአብዛኛው የበጀታቸው ምንጭ የፌዴራል መንግሥት ድጎማ ነው፡፡ ከራሳቸው የገቢ ምንጭ የሚያሰባስቡት ከ20 በመቶ እንደማይበልጥ በተደጋጋሚ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ክልሎች በድጎማ ብቻ ልማታቸውን ማካሄድ አይችሉም፡፡ የራሳቸውን ገቢም አሟጠው መሰብሰብ አለባቸው፡፡ ሚኒስቴሩም ድጋፍ ያደርግላቸዋል ብለዋል፡፡ ‹‹ክልሎች ገቢያቸውን አሟጠው ለመሰብሰብ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ምልክት እያሳየ ነው፡፡ ክልሎች ወጪያቸው በጣም እየጨመረ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ድጎማ የወጪ ፍላጎታቸውን ማርካታ እንደማይቻል ተገንዝበዋል፤›› ሲሉ ዶ/ር አብርሃ ክልሎች ገቢያቸውን በቁርጠኝነት ለመሰብሰብ መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

ግብር የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው አብዛኞቹ አነስተኛ ነጋዴዎች የሚያምኑ ቢሆንም፣ የገቢ መሥሪያ ቤቶች ግምት በሚያካሂዱበት ወቅት የመደብሮችን መረጃ አጣርቶ አለመለየት፣ ተመሳሳይ ለሆኑ መደብሮች የተለያየ ግመታ ማካሄድ፣ አጋኖና አሳንሶ መገመት ዋነኞቹ ችግሮች መሆናቸውን ነጋዴዎቹ እየተናገሩ ነው፡፡

የቅሬታ ሰንሰለቱ ረዥምና ቅሬታ ተሰማ ከተባለም ከእውነታው ጋር ያልተቀራረበ ማስተካከያ ማድረግ ተጠቃሾች ችግሮች ሆነው ቀርበዋል፡፡ የገቢ መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ቅሬታ እየቀረበ ባለበት ወቅት ጉዳዩን ለማስረዳት ታች ላይ እያሉ ይገኛሉ፡፡ ግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ አካባቢም ችግር እንዳለ መንግሥት እየገለጸ ነው፡፡ ከችግሮቹ መካከልም ግምት በሚከናወንበት ወቅት ዕቃ ማሸሽ፣ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ መረጃ አሳንሶ መስጠት፣ ውክልና የሌለው ሰው በመደብር ውስጥ ማስቀመጥና ዘግቶ መጥፋት ተጠቃሽ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በቀን ገቢ ግምት ሒደት ወቅትም የሚከፍሉትን ሳያውቁ ቅሬታ ማቅረብ፣ ውጤቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆን፣ የታክስ ኦፊሰሮችን ማስፈራራትና የደረጃ ለውጥ ሊደረግብን አይገባም የሚሉ ጭምር እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡

የተፈጠረውን ችግር ለማርገብ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ከንግድና ዘርፍ ማኅበራት አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ የቀን ገቢ ግምት ተካሂዶ ውጤቱ የተለገጸበትንና ቅሬታ የማስተናገድ ሒደት ላይ ያለውን ጉዳይ አስመልክቶ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አመራሮች ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ አማካይ የቀን ገቢ ግምት መሠረትና ፍትሐዊነት ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የአዲስ አበባ ታክስ ፕሮግራም ልማት ሥራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ፣ በየጊዜው እያደገ ያለ ኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መንገድ የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆች ላይ ማሻሻያ በመደረጉ የግብር ማስከፈያ ማዕቀፎች መለወጣቸውን አስታውሰዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የቀን ገቢ ግምት ያካሄደበት ምክንያት፣ በከተማ ደረጃ የቀን ገቢ ግምት ከተገመተ ከ2003 ዓ.ም. በኋላ ወደ ንግድ ሥርዓቱ የገቡና ግምት ያልተካሄደባቸው አዳዲስ ግብር ከፋዮች ቁጥር በርካታ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እንዲሁም በ2003 ዓ.ም. የቀን ገቢ ግምት የቀረበባቸው፣ ነገር ግን ዘርፍ የለወጡ፣ የጨመሩና የቀነሱ ግብር ከፋዮች ቢኖሩም በዚሁ መሠረት ማስተካከያ ሳይደረግ በመዘግየቱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ግምቱ በተካሄደበት ወቅት በአንዳንድ ግብር ከፋዮች ዕቃ ማሸሽ፣ የንግድ ቦታ መዝጋት፣ መረጃ አሳንሶ መስጠትና የመሳሰሉ ችግሮች ግምቱ ሙሉ በሙሉ ፍትሐዊ እንዳይሆን ቢያደርገውም፣ እነዚህን ሰዎች የኢንስፔክሽን ኮሚቴ ተከታትሎ እርማት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ደንበኞች አገልግሎትና ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ቱሉ ፊጤ፣ በግምት ሥራው ላይ ለምሳሌ በርበሬና ቅማመ ቅመም ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ነጋዴ የቀን ገቢው 1,500 ብር ከሆነ በዓመቱ ቀናት ተባዝቶ ግብር የሚከፈልበት አሥር በመቶው ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይኼም ተከፋይ ዓመታዊ ግብር 5,370 ብር ይሆናለ፡፡ በቀን ገቢ ግምት የሽያጭ መጠኑን በማየት ብቻ ያንን ያህል ግብር ክፈሉ እንደተባሉ ቆጥረው፣ የመደናገጥና የማማረር ሁኔታዎች መስተዋላቸውን አብራርተዋል፡፡ የግብር ከፋዮች ዓመታዊ የቀን ገቢ ግምቱንና ዓመታዊ ሽያጩን መሠረት አድርጎ ገቢ ግብር እንዴት እንደሚሠላ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚከተለውን ቀመር አቅርቧል፡፡

ምሳሌ 1፡- በርበሬ ቅመማ ቅመም ንግድ ዘርፍ

የቀን ገቢ ግምት መጠን 1,500 ብር

ብር 1,500 x በ365 ቀናት = 547,500 ብር (ዓመታዊ ጠቅላላ የሽያጭ ገቢ)

የዘርፉ ትርፍ መተመኛ 10%=547,500 ብር

ግብር የሚከፈልበት ገቢ = 54,750 ብር

ግብር ምጣኔ 20% = 10,950 ብር

ተቀናሽ 3,630 ብር

ተከፋይ ግብር = 7,320 ብር

ምሳሌ 2፡- የባህል ዕቃዎች ንግድ ዘርፍ

የቀን ገቢ ግምት መጠን፡- 2,000 ብር

ብር 2000 x በ300 ቀናት = ብር 600,000 (ዓመታዊ ጠቅላላ የሽያጭ ገቢ)

የዘርፉ ትርፍ መተመኛ 14% = 600,000 x 14% = 84,000 ብር

ግብር የሚከፈልበት ገቢ = 84,000 ብር

ግብር ምጣኔ 25% = 84,000 x 25% = 21,000 ብር

ተቀናሽ = 6,780 ብር

ተከፋይ ግብር = 14,220 ብር

ምሳሌ 3፡- የፀጉር ቤት የሥራ ዘርፍ

የቀን ገቢ ግምት መጠን = 2,800 ብር

2,800 ብር x በ365 ቀናት = 1,022,000 ብር (ዓመታዊ ጠቅላላ የሽያጭ ገቢ)

ዓመታዊ ጠቅላላ የሽያጭ ገቢ = 1,022000 ብር

የዘርፉ ትርፍ መተመኛ 10% = 102,200 ብር

ጠቅላላ ወጪ = 919,800 ብር

ጠቅላላ ግብር የሚከፈልበት ገቢ = 102,200 ብር

ግብር ምጣኔ 30% = 30,660 ብር

ተቀናሽ 11,460 ብር

ተከፋይ ግብር = 19,200 ብር

የቀን ገቢ ግምቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ የተነሳውን ቅሬታ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደመረምሩት ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ለንግዱ ኅብረተሰብ መረጃው ሲቀርብ የቀን ሽያጭ ግምቱ ብቻውን መቅረብ እንዳልነበረበት፣ ይልቁንም ታክስ የሚከፈልበትና ፍሬ ግብሩ ተያይዞ ሊቀርብ ይገባው እንደነበር መግባባት ላይ ተደርሶበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የገቢ መሥሪያ ቤት ባለሙያዎች ግመታ ሲያካሂዱ በቂ መረጃ ያላገኙበትን መደብር ከጎረቤት መደብሮች በመነሳት መገመታቸው ተደርሶበታል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ በርካታ ቅሬታዎች እየቀረቡ መሆኑን አምነው፣ መፍትሔም እየተሰጠ ነው፡፡ አቶ ከበደ እንዳሉት በብዛት ቅሬታ እያቀረቡ የሚገኙት፣ በዝቅተኛና በአነስተኛ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

‹‹በእነዚህ ላይ የተወሰደው ግምት ከፍተኛ ጫጫታ አስነስቷል፤›› ያሉት አቶ ከበደ፣ ‹‹እነሱ ራሳቸው በልተው ካደሩ በቂ አይሆንም ወይ? ለምንድነው እነሱ ላይ ይህንን ያህል ግምት የሚጫነው? የሚል ተደጋጋሚ ስሞታ ቀርቧል፤›› በማለት የቅሬታውን ስፋት አስረድተዋል፡፡

አቶ ከበደ ከዚህ አንፃር መንግሥት የደረሰበትን ውሳኔ ሲያስረዱም፣ በዝቅተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ተለይተው በተለይ የጀበና ሥራ፣ ልብስ ስፌት፣ ፑል ቤትና በመሳሰሉት ንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያመኑበትን እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡

‹‹ያላግባብ የተጫነባቸው ካሉ እንዲነሳላቸው አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ችለው በልተው ካደሩ የመንግሥትን ሸከም ማቃለል በመሆኑ፣ ነገር ግን ትንሽም ቢሆን ከሚያገኙት ገቢ በራሳቸው እምነት በመክፈል ወደ ታክስ ሥርዓቱ መግባት አለባቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የደረጃ ለውጭ ያደርጉ ነጋዴዎችም ከ ‹‹ሐ›› ወደ ‹‹ለ› እና ከ‹‹ለ›› ወደ ‹‹ሀ›› የተሸጋገሩ አሉ፡፡ በተለይ ደረሰኝ የማይገኝላቸው የንግድ መስኮች ላይ አስቸጋሪ የሆኑ፣ ሲገመትላቸው ባልተሟላ ማስረጃ የተጋነነ ግምት እንደተጣለባቸው የሚናገሩ አሉ፡፡

አቶ ከበደ እንደገለጹት፣ ቅሬታ አቅራቢዎች የደረጃ ‹‹ሐ›› የመጨረሻ ጣሪያ ላይ ሆነው የሚታዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ የደረጃ ‹‹ለ›› ሆኖ 600 ሺሕ ብር የነበረ ከሆነና የተጋነነ ከሆነ ወይም ባልተሟላ ደረጃ የተገመተ ከሆነ በደረጃ ‹‹ሐ›› የመጨረሻ ጣሪያ ከ400 ሺሕ ብር እስከ 500 ሺሕ ብር ባለው ውስጥ እንዲስተናገዱ ተወስኗል፡፡

ከንቲባ ድሪባም ይህንኑ ሐሳብ ከአቶ ከበደ ጋር ይጋራሉ፡፡ ከንቲባው እንዳሉት መንግሥት ዝቅተኛ ንግድ ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በልተው እንዲያድሩ ነው የሚፈልገው፡፡ ነገር ግን ወደ ታክስ ሥርዓቱ መግባታቸው ለእነሱም ቢሆን ጠቃሚ ነው በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የንግዱ ኅብረተሰብ ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረበ ነው፡፡ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችም ተገቢው ምላሽ በወቅቱ እየቀረበ አይደለም፡፡ መንግሥት ለንግዱ ማኅበረሰብም ቁርጥ ግብርን የሚመለከት የተሟላ መረጃ እየቀረበ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ እነዚህ ችግሮች ተፈተው ወደ ትክክለኛው የንግድ ሥራ ለመግባት አቶ መኮንን፣ ወ/ሮ ጌጤና አቶ ፈቃዶን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ አነስተኛ ነጋዴዎች እየጠየቁ ናቸው፡፡ (ለዚህ ዘገባ ዘመኑ ተናኘ፣ ዳዊት ቶሎሳና ዳዊት እንደሻው አስተዋጽኦ አድርገዋል)