Skip to main content
x

ቴዲ አፍሮ ሙታኖቻችንን እየገነዘ ታሪክ መሥራቱን ቀጥሏል

በቶፊቅ ተማም

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሰፊ ዕውቅናና ቅቡልነት ካላቸው ድምፃውያን መካከል አውራው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም ቴዴ አፍሮ ሲሆን፣ ድምፃዊው በተለይ ከ1990ዎቹ መባቻ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ አምስት ያህል በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኙ የሙዚቃ አልበሞችን አበርክቷል፡፡ ቴዲ በተለይ ከሌሎች ድምፃውያን በተለየ በሚያነሳቸው ሐሳቦች የሚሊየኖችን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡

ድምፃዊው ከሌሎች የሙያ አቻዎቹ ላቅ ባለ ሁኔታም የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቧል፡፡ ድምፃዊው ዕድሜው እያሻቀበ ቢገኝም እስካሁን ሠርቶ ባቀረባቸው ሥራዎች አሁንም ድረስ እንደ ብላቴና ሁሌም የማይሰለች ሥራ ይዞ እንደመቅረቡ፣  እንዲሁም ብዙ አድናቂዎቹ እንደሚጠሩት ብላቴናው ብዬ እየጠራሁት ሐሳቤን እቀጥላለሁ፡፡

ብላቴናው በተለይ አራተኛ ከሆነውና ጥቁር ሰው ከተሰኘው አልበሙ በኋላ አዲስ አልበም ለማውጣት ዝግጅት ላይ ባሳለፈባቸው በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብላቴናውን አስመልክቶ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን የተዘገበ ጉዳይ በግሌ ባያጋጥመኝም፣ በሪፖርተር ጋዜጣ መስከረም 18 ቀን 2007 ዓ.ም. እኔ  እምለው ዓምድ ላይ ብርቱካን ወለቃ በተባሉ ጸሐፊ ‹‹ቴዲ አፍሮ ለምን ከሙት ገናዥነት አይወጣም?›› በሚል ርዕስ የቀረበውን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሞጋች ጽሑፍን ግን ልዘነጋው አልችልም፡፡

ጸሐፊዋ በጽሑፏ ካነሳቻቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ጥቂት አካፍዬ ወደ ራሴ ሐሳብ ልግባ፡፡ የጸሐፊዋ ዋና ትኩረት ድምፃዊው ከሁለት ዓመታት በፈት በኔዘርላንድ አንድ መድረክ ላይ ያቀነቀነው ዜማ ነው፡፡ ድምፃዊው ግጥሙን እዚያው መድረክ ላይ በደቂቃዎች ልዩነት እዚያው መድረክ ላይ የገጠመው መሆኑን ቢናገርም፣ ጸሐፊዋ ግጥሞቹን ከስሜት በዘለለ በሥሌት ሊጤን ይገባል በማለት ባቀረበው ዘፈን ውሰጥ ያሉትን ግጥሞች በመምዘዝ የራሷን ሐሳብ ያቀረበችበት ጽሑፍ ነው፡፡ ጸሐፊዋ ያልተስማማችባቸው ሁለት ግጥሞች ሲሆኑ የመጀመሪያው፣

                ‹‹ቀስተደመናው ላይ አንበሳው ከሌለ፣

                የኢትዮጵያ ባንዲራ ትርጉሙ የታለ?››

የሚለው ሲሆን፣ አንበሳው የተጫነበት የኢትዮጵያ ባንዲራ ትርጉሙ ምንድነው? ዳግመኛ ላይመለስ ከመቃብር የወረደውን ሥርዓት ከመናፈቅ ውጪ  በማለት የራሷን ሐሳብ ያቀረበች ሲሆን፣ ሁለተኛው ግጥም ደግሞ፣

                     ‹‹ሳባና ሰሎሞን እናትና አባቴ፣

                  አትማልዷትም ወይ ለኢትዮጵያ እናቴ፤››                       

የሚለው ነው፡፡ ይህም ‹‹የሰሎሞናዊ›› የዘር ሐረግ እውነትን አደርጎ በመቀበልና ባለመቀበል ዙሪያ ሰፋ ያለ ጽሑፍ ያስነበበች ሲሆን፣ ብላቴናው አሁንም ይህን ጉዳይ  በአዲሱ አልበሙ ‹‹ኢትዮጵያ›› በሚለው ዘፈን ‹‹የሰለሞን ዕፅ ነሽ›› በማለት ንጉሥ ሰለሞንን ያነሳ ሲሆን፣ በሌላኛው የትግርኛ ሥራው ‹‹ሳባ አደይ›› ሳባ እናቴ ሲል አቀንቅኗል፡፡

ጸሐፊዋ ባስነበበቸው ጽሑፍ በብላቴናው ላይ ያላትን ቅሬታ አቅርባለች፡፡ ቅሬታዋም ባጭሩ ‹‹ድምፃዊው  መዝፈን ከጀመረ ጀምሮ የሚያቀነቅነው ራሱን ብቻ ‹የሐሳዊው ሰለሞን› ወራሽ ብሎ ለሰየመው አንድ መንደር ብቻ ለተገኙ መሪዎች መሆኑ የሚቃወመውን ዘረኝነትና ጠባብነት እየተገበረ ያለው ከአንገት ወይስ ከአንጀት?›› ስትል ቅሬታዋን አቅርባ ነበር፡፡

በመቀጠልም በጽሑፏ እንዲህ ትለናለች፣ ‹‹. . .አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አሉላ አባነጋና ሌሎች ጀግኖች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲታገሉ መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የእነዚህን ታላላቅ መሪዎች ተጋድሎና ምግባር የሚያወድስ አንዲትም ስንኝ አልተቃኘም በእርግጥ የፈለገውን ማወደስ የማይፈልገውን መተው ግላዊ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ መሪዎች ብቻ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት የታገሉ አስመስሎ መደስኮር ምክንያቱ በጣም ግልጽ ነው. . .››

የጸሐፊዋን ሙሉ ሐሳብ ከጋዜጣው እንድታናቡ እየጠየቅኩ ወደ ግሌ ሐሳብ ስገባ፣ ጊዜ ዳኛው እንዲሉ ብላቴናው ከላይ ከተነሳው ሐሳብ በተቃራኒ በአምስተኛ አልበሙ ለኢትዮጵያ አንድነት ራሱን የሰዋውን አፄ ቴዎድሮስን መነሻ አድርጎ ግሩም በሆነ ሁኔታ ግሩም ዜማ ተቀኝቶ ለሕዝብ ጆሮ ማድረስ ችሏል፡፡ በእርግጥ በአብዛኞቹ የዚህ ትውልድ አባላት  የአንድነት ድምፅ (Voice of Unity) እየተባለ የሚሞካሸው ብላቴናው በአንድነት ዙሪያ ሲያቀነቅን ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት በሠራቸው ሁለት ተከታታይ አልበሞች የኢትዮጵያ ትንሳዔ ዕውን ይሆን ዘንድ በፍቅር የአንድነት ሱባዔ እንድንገባ፣ እንዲሁም አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል  በማለት አብሮ ከመኖር ባለፈ ውስጣዊ  አንድነት እየራቀን መሆኑን በሥራው ነግሮናል፡፡

ብላቴናው አፄ ቴዎድሮስን ከመዘከር ባለፈ በተለይ በአሁኑ ወቅት በእጅጉ የሚያፈልገንን አገራዊ  አንድነትና ተግባቦት በዘፈኑ የጠቆመን  ሲሆን፣ ፊተኞች ኋላ ኋለኞች ፊት እንዲሉ ፍቅርና አንድነት አንድን አገር ወደ ፊትም ወደ ኋላም የማድረግ ኃይል እንዳለው በዜማው ነግሮናል፡፡ አገሪቱ የመጪው ዘመን ፊትና መሪ ትሆን ዘንድ ፍቅርና አንድነት ወሳኝ መሆኑን በሥራው ጠቁሞናል፡፡

ከብላቴናው በመለስ ወደ ሥልጣን ከመጣ በያዝነው ወር 26 ዓመታትን የሚያስቆጥረው ገዥው መንግሥት ኢሕአዴግ በእነዚህ የሥልጣን ዘመናት ከሰጠን ሰላም፣ እንዲሁም አበረታች የልማት ተግባራት በመለስ ከሚከተለው የአመራር ዘይቤ  ጋር ተያይዞ በአገራዊ አንድነት ዙሪያ የሠራቸውን ሥራዎች መለስ ብሎ ሊፈትሻቸውና ከአሁን በኋላም የበለጠ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ልዩነታችን ውበታችን፣ ውበታችን አንድነታችን እየተባለ በየቦታው ቢደሰኮርም ልዩነታችን ውበት ከመሆን በመለስ ለአንድነታችን ያመጣው ፋይዳ አጠያያቂ ይመስላል፡፡

በአንድ ገበሬ ጎጆ በየጊዜው የሚጨሰው ጭስ ቀስ በቀስ ጎጆውን ሙሉ በሙሉ እንደሚያጠላሸው ሁሉ፣ የበፊት አንድነታችን ቀስ በቀስ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ባለፉት ዓመታት እንደ ገበሬው ጎጆ እየጠለሹ መጥተዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ብላቴናው  አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል ብሎ ያዜመው፡፡ አብሮ መኖር ብቻውን ለአንድነት አብነት መሆን የማይችል ከመሆኑ በተጨማሪም፣ ልማት ያለ አንድነት ሙሉ እንደማይሆን እንዲሁም የልማት ዋስትናው አንድነት መሆኑን  ሲጠቁመን ነው፡፡

ብላቴናው በዘፈኑ መይሳው ካሳን ‹ዳኘን ዳኝን አንድ ህልም አሳየን› እያለ ይቀኛል፡፡ አንድነት የጠፋ እንደሆነ የሚያስከትለውን ዳፋ  እንድንገነዘበው በማሰብ፣ አለፍ ሲልም አንድነት ለዚህች አገር የሚያመጣውን በረከት ይገለጽልን ዘንድ ያሳስብናል፡፡ ለማንኛውም መይሳው አንድ ህልም እስኪያሳየን ድረስ እንደ ብላቴናው ያለ የጥበብ አርበኛ ስለአንድነታችን እያዜመና በዕውን በጥበብ እየገሰጸ፣ የመይሳውን ሽሩባ አግኝተን ስለአንድነታችን ማሰር ባንችልም፣ የጠፋንን አንድ የአንድነት ገመድ ፈልገን እንድናገኝ የሚረዳን ከያኒ እንዲበዛልን እንመኛለን፡፡     

በሌላ በኩል ስም ከመቃብር በላይ ነው እንዲሉ ለክብር ሐዲስ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ይህ ወቅት በሁለት ምክንያት ስማቸው ከመቃብር በላይ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የመጀመርያው በምሥላቸው የተቀረፀው ሐውልት በደብረ ማርቆስ ከተማ የተመረቀበት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ብላቴናው በዚህ አልበሙ ከፍ አድርጎ ያቀረበልን በ1958 ዓ.ም. በእሳቸው የተጻፈውን ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍን መሠረት አድርጎ የተሠራው ግሩም ዘፈን ነው፡፡ ዘፈኑም ብዙኃኑን የፍቅር እስከ መቃብር ምርኮኛ ያደረገ ሲሆን፣ ከክቡር ሐዲስ ዓለማየሁ በመለስ ለብላቴናው እጅ እንድነነሳ አድርጎናል፡፡

ብላቴናው በዘፈኑ የፍቅር እስከ መቃብር ዋነኛ የሆኑትን ክቡር ሐዲስ ዓለማየሁን አዲስ ዓለማየሁ እያለ፣ የበዛብህን ባህሪ ራሱ ብላቴናው ወክሎ፣ ‹እንዳልወስዳት አባብዬ ሰብልዬ ናት እማሆየ. . .› እያለ  ተጫውቷል፡፡  እንዲሁም ሰብለ ወንጌልን፣ መጸሐፉን በግሩም ሁኔታ ተርኮ ነፍስ የዘራበትን ወጋየሁ ንጋቱን በአንቺ ስል ወግአየሁ እያለ፣ የመጽሐፉን መቼት ጎጃምን፣ ዲማ ጊዮርጊስንና ሌሎችን በማንሳት ከጥልቅ ንባብ እንደ ማር የሚጠፍጥ መሳጭ ሥራ ማቅረብ እንደሚቻልም አሳይቷል፡፡ ከዚህ በላይ ውስጣችን ያለ ታሪክን መሠረት አድርጎ ግሩም ዜማ መቃኘት እንደሚቻል አብነት ሆኗል፡፡  በተጨማሪም በዚህ ‹ማር እስከ ጧፍ› በተሰኘው የብላቴናው ዜማ ምክንያት የክቡር ሐዲስ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ሥራ የሆነው ፍቅር እስከ መቃብር የተሰኘው መጽሐፍ በአሳታሚው ሜጋ አሳታሚዎች አማካይነት ዳግም ወደ ኅትመት ተመልሶ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይህም ብላቴናው የራሱን በንባብ ላይ የተመሠረተ የበኩሉን ሚና መጫወት አስችሎታል፡፡

አንድ ከያኒ የአገሩንና የሕዝቡን ታሪክ አውቆ ሲያሳውቅ በሕዝቡ ውስጥ ግዙፍ ሆኖ ብቅ ይላል፡፡ ለዚህም ነው ብላቴናው በሕዝቡ ውስጥ እንደ ዝግባ ግዙፍ ሆኖ ብቅ ማለት የቻለው፡፡ ለማጠቃለል ያህል ብላቴናው ካለው ከፍተኛ ተቀባይነት አንፃር ከላይ እንደተገለጸው፣ ለአገር ታሪክ የሠሩ ሰዎችን ከፍ ባለ ደረጃ ሥራቸውን ሕዝብ ዘንድ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ይሰርፅ ዘንድ ከፍ ያለ የጥበብ ሥራ በማቅረብ ለአገር ለወገን ዕድገት የሚበጁ ሐሳቦችን ማንሳት  የሚጫወተው አዎንታዊ ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡

በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ብላቴናው ከዓመታት በፊት ኔዘርላንድ ባቀነቀነው ዜማ ላይ ተመርኩዛ ብርቱካን ወለቃ፣ ‹‹ቴዲ አፍሮ ለምን ከሙት ገናዥነት አይወጣም?›› ስትል እንደተሟገተችው ሁሉ፣ አሁን ለገበያ ባዋለው አምስተኛ አልበሙ በተለይ አፄ ቴዎድሮስን፣ እንዲሁም የፍቅር አስከ መቃብሩን ደራሲ ክቡር ሐዲስ ዓለማየሁን መሠረት አድርጎ ያቀረባቸው ሁለት ሥራዎች ከሙት ገናዥነት በላቀ፣   በአሁኑ ወቅት በእጅጉ እንደ አገር የሚያስፈልገንን ፍቅርን፣ አንድነትን፣ እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪ ለአገር ዕድገት የሚበጀውን ንባብን የሚሰብኩ ግሩም ሥራዎች መሆናቸውን ስመለከት ‹ብላቴናው ከሙት ገናዥነት ባይወጣስ?› እንድል አድርጎኛል፡፡

እርግጥ ነው ብርቱካን በጽሑፏ እንዳለችው ሙት ገናዦች ሙትን እንዳስፈለጋቸው ይክቡና ያሽሞነሙኑት ይሆን እንጂ ነፍስ ሊዘሩበት አይችሉም፡፡ እንዲህ በማረ ደረጃ ሥራቸውን  የጥበብ ነፍስ ዘርተውበት ለህያዋን የሐሴት ምንጭ ሊሆኑ  እንደሚችሉ ብላቴናው ያሳየን ይመስለኛል፡፡

ብርቱካን ወለቃ በጽሑፏ መጨረሻ ላይ እንዲህ ትለናለች፣ ‹‹ሁላችንንም ከሙት ገናዥነት አውጥቶ የራሳችንን ታሪክ ሠሪ እንድንሆን ፈጣሪ ይርዳን፡፡›› ብላቴናው እስካሁን በሠራቸው ሥራዎች ሕዝብ ልብ ውስጥ በመግባት የራሱን ታሪክ የሠራ ሲሆን፣ ከሥራው ጎን ለጎን ለአገር ለወገን ታሪክ ሠርተው ያለፉ ሙታንን ከፍ ባለ ጥበብ እየገነዘ ታሪክ መሥራቱን ቀጥሎበታል፡፡ ብላቴናው እንደ ምርጫ 97 እንከን የለሽ አልበም ስላቀረብክ እያመሰገንን፣ ዳሩ አንተን አይገርምህም እንጂ ሚሊዮኖች እንዲህ የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ባይገርምህ ገና እንወድሃለን፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]   ማግኘት ይቻላል፡፡