Skip to main content
x
አራት ዘመናዊ የአውቶብስ መናኸሪያ ዲፖዎች ሊገነቡ ነው

አራት ዘመናዊ የአውቶብስ መናኸሪያ ዲፖዎች ሊገነቡ ነው

ከአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሊተገበሩ ይገባቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ መሠረት ልማቶች መካከል አንዱ የሆነው፣ የተሽከርካሪዎች መናኸሪያና ከዚሁ ጋር የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከሎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የራሳቸው የሆነ የተሽከርካሪዎች መናኸሪያ ወይም ዲፖ የላቸውም፡፡ የተደራጀ የተሽከርካሪዎች ማሳረፊያ ያለው ድርጅት ካለ የአንበሳ አውቶብስ ድርጅት ቢሆንም፣ እያደገ ከመጣው የአውቶብሶች ቁጥር አንፃር እሱም በቂ የሆነ የተሽከርካሪዎች ማቆያና መናኸሪያ የለውም፡፡ በአውቶብሶች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ድርጅቶች የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ሥፍራ የሌላቸው መሆኑ ደግሞ፣ በተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ እያሳረፈባቸው ስለመሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ችግር በጊዜያዊነትና ለዘለቄታ ለመቅረፍ የትራንስፖርት ድርጅቶቹ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ቢሆንም፣ ጊዜያዊ መፍትሔያቸው ግን ከወጪና ከእንግልት አላወጣቸውም፡፡ ከእነዚህ የትራንስፖርት ድርጅቶች ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርትን ችግር ለመቅረፍና ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቶች የተቋቋመው የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ የተደራጀ ጥገና አገልግሎት የሚሰጥበትም ማዕከል ስለሌለው በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ስለማሳረፉም እየተነገረ ነው፡፡

በዋናነት ለመንግሥት ሠራተኞች በነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከተቋቋሙ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አምባቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተሽከርካሪዎች ማረፊያ የሚሆን ቦታ ያለመኖሩ ትልቅ ፈተና መሆኑን ነው፡፡

ድርጅቱ የሚያስተዳድራቸው አውቶብሶች በሙሉ ለማደሪያ የሚሆን ቦታ የላቸውም፡፡ ቀን ላይ ቋሚ የሆነ ማረፊያም ስለሌላቸው በየቦታው እየዞሩ ነው ማቆሚያ የሚያፈላልጉት፡፡ ማታ ማታም ቋሚ የማደሪያ ቦታ ስሌላቸው ተለያዩ ድርጅቶች ትብብር እየተጠየቁ እንዲያድሩ ይደረጋል፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ ማደራቸው ደግሞ ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ለተሽከርካሪዎች የሚደረግ ጥበቃም ቢሆን ፈታኝ ነው፡፡ ሹፌሮች ከሥራ በኋላ ተሽከርካሪዎችን የት እንደሚያቆሙ እንኳን ስለማያውቁ፣ በቦታ መረጣ ረዥም ጉዞ የሚጓዙ በመሆኑ ሥራቸውን አሰልቺ በማድረግ ጭምር እየፈተናቸው ነው፡፡

የመናኸሪያው እጦቱ የተሽከርካሪዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ፈታኝ ከመሆኑ ሌላ፣ ማረፊያ ቦታ ለማግኘት ከአንዱ የከተማው ክፍል ወደ ሌላው ሲጓዙ የሚያቃጥሉት ነዳጅ ለአላስፈላጊ ወጪ ስለመዳረጉም ይኼ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ እንዲህ ያለ የማቆያ ቦታ እጦት የፐብሊክ ሰርቪስ ድርጅትን የራሱ የሆነ የተሽከርካሪዎች ዲፖ ለማስገንባት ወደሚያስችለው ምዕራፍ እንዲሸጋገር እያደረገው ነው፡፡ ሥራውን  ለማቀላጠፍም የተሽከርካሪዎች በማኸሪያና ዴፖ መግባት ወሳኝ በመሆኑ፣ ይህንኑ እውን ለማድረግ የሚያስችለው እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡

ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በአሁን ወቅት ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ማረፊያ እጦት ለመቅረፍ ዘመናዊ የተሽከርካሪዎች ዴፖ ለመገንባት የሚያስችል የግንባታ ዲዛይን በማሠራት ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ችግሩን በመገንዘብ በአዲስ አበባ ከተማ በአራት ቦታዎች ዘመናዊ መናኸሪያ ዴፖ ለመገንባት የሚያስችሉ ቦታዎች ለመሰጠት ፍቃደኛ በመሆኑ፣ የአራቱ ቦታዎች መረጣ ተጠናቅቆ ተከልሏል፡፡ ቦታዎቹም ጀሞ፣ ሸጎሌ፣ አቃቂና ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ናቸው፡፡ ወደ ግንባታ ለመግባት በአሁኑ ወቅት የቦታዎቹን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ የካርታ ሥራዎች ብቻ ይቀራቸዋል ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻም፣ አስተዳደሩ ለግንባታ የሚውሉትን ቦታዎች በመፍቀድ የተባበረ ሲሆን፣ በቅርቡም ካርታ ተሠርቶ ድርጅቱ እንደሚረከባቸው እምነት አላቸው፡፡ እነዚህ አራት ቦታዎች ላይ  የሚገነቡት ዘመናዊ ዴፖዎችን ዲዛይንና አጠቃላይ ግንባታውን ለማከናወንም ከግዙፉ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ውለታ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኮርፖሬሽኑና በድርጅቱ መካከል በተደረሰው ስምምነት በአዲስ አበባ በአራት የተመረጡ ቦታዎች ሊገነባ የታሰበውን ልዩ መናኸሪያ ዲፖ የዲዛይን ሥራውንና  ግንባታውን አጠቃሎ ለመሥራት የሚያስችል ነው፡፡

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፐብሊክ ትራንስፖርት ጋር በደረሰነው ስምምነት መሠረት የዴፖዎቹ ዲዛይን የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት በሚያስችል መልኩ እየተሠሩ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ደረጃ ዲዛይን ሥራውም ተጠናቋል፡፡ እንዲሠሩ የታቀዱት መናኸሪያዎች በተለመደው ዓይነት የመናኸሪያ አገነባብ የሚሠሩ ያለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይለ መስቀል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ የፐብሊክ አውቶብሶች ዴፖ በሚሰጡት ዓይነት አገልግሎት ታሳቢ ተደርገው እንደሚገነቡ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ዴፖዎች ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያነት ከሚሰጡት አገልግሎት በላይ ዘመናዊ የተሽከርካሪዎች ጥገና ለመስጠት የሚያችሉ ማሽኖችን የያዙ ይሆናሉ፡፡ የራሳቸው መካኒካል ወርክ ሾፖችንና የተለያዩ ማሽነሪዎች የሚኖራቸው ሲሆን፣ ትልልቅ የሚባሉና ተሽከርካሪዎችን በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚችሉ ክሬኖች ጭምር የሚኖራቸው ናቸው፡፡ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎትን ከመስጠት አኳያ እነዚህ ዴፖዎች እንደ ስምሪት ማዘዢያ የሚያገለግሉም ይሆናሉ፡፡ እነዚህ የተሽከርካሪዎች ዴፖዎች ለሌሎች ተመሳሳይ ዴፖዎች ሞዴል ሊሆኑ በሚችል ደረጃ የሚገነቡ እንደሚሆኑም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ አቶ ሰለሞንም ዴፖዎቹ ጋራዥ፣ የተሽከርካሪዎች እጥበት አገልግሎት፣ ሱፐርማርኬትና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችንም አካትተው የሚሠሩ ዘመናዊ ዴፖዎች ስለመሆናቸውና የሚሰጡት አገልግሎት ዘርፈ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ዘመናዊ የፐብሊክ ዴፖዎች ለመገንባት የተለያዩ አገሮችን ልምድ ለማየት እንደተሞከረ የጠቀሱት አቶ ኃይለ መስቀል፣ ለምሳሌ የቤጂንግ ከተማ የፐብሊክ ባስን ጠቅሰዋል፡፡ በፐብሊክ ባስ የሚሠሩት ዴፖዎች ለሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ የትራንስፖርት ማኔጅመንት ቅንጅት ይጠይቃል ያሉት አቶ ኃይለ መስቀል፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ የትራንስፖርት ድርጅቶች በግለሰብ፣ በኩባንያም ሆነ በመንግሥት የተያዙም ቢሆን አገልግሎቱን የሚሰጡት ለሕዝብ ስለሆነ በቅንጅት መሥራት ስለሚኖርባቸው በሒደት ዘመናዊ ዴፖዎች ሌሎችም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን በሚጠቅም ደረጃ የሚያገለግሉ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል፡፡ የእነዚህ ዴፖዎች ሥራ መጀመር አሁን የሚታዩትን ችግር ከመቅረፍ አልፎ ድርጅቱ ካላስፈላጊ ወጪ እንዲድን ያደረገዋል ያሉት አቶ ሰለሞን፣ በዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ እነዚህ የዴፖ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው ተብሏል፡፡ አቶ ኃይለ መስቀል እንደገለጹት ደግሞ፣ ፕሮጀክቱ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ያካተተ ስለሆነ የግንባታ ወጪው ከሦስት እስከ አራት ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት ከ410 በላይ በሚሆኑ አውቶብሶች አገልግሎት  እየሰጠ ሲሆን፣ ለመንግሥት ሠራተኞች በነፃ የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት በቀን በአማካይ 70 ሺሕ ሠራተኞችን እያጓጓዘ ስለመሆኑ አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል፡፡

ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎችን በመያዝ እየተንቀሳቀሰ ያለው ይህ ተቋም፣ የመንግሥት ሠራተኛውን በነፃ ማጓጓዝና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በተመጣጣኝ ዋጋ የታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

የመንግሥት ሠራተኞችን በነፃ ከማስተናገድ ጎን ለጎን የከተማውን የትራንስፖርት ተጠቃሚ ለማገልገል የሚሰጠው የታክሲ አገልግሎት፣ በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር በማቃለል ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ ይህ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡት አውቶብሶች ሠራተኛውን ካደረሱ በኋላ ወዲያው የታክሲ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ሲሆን፣ የተወሰኑ አውቶብሶች ደግሞ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ላይ የታክሲ አገልግሎት  እንዲሰጡ በማድረግ ጭምር ነው፡፡ አገልግሎቱም 135 በሚሆኑ አውቶብሶች ይሰጣል ተብሏል፡፡

በታክሲ አገልግሎቱ የሚጠቀሙ መኪኖች ቁጥር እያደገ ሲሆን፣ በ2009 በጀት ዓመት ብቻ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተጓዦች የድርጅቱን የታክሲ አገልግሎት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡