Skip to main content
x
አርሶና አርብቶ አደሮች በብዛት በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ጤና ጣቢያዎች ሊገነቡ ነው

አርሶና አርብቶ አደሮች በብዛት በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ጤና ጣቢያዎች ሊገነቡ ነው

  • ንግድ ባንክ የ70 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደርጋል

አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በብዛት በሚገኙባቸው በዘጠኙ ክልሎች በተመረጡ ሥፍራዎች ከ200 ሺሕ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጤና ጣቢያዎች ሊገነቡ ነው፡፡ የጤና ጣቢያዎቹ ግንባታ በስምንት ወራት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፤ በጋምቤላ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች  የሦስት ጤና ጣቢያዎች ግንባታ 60 በመቶው ያህል ተጠናቋል፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አርብቶና አርሶ አደሮች በብዛት በሚገኙባቸው ሥፍራዎች የጀመረውን የጤና ጣቢያ ግንባታ ለማጠናከርም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ70 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ተስማምቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለስድስት ጤና ጣቢያዎች ግንባታ የሚውል የ70 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመበት ወቅት፣ በንግድ ባንኩ ተጠባባቂ ዋና የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት መኮንን አቶ ለገሠ ጠቆ እንዳሉት፣ ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው የተለያዩ ጉዳዮች መካከል የጤናው ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ ለጤና ጣቢያዎቹ ግንባታ እንዲውል የሰጠው የገንዘብ ድጋፍም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ነው፡፡ ጤና ጣቢያዎቹ ከተገነቡ በኋላ አስፈላጊውን ቁሳቁስ የማሟላቱ ኃላፊነት የጤና ጥበቃ ነው፡፡

‹‹ግንባታው በአገሪቱ የጤና ዘርፍ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው›› ያሉት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አሚር አማን ናቸው፡፡ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ከውጭ ከሚመጣ ዕርዳታ ይልቅ የአገር ውስጥ ድጋፎችን የመጠቀም መርህ ሚኒስቴሩ እንደሚከተልም ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከመሥሪያ ቤቱ ጋር አብረው መሥራት የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱንም ዶ/ር አሚር ሳይናገሩ አላለፉም፡፡